Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉጦር መሳልና ጠብመንጃ መወልወልን በአንድ ድምፅ እንቢ ልንል ይገባል

ጦር መሳልና ጠብመንጃ መወልወልን በአንድ ድምፅ እንቢ ልንል ይገባል

ቀን:

በሰይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር)

‹‹በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፡- ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሥፍራው መልስ››

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፮ ቁጥር ፶፪

- Advertisement -

ዛሬ የሕዝቧ ቁጥር አንድ መቶ ሚሊዮን እንደተጠጋ (በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ግምት) የሚነገርላት አገራችን ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ስቃይና መከራን አስተናግዳለች፡፡ የስቃይና የመከራዋ ማብቂያ እንደ ሰማይ ርቋት በችጋር ተወልደው ማደጋቸው ሳያንሳቸው ዘልለው ያልጠገቡ ሕፃናት ልጆቿ፣ ወጣቱ፣ ጎልማሳው፣ አዛውንቱ በተለያዩ ጊዜያትና ምክንያቶች ለስደት ባስ ሲልም ለሞት መዳረጋቸውን ጆሮዎቻችን ተላምደው በየዕለቱ የምንሰማው መፈናቀል፣ ስደትና ሞት ተራ ነገር እየሆነብን መጥቷል፡፡ ይህ በአገራችን ያመጣነው ክፉ ነገር ነው፡፡ ክፉ ነገር ደግሞ በየትኛውም መሥፈርት ልንላመደው የሚገባ ነገር ሳይሆን፣ በተቻለ ፍጥነትና በተገኘ ዘዴ ሁሉ ልናስወግደው ይገባል፡፡ ይህ ጉዳይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊያሳስብ እንደ አገር ልጆች ቆም ብለን መንገዳችንን እንድንፈትሽ በጋራ እንድንመክር መክረንም መውጫ መንገድ እንድንፈልግ ያስገድደናል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ታሪኳ ብዙ ባዕዳን ጠላቶችን በጦር ሜዳ አስተናግዳለች፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጋር ገጥሞ መቅደላ አምባ ላይ ሕይወቱን የሰጣት ይህች አገር፣ አፄ ዮሐንስ ከደርቡሾች ጋር መተማ ላይ ተዋግቶ የሞተላት ይህቺ አገር፣ ዓለምን ባስደመመ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ ከዳር እስከ ዳር ወጥቶ በአፄ ምኒልክ መሪነት በወራሪው ጣልያን ላይ የተቀዳጀው ድል፣ የቀደመው ሽንፈት ቁጭት ይዞት ዳግም ከ1928-33 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ የሞሶሊኒዋ ጣሊያን በተነሳችበት ወቅት እንቢኝ ለነፃነቴ ብሎ በዱር በገደሉ የተደረገው ውጊያ፣ የመስፋፋት አባዜ የተጠናወተው የዚያድ ባሬው ሶማሊያ መንግሥትን ለመመከትና ከአገር ለማስወጣት የተደረገው ጦርነት፣ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ከኤርትራ ጋር የተደረገው ጦርነት በሙሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እምቢኝ ለአገሬ እምቢኝ ለድንበሬ እንቢኝ ለነፃነቴ ብለው የመጨረሻ ስጦታ የሆነውን ውድ ሕይወታቸውን ያበረከቱበት ሁኔታ ዘወር ብለን ስንመለከት እኛ የተረከብናት ኢትዮጵያ ከአፈርና ከውኃ ብቻ ሳይሆን፣ በተደጋጋሚ እንደሚነገረው በአባቶቻችን ደምና አጥንት ጭምር የተገነባች ታላቅ አገር ናት፡፡

የዚህች የመከራዋና የስቃይዋ ማብቂያ የራቀ የመቶ ሚሊየኖች እናት ኢትዮጵያ ችግሯ ዕለት ዕለት መልኩን እየቀየረባት ከኤርትራ ጋር ካደረገችውና ውድ የሕይወት ዋጋ ከተከፈለበት ጦርነት ወዲህ ከውጭ አገር ሌላ የደረሰባት ወረራ ባይኖርም፣ ከባዕዳን ወረራ ዕፎይ ያለችው ኢትዮጵያ አገራችን ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት መከራዋ መልኩን ቀይሮ በወለደቻቸው ወንድማማች ልጆች መካከል የእኔ ቦታ ነው ያንተ ቦታ እዚህ አይደለም፣ የእኔ አገር ነው ከአገሬ ውጣልኝ መርዛማ ጨዋታን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ በዚህም የተነሳ ቀደም ሲል በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች (በዋነኛነት በኦሮሚያ ክልል) ይኖሩ በነበሩ አማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ላይ ሞትና ከኖሩበት ቀዬ የመፈናቀል ግፍ ሲደርስባቸው የእርምት ዕርምጃ በወቅቱ መውሰድ ባለመፈለጉ፣ የችግሩ መጠን ከጫፍ ሲደርስ ባለፈው 2010 ዓ.ም. ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኦሮሚኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን በሶማሌ ክልል ለሞት እንዲዳረጉ፣ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ደግሞ ተወልደው ያደጉበትንና የኖሩበትን ቀዬ ለቀው በዚሁ ከክልሌ ውጣልኝ መርዛማ ጨዋታ ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ችግሩ በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይወሰን መላ አገራችንን በሚባል ሁኔታ ማለት ይቻላል፡፡ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ አዳርሶ ዛሬ ላይ ቋንቋችን መግባቢያችንና የመገናኛ ድልድያችን መሆኑ ቀርቶ ቋንቋችን የመለያያ መስመራችን ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን ሦስት ሚሊዮን የሚያህል ሕዝቧ ከመኖሪያ ቀዬው ተፈናቅሎ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ከዓለማችን ግንባር ቀደሙን ሥፍራ እንድትይዝ አድርጓታል፡፡

በአገርህ አይደለም ከአገሬ ውጣልኝ ምክንያት አካባቢን ለቅቆ ወደማያውቁት ሥፍራ ስደት ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት አርሰው ከራሳቸው ተርፎ ሌላውን የሚመግቡ እጆች ተፈጥሮ ፊቷን ሳታዞርባቸው ለወትሮው የስደት ምክንያት የሆነ ድርቅና ረሃብ ሳይሆን፣ እኛው በሠራነውና በፈጠርነው ችግር ለምፅዋትና ለሰው እጅ ጥበቃ ተዘርግተዋል፡፡ ይኼንንም አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ እንደ አገር ተላምደነዋል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ በየክልሉና በየከተማ መስተዳድሩ በሕገወጥ ግንባታና በመሬት ይዞታ ሽፋን በየከተማው እየፈረሱ ባሉ ቤቶች ሳቢያ (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንደምንሰማው በመቀሌ፣ በተለያዩ የአማራ ከተሞች፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች፣ በደቡብ ክልል) አካባቢያቸውን ለቀው የተሰደዱ ተፈናቃዮች ባያረጋቸውም፣ ቀላል የማይባል ሕዝብ ጎዳና ላይ እንደወደቀ ሻል ሲልም በየዘመዱና በጎ አድራጊ ቤት ጥገኛ ለመሆን እንደተገደደ ለመገመት ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ይህም የአገራችን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃና ስቃይ ከፍ በማድረግ የችግሮቻችንን መወሳሰብ አንድ ዕርምጃ ወደፊት አስኪዶታል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከሁለት ወራት በፊት በሥራ ምክንያት በሰመራ በኩል የሰርዶ – አፍዴራ – አብአላን መንገድ ተከትሎ ወደ መቀሌ ለመጓዝ ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ አብአላ ወደ ደጋማው የትግራይ ክፍል መዳረሻ የቀረበች የአፋር ከተማ ስትሆን፣ በዚህች ከተማና በሰርዶ መካከል ያለው 362 ኪሎ ሜትር መንገድ ዝቅተኛውንና ከባህር ወለል በታች 100 ሜትር ላይ የሚገኘውን የአፍዴራ ከተማን ጨምሮ አራት ትንንሽ ከመንደር ያልተሻሉ ከተሞች ብቻ የሚገኙበት ተፈጥሮ ጨካኝ የሆነችበት የሚባል በረሃማ መንገድ ነው፡፡ መንገዱ እንደ መንገድ በጣም ጥሩ አስፋልትና እንከን የሌለው (የባለሙያ ባልሆነ ዕይታዬ) ቢሆንም፣ ከቦታው በረሃማነት አኳያ የሰዎች እንቅስቃሴ እጅግ ውስን የሆነበትና ተሸከርካሪም ቢሆን አልፎ አልፎ ብቻ የሚያልፍበት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ላይ ፈጣን አገር አቋራጭ አውቶቡሶች ሕዝብ ጭነው ሲከንፉበት ሳይ ምንም እንኳን ቀደም ሲል ጉዳዩን የሰማሁት ቢሆንም፣ አሁን መንገዱ ላይ እየተጓዝኩና እያየሁት ስለሆነ ልቤ እጅግ አዘነ፡፡ የሐዘኔ ምክንያትም የበረሃውን ሙቀት ካየሁኝ በኋላ ከእነዚህ አውቶቡሶች አይበለውና አንዱ ቢበላሽ ከተሳፈሩት ውስጥ ሕፃናትና አረጋውያን ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳስብ፣ ወጣትና መካከለኛ ዕድሜ ላይ ያለውም ቢሆን የተሟላ ጤና የሌለው ሰው እንደሚኖርና ዕርዳታ ከሆነ ቦታ እስከሚመጣ ከሙቀቱ ኃይለኝነት የተነሳ ሊያልፍ የሚችል የወገኔ ሕይወት መኖሩ አሳዛኝ ነበር፡፡ አዎን ይህ ሊሆን የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ ለእነዚህ ተሸከርካሪዎች አጭሩንና ቀናውን መንገድ ትቶ ረጅሙንና ‹‹ጨካኙን›› መንገድ መምረጥ ምክንያቱ ኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ ፖለቲከኞች ለገዛ ጥቅማቸውና ለወንበራቸው ሲሉ፣ እንዲሁም ዘመን ባለፈበት ርዕዮተ ዓለም ባለፉት 27 ዓመታት የዘሩት የቋንቋና የክልል መዘዝ እንደሆነ ማንም የሚረዳው ነው፡፡ ጉዞዬ ከላይ በጠቀስኩት መንገድ አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆንም ከዚያ በኋላ በደሴ – ቆቦ – መቀሌ መንገድ በተደጋጋሚ ስመላለስ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች መነሻና መድረሻቸው የት እንደሆነ ባላውቅም፣ ሲንቀሳቀሱ መመልከቴ በዚያኛው የተሰማኝን የልብ ስብራት ባይጠግንልኝም ነገሮች በሙሉ ጨለማ እንዳልሆኑ አመላክቶኛል፡፡

በኢትዮጵያ አገራችን ቋንቋ መግባቢያችን መሆኑ ቀርቶ የመለያያ መስመራችን የሆነበት ፖለቲካ፣ ባለፉት ዓመታት እዚህና እዚያ በሚነሳ ከአካባቢዬ ውጣልኝና ልቀቅልኝ ጥያቄ አልፎ ዛሬ የፌዴራል መንግሥቱን የሚመሠርቱ የክልል መንግሥታትን ለፍጥጫ የዳረገበትን ሁኔታ እያሳየን ነው፡፡

በዚህም ምክንያት በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ጦር መሳልና ጠብመንጃ መወልወል ከተጀመረ ውሎ ያደረ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ሊነሳ የሚችል አነስተኛ ግጭት ከዚህ የሚያተርፉ የሚመስላቸው ፖለቲከኞች ባሉበት ሁኔታ፣ ወደ ከፋ የደም መፋሰስ ሊሻገር የሚችልበትን አጋጣሚ ሊፈጥር መቻሉን ሁሌም በማሰብ የተያዘው ፍጥጫ ረግቦ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ የሚገባበትና ከሥጋት የፀዳ ሁኔታ መፍጠር የግድ ነው፡፡ በግልጽ አውጥተን ተናገርነው ወይም ሸፋፍነን ለማሳለፍ ሞከርነው መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንደሌለ ማድረግ አይቻልም፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ ጦር እንዲስል ማድረግ ለዘመናት በኋላቀር ግብርና ከመሬት ጋር ለሚታገል የአገሬ አርሶ አደር ማረሻ ማቀበል ሊሆን አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ በየትኛውም ወገን በኩል ቢሆን ለጠብመንጃ ውልወላ ጥሪ ማስተጋባት ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ለዚህ አርሶ አደር ማቀበል አለመሆኑን ፖለቲከኞቻችንም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ልባቸው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ አርሶ አደር የሚሻው ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ለዘመናት ከኖረበት ከእጅ ወደ አፍ አኗኗር የሚያላቅቀውን መላ የሚያበጅለትን እንጂ፣ ጠላት አገርን የወረረ ይመስል በወንድሙ ላይ ጦር የሚያስልና ጠብመንጃ የሚያስወለውል ፖለቲካና ፖለቲከኞችን አይደለም፡፡

ዛሬ በክልሎች መካከል እየታየ ያለውን ፍጥጫና ውስጥ ለውስጥ እየተደረገ የሚገኘውን ዝግጅት ካወቅንበት ሳይቃጠል በቅጠል ብለን በእንጭጩ ልንገታውና የችግሩ ቆስቋሽ የሆኑትን ልናሳፍርበት ይገባል፡፡ በተቃራኒው ተገቢውን ጥንቃቄና ተግባራዊ ዕርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ባልተጠበቀ ሁኔታ የአንዲት አገር ወንድማማች ልጆችን ወደ ከፋ ችግርና ቀውስ ሊከተን፣ በጀግኖች አባቶቻችን ድሎች በአንድ ወቅት መልካም ስምንና ዝናን ተቀዳጅታ የኖረች አገር ያልተጠበቀ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብታ ሕዝቧን ለሞትና ለስደት ከመዳረጉም ባሻገር ወትሮም አፍሪካውያን ተብለን የዓለም መሳቂያና መሣለቂያ እንደሚያደርገን ከወዲሁ ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በዚህ ጉዳይ የተጠመዱ ፖለቲከኞቻችንና አጃቢዎቻቸው ቆም ብለው መልሰው መላልሰው ሳይረፍድ በአግባቡ ሊያስቡበት ይገባል፡፡

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት በወንድማማች ሕዝብ መካከል ጠብ እንዲጫር ማድረግ፣ የጉዳዩን መሪዎችና ዋነኛ ተዋንያን በቀጥታ የሚያስጠይቅበት ሁኔታ የማይቀር ሆኖ በታሪክም የማይፋቅ መጥፎ አሻራን ጥሎ የሚያሳልፍ በመሆኑ፣ ቆም ብለው አካሄዳቸውን እንዲያጤኑ ሕዝባችን በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት ጎዳና የቀደመውን ወንድማማችነቱን ጠብቆ እንዲጓዝ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ ይገባል፡፡

የሃይማኖት አባቶች በአገር ላይ እየመጣ ያለውን አደጋ በተለመደ ሁኔታቸው ምንም እየተፈጠረ እንዳልሆነ ሁሉ በዝምታ ቆሞ ከመመልከት፣ የፖለቲከኞቹን ዓይን ከማየትና የልብ ትርታ ከማድመጥ ወጥተው ድምፃቸውን ጮክ አድርገው ሊያሰሙ አሁን ከምንጊዜውም በበለጠ ወቅቱ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች በጋራ ሆነው እንዲሁም በየአብያተ እምነታቸው በወንድማማች መካከል ጠብን መዝራት በፈጣሪ ዘንድ የሚያስጠይቅ በምድርም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ጮክ ብሎ በማስተጋባት፣ መምከርና መገሰጽ ፉከራውና ቀረርቶው ቆሞ የአንድ አገር ልጆች የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለ ሥጋት ሰላማዊ ኑሮውን እንዲመራ በማስቻል ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል ሊነሳ የሚችል ግጭት በሁለቱ ክልሎች ብቻ የሚገደብ ሳይሆን፣ አገራችንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ሊነካ እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡ ከዚህ በመነሳት ምንም እንኳን የየክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የሚገናኙበት መደበኛ የሆነ መድረክ መኖሩን እርግጠኛ ባልሆንም፣ ሁኔታውን በማርገብ ረገድ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ክልሎች አመራሮች ጋር የአቻ ለአቻ ግንኙነት በማድረግ የተጋረጠውን አደጋ በማስወገድ ረገድ የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

የፌደራል መንግሥቱ ይህን ጉዳይ በተመለከተ እያደረገ ያለው ነገር ለሕዝብ ግልጽ ባይሆንም፣ የተጋረጠውን አደጋ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት የሚገባው ነው፡፡ እንደ መንግሥት አገርን የመምራት፣ መንገድ የመቀየስ፣ አቅጣጫ የማመላከት የግጭቶችን አዝማሚያ አስቀድሞ በመረዳት ለግጭቶች በር የሚከፍቱ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች የመገደብ፣ ግጭቶች ሲነሱ አግባብ ባለው መንገድ የመፍታትና የመሳሰሉት ጉዳዮች በዋነኛነት በዚሁ በፌደራል መንግሥቱ ጫንቃ ላይ ያለ ነው፡፡  ይህንን በአገር ላይ ያንዣበበ አደጋ በማስወገድ ረገድ ሕዝብ በግልጽ የሚያየውና የሚረዳው ተጨባጭ እንቅስቃሴ መጀመሩንና ለዚሁ የሚመጥን ዕርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ፣ የመንግሥትነት አደራውን ለሰጠው ሕዝብ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ተገንዝቦ ሕዝባችን ከሥጋት በማውጣት የዕለት ተዕለት ኑሮውን እንዲመራ ማስቻል አለበት፡፡

ከመነሻዬ ባሰፈርኩትና እኔ የምከተለው የክርስትና እምነት መመርያ ከሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደው ጥቅስ እንደሚያመለክተው፣ ‹‹ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሥፍራው መልስ›› የሚለው ኃይለ ቃል ዛሬ የኢትዮጵያ ልጆች ላለንበት ሁኔታ ትክክለኛ መልዕክት የሚያስተላልፍ ኃይለ ቃል ነው፡፡ ጦር ስትስል ጦር የሚሳልበትም በበኩሉና በአቅሙ እንደሚስል፣ ጠብመንጃ ስትወለውል ጠብመንጃ የሚወለወልበትም በበኩሉና በአቅሙ በእጁ የተገኘውን እንደሚወለውል ለአፍታም ቢሆን ሊረሳ አይገባም፡፡ ጦር መሳሉንና ጠብመንጃ መወልወሉን ክፉ የክፉም ክፉ የሚያደርገው ደግሞ በአንድ እናት ልጆች መካከል የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ ቃየል በአቤል ላይ እንደተነሳና እንደ ገደለው ማለት ነው፡፡ ዋነኛው ርዕሰ ጉዳይ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ውስጥ ውስጡን እየተብላላ ያለው ጉዳይ ሆነ እንጂ፣ ዛሬ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ምን እያደረግን ምን እየተደረገ መሆኑን ቆም ብለን ልንጠይቅና ሳንዘገይ ወደ አዕምሮአችን ልንመለስ ከክፉ ሥራዎቻችንም ልንታቀብ እንደሚገባን፣ በየአካባቢው የሚደረጉ ክፉና ኢትዮጵያዊነታችንን የማይገልጹ እኩይ ተግባራት አመልካቾች ናቸው፡፡

የምንራመዳት እያንዳንዷ ዕርምጃ ምን ልታስከትል እንደምትችል በእርስ በርስ ግጭት እየተናጡና የሩቁን ጊዜ ትተን በቅርቡ እየፈራረሱ ካሉ እንደ ሊቢያ፣ ሶሪያና የመን ካሉ አገሮች እንደ ባለ አዕምሮ ትምህርት ልንወስድና ሕዝባችንን ከተጋረጠበት አደጋ በፍጥነት ልንታደግ ይገባል፡፡ ዛሬ በየቦታው ከምንሰማው ግድያና መፈናቀል፣ እንዲሁም ውስጥ ውስጡን እየተብላላ ካለው የክልሎች እርስ በርስ ፍጥጫ እንደ አገርም፣ እንደ ማኅበረሰብም፣ እንደ ግለሰብም አንዳችም አሸናፊ እንደማይኖር ይልቁንም ሁላችን ተሸናፊዎች እንደምንሆን ያለ ብዥታ አጥርተን ልናይ ይገባል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ስብሰባን ተከትሎ በአማራ ክልል ምክር ቤት መግለጫም ሆነ በትግራይ ክልል በተሰጠው ምላሽ የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች የጋራ ባህል የጋራ ሃይማኖትና ማኅበራዊ ትስስር ያላቸው፣ እንደ አንድ አገር ልጆች ለአገራቸው አብረው የሞቱና ዛሬም አብረው ያሉ መሆናቸውን በመግለጽ ከወጡት መግለጫዎች ስለሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት የተነገረውን በጎ ነገር ተከትለን ያንዣበበው የግጭት ድባብ ተወግዶ ወደ ፍቅር፣ ወደ መተሳሰብና ወደ አንድነት እንድንጓዝ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ሲሆን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዚህ ተግቶ ሊሠራና የራሱን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል፡፡ በሁለቱም ክልሎች የተነገሩት በጎ ነገሮች ወደ በጎ ጎዳና ይወስዱናል ብለን እያሰብን ውስጥ ውስጡን ወደ ግጭት የሚወስደን ነገር እንዳይፈጠር፣ ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ባልረፈደበት በዛሬው ቀን በተባበረ ድምፅ ጮክ ብለን ጦር ለመሳልና ጠብመንጃ ለመወልወል እንቢኝ ልንል ይገባል፡፡ ለበጎ ሥራ ልናውለው በተነሳንና ይልቁንም የጥላቻ መዝሪያ ባደረግነው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ይኼንኑ የእንቢ ለግጭት ድምፃችንን በሠለጠነ መንገድ ልናስተጋባና አገራችንን ከአንዣበበባት አደጋ ልንታደግ ይገባል፡፡   

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...