Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‘ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል’

‘ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል’

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ዕድል ፈንታው ሆኖ ጨዋታ በቀላሉ የሚደምቅለት አንድ ወዳጄ በዚያ ሰሞን፣ ‹‹ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ዘንድሮ 44ኛውን የልደት በዓሉን መቀሌ ላይ በመታደም ያከበረው ብቻውን እየቆዘመ ነበር፤›› በማለት አላግጦ ሳይጨርስ፣ በአቃቂር አውጪነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሌላው ትንታግ ጓደኛችን ወዲያውኑ ከአፉ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹አበው እኮ ‘ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል’ ይላሉ፤›› ሲል ሁላችንንም ትንሽ ፈገግ አላደረገን መሰላችሁ? ይኼኔ ነበር እኔ ደግሞ እንደ አቅሚቲ የራሴን ድርሻ የተወጣሁ መስሎኝ፣ በድሮ ጊዜ አንድ ታዋቂ የአገራችን የቅኔ ዘራፊ ‘ሚ በዝሁ’ በተሰኘውና ከጉባዔ ቃና እስከ ዕጣነ ሞገር ከተዘረጋው የቅኔ መሰላል በሦስተኛው ዕርከን ላይ በሚመደበው የቅኔ ዘውግ አማካይነት አባባሉን እንዴት አዋዝተው እንዳቀረቡልን፣ በታሪክ የኋሊት ተጉዤ ለማስታወስ የተገፋፋሁት፡፡

 እስካሁን ድረስ ዝነኛ ሆኖ የዘለቀው ያ የሚ በዝሁ ቅኔ በልሳነ ግዕዝ እንዲህ ይሰነኛል፡፡ ሐሜተ ክልኤቱ አሃው ዘ ኢ ፈርኃ ወልድ በልአ በተከብቶ ሥጋ ጥኡመ እንዘ የአፁ ሆህቶ፣ ወ ፍሉጠ ሞት ኮነ ባህቲቶ ዘ በልአ እስመ ይመውት ባህቲቶ፡፡ እንደ ግዕዙ አደራደር አብዝቶ ላይጥማችሁ ቢችልም ተከታዩ ደግሞ ግርድፍ የአማርኛ ትርጉሙን ሊወክል ይችላል፡፡

የሁለት ወንድማማቾችን ሐሜት ያልፈራው ወልደ እግዚአብሔር ከስስታምነቱ የተነሳ ድንገት ያገኘውን ጣፋጭ ሥጋ የበላው ራሱን ደብቆና በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ ነው፡፡ ያም ሆኖ ገደብ የለሽ ስስታምነቱ ከሞት ሊያድነው አልቻለም፡፡ እንዲያውም ከሁለት ወንድሞቹ ቀድሞ ብቻውን ነበር ወደ መቃብር የወረደው፡፡ ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታልና፡፡

እንግዲህ የዚህ ታሪክ ቀመስ ቅኔ ወርቁ እግዚአብሔር ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ በመነጠል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ወንድ ዓይታ በማታውቀው በድንግል ማርያም ማህፀን ካደረ በኋላ፣ የሰው ሥጋ ለብሶ መወለዱንና በኋላም ለአዳምና ለሔዋን ልጆች ደኅንነት ሲል በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ ብቻውን እስከ መሞት ያደረሰውን ፍዳና መከራ መቀበሉን የሚያመሰጥርልን ሲሆን፣ ሰሙ ደግሞ በገሃዱ ዓለም አንድ ስስት የጠናበት ግለሰብ ሆዱ በለጠበትና በሩን ዘግቶና በጓዳው ተደብቆ ሲበላ ቢቆይም ከወንድሞቹ ጋር ተካፍሎ በመብላት ፋንታ፣ ከስስቱ የተነሳ ምናልባት ቸኩሎ በሚገባ ሳያላምጥ ሊውጠው በሞከረው ሥጋ ታንቆ ያን ያህል የሳሳላትን ሕይወቱን እስከ ማጣት የደረሰ መሆኑን ይገልጽልናል፡፡

እኔ እስከ ማውቀው ድረስ የየሠፈራችን እምቦቀቅላ ሕፃናት የልደት በዓላቸውን የሚያከብሩት የዕድሜ እኩያዎቻቸውን ጠርተው፣ የመልካም ልደት ስጦታዎችንና የምኞት መግለጫዎችን በመለዋወጥ ነው፡፡ ዓይነተኛው የሐሴታቸው ምንጭ አብሮነታቸው ነውና፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የቱንም ያህል ስስታም ሆኖ ቢፈጠር በዘልማድ ሆዳም እየተባለ የሚነቀፈው ጅብ እንኳ አንድ የሆነ ምራቅ የሚያስውጥ ጥንብ በመንገዱ ላይ ሲያጋጥመው ዜና ብሥራት ይሁን ለወዳጅነት ግብዣ የሚደረግ ጥሪ ገና ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ ጓደኞቹን ለማሰባሰብ ደጋግሞ መጮህ የተፈጥሮ ግብሩ እንደሆነ እናውቃለን፡፡

ሕወሓት ባለፈው የካቲት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. 44ኛ የልደት በዓሉን ለማክበር መቀሌ ላይ የከተመው ግን አንዳች የአገር ውስጥ እንግዳም ሆነ የውጭ ተጋባዥ አድማቂ መጥራትና መቀላቀል ሳያስፈልገው በብቸኝነት መሆኑ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በዚያ በዓል ላይ ከታደሙት መካከል እንደ ወትሮው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ተወካዮች እንኳ አይገኙባቸውም፡፡ እንደ ቀድሞው አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያስተላልፏቸው የድጋፍ መልዕክቶችም በአደባባይ ሲነበቡ አላየንም፣ አልሰማንም፡፡ በተቃራኒው ሕወሓት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዘንድሮ የቀድሞ ተጋዳላዮችን ሳይቀር ራሱን ከእየ ጥጋጥጉ አሰባስቦ ተመልክተነዋል፡፡ ከወጣት እስከ ጡረተኛ መላ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ተዛዝለው ሲታዩ፣ ስብስቡ አንድ ዓይነት ያልታሰበ መከራ የደረሰባቸውና ትኩስ ሐዘን የተቀመጡ አስመስሏቸው አልፏል ቢባል ፈጽሞ ማጋነን አይሆንም፡፡

እነሆ የሕወሓት ኮር አመራር ከመዲናይቱ ከአዲስ አበባ በለውጥ ዕርምጃው ተደናግጦ ወደ ሰሜናዊቷ ኮከብ ወደ መቀሌ ከተማ ከሸሸና ቋሚ መቀመጫውን በዚያ ካደረገ ጥቂት ሰነባብቷል፡፡ ይኼንን የታዘቡ አንዳንድ ወገኖች ታዲያ ‘ምንድነው ነገሩ?’ ሲሉ በአጽንኦት መጠየቃቸው አልቀረም፡፡ እነዚህ ወገኖች በእርግጥ ኢሕአዴግ እያካሄድኩት ነው ያለው ጥልቅ ተሃድሶ መኮላሸቱንና በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል እነርሱ እንደሚሉት የእርስ በርስ ጥርጣሬና አለመተማመን ብቻ ሳይሆን፣ ማባሪያ የሌለው ቁርሾ መፈጠሩን ያልሰሙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ዕለቱን ምክንያት በማድረግ እንደተለመደው ሕወሓት ያወጣው ድርጅታዊ መግለጫ ደግሞ እውነትም አበው አሉት እንደተባለው ብቻውን መቅረቱን የሚያሳብቅበት ሆኖ ተመልክተነዋል፣ አድምጠነዋል፡፡ “ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል”፣ “የፌዴራል ሥርዓቱ ፈርሷል”፣ ‹‹ዋጋ የከፈልንበት ሥርዓት መቀመቅ ሲወርድ እያየን እጅና እግሮቻችንን አጣምረን አንመለከትም››. . . የሚሉ መፈክሮችን አካቷል፡፡

ከፍተኛ ቅሬታዎችና የፀብ አጫሪነት ፉከራዎች በአንድ ላይ ተቀላቅለው የተስተጋቡበት ይህ መግለጫ የጤንነት ነበር ለማለት አዳጋች ነው፡፡ ቀረርቶ ተሰምቶበታል፣ ግልጽ ዛቻ ተሰንዝሮበታል፣ ጦር ተሰብቆበታል፡፡ ሻዕቢያ ከዓመታት በፊት በባድመ ግንባር ከፍታው የነበረውን የግፍ ወረራ በተናጠል ለመመለስ ወኔ ከድቶትና አንገቱን አቀርቅሮ የነበረው ኃይል፣ እነሆ ያኔ ፈጥኖ በመድረስ ህልውናውን በታደገለት ወንድም የጎረቤት ሕዝብ ላይ በእኩይ የውለታ ቢስነት መንፈስ ተነሳስቶ ጥቃት ለመሰንዘር አካኪ ዘራፍ ከማለት ወደ ኋላ አላለም፡፡

ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ በማግሥቱ የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና ዘውግ ተኮር ሆኖ አገሪቱ ውስጥ በተተከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ላይ አንደራደርም ሲል ያሰማው የአጋርነት እንጉርጉሮ ነው፡፡ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በጋራ ተስማምቶ ያወጣው የአቋም መግለጫ ይሁን አቶ ታየ ደንደአ ለአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው አገልግሎት እንደገለጹት፣ አባላቱን ለማወያየት ተዘጋጅቶ የተሠራጨ ጽሑፍ እስካሁን ምንነቱ በውል ያለየለት ያ የኦዴፓ የድጋፍ መልዕክት ሕወሓትን ለጊዜውም ቢሆን ከብቸኝነት ዳፋ ለመገላገል የቀቢፀ ተስፋ ሙከራ የተደረገበት ነበር ለማለት ሳያስደፍር አይቀርም፡፡

ይሁን እንጂ ኦዴፓ ዘግይቶ በተሰማው በዚህ አክራሪ መልዕክቱ ከሕወሓት ጋር እንደገና ጡት የተጣባ ቢመስለውም፣ ራሱን በራሱ ከተራማጅ ኃይሎች ሠፈር ነጥሎ ያወጣና ጥንቃቄ በጎደለው ፖለቲካዊ ዕርምጃው ‘የውኃ ላይ ኩበት’ የሆነ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ዘመን ከአገራዊ ህልውናና ከፖለቲካዊ ነፃነት ባሻገር በየትኛውም ጉዳይ ላይ ቢሆን፣ ራሱን ለሰላማዊና ሕጋዊ ድርድርና ውይይት ዝግጁ ያላደረገ የፖለቲካ ቡድን ከተራ የአማፅያን ስብስብነት ሊዘል አይችልምና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ በነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...