Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትከተቀረቀርንበት ጉድጓድ እንዴት እንውጣ?

ከተቀረቀርንበት ጉድጓድ እንዴት እንውጣ?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

ዛሬም መማረር ታመመ እንጂ ገና ነፍሱ አልወጣም ለምን? የሕወሓት ኢሕአዴግ ብልጣ ብልጥ አገዛዝና የክልል ገዥዎች ‹‹ተለጣፊነት››፣ ወዲያውኑ ፈጦ የወጣና ማንም ተራ ሰው የማይደናገርበት እውነታ ሆኖ ሳለ፣ አንድ ላይ ተያይዞ መነሳት እንደምን ተሰለበን? የአገዛዙ ሸረኛና ፖሊሳዊ ጥርነፋ፣ ለውጥ ፈላጊዎች ለመተባበር ካደረጉት ጥረት በልጦ፣ ብሔረተኛ አስተሳሰብና አገዛዝ ደጋፊዎቹንም ተቃዋሚዎቹንም በጥላቻ ስሜት እየመረዘ አዕምሮና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ለመከታተፍ ከሩብ ምዕት ዓመት በላይ ዕድሜ ማግኘቱ ዋናው ምክንያት ነው፡፡ የለውጥ ብርሃን ፈንጥቆ የአገዛዙ ድቆሳ ሲረግብ ደግሞ፣ በሥልጣን ላይ የቆዩት ልሂቃን ገዥነታቸውን ለማደስ፣ ሥልጣን  ላይ ያልነበሩትም በሕዝብ ጎሽታ ወደ ሥልጣን  ለመውጣት፣ ታፍነው የኖሩ የ‹ጥቅም ቀረብኝ› የመዋቅርና የወሰን ጥያቄዎችን/ውዝግቦችን እየቀሰቀሱ የፖለቲካ መነገጃ ማድረጋቸው ሁለተኛው ነው፡፡

ክፍልፋይ ፖለቲካዊ ንግዱ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ግጭት፣ ጨካኝ ጥቃትና መፈናቀልን ሲያመርት ደግሞ፣ በዚህ ዓይነቱ የመከራ ምርት በቀል ለመለዋወጥ፣ በክልሎች አወቀቀር ውስጥ አንዱ ጋር ባይተዋር የተደረገ ሌላ ቦታ የክልል ባለቤት መሆኑ፣ አንዱ ጋር ባለቤትነት የተሰጠውም በሌላ ክልል ውስጥ ባይተዋርነት እንዲሰማው መደረጉ ጠቀመና ከዚህ አዙሪት ለመውጣት የሚደረገውን ከሲታ ጥረት ክፍልፋይ ትርምሶች እየተቀባበሉ አድፈቀፈቁት፡፡ ሁላችንም የዚህ ዓይነት የድቀት ኪሳራዎች ባሉበት ጉድጓድ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ዋናው ጥያቄም ከዚህ ጉድጓድ እንዴት እንውጣ? ከመሸካከር ድቀት እንዴት እንገላገል ነው፡፡ እናም በኢትዮጵያ ሕዝቦች ግንኙነት ውስጥ ዕርቅና ሰላም የመፍጠርና መተሳሰብን የመገንባት ሥራ በአዳራሽ እየሰበሰቡ ዲስኩር በመደርደር ወይም ይቅር እንባባል እየተባባሉ ዕንባ በመራጨት የሚገላገሉት አይደለም፡፡ ዋናው መፍትሔ ያለው አሸማቃቂነትም ተሸማቃቂነትም ተከፋፍሎ የመድቀቅ ገጾቻችን መሆናቸውን ማስተዋልና ለዚያ ያጋለጡንን ብሔርተኛ ገዥነትንና አወቃቀርን ማረም ላይ ነው፡፡

- Advertisement -

ክፋቱ ሕዝቦች ዓይተውት የማውያቁትን ጭካኔ ካዩና በሚሊዮን ቁጥር ተፈናቅለው ምፅዋት ጠባቂ ከተደረጉም በኋላ እንኳ፣ የችግሩን እውነተኛ ምንጭ መቀበልና ከጥፋት ተምሮ በሚያዛልቅ መፍትሔ የሕዝብን ሰላም መካስ ሰማይን እንደ መቧጠጥ መክበዱ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ገዥነት ውስጥ የቆዩ ግትር ብሔረተኞች ‹‹ችግሩ የአፈጻጸም እንጂ የአወቃቀሩ አይደለም›› እያሉ ሲያጭበረበሩ፣ የብሔርተኛ ገዥነቱን ተራ ይናፍቁ የነበሩ ተቁለጭላጮች ደግሞ ችግሩ የብሔር አደረጃጀትና የአወቃቀሩ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲ ስላልነበረ ነው እያሉ ራሳቸውንም ሕዝብንም ሊያሞኙ ይለፋሉ፡፡ ከእነዚህ በተቃራኒ ደግሞ የብሔረሰብ ማንነት ፖለቲካን በአግላይነት ጥለው፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዜግነት መብት ላይ ነው መቋቋም ያለበት የሚል ፖለቲካን የሚያራምዱ እናገኛለን፡፡

ዜግነት ላይ ብቻ የተሰካ ፖለቲካ ለብሔርተኞች ጥሩ ማደናገሪያ ሆኗቸዋል፡፡ ‹‹ማንነትህን ጥለህ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብቻ ሁን የሚሉ መጡልህ›› እያሉ ሕዝብ ያምታታሉ፡፡ የፖለቲካ ኪሳራቸውን ለመጋረድ የትችት ስንቅም አድርገውታል፡፡ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ለ27 ዓመታት የተባዛን የብሔርተኛ ምላስና ድርጅት ሁሉ፣ በምን መተትና ተዓምር ዘለውና አፍዝዘው የዜግነት ፖለቲካ ሰገነት ውስጥ እንደሚያስገቡንም ተዓምር ሆኖብል፡፡ በእነዚህ ሁለቱ ፅንፎች መሀል በኅብረ ብሔራዊ ግቢ ውስጥ የብሔረሰቦች መብትን ከዜግነትና ከሰብዓዊ መብት ጋር አጣጥሞ ለማስከበር የቆሙት (የብሔር መብት መረጋገጥን ከአግላዩ የብሔር ፓርቲ ገዥነት ጋር ያላሳከሩት) ወገኖች ተጣብቀውና የሁለቱ ጫጫታ አጥልቶባቸው ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የእኩልነት ጥማት እውነተኛ መልስ በሚያገኝበት ፈር ውስጥ የመግባቱ ነገር፣ ሁለቱ ጫፎች ከድርቅና ወጥተው ወደ መሀል ለመምጣት በመቻላቸው (ወይም ጫፎቹ እየሳሱ በስተመሀል ያሉት በመጎልበታቸው) ይወሰናል፡፡

አዕምሮን ክፍት አድርጎ ለመወያየት ዝግጁነት ካለም ወደ መሀል መምጣት ይህን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ እየተባለ ያለው ሁለቱም ወገኖች ሙጥኝ ያሏቸውን መብቶች አካቶ የሚያስተናግድ ፌርማታ ነገር ወይም ድልድይ ቢጤ ምዕራፍ ይኑረን፣ በእዚያ ቆይታችን የምናገኘውን ልምድና ትምህርት ቀስመን እንደገና ወደፊት እንራመዳለን ነውና፡፡ ይኼንን ያህል ቀላል የሆነው ነገር ላይ ሁለቱ ወገኖች ስምምነት የመድረሳቸው ጉዳይ ግን ያሳስባል፡፡ መጠማመድ አልበጀንም በሚባልበት በዚህ ወቅት እንኳ፣ በሁለቱ ወገኖች ዘንድ ተሸፋፍኖ የሚራጭ ድፍርስ ስሜት አለ፡፡ በቴሌቪዥን ውይይት ላይ ደመ መራራነትና ጨዋነት ተላብሶ ሲወራጭ አስተውለነው ስለወደፊታችን ሠግተናል፡፡ የዜግነት ፖለቲከኞች በሁሉም አካባቢ ጥቃት ሳያገኛቸው አቋማቸውን የማራመዳቸው ነገር በአሁኑ ሁኔታ የማይሞከር ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ እውነታ መከራከሪያዎቹ ሁሉ የተውለቀለቁበት፣ ብሔርተኝነት ይህንን ገመናውን ለመሸፈን ጉልበተኛነትን ቢያንስ በእጅ አዙር ከመጠቀም አይመለስም፡፡

 መንግሥት ተጠናክሮ በየትም የአገሪቱ ሥፍራ ሐሳብን የመግለጽ መብትን ማስከበር አለበት ይባላል፡፡ ይህ ግን አሁንም በውድም በግድም ሕግ በማስከበር የሚሰምር አይደለም፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ሕዝብን ያነቃነቀ ሞገድ ተፈጥሮ ሕግ አስከባሪነት ከሞገድ ጋር የሚተናነቅበት ሁኔታ እንዳይመጣ፣ በሁለቱ መካከል የተጣበቀው አማካይ አማራጭ በአገሪቱ የፖለቲካ ሜዳ ውስጥ አይሎ መውጣቱ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የብሔር ማንነትን እውነታ የማይዘነጉት እነ ኦዴፓ ‹‹አጋር›› ይባሉ ከነበሩ ቡድኖች ጋር አንድ ላይ ሆነው፣ ከብሔርተኛ የአስተሳሰብና የአደረጃጀት ቁርጥራጭነት ወደ ውህድነት ለማለፍ መወሰናቸው ጉልህ እመርታ ነው፡፡

 እውነቱን ለመናገር ዛሬ የመጠማመድና የበቀል ፖለቲካ መጉረጥረጥ ለአገርና ለሕዝብ አለመጥቀሙ ተሳጥቶ ዓይኑን ሰበረ እንጂ፣ ገና ከኢትዮጵያ ፖለቲካና ከብዙኃን መገናኛ ተገፍቶ ዳር አልወጣም፡፡ በፊት ትምህርት ቀመሶችንም ሕዝብንም በጥላቻ ምች እያጠናፈረ ይጥል የነበረው የሕወሓት ኢሕአዴግ አገዛዝ ነበር፡፡

ሕወሓት ከበላይነት ዘወር ባለበትና የዴሞክራሲ ለወጥ በተጀመረበት የዛሬ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ፣ ቀደም ሲል የሕወሓት ኢሕአዴግ አገዛዝ ቅጥቀጣ በጥላቻና በበቀል ያጠናፈራቸውና ከዚያ መላቀቅ የተሳናቸው ወገኖች ብድር የመለሱ መስሏቸው ዋና የጥላቻ አራቢነቱን ሚና ተያይዘውታል፡፡ ሕወሓትን የሁሉ ቀውስና ችግር መንስዔ አድርገው ያላንዳች ማስረጃ በሚዲያ ከመርጨታቸውም በላይ፣ በኢትዮጵያና በትግራይ ሕዝብ ላይ የወረደ ሳጥናኤል እሱ ካልጠፋ ጤና የማይገኝ አድርጎ እስከ መለፈፍ ድረስ ያክፋፋሉ፡፡ በሕወሓታዊ ተዋናይነት አጎብዳጅነት ያለፈ ሆኖ ሳይተናኮሉትና ሳይነክሱት የሚምሩት ሰው የለም፡፡ እንደ ጌታቸው ረዳና በረከት ስምዖን ዓይነቱማ ከአንደበት እንዴት ሊጠፉ! በረከት ስምዖንና ታደሰ ‹‹ጥንቅሹ››፣ የ‹‹ጥረት››ን ኩባንያ ለምዝበራ አጋልጦ በመስጠት ተጠርጥረው ሲታሰሩ፣ ከፍርድ በፊት እንደ ንፁህ የመቆጠር መብት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲተከል ማገዝ ይቅርና ሰዎች እንዳይፈቱ የሚያደርግ ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዘ ብርቱ ወንጀል እንዲፈለግ እስከ ማማከር ድረስ የታወረ በቀል ሲረጩም ሰምተናል፡፡

ይህንን የመሳሰለ ዘመቻ በማድረጋቸውም የአማራንም ሆነ የትግራይን ሕዝብ ወይም በደፈናው የኢትዮጵያን ሕዝብ የጠቀሙና ከሕወሓት አጋንንት የጠበቁ (የለውጡ ባለውለታ የሆኑ) ይመስላቸዋል፡፡ በተግባር የተያያዙት ግን ጥላቻና በቀልን እየኮተኮቱና እያፋፉ ህሊናን መመረዝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የዕርቅና የሰላም ደመና እንዳይከማች ማወክ፣ ከለውጥ ንቁ አጋዥነት ይልቅ ፍጥጫና ምሸጋ ውስጥ ያለው ሕወሓታዊ ክንፍ በዚያው እንዲቀጥልበትና ይበልጥ ለውጡን እንዲርቅ፣ ርቆም የትግራይ ሕዝብን ህሊና በተከበብን ውስወሳ ገንዞ እንዲቆይ መጥቀም ነው፡፡ በአጭሩ እያገለገሉ ያሉት ለውጥን ሳይሆን ፀረ ለውጥን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሰላምና ፍቅር ሳይሆን መሸካከርና መበቃቀልን ነው፡፡ ሕወሓቶች ባለፈ የበላይ አገዛዛቸውና እብሪታቸው ምን ያህል ጠንቅ እንዳመጡ፣ የለውጥ ክንፎችና ሌሎች ትግራዊ ቡድኖች አፍረጥርጠው ለማጋለጥ ባለመቻላቸውና ከወልቃይት ራያ ጋር የተያያዘው ጣጣም በአጠቃላይ በመዋቅር ማሻሻያ በኩል ፖለቲካዊ ቀውስ በማይጎትት መንገድ ሊፈታ የሚችልበትን መንገድ ለማመላከት ባለመድፈራቸው፣ የጥላቻና የበቀል ኃይሎች መርዘኛ ጥፋታቸውን እያሟሟቁ እንዲቀጥሉበት ፈቅደውላቸዋል፡፡

ጀብደኛ ሆይ ሆይታና ሚዲያ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ጥላቻና ቂም ባጠናፈራቸው ኃይሎች አካባቢ ጀግንነት ሆኖ አዕምሮና ዓይናቸውን የሞላው ጀብደኝነት ነው፡፡ ጀብደኛ ነገር አድርጎ ማጣፊያ ሲያጥር ቴዎድሮሳዊ ፅዋ መጎንጨት ቁንጮ የጀግና ሙያ ነው፡፡ በሕግ ከለላ ራስን መጠበቅ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ማስረጃ ሊያቀርቡ የማይችሉበትን አናዳጅና ጅል ንክሻ ተናክሶ (ለምሳሌ ‹‹ሕወሓት በረሃብ ጊዜ የዕርዳታ እህል ሸጦ መሣሪያ ገዝቷል›› የሚል ነገር ተናግሮና ጽፎ) በእስር መማቀቅ፣ ለስደት መዳረግ የቆራጥ ጀግና ገድል ነው፡፡ አንገቱን ደፍቶ ወይም የፖለቲካ ፍትጊያ ውስጥ ሳይገባ በሙያው የተመሰገነና (ገዥውም ቡድን ለዝና መነገጃነት ሊጠቀምበት የበቃ) የሥራ ፍሬ ያሳየ ባለሙያ አድርባይ ወይም ሆዳም ሊባል ይችላል፡፡ 

ጀግንነት ከዘራፍ ባይነት ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ በሚያስገኘው ውጤት የሚለካ መሆኑ፣ በዛሬዋ የኢትዮጵያ ምድር እንኳ ተገቢውን ሥፍራ ገና አላገኘም፡፡ በዘመነ ራስ ተፈሪ መኮንንም ሆነ በአፄ ኃይለ ሥላሴነት ጊዜ የዘመኑን ዓለማዊና መንፈሳዊ ገዥዎች በጥበብ ይዞ ለውጥ ለማምጣት አቅቷቸው፣ በብቸኝነት ተቆራምደው ወይም በሴራ ተጠልፈው ካለፉት ትምህርት ቀመሶች ይበልጥ ለጊዜው ባህልና ሥልጣን እየሰገዱ ብዙ ፍሬ ያፈሩ ብዙ ጀግኖች ከእነ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል አንስቶ እስከ ወለጌው አማኑኤል አብርሃም ድረስ (ከዚያም ወዲያ) መቁጠር ይቻላል፡፡

በሕወሓት ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን ውስጥ ገና ከአጀማመሩ ከዓይን ያውጣው/ያዝልቅለት የተባለ ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ ወዲያው መለስ ዜናዊን ጭምር ባልማረ ጅል ንክሻ ራሱን በተቃዋሚነት አስፈርጆ ራሱን ሲቀጭ (ለሕዝብ ኪሳራ፣ ለግለሰብ ጋዜጠኞቹ የስደት እንጀራ መጋገሪያ ሲሆን)፣ ከዚያ በተቃራኒ ደግሞ በፀረ ሰላምነት ተወንጅሎ ከሥራ ውጪ ለመሆን ራሳቸውን አጋልጠው ሳይሰጡ፣ በአገም ጠቀም፣ በቆንጠጥ ለቀቅ ብልኃት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ግንዛቤና ሰላማዊ ለውጥን ለማጎልበት የጠቀሙ ትንታኔዎችንና መረጃዎችን በማቅረብ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ ጥቂት የግል ሚዲያዎች ነበሩ፣ ዛሬም እያገለገሉ ነው፡፡ ይህ በአጭር ከቀሩት የበለጠ ጀግንነት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሚናን የሚጫወቱ ሚዲያዎች በአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ውስጥ ዋናውን ሥፍራ ለመያዝ አለመቻላቸውና ሾኬና መሰሪነትን የራቀ ለሕዝብና ለሀቅ የታመነ ሥነ ምግባር የሚዲያ ሥራን አለመግዛቱ፣ ከዴሞክራሲ ለውጡ ጮርቃነትና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና ዕርቅ አኳያ ‹‹እስከ ጊዜው እንለፈው›› የሚባል አይደለም፡፡

ሚዲያዎቻችን ላይ ያለው ችግር በዚህም ሆነ በዚያ በኩል የፖለቲካ ፓርቲ ልሳን/አጨብጫቢ የመሆን ወይም የቂም አናፋሽ የመሆን ችግር ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ቡና አንቃራሪና መጠጥ ገልባጭ ያላወቁትን፣ ያላጣሩትን ጉዳይ በመሰለኝና በግምት መንዳትና ማዛቆንም አለበት፡፡ በ2011 ዓ.ም. የካቲት የመከላከያ ሠራዊት ቀን ከመከበሩ ጋር ተያይዞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እያነሳሱ፣ መከላከያ የሕገ መንግሥቱ ጠባቂ መባሉንና የትግራይ መንግሥት ‹‹የማንነትና የወሰን ጉዳይ ኮሚሽን›› መቋቋምን ከሕገ መንግሥት ውጪ ማለቱን አገናኝተው፣ ‹‹የትግራይ መንግሥት ለመከላከያ ደብዳቤ ቢጽፍስ . . .? መከላከያ ምን ይወስናል . . . ?›› የሚል ቅጥ አምባሩ የጠፋ መከላከያ ደብዳቤ እየተቀበለና አቤቱታ እየሰማ ሕገ መንግሥት የሚጠብቅ ያስመሰለ ደንባራ ጭውውት ሲደረግ በ‹ኢሳት› የሰማ፣ የምለውን ችግር ይረዳል፡፡

እንዲህ ያሉ ሊጥ ነገሮች በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ላይ እንዲረጩ መፍቀድ፣ በምንም ዓይነት ለዴሞክራሲ መጎልበት ከሚደረግ ትዕግሥት ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም፣ ሥርዓት አልባነት እንዲደገስ መፍቀድ እንጂ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹መከላከያ ብሔር የለውም፣ ወዘተ›› የማለታቸውም መልዕክት፣ መከላከያ አሁን የተያያዘውን የኢወገንተኛነት ለውጥ በማበረታታት ላይ አትኩሩ ማለት መሆኑን መረዳት ከባድ አልነበረም፡፡ ለውጡ በቋፍ ላይ ያለበትን የአሁኑን ወቅት አጢኖ ከመልዕክቱ ጋር በመግባባት ፈንታ፣ ‹‹መከላከያ ብሔር ነበረው . . . ወገንተኛ የሆነ ብዙ ጥፋት ሠርቷል . . . አሁንም ኢወገንተኛ የመሆኑ ነገር ገና ተጀመረ እንጂ . . . ›› እያሉ መቀበጣጠርም ኃላፊነት ከሚሰማው ጋዜጠኝነት የሚጠበቅ አልነበረም፡፡

የለውጡ መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ መሰናዶ አጠናቆ የሚዲያዎች እንቅስቃሴ ሙያቸው በሚጠይቀው ሥነ ምግባር ውስጥ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ሚዲያዎችም ራሳቸው ሙያቸውን በሾኬና በፓርቲነት ባህርይ ከሚያበሻቅጡ ተግባራት የሚከላከሉበት ሥርዓት በቶሎ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ በተቃዋሚነት ወይም በአጨብጫቢነት ውስጥ ይዳክሩ የነበረበትን ባህል አራግፎ የተዋጣለት የሕዝብ አገልጋይ መሆን በቀላሉ የሚሰምር አይደለምና ሁሉም ነቅቶ ራሱን መፈተሽም ያስፈልገዋል፡፡

በፖለቲካ ወገንተኛነት ውስጥ ባይነከሩም፣ የጋዜጠኝነት ኃላፊነት የተገኘችን ዜና ከመነስነስ ያለፈ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ዛሬ ባለችበት ዴሞክራሲን በመጨበጥና ባለመጨበጥ የግብግብ ምዕራፍ ውስጥ የሚኖረው ኃላፊነት በጣም ትልቅ ነው፡፡ ለጋዜጠኛውም ለኢትዮጵያ ሕዝብም ህልውና በጣም አስፈላጊ የሆነውን ዴሞክራሲ ማዋለድ ውስብስብ ተግባር በሆነበት በአሁኑ ሰዓት፣ ክንዋኔዎችን ከላይ ልጣቸው ጠልቆ መግባት፣ መዝለቅና ማስተዋል፣ በአመጣጣቸው መስተጋብራዊ ግፊትና በሚያስከትሉት ተፅዕኖ ውስጥ መመርመርና መተንተን ያሻል፡፡ አሁንም በምሳሌ ሐሳቤን ላሳይ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችንና ፓርቲዎችን አያይዞ ጋሬጣዎችን እየገፉ ወደ ዴሞክራሲ ለመጓዝ፣ የኢትዮጵያ የዛሬ የፖለቲካ እውነታ በዋናነት የለገሰን (የሰጠን) እነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመሩትን የለውጥ ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን በብዙ ምኞትና ተስፋ የተከበበ፣ ብዙ ሳቢና ግፊት አድራጊ አለበት፡፡ ብሔርተኛነት ተጠራርጎ ሲወገድ እየታየው ቡድኑን የፍላጎቱ አሳኪ ለማድረግ የሚጥር እንዳለ ሁሉ፣ ብሔርተኛውም ያንኑ ያህል እንዲያውም በበለጠ ያካልባል፡፡

በቁጥር ብዙኃን ሆኖ ሳለ ከረባ የሥልጣን ድርሻ ለረዥም ጊዜ ተገልሎ ለቆየው ኦሮሞ፣ ዛሬ በሥልጣን ላይ ደመቅ ብሎ መታየት ያለው ትርጉም ቀላል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ማገርና ማስተሳሰሪያ ልጥ ኦሮሞ እንደ መሆኑና የለውጡ መሳካትና አለመሳካት ኦሮሞንና ቀሪውን ሕዝብ አንድ ላይ ለማንቀሳቀስ ከሚችል ፖለቲካዊ አመራር ጋር የተያያዘ እንደ መሆኑ፣ የኦሮሞ በመሪነት መድመቅ በመሠረቱ በዛሬዋ ሰዓት የሁላችንም ጥቅም ነው፡፡ በኦሮሞ ብሔርተኛነት ውስጥ ከዚህም የሚያልፍ ፍላጎት ኖሮት እነ ዓብይን እንደ እንቅፋት የሚቆጥር ዝንባሌም አለ፡፡ ብሔርተኛነት፣ ፀረ ብሔርተኛነት፣ ሸር፣ ውስጠ ወይራ አካሄድ ሁሉ ሠልጥኖ በኖረበት ኅብረተሰብ ውስጥ ሆኖ፣ ፍጥጫና ግብግብ ባለበት የሽግግር ምዕራፍ፣ የፌዴራል መንግሥት አመራርን የፖለቲካ ቅኔ በማይቀኙ ሰዎች አዘማምዶ ማስኬድ የዋዛ ፈተና አደለም፡፡ ፈተናው ራሱ ወደውም ሳይወዱም በቅርብ ወደሚያውቋቸው የድርጅት ባልደረቦች ማዘንበልን ያመጣል፡፡ ከዚህ የተለየ ነገር ይጠብቅ የነበረ ወይም ሰበዞችን በቅጡ ያላገናዘበ ተመልካች ደግሞ፣ ‹‹እንዲህ ከተደረገማ ከወያኔ በምን ተለዩ?›› የሚል ትዝብት በሆድ ይይዛል፡፡ በአንደበትና በብዕር ይሰነዝራል፡፡ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በተደረገ ሕገወጥ ቤት የማፍረስ ዕርምጃ ላይ የተፈጠረው ጩኸት፣ ‹‹የአዲስ አበባን የሕዝብ ጥንቅር ለመቀየር ያለመሸኛ መታወቂያ እየተሰጠ ነው›› ባዩ ‹‹ቅሬታ››፣ ‹‹አዲስ አበባ ለአዲስ አበቤ›› የሚለው እንቅስቃሴ ሁሉ፣ በኦሮሞ ልንሰነግ ነው የሚል የጥርጣሬና የሥጋት ጀርባ ያላቸው ናቸው፡፡

ይሁኑ እንጂ ሥጋቶቹን የሚቃረን ሒደት እንዳለ መረሳት የለበትም፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የፊት መሪ የሆኑበት የዴሞክራሲ ጉዞና የእነ ኦዴፓ መሀል አገሩን ከዳርቻዎች ጋር ያላላሰ ውህድ ፓርቲ ወደ መፍጠር ማምራት ሥጋቱን የሚቃረን ነው፡፡ አሁን የምንገኝበትን የፖለቲካ ዝንባሌዎች ግንኙነትና መገፋፋት በቅጡ እያስተዋልን፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አዲስ አበባን በሚመለከት የተቀመጠውን ‹‹ልዩ መብት›› ሳንዘነጋ፣ የኦሮሞንም የአዲስ አበቤንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ጥቅም አግባብቶ ለመፍታት የሚበጅ (የሁሉንም የተቻቻለ ተቀባይነት የማግኘት ዕድል ያለው) ቡድን ማነው ብለን ብንጠየቅ፣ የምናገኘው መልስ አሁን ካለው አመራር አይርቅም፡፡ አዲስ አበባ የአዲስ አበቤና የኦሮሞ ብቻ ሳትሆን የመላው ሕዝቧ እንደ መሆኗ የሁሉም ሕዝቦቿን ጠረን መያዝ አለባት፡፡ ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ሙያተኛ ቅጥር፣ ከአዲስ አበባ ባሻገር እየሄደ፣ ጥራትን መስዋዕት ባላደረገ አኳኋን ጋሞዎችን፣ ሲዳማዎችን፣ ጌዴኦዎችን፣ ሶማሌዎችን፣ አኙዋኮችን፣ ኑኤሮችን፣ አፋሮችን፣ ወዘተ፣ ወዘተ ማካተት አለበት፡፡ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ሳያገናዝቡ ብዙ የቀውስ ገደላ ገደልና የሚጋጭ ንፋስ ባለበት በዚህ የሽግግር ሰዓት፣ የግራ ቀኝ ወከባ መፍጠር የጓጉለትን ለውጥ ሁሉ የሚያሳጣ አዙሪት ውስጥ ሊከተንም ይችላል፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች መሬት ጠባቂ እንደሌለው እየተቆጠረ ከሕግ ውጪና በጉቦ እየተለባበሰ የሚያዝበት ጨለማ መወገድ አለበት፡፡ ያለ ሕጋዊ ባለቤትነት ግብር እየተቀበሉና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እያካሄዱ ሕገወጥ ግንባታን ሕጋዊ እያስመሰሉ የማሰንበቱ አሠራር መቆም አለበት፡፡ የሰነበተ ሕገወጥ ግንባታን በገንዘብና በፖለቲካዊ ድጋፍ ግብይት ወደ ሕጋዊነት ማዞርም መቆም አለበት፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ጋር ደግሞ በኪራይም በግዥም ሆነ ቤት በመሥራት መንገድ ሕጋዊ የመኖሪያ ቤት የማግኘት ጉዳይ በከተሞች ውስጥ ሁሉ መልስ ማግኘት አለበት፡፡ አሁን ካሉት የከተማ ተፈናቃዮች ውስጥ እውነተኛ ቤት የለሾችስ እንደ ምን መፍትሔ ያግኙ? ችግሩ እንዳያዳግምስ ምንድነው መደረግ ያለበት? ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ይዞ እነዚህን ለመሳሰሉ ጉዳዮቻችን መልስ መፈለግ፣ ሐሳቦችን መተንተንና ማስተንተን ከጋዜጠኞች ይጠበቃል፡፡

የጉዳዮች በሚዲያ መስተንግዶ እንደ ጉዳዮቹ ባህርይ፣ እንደ ወቅታዊነታቸውና ለሕዝብ እንዳላቸው ከጊዜ ጋር ያልተያያዘና የተያያዘ ፋይዳ የሚወሰን ነው፡፡ ለግንዛቤ እንዲበጅ ልጠቃቅስ፡፡

ወቅታዊ የሆኑ ድርጊቶች መገለጣቸው ከመዘዝ ይልቅ አፋጣኝ ዕርማትን የሚያነቁ ሲሆን፣ ሚዛናዊና የተሟላ መረጃ ለማግኘት ተሞክሮ የተገኘው ርጋፊም ቢሆን፣ የተሟላ መረጃ ለማግኘት እየጣሩ በእጅ ያለችውን መረጃ ሳያጋንኑ በማቅረብ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ለበጎ ዕርምጃና ዕርማት ማንቃት አግባብ ይሆናል፡፡

ጤና ነክ የሆኑትን መድኃኒትና መቆነጃጃዎችን በተመለከተ የተገቢውን ሙያተኛ ምስክርነትና ምንጭነት ሳይንተራሱ ለሕዝብ መበተን (ዛሬ በ‹‹ኤፍኤም›› ሬዲዮና በቲቪ አስተናጋጆች በኩል ሲደረግ እንደምናየው) ፈጽሞ መቀጠል የሌለበት ጥፋት ነው፡፡

ለዛሬው ወቅት አጣዳፊ ፋይዳ የሌላቸውና ሊያወዛግቡ የሚችሉ ታሪክ ቀመስ መረጃዎችን የግራ ቀኝ ማነፃፀሪያዎችን አጎዳኝቶ በማቅረብ፣ ሕዝብ የራሱን የግንዛቤ ፍርድ እንዲያደርግ ማገዝ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ ይህንን ያሟላ የሚዲያ ዝግጅት ለማድረግ ተሞክሮ የተገኘው አንድ ዓይና መረጃ/ምስክርነት ብቻ ቢሆን፣ የሌላው ወገን መረጃ ከመጠይቅም ሆነ ከጽሑፍ ወይም ከሰነድ ምርመራ እስኪገኝ ድረስ ይቀመጣል እንጂ፣ ‹‹ተባባሪ አጣሁ›› ወይም ‹‹የተለየ አመለካከት አለኝ የሚል ካለ እናስተናግዳለን›› የሚል ማስታወቂያ ተመርኩዞ ማቅረብ፣ ለአንድ ዓይናው አወዛጋቢ መረጃ ዓይን አይጨምርለትም፡፡ በሐሜት ቀለበት እንዳይጠለፍ ያልተጠነቀቀ ሚዲያ ተሰሚነትና ተከባሪነቱን ለጉዳት ይሰጣል፡፡

የፖለቲካ ሰዎችን በቃለ መጠይቅ በማቅረብ ረገድ በጊዜያችን ፈር ቀዳጅና ለብዙ ሚዲያዎች ምሳሌ የሆነው ‹‹ናሁ›› ቲቪ፣ በ97 የምርጫ ጊዜ የነበረን የ‹ቅንጅት› ክፍፍል ታሪክ፣ በልደቱ አያሌው ተበደልኩ ባይ ምላስ ብቻ በማቅረቡ የዛሬዎቹን የእነ ብርሃኑ ነጋን የፖለቲካ ተቀባይነት ለመጉዳት ለሚሻ መሰሪነት አውቆትም ሆነ ሳያውቀው መሣሪያ ሆኗል፣ ያውም ደጋግሞ እያቀረበ፡፡ የ‹አርበኞች› ታጋይ ነበርን የሚሉ ሰዎች በቃለ መጠይቅ የደረደሩት ስንክሳርማ ከለየለት ዘመቻ የማይለይ ነበር፡፡

አፋጣጭ ጥያቄ የሚያቀርቡ ቃለ መጠይቆች መጀማመራቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለት ችግሮች ይታያሉ፡፡ አፋጣጭ ጥያቄ የማቅረቡ ነገር ቃለ መጠይቅ ከሚሰጠው ሰው  ባለሥልጣን  መሆን አለመሆን፣ ወይም ክብረ ብዙ መሆን አለመሆን ጋር የሚሰለብና የሚመዘዝ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛ የሞጋች ጥያቄዎች ዓላማ የተሟሉ መረጃዎችን አደራጅቶ እየመዘዙና የማለባበስ መንገዶችን እየከለከሉ እውነት ላይ በመድረስ የሕዝብን ግንዛቤ መጥቀም እንጂ፣ በሾኬ (Crooked) ጥያቄዎችና መሞገቻዎች እንግዳውን እያንጨረጨሩ ለማንደባለል የመሞከር ወይም ኃይለኛ ጠያቂ ተደርጎ የመፈራት ፍላጎትን የማርካት ጉዳይ አይደለም፡፡

የዛሬ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በኢሕአዴግ ሕወሓት ዘመን ደርተው ከቆዩ የሾኬና የማምላጫ ወልጋዳ ሥልቶች ለመላቀቅ ብርቱ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ አሁንም ምሳሌ ልስጥ፡፡ የሳዑዲው ተወላጅ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊን የግፍ አገዳደል አደባባይ አውጥቶ ለመፋረድ በመታገል ረገድ የቱርክ መሪ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዟል፡፡ ይህ የሆነው ወንጀሉ ከቱርክ ምድር ጋር ስለተያያዘ ብቻ ሳይሆን፣ ጎራ ነክ ጀርባ እንዳለውም ይታወቃል፡፡ የጀርባም የፊት ለፊትም ሺሕ ምክንያት ቢኖርም ግን፣ የጋዜጠኛው የግፍ አገዳደል ፍትሕ እንዲያገኝ የመቆምን ትክክለኝነትና ተገቢነት አይቀንሰውም፡፡ ሁለቱን አገናኝቶ ለጋዜጠኛው የመቆም አቋምን ለማዋደቅ መሞከር ሙልጭ ያለ ወልጋዳነት ይሆናል፡፡

በእኛ አገር ዘልማድ ቢሆን ኖሮ ታዲያ፣ ‹‹የቱርኩ ኤርዶዋን በግፍ አስሮ ለሚያሰቃያቸው ሰዎች ምነዋ ሲቆረቆር አላየነው? ዛሬ ለሰብዓዊ መብት ማሰብን ከየት አመጣው? ይህ ተራ አጭበርባሪነትና አካባቢውን የማመስ ሥውር ተንኮል ነው! …›› የሚል ስንት ጉድ በተደረደረ ነበር፡፡ በሕዝብ መታመንንና መከበርን የሚሹ ሚዲያዎች ለጥላቻ/ለቂም፣ ለወሽካቶች፣ ለመሰሪዎችና ለፖለቲካ ወገናዊነት ፈረስ የማያደርግ የአሠራር ዘልማድ ማበጀት ግዳቸው ነው፡፡ በዚህም ልፋታቸው የኢትዮጵያ ሕዝቦችን መልካም ግንኙነት በእጅጉ ይጠቅማሉ፡፡

ሰፊ የጋራ መድረክ የፈጠሩትና በአንድ አዳራሽ ስጥ መወያየት የጀማመሩት የዛሬዎቹ የፖለቲካ ቡድኖች፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሰላምና ዕርቅ በማገዝ ረገድም ሆነ ሚዲያዎች የሙያ ሥራቸውን የፖለቲከኝነት ሰለባ ከማድረግ እንዲርቁ የሚጫወቱት ሚና የዋዛ አይደለም፡፡ በቅርቡ በጀመሩት አኳኋን ብስል ምሁራዊ ጥናቶችን መጠቀም ባወቀ መልክ በአንኳር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩና ለመግባባት ያለሙ ውይይቶችን ፓርቲዎች እያካሄዱ በተስማሚ ሰዓት ለሕዝብ እንዲሠራጩ ቢያደርጉ፣ የዴሞክራሲን ደመና በማዳበርና የኢትዮጵያን ሕዝቦች በማቀራረብ ረገድ የሚያመጡት ለውጥ አሁን ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ ነው፡፡

ሁለት ጉዳዮችን እንደ ምሳሌ ወስጄ ነጥቤን ልፈልቅቅ፡፡ አንደኛ ማርክሲዝምና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል አስተሳሰብ ከኢትዮጵያ ካልተነቀለ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ (የብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲ) የማይሰምር የሚመስላቸው ሰዎች በዩኒቨርሲቲ አስተማሪነት ደረጃም ዛሬ እናገኛለን፡፡ ማርክሳዊ አስተሳሰብ የከበርቴ ዴሞክራሲ ፍሬ መሆኑ፣ በታላላቆቹ አገሮች የከበርቴ ዴሞክራሲ ውስጥ የምናገኛቸው ‹‹የሶሻሊስት›› ፓርቲ፣ ‹‹የሠራተኛ›› ፓርቲ፣ ‹‹የሶሻል ዴሞክራሲ›› ፓርቲ የሚባሉ ሁሉ የሰው ልጅን ወደ ፍትሐዊ ሥርዓት እንደምን መውሰድ ይቻላል የሚል የአዕምሮና የትግል ጥረት ውርዴዎች፣ ወይም ከፀረ ከበርቴ የፍትሕ ትግል ከተገኙ እሴቶችና አስተሳሰቦች ጋር የከበርቴ ፖለቲካን አዳቅሎ ሥርዓቱን ከነውጥ የማዳን ውጤት እንደሆኑ በእኛ አገር የሚታወቅም አልመስል ብሏል፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራምና ‹‹እኔ ብቻ ልክ›› ባይነት በውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲም ሆነ ከዚያ ውጪ ባለ የብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲ ውስጥ፣ በክርክርና በትንታኔ ለመርታት የሚሠራ እስከሆነና በሕዝብ ምርጫና ፍላጎት የሚወዳደር እስከሆነ ድረስ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲና የኅብረተሰባችንን ፍትሐዊነት በማበልፀግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ያልተገነዘበ አያሌ ነው፡፡ እንኳን ስለማኅበራዊ ፍትሕ የሚጨነቁትን ማርክሳዊና ሶሻሊት አስተሳሰቦች ይቅርና የቀኝ አክራሪ የሚባሉ አስተሳሰቦችን መድረክ ነፍጎ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንደምን በሐሳበ ብዙነት ሊበለፅግ ይችላል!? ከሚጣሉ አስተሰሳቦች ጋር ተቻችሎ የመኖር አቅምስ እንደምን ሊያጎለምስ ይችላል!? በዚህ ጉዳይ የምሁራኑና የፖለቲከኞቹ መወያየትና የራሳቸውንም የሕዝብንም ህሊና ማስፋት በዛሬ ጊዜ ወቅታዊ ነው፡፡

ሁለተኛ ብሔርና የዜግነት መብቶች ይጣላሉ? የብሔር መብት መረጋገጥና ራስን በራስ ማስተዳደር የግድ የቋንቋ አጥር መሥራትንና የብሔር ፓርቲ መፍጠርን ይሻሉ? ሁለቱ መብቶች በኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎችና በኅብረ ብሔራዊ የአስተዳደር ግቢዎች ውስጥ መሟላት አይችሉም? በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሁራንና ፓርቲዎች ‹‹ዓይኔን ግንባር ያድርገው›› ከማለት የወጣ ውይይት ማካሄድ ከተሳካላቸው፣ ከስንጥርጣሪ የፖለቲካ ቡድንነት ወጥተው በመሰባሰብ ጥቂት ግን ትልልቅ ተፎካካሪ ፓርቲ የመሆን ጉዞ ውስጥ መግባት ይችላሉ፡፡ ይህ ሒደት መጣ ማለት ደግሞ ተከታትፎ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አመለካከት እየተያያዘ ሰላምና ዕርቁ ተቃና ማለት ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...