ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ
ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) በተለይም በኢትዮጵያ ግብርና መስክ ከሚጠቀሱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ለዓመታት ከመምህርነት እስከ ተማራማሪነትና አማካሪነት በካበተው ተሞክሯቸው፣ በሚያቀርቧቸው ጥናታዊ ሥራዎችና በሚጽፏቸው መጻሕፍት በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ በጉልህ የሚታወቁት ደምስ (ዶ/ር)፣ ከሙያቸው አኳያ መንግሥትንም ሆነ ሌሎች አካላትን በድፍረት በመተቸት የሚታወቁና ለሙያቸው ተገዥ ከሚባሉ ምሁራን መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በበርካታ አገራዊና አኅጉራዊ ጥናቶችና ምርምሮች ላይ በመሪነት በመሳተፍ አስተዋጽኦ ካበረከቱባቸው መካከል ጎልተው የሚጠቀሱት፣ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ዝግጅት ወቅት ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብትን በማካተት ለድህነትና ለረሃብ ቅነሳ ሥራዎች 36 ቢሊዮን ብር መመደብ አለባት በማለት የተከራከሩበት የጥናት ሥራቸው አንዱ ነው፡፡ በመላው አፍሪካ ደረጃም የአፍሪካ ሁሉ አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (Comprihensive Africa Agricultural Development Program – CAADP) በመባል የሚታወቀው በትልቁ ከሚታወቁበት ሥራቸው አንዱ ነው፡፡ ይኼንን ፕሮግራም በማስተባበርና ከጥናት ወደ ተግባር በማሻገር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮችም ለዚህ ፕሮግራም ማስፈጸሚያነት ለግብርና ዘርፍ በዓመት እስከ አሥር በመቶ ከኢኮኖሚያቸው ለመበጀት የተስማሙበት ሰፊ ፕሮግራም ነው፡፡ እንዲህ ባሉት ሥራዎች የሚታወቁት ደምስ (ዶ/ር)፣ በምሥረታ ላይ የሚገኘውን የግብርና ዘርፍ የምሁራን አማካሪ የቴክኒክ ቡድንንም በሰብሳቢነት እያደራጁ ነው፡፡ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ መንግሥት በመስኖ ልማት መስክ ለመሥራት ስላቀደው ጉዳይ፣ ስለአገሪቱ የስንዴ ግዥ ደባዎችና ስለሌሎችም የግብርናው ችግሮች ብርሃኑ ፈቃደ ከደምስ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ የወጣው የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮችና የኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ ሪፖርት በኢትዮጵያ ከ8.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም የሚያሳየው ግብርናው ምርት በማምረት ረገድ ብዙ እንደሚቀረውና ዓመታዊ ዕድገቱም ቢሆን ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች አኳያ በየጊዜው ቅናሽ እያሳየ እንደመጣ ነው፡፡ በጠቅላላው በዚህ መስክ ስላለው ሁኔታ እርስዎ ምን ይላሉ?
ደምስ (ዶ/ር)፡- እስካሁን በግብርናው መስክ ብዙ ተሠርቷል፡፡ አንዳንድ ውጤቶችም ተገኝተውበታል፡፡ ከምግብ ዕርዳታ አኳያ አያይዘህ እንዳነሳኸው በዘርፉ የተገኙት ውጤቶች በቂና አመርቂ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና መስክ አዎንታዊ ለውጦች ስለመመዝገባቸው ግን ማመን አለብን፡፡ እኔ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያ መናገር የምችለው በተጨባጭ እውነታዎች ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ዕድገትን እንዴት ነው የምንለካው? ዕድገቱን የምንለካው እየጨመረ በሚሄደው ምርትና ምርታማነት ደረጃ ነው? ወይስ በዓመቱ በአንድ ግለሰብ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ልኬት ነው? እንዲህ ያሉ መለኪያዎችን መጠቀም ምናልባት ዘርፉ የሚገኝበትን ትክክለኛ ሁኔታ ሊያመላክተን ይችላል፡፡ በጠቅላላው ሲታይ ግን አንዳንድ ውጤቶች ማሳየት የቻለ ዘርፍ ስለመሆኑ ልንስማማ እንችላለን፡፡ ችግሩ ምንድነው ያልን እንደሆነ ግን፣ ለምሳሌ አንዳንድ መለኪያዎች በኢትዮጵያ የሚታየው የድህነት መጠን እየቀነሰ እንደመጣ የሚያመላክቱ ቢሆኑም፣ ረሃብ ወይም የምግብ እጥረት ግን በአገሪቱ በሰፊው የሚታይ ችግር እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ በአንዳንድ ኪስ ቦታዎች ረሃቡ በሰፊው ይታያል፡፡ የጠና ችግር ነው፡፡ በግብርናው ዘርፍ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው፡፡ ባለሥልጣናት ብዙ ጊዜ ይህን እናደርጋለን፣ ለግብርናው መስክ እንዲህ ታቅዷል ሲሉ እንሰማለን፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ግብርናው ሜካናይዝድ በሆነ መንገድ ሰፋፊ የእርሻ ሥራዎች እንደሚበራከቱ ሲያወሩ እንሰማለን፡፡ አንዱንም በአግባቡ ሲፈጽሙት ግን አናይም፡፡ በርካታ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ ይባላል፣ ግን አንዱንም በተግባር ሲተረጎም አናይም፡፡ ግብርናው ዝቅተኛ የኢንቨስመንት ዕድል ነው ያገኘው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ኢንቨስት የተደረገባቸው የዘርፉ ሥራዎችማ ኪሳራ ብቻ ነው ያስከተሉት ማለት ይቻላል፡፡
ለአብነት ያህል በቅርቡ የወጣው ‹‹የድህነትና የረሃብ ስትራቴጂካዊ ግምገማ›› የተሰኘ ሪፖርት በሥራ አጋሮቼ የተሰናዳ ሲሆን፣ ሪፖርቱ እንዳመለከተው የግብርና ልማት ሠራተኞችን ለማሠልጠን የወጣው ኢንቨስትመንት የገንዘብ ብክነትና ኪሳራ ያስከተለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ እስካሁን ከ80 ሺሕ በላይ የልማት ሠራተኞች በመላ አገሪቱ ሠልጥነዋል፡፡ ይኼንን ለማሳካትም በርካታ ገንዘብ ኢንቨስት ተደርጎ በርካታ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህ ሳቢያ ኢትየጵያ ከቻይና ቀጥላ በግብርና ባለሙያዎች ወይም በግብርና ልማት ሠራተኞች ከዓለም ሁለተኛዋ አገር ለመሆን የበቃችበትን ሰፊ ኢንቨስትመንት አካሂዳለች፡፡ ይኼንን አድርገን ብዙ ገንዘብ አውጥተን ለምንድነው ያልተሳካልን ካልከኝ፣ እኔ ከዚህ ቀደም ባጠናሁት መሠረት ከ80 በመቶ በላይ ያሠለጠንናቸው የግብርና ልማት ሠራተኞች ለዘርፉ የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት የማይችሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ብቁ አይደሉም፡፡ ወይም ዘርፉን ጥለው ወደ ሌላ ሥራ ይሄዳሉ፡፡ የተጠቀሱት የሥራ አጋሮቼ ሪፖርት እንዳሰፈረውም 64 በመቶ የግብርና ልማት ሠራተኞች በቦታቸው የሉም፡፡
ሪፖርተር፡- ይህን ያህል ብዛት ያላቸው ባለሙያዎች ከሠለጠኑ እንዴት ነው ብቃት የላቸውም የሚባለው?
ደምስ (ዶ/ር)፡- በአንድ ወረዳ እስከ 150 የሚደርሱ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ተሠማርተው ገበሬዎችን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ ይሁንና በዚህን ያህል መጠን አለ የሚባለው ባለሙያና በአካል ወረዳዎቹ ጋ በመሄድ የምታየው አይገናኝም፡፡ የተመደበው የልማት ባለሙያ በቦታው የለም፡፡ ልምድ ያለውና በርካታ ሥልጠናዎችን የወሰደው ባለሙያ ሥራውን ለቆ ሄዷል፡፡ በእሱ ምትክ አዳዲስ ሠራተኞችን ነው የምታየው፡፡ ከፍተኛ ፍልሰት አለ፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ነባሩ ባለሙያ በአዲስ ሠልጣኞች ተተክቷል፡፡ አንድ የግብርና ልማት ሠራተኛ በመጀመርያው ዓመት ውጤታማ ሥራ ይሠራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛ ገበሬውም ቢሆን እንዲሁ የልማት ሠራተኛ ስለሆነ ብቻ አይቀበለውም፡፡ ራሱን ማስፈተሽና የሚቀበሉት ዓይነት ሰው ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ ገበሬው የልማት ሠራተኛውን ዕውቀት፣ ባህሪይና ፀባይ ፈተሾና አጥንቶ ነው የሚቀበለው፡፡ አንዳንዴ ገበሬው ራሱ የሚቀበለው ዓይነት ሰው ሆኖ ሲያገኘው እኮ፣ ራሱ እያሳየና እያስተማረ ነው የልማት ሠራተኛውን የሚያላምደው፡፡ ገበሬዎች ምክሩን የሚቀበሉት ዓይነት ጎበዝ የልማት ሠራተኛ ለመሆንና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት አንድ ዓመት በቂ አይሆንም፡፡ ውጤታማና ትክክለኛ ሥራ መሥራት የሚጀምረው ምናልባትም ከሁለትና ከሦስት ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ሆኖም ገና ወደ ሁለተኛውና ሦስተኛው ዓመት ወደ ዋናው የሥራ መደብ ከመግባታቸው በፊት፣ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት የልማት ሠራተኞች ሥራውን ትተው ይሄዳሉ፡፡ ይህ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ለዚህም ነው በዚህ መስክ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት ኪሳራ ነው የምንለው፡፡ ለምን ሥራውን ለቀው ይሄዳሉ የሚለው የራሱ በርካታ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ እኔ ማለት የምችለው በግብርናው መስክ በተለይም በሰው ኃይል ልማት ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ግን አክሳሪና ችግር ያለበት እንደሆነ ነው?
ሪፖርተር፡- ለግብርና ልማት ሠራተኞች ምን ያህል ገንዘብ ወጪ ሲደረግ እንደቆየ መረጃው ካለዎት ቢያካፍሉን፡፡
ደምስ (ዶ/ር)፡- ዝርዝር መረጃው የለኝም፡፡ ከበርካታ የመረጃ ምንጮች ልታገኘው ትችላለህ፡፡ ሆኖም ከመነሻው ለዚህ የሚውለው ኢንቨስትመንት ግን ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ በርካታ የሥልጠና ኮሌጆችና ፋሲሊቲዎች ተከፍተዋል፡፡ በርካታ የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛዎች ተከፍተው በርካታ የልማት ሠራተኞችን ሲቀበሉ ቆይተዋል፡፡ የልማት ሠራተኞች ብዙ ኢንቨስት ቢደረግባቸውም የተፈለገውን ውጤት አላስገኙም፡፡ የልማት ሠራተኞቹ ብቻም ሳይሆኑ፣ ገበሬዎች ራሳቸው እኮ የተሻሻለ ምርጥ ዘርና ሌላውንም የግብርና ግብዓት እንደ ልብ ማግኘት አልቻሉም፡፡ እንዲህ ያለውን አቅርቦት የሚያገኙት ለምሳሌ ከአሥር ሚሊዮን ገበሬዎች ውስጥ 30 በመቶ አይሞሉም፡፡ ጥናቶችም ይኼንኑ አረጋግጠዋል፡፡ በአገሪቱ ስንትና ስንት የምርጥ ዘር አቅራቢ ኢንተርፕራይዞች ቢከፈቱም፣ ምርጥ ዘር የሚያገኘው ገበሬ እኮ ከ15 በመቶ አይበልጥም፡፡ አንድ መሠረታዊ ችግር እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ከላይ ያለው የአመራር አካል ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ያወጣል፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ግን እስከ ታች ወርደው እንዴት እንደሚፈጸሙና በምን ዓይነት አሠራር እንደሚተገበሩ የምናውቅበት መንገድ የለንም፡፡ በአግባቡ እየተፈጸሙ ስለመሆናቸው የመከታተያ መንገዱም የለም፡፡ እነዚህን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለመተግበር በሚደረገው ሙከራ ችግሮች አጋጥመው ከሆነም፣ ችግሮቹን በምን አግባብ መፍታት እንደሚቻል የተዘረጋ ሥርዓት የለም፡፡ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ለዘርፉ የሚሰጡት ጠቀሜታ ዋጋ ከሌለው ለምንድነው እንዲሁ እነሱ ላይ ገንዘብ የምንጨርሰው? በሚሊዮኖች ኩንታል የሚቆጠር ማዳበሪያ እየገዛን እናሠራጫለን፣ ግን ውጤቱ ምንድነው? ስለምንሠራው ነገር በደንብ መነጋገር አለብን፡፡ ሥራችንን መፈተሽ አለብን፡፡ በአሁኑ ወቅት ውኃ ተኮር ግብርናን በሚገባ ማጤን ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለረጅም ጊዜ ስንመክርና ስንጮህበት ኖረናል፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ በጥንቃቄ ልንገባበት እንደሚገባ እንመክራለን፡፡ አካሄዳችንን በጣም በተጠና መንገድ በመምራት ከምንፈልገው ውጤትና ግብ አኳያ ተግባራችንን መቃኘት አለብን፡፡ ከዚህ ቀደም ውኃ ማቆር እየተባለ በርካታ ቦታ ስንት ነገር ተጀምሮ ከሽፏል፡፡ ወዲፊትም እንዲህ ያሉ ውድቀቶችን ላለመድገም በሚገባ አስበንና አቅደን ልንራመድ ይገባናል፡፡
ሪፖርተር፡- የውኃን ጉዳይ ካነሱ መንግሥትም በዚሁ አቅጣጫ ግብርናውን የመቃኘት ሐሳብ ያለው ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመስኖ እርሻ ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ የመስኖ እርሻ እንደ ኢትዮጵያ ላለ አነስተኛ ይዞታ ላለው ገበሬ አዋጭ አይደለም፣ በአማካይ ከአንድ ሔክታር በታች ለሚያርስ ገበሬ መስኖ ውድ ነው፣ አይመከርም የሚሉ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ይኼንን እርስዎ እንዴት ያዩታል?
ደምስ (ዶ/ር)፡- ለረጅም ዓመታት በመስኖ እርሻ ውጤታማነት ላይ ስከራከር ቆይቻለሁ፡፡ ከማንም ይልቅ በልበ ሙሉነት አዋጭ ነው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ የመስኖ እርሻ በኢትዮጵያ አዋጭ አይደለም ከሚሉት ጋር አልስማማም፡፡ ከበርካታ ዓመታት በፊት መንግሥት መካከለኛና ትልልቅ የመስኖ እርሻ አያስፈልገንም ሲል በሰፊው ከተከራከሩና መስኖ እንደሚያስፈልገን አጥብቀው ሲሟገቱ ከነበሩ ባለሙያዎች አንዱ ነኝ፡፡ በጊዜው የመንግሥት ውሳኔ ስህተት ነው ብለን ነበር፡፡ የስህተት ውሳኔ ነበር፡፡ ከማስታውሳቸው ክስተቶች አንዱና ከተሟገትንባቸው መድረኮች መካከል የሚሊኒየሙ የልማት ግቦችን የፍላጎት ግምገማ ጥናት እንድንሠራ ተጠይቀን ያቀረብንበት መድረክ አይረሳኝም፡፡ ጥናቶቹን በመምራት በተለይ በግብርናና በገጠር ልማት ዘርፍ ያሉትን እኔ አስተባብር ነበር፡፡ ድህነትንና ረሃብን በግማሽ ለመቀነስ እንዲያስችሉ ተብለው በተቀመጡ ግቦችና ዕቅዶች መሳካት የሚችሉባቸውን መንገዶች እንድናቀርብ ነበር የተጠየቅነው፡፡ ጥናቶቹ የተፈጥሮ ሀብትንና አካባቢንም እንዲያካትቱ ሆነው ከልማት ግቦቹ ጋር ተካተው ነበር፡፡ ግቦቹን ለማሳካት የሚያስፈልጉትን ጉዳዮች ከ15 ዓመታት በፊት በምናጠናበት ወቅት፣ ለግብርናው ዘርፍ የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች መሳካት 36 ቢሊዮን ብር የሚገመት በጀት ያስፈልጋል ብለን ነበር፡፡
ሪፖርተር፡– የውኃ ሀብት ልማት ለግብርናው መስክ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አኳያ ጥናቶቹ እንዴት ነበር ዘርፉን የቃኙት?
ደምስ (ዶ/ር)፡- ያስፈልጋል ብለን ካስቀመጥነው በጀት ውስጥ አብዛኛው ገንዘብ ለመልሶ ማልማትና ለተፈጥሮ ሀብቶች ጥበቃ፣ እንዲሁም ለውኃ ሥራዎች የሚውል ነበር፡፡ ግብርናው ከዝናብ ተኮር ወደ መስኖ ሥራ መለወጥ አለበት የሚል ጥናት ነበር የሠራነው፡፡ የጥናት ውጤታችንን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የቀድሞው የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና ሌሎችም ትልልቅ ኃላፊዎች በተገኙበት ከ15 ዓመታት በፊት ስናቀርብ፣ በተለይ ከዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በኩል ጥናታችን የማይደረስበት ዓይነት እንደሆነ የሚጠቁም አስተያየት ተሰንዝሮብን ነበር፡፡ እንዲሁም ኢንቨስት ከሚደረገው ገንዘብ በምላሹ የሚገኘው ጥቅም ወይም ትርፍ ምንድነው የሚል ዓይነት ጥያቄም አቅርበው ነበር፡፡ ከመስመርዎ ወጥተዋል ነበር ያልኳቸው፡፡ ጥናቱ የተፈለገው ምን ያህል ኢንቨስት ተደርጎ ምን ያህል ትርፍ ያስገኛል የሚል ውጤት ለማግኘት ሳይሆን፣ ኢንቨስት በሚደረገው ገንዘብ ምን ያህል ሕይወት ማትረፍ ይቻላል? ምን ያህል ድህነትንና ረሃብን መቀነስ ይቻላል? የሚሉትን መፍትሔዎችን ለማፈላለግ እንጂ የኢንቨስትመንት ውጤቱ በምላሹ ገንዘብ ማስገኘት የሚችልበትን መንገድ ማፈላለግ አልነበረም፡፡ የሠራነው ስሌትም ሕይወት ለማዳንና ችግርን ለመቀነስ ምን ያህል ያስፈልጋል የሚል ነበር፡፡ እኔ በአገር ደረጃም ሆነ በአኅጉር ደረጃ በርካታ ጥናቶችን መርቻለሁ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያን የግብርና ፖሊሲና ኢንቨስትመንት ማዕቀፍ›› ጥናት ከዕውቁ የዘርፉ ምሁር ፕሮፌሰር ጆን ሚለር ከተባሉ ባለሙያ ጋር በመሆን የተሳተፍንበት ሥራ አንዱ ነው፡፡ ጥናቱ የሚያረጋግጠው ኢትዮጵያ በእርግጥም ግብርናዋን ለመቀየር ከፈለገች፣ በተፈጥሮ ሀብቷና በመስኖ ሥራዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚጠበቅባት ነው፡፡ ለኢንቨስትመንት የለየናቸው አሥር ዋና ዋና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ መስኮች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት በመጀመርያውና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ለዘርፉ ልማት 18.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስልተናል፡፡ ከዚህ ውስጥ 54 በመቶው በመስኖና በግብርና ውኃ ልማት ሥራዎች ላይ መዋል የሚገባው ገንዘብ እንደሆነም አመላክተን ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ የጥናት ውጤቶችን ባቀረብንበት ወቅት በተለይ ከለጋሽ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞን ነበር፡፡ ጫጫታው ከፍተኛ ነበር፡፡ ይኼንን ያህል ገንዘብ እንዴት በግብርና ላይ ያውም በውኃ ሥራዎች ላይ መዋል አለበት ይላሉ ተብለን ነበር፡፡ እኛም ይህን ያህል ገንዘብ ለምን እንደሚያስፈልግ ዕይታችንንና መከራከሪያችንን አቅርበን ነበር፡፡ ቅሬታውና ተቃውሞው ለምን እንደሚቀርብም በሚገባ እንገነዘብ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ግን በአማካይ ከአንድ ሔክታር በታች በሚታሰብበት አገር ውስጥ የመስኖ እርሻ ምን ያህል ተግባራዊ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
ደምስ (ዶ/ር)፡- ለዚህ እኮ ነው የግብርና ልማትና ማኔጅመንት መምጣት እንዳለበት የምንመክረው፡፡ የመስኖና የውኃ ሥራዎችን ማልማቱ አንዱ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ተገቢው አመራርና አስተዳደራዊ ሥራም ያስፈልገዋል፡፡ እንደማስበው ኢትዮጵያ በመስኖና በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ የላትም፡፡ ይህ በአግባቡ እንዲሳካና እንደሚገባው እንዲተገበር ግን መንግሥት ለአገሩ ባለሙያዎች ቅድሚያውን መስጠት ይኖርበታል፡፡ የውጭዎቹን እናማክር እያሉ እየመጡ ምን እየሠሩ እንደሚሄዱ ብዙ ዓይተናል፡፡ ወደ ራሳችን መመልከትና ባለን አቅምና ሀብት መሠረት መንቀሳቀስ ውጤታማነታችንን ያጎላዋል እንጂ አይጎዳንም፡፡ በአገር ሀብትና ዕውቀት መጠቀሙ ክፋቱ ምንድነው? የአገር ውስጥ ሀብትና ዕውቀት አለ፡፡ በግብርናው መስክ በቂ ሰው አለ፡፡ አንዳንዴም ከስህተታችንም ጭምር እየተማርን በእኛው ሙያና ክህሎት ካልመራነው የውጭውማ የመሰለውን አድርጎና ሠርቶ ዞር ይላል፡፡ የእኛው አገር በቀል ዕውቀትና ሀብት ነው መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ትክክለኛው አማራጭ፡፡ አካሄዳችንን ማስተካከል አለብን፡፡ ከዘመቻና ሩቅ አልመው ከማይመለከቱ ፖለቲካዊ ቅኝት ካላቸው አሠራሮች መውጣት አለብን፡፡ ሥልታችንን መቀየር አለብን፡፡ በተለመደው አካሄድ የትም አንደርስም፡፡
ሪፖርተር፡- ቅድም የጠቀሱትን ያህል ገንዘብ በዚህ ወቅትም ለመስኖ ሥራ ያስፈልጋል ማለት ይቻላል?
ደምስ (ዶ/ር)፡- እዚህ ጋ ሁለት ችግሮች አሉ፡፡ እርግጥ መንግሥት አምኖበት አስፈላጊነቱን የተቀበለው ይመስላል፡፡ ጥሩና አዋጭ ለባንክ ብድር ብቁ የሆኑ ፕሮጀክቶች በግብርናው መስክም መምጣት መቻል አለባቸው፡፡ ቅድም እንዳልኩት ውጤታማ ለመሆን መንግሥት አገር በቀል አካሄዶችንና ዕውቀቶችን መጠቀም መቻል አለበት፡፡ የመንግሥትን ፍላጎትና ዕቅድ ከመንገድ ጠልፈው ለማስቀረት የሚሞክሩ አካሄዶችን እያስተዋልን ነው፡፡ በርካታ ማሳያዎች አሁን በጫት እየተጥለቀለቁ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ከምግብ ዋስትናም፣ ከምግብ ምርትና ምርታማነት ጋር የሚያዛምደው ምንም ጉዳይ የለውም፡፡ ሰዎች በሕይወት ለመቆየት በሚፍጨረጨሩበትና አስከፊ ችግሮች ባሉበት ወቅት፣ ስለኢንቨስትመንት አዋጭነት ሥሌት የምትሠራበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሰዎችን ከዚህ ዓይነቱ ወጥመድ ማውጣትና ማላቀቅ መቻል ከየትኛውም ትርፍ በላይ ነው፡፡ ሕይወት ከኢንቨስትመንት ትርፍና አዋጭነት በላይ ትርጉም ያለው ነገር ነው፡፡ ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት አንድ አዲስ አካሄድ እየተፈጠረ ነው፡፡ መንግሥት በግብርናው መስክ የባለሙያዎች አማካሪ ቡድን እያደራጀ ሲሆን፣ በሒደቱ የተሳተፉ አካላትም አምስት ዋና ዋና መስኮችን ከወዲሁ ለይተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብት፣ የገቢ ማሻሻያ ሥራዎች፣ የመስኖ ሥራ ተጠቃሚነት ሥርዓት ከአምስቱ ዋና ዋና ቅድሚያ የተሰጣቸውና ለወደፊት በግብርናው መስክ ውስጥ እንዲተገበሩ የሚታሰቡ ሥራዎች ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የመስኖ ውኃን በክፍያ ለገበሬው ለማቅረብ የሕግ ማዕቀፍ አርቅቋል፡፡ በመስኖ ለሚቀርበው ውኃ ታሪፍ ማውጣቱ ምን ያህል ትክክል ነው ይላሉ?
ደምስ (ዶ/ር)፡- እርግጥ የውኃ ሥራው ከእኛ ሥራ ውጪ ቢሆንም፣ ማሰብ የሚገባን ግን በጊዜ ሒደት ውኃ አላቂ ከሚባሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ነው፡፡ ለዘለቄታው በሚያመችና በሚገባ ልንጠቀምበት የሚገባ ሀብት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የውኃ ሥራ ማኅበራት አሉ፡፡ አብዛኞቹ ለውኃ የሚከፍሉት ሒሳብ አይደለም ችግራቸው፡፡ ውኃውን በአግባቡ ማግኘት መቻልና አቅርቦቱ ነው ወሳኙ ነገር፡፡ ይህም ሆኖ ውኃውን የሚያለማው አካል በተገቢው ጥራትና ብቃት ባለመገንባቱ የተነሳ የሚገጥመውን ወጪና ኪሳራ ማካካሻ ሊያደርጋቸው ግን በጭራሽ አይገባም፡፡ መሠረተ ልማቱ በተገቢው ክህሎትና አቅም ሊገነባ ሳይችል ሲቀር ብዙ ወጪ ሊያስክትል ይችላል፡፡ ይህን ኪሳራ ማካካሻ የምታደርገው በውኃ ተጠቃሚው ላይ ዋጋ በመጫን አይደለም፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ወጪን የማስመለስ አካሄድ ትልቅ ጉዳት ያመጣል፡፡ ገበሬዎች እኮ ውኃውን ማግኘቱ ነው የመጀመርያው ፍላጎታቸው፡፡ ውኃውን በቀላሉ ማግኘት እስከቻሉ ድረስ የዋጋው ጉዳይ የሚያሳስባቸው አይመስለኝም፡፡ ውኃው እኮ እንደ ልብ አልቀረበላቸውም፡፡ የውኃ መሳቢያ ፓምፕና ሌሎችም አቅርቦቶች የላቸውም፡፡ የመስኖ ቦይ የለም፡፡ ለዚህ መፍትሔው ገበሬው ራሱ ኢንቨስተር እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡
በግሉ ዘርፍ ገበሬ የራሱ ባለሀብት መሆን መቻል አለበት፡፡ በእውነቱ ለትክክለኛ ግብዓት የሚጠየቀው ወጪ ይህን ያህል ከገበሬው አቅም በላይ ላይሆን ይችል ነበር፡፡ ዋናውና ትልቁ ጉዳይ ግን ለግብዓት የሚጠየቀው ወጪ ሳይሆን፣ ውጤቱ ነው ወሳኙና ትኩረት የሚሻው ጉዳይ፡፡ የእኛም ትኩረት መሆን የሚገባው ውጤቱ ምንድነው በሚለው ላይ ነው፡፡ በምርት ሥራ ላይ ስትሰማራ ትርፍን ታስባለህ፡፡ ይኼንን ለማሳካት በሚገባ ማምረት እንዳለብህ ትገነዘባለህ፡፡ ተገቢውን ምርት የሚሰጥህን ትክክለኛውን ግብዓት ስለመጠቀምህም ማረጋገጥ አለብህ፡፡ የእነዚህ ድምር ዋጋና የምታገኘው ምርት ልዩነት ከወጪው በላይ ውጤት ካስገኘ ትርፍ አመጣልህ ማለት ነው፡፡ ገበሬው በዚህ አኳኋን ነው መንቀሳቀስ ያለበት፡፡ ወጪና ገቢውን ማወቅ መቻል አለበት፡፡ የራሱን ድርጅት የሚያንቀሳቅስ አምራች መሆን መቻል አለበት፡፡ ይኼንን ለማሳካት ቁልፉ ተገቢው የእርሻ ሥራ አመራርና የሒሳብ መዝገብ መያዝ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በእኛ ግብርና ሥራ በአብዛኛው ለብዙ ጊዜ ተዘንግቶ የቆየ ነው፡፡ ጨርሶ ቦታ የለውም፡፡ ግን በሰፊው ጠቀሜታ ያለውና ለገበሬው ድርጅታዊ አቅም እንዲያገኝ የሚያግዝ አሠራር ነው፡፡ ወደ ውኃው ስንመለስ ገበሬው ውኃ እንደ ልቡ ያግኝ እንጂ ለመክፈል አያቅማማም፡፡ ከሚያገኘው ውኃ ምን ያህል ጥቅም ያገኝበታል የሚለውም እግረ መንገዳችንን ማንሳት የሚገባን ወሳኝ ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በአገሪቱ በአንድ ወቅት ድርቅ በመከሰቱ ሳቢያ በገበሬዎች የተፈጠረና አሁንም ድረስ አዋጭ ሆኖ የዘለቀ የውኃ አጠቃቀም ዘዴ በአካባቢው አለ፡፡ ገበሬዎች ተገቢውን የእርሻ ማሳ አመራር በመተግበር አትራፊ መሆን የቻሉባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ትኩረት የሚሰጠው አላገኘም እንጂ ማስረጃውማ ሞልቷል እኮ፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ዓመት የምርት መጠን ዕቅድ እናንሳ፡፡ መንግሥት ከ370 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እህል እንደሚመረት አስታውቋል፡፡ በአንፃሩ ከ800 ሺሕ ቶን በላይ ስንዴ ከውጭ ለማስገባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ በአንድ በኩል ምርቱ ጨምሯል እየተባለ በሌላ ጎን ከውጭ የሚገባው የግዥ እህል መጠን ሲታይ፣ ተቃርኖው በየጊዜው እየሰፋ እንደመጣ ያመላክታልና እንዴት ያዩታል?
ደምስ (ዶ/ር)፡- የምግብ ሰብል ለማምረት ከሚያስችለንና ካለን አቅምና ሀብት አኳያ ሲታይ፣ ቀድሞውንስ 370 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ማቀዱ በራሱ በቂ ነበር ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ከዚህም በላይ መታቀድ ነበረበት፡፡ ሌላው ቀርቶ ሞዴል ሚሊየነር ተብለው የሚጠቀሱ ገበሬዎች ብቻ እንኳ በአግባቡ እንዲያመርቱ ቢደረግ፣ ከታቀደውም በላይ ብቻቸውን ማምረት ይችሉ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ገበሬዎች ግን በጥናት የተለቀቁ ግብዓቶችን ማግኘት እያቃተቸው፣ ስንት የተለፋባቸውና ብዙ የተደከመባቸው የምርምር ውጤቶች ገበሬው ዘንድ በአግባቡ ሳይደርሱ የወረቀት ሲሳይ ሆነው እየቀሩ ነው፡፡ ገበሬው በሳይንሳዊ መንገድ ከሚወጡት እጅግ በርካታ የምርምር ውጤቶች ውስጥ ቢያንስ 50 ወይም 60 በመቶውን ማግኘት ቢችል ምን ያህል ተዓምር መሥራት በቻለ ነበር፡፡ በአገሪቱ በርካታ የግብርና ምርምር ማዕከላት አሉ፡፡ ገበሬው ግን ተገቢውን የምርምር ውጤት እንደ ልብ ማግኘት አልቻለም፡፡ ምንም ሌላ ተጨማሪ ሥራ መሥራት ሳያስፈልግና የቴክኖሎጂ ዕገዛ ሳይደረግ፣ ባለው ሀብት ብቻ የምርት አቅምን በእጥፍ ማሳደግ የሚቻልባቸው ሰፊ ዕድሎች አሉ፡፡ ለምንድነው ታዲያ የሚፈለገውን መጠን ማምረት ያልቻልነው ቢባል ብቃት ስለሚጎድለን ነው፡፡ በቂ ዕቅድና ዝግጅትም ስለማናደርግና ለእያንዳንዱ ሥራችን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ስለማንሠራ የምንፈልገውን ያህል ውጤት ማግኘት አልቻልንም፡፡
ሪፖርተር፡- የታቀደውንም ያህል ማምረት እኮ በራሱ ከባድ ፈተና ሆኖ ይታያል፡፡
ደምስ (ዶ/ር)፡- አዎን! እሱ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ከውጭ የሚገባው ስንዴም በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ከፕሮፌሰር ጆን ሚለር ጋር በመሆን አንድ ጥናት አጥንተን ውጤቱንም በዓውደ ጥናት አቅርበን ነበር፡፡ ጥናቱ በየጊዜው እየጨመረ ስለመጣውና ከውጭ ስለሚገባው ስንዴ የሚያትት ነበር፡፡ እኛ ጥናቱን ባቀረብንበት ወቅት ኢትዮጵያ በዓመት 600 ሺሕ ቶን ስንዴ ማስገባት ጀምራ ነበር፡፡ በጥናታችን ኢትዮጵያ ከስንዴ አስመጪነት ልትላቀቅ የምትችልባቸውን ምክረ ሐሳቦችም አቅርበን ነበር፡፡ እንዲያውም ትርፍ አምራች ስለምትሆንባቸው መንገዶችም አመላክተናል፡፡ የጥናት ምክረ ሐሳቡን ያቀረብነው ከስድስት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከስንዴ ግዥ ተላቃ ምርቷን ጨምራ ለሌሎች መትረፍ የምትችለበት ጊዜ በሆነ ነበር፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከ800 ሺሕ ቶን በላይ ስንዴ ከውጭ ለማስገባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን አገሪቱ ለዓለም የስንዴ የልቀት ማዕከል ለመሆን የሚያበቃት አቅም ያላት መሆኗ ነው፡፡ በዚህ ዑደት ውስጥ መዘፈቃችን አለመታደል ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ወደድንም ጠላንም ከመጋረጃው ጀርባ የንግድ ፍላጎታቸውን የሚያራምዱና ስንዴ ከውጭ እንዲገባ ሆን ብለው የሚፈልጉ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላት አሉ፡፡ በርካታ ዱቄት አምራቾች ከስንዴ ግዥው ጀርባ ብዙ አሻጥር አላቸው፡፡ አብዛኛውን ከውጭ የሚገባ ስንዴ ዱቄት አምራቾች በተለይም ዳቦ ቤቶች ናቸው የሚጠቀሙበት፡፡ ይሁንና ግዥው ግን እንዴት በሌላ አቅጣጫ ወዴት እንደሚሄድ እናውቃለን፡፡ ይኼንን በግልጽ መነጋገር አለብን፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የግዥ ስንዴ ወደ ኬንያና ወደ ሌሎች አገሮች የሚወጣበት መንገድ ሰፊ ነው፡፡ እዚያ የሚሸጥበት ዋጋ በኢትዮጵያ ከሚሸጥበት ዋጋ በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ እዚህ አንድ ከረጢት ስንዴ ማግኘት እያስቸገረ ለኢትዮጵያ የተገዛው ስንዴ ግን በሱዳን እንደ ልብ ይቸበቸባል፡፡ ስንዴው ተገዛ ይባላል ግን አይገኝም፡፡ ነዳጅን ጨምሮ ሌሎችም ሸቀጦች ላይ የምናየው እንዲህ ያለውን አድራጎት ነው፡፡ ሸቀጡ ተገዛ ይባላል ግን ገበያ ላይ አታገኘውም፡፡
ከውጭ የሚገባው ስንዴ በተወሰነ መጠን በድጎማ ለዱቄት ፋብሪካዎች የሚከፋፈል እንደ መሆኑ መጠን ዋጋው መቀነስና እንደ ልብ መገኘት ነበረበት፡፡ የአገር ውስጥ ገበሬ የሚያመርተውን ስንዴማ የትኛው ዱቄት አምራች ፈልጎት፡፡ ግፋ ቢል ለንፍሮና ለቂጣ ነው የሚውለው እንጂ ለምን ብለው የገበሬውን ስንዴ ይገዛሉ? እንደ ልብ በገፍ ከውጭ ስለሚገባ የኢትዮጵያ ገበሬ ያመረተውን ማን ይፈልገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የአገር ውስጥ ምርትና አቅርቦት እንደ ልብ እንዲሆን አይፈልጉም፡፡ በአብዛኛው ከውጭ የሚገባው ስንዴ ለከተሞች ፍጆታ ይውላል፡፡ ዳቦ ቤቶች በዚህ ስንዴ ላይ ጥገኞች ናቸው፡፡ እርግጥ የድጎማ ስንዴ የሚቀርበው የድጎማ ዳቦ ማግኘት እንዲቻል ነበር፡፡ ዋጋው ግን ይኼንን አያሳይም፡፡ በስንት ልፋት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም ለስንዴ ግዥ ይውላል፡፡ ነገር ግን ማንም ስንዴው በምን አግባብ ጥቅም ላይ እንደሚውልና እንዴት እንደሚሠራጭ አይከታተልም፡፡ እንጂማ ያለምንም ተጨማሪ ግብዓትና ሀብት አሁን ከሚጠበቀው ምርት ይልቅ በትንሹ በእጥፍ ጨምረን እስከ 600 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት የምንችልበት አቅም አለን፡፡ ይኼንን በቀላሉ ማድረግ እንችላለን፡፡