Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የንብ ባንክ ፕሬዚዳንት ሹመት አፀደቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የሌሎች ኃላፊዎችንም ሹመት አፀደቀ፡፡

የንብ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ሹመታቸው ከፀደቀላቸው ውስጥ የባንኩ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾሙት አቶ ገነነ ሩጋ ናቸው፡፡

አቶ ገነነ የንብ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ የሚያበቃ ሁኔታ ስለማሟላታቸው ባደረገው ማጣራት ገዥው ባንክ ማረጋገጡን አስታውቆ፣ ሹመታቸውን ያፀደቀበትን ደብዳቤ በሳምንቱ አጋማሽ ለባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ መላኩ ታውቋል፡፡

አዲሱ የንብ ባንክ ፕሬዚዳንት በባንኩ አዲሱ አሠራር መሠረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ የኃላፊነት ቦታውን የተከረቡት ባንኩን ላለፉት ስድስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ ከቆዩት ከአቶ ክብሩ ፎንዥ በመረከብ እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ባንኩ ተግባራዊ እያደረገ ካለው የመዋቅር ማስተካከያ አኳያ አዲስ የአመራር ለውጥና የመተካካት እንቅስቃሴ መተግበሩን አስታውቆ፣ አቶ ገነነም የባንኩ ፕሬዚዳንት ወይም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እስከተሰየሙበት ጊዜ ድረስ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡

አቶ ገነነ ንብ ባንክን ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች እስከ ምክትል ፕሬዚዳንት ድረስ እንዳገለገሉ ከሥራ ማኅደራቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ንብ ባንክ ያሰናዳውን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለመተግበር ከተቀመጡ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የሠራተኞች ምደባ ላይ የዕድሜ ጣሪያን ማስቀመጡ አንዱ እንደሆነ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት ባንኩ በአዲሱ ምደባ ለጡረታ የደረሱና ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ በምደባው እንዳይካተቱ፣ አዳዲሶቹም ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች እንዲሆን በማድረግ ምደባ ማካሄዱ ተዘግቧል፡፡

በተቀመጠው የዕድሜ ጣሪያ መሠረት የቀድሞውን የባንኩን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ዕድሜያቸው ወደ ስልሳ ዓመት የተጠጋና ከዚያም በላይ የሆኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች በጡረታ እንዲገለሉና በአዲስ እንዲተኩ እያደረገ ይገኛል፡፡

እስካሁንም የባንኩን በአዲሱ መዋቅር አምስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች የሚኖሩት ሲሆን፣ ለአራቱ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታዎች ምደባ ተደርጓል፡፡ ለሦስቱ አዲስ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ናቸው፡፡ አንዱ ግን ቀደም ብለው በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲሠሩ የቆዩ ሲሆኑ፣ እነዚህ አራት ምክትል ፕሬዚዳንቶችም ሹመታቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መፅደቅ ስላለበት በቀረበው ጥያቄ መሠረት የሦስቱም የአዳዲስ ተሿሚዎች ሹመት ሊፀድቅ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ጋር ሹመታቸው የፀደቀላቸው ሦስቱ ምክትል ፕሬዚዳንቶች አቶ ሰይፉ አገንዳ የባንኪንግ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ፣ አቶ ልዑል ሰገድ ንጉሤ የስትራቴጂክና ኢንፎርሜሽን ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚና አቶ ከድር በደዊ የደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ አራተኛው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ጎሽሜ ቀድሞም በቦታው የነበሩ ሲሆን፣ በአዲሱ ምደባ የባንኩ የሀብት አቅርቦት ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ በመሆኑ ተሰይመው እየሠሩ ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ በዚህ ሳምንት ውስጥ ሹመታቸውን ያፀደቀላቸው ኃላፊ አቶ ይሳቅ ይፍሩ ናቸው፡፡ አቶ ይፍሩ የባንኩ የሪስክና ኮምፕላይንስ ማኔጅመንት ዳይሬክተር በመሆን እንዲሠሩ የቀረበው ሹመታቸው ፀድቆላቸዋል፡፡ ባንኩ ለአራቱ የምክትል ፕሬዚዳንቶች የኃላፊነት ቦታውን ቢያፀድቅም የአምስተኛውን ምክትል ፕሬዚዳንት ቦታ ግን እስካሁን ምደባ አላካሄደበትም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች