Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መልካም ስም ከሽቶ በላይ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰባ ዓመታት በላይ በዘለቀው የአገልግሎት ታሪኩ አስከፊ ከሆኑ አደጋዎች አንዱን ከሰሞኑ አስተናግዷል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ 157 መንገደኞችንና የበረራ ሠራተኞችን በማሳፈር ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ መጓዝ በጀመረ በስድስት ደቂቃ ውስጥ ካሰበበት ሳይደርስ ከተከሰከሰ ሳምንት አስቆጥሯል፡፡

በዕለተ ሰንበት ማለዳ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰማ ድንገተኛ መርዶ በመላው ዓለም ሲስተጋባ እስከ ዛሬ ድረስ ሰንብቷል፡፡ ኢትዮጵያ አለኝ የምትለው የግዙፍ ኩባንያዋ ዘመናዊ አውሮፕላን የ35 አገሮች ዜጎችን በሆዱ እንዳጨቀ ወደ ምድር ተምዘግዝጎ በወደቀበት ወቅት አንድም ሰው አልተረፈም፡፡ አደጋው በደረሰ በጥቂት ጊዜ ውስጥም የዓለም ዜና አውታሮች ሰበር ዜናቸው በማድረግ ተቀባበሉት፡፡ አደጋውን የተመለከቱ፣ የተሳፋሪዎች ማንነትና አሳዛኝ ገጽታዎች ሲደመጡ ከረሙ፡፡ ከአደጋው በኋላ በዓለም ደረጃ አዳዲስ ክስተቶች እንዲፈጠሩም ምክንያት ሆኗል፡፡ አደጋው አሁንም ድረስ አነጋጋሪነቱና አስከፊነቱ እየተወሳ፣ ዘመድ አዝማድም ሐዘኑንና እርሙን እያወጣ ነው፡፡ ሐዘን የሰበራቸው ገጽታዎች በርካቶችን አላቅሰዋል፡፡ እያላቀሱም ነው፡፡

በዓለም የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ውስጥ በደኅንነቱ መልካም ስምና ዝና የተጎናፀፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የደረሰበትን አደጋ ተከትሎ ከየአቅጣጫው ፈጣሪ ያፅናችሁ የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጥቁር ሱፍና ክራቫት ሐዘን ያጠላበት ገጽታ ተላብሰው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ እንዳጋጠማት አርድተውና መፅናናትን ተመኝተው የደረሰውን አደጋ ለሕዝብ አሰምተዋል፡፡ በአደጋው ሁሌም ሊያጋጥም የሚችል ነው፡፡ አስከፊነቱና አሳዛኝነቱ ግን ምንጊዜም አይሽሬ ጠባሳ ትቶ ያልፋል፡፡ ይህም ሆኖ የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ጊዜ መፍጀቱ አይቀሬ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው 737 ማክስ 8 አውሮፕላን መከስከሱ ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ ለወትሮም ሥጋትና ጥርጣሬው የነበራቸው የሚመስሉ በርካታ መንግሥታትና አየር መንገዶች እንዳይበርባቸው ሲያግዱት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ስታቅማማ የሰነበተችው አሜሪካም በሳምንቱ አጋማሽ በፕሬዚዳንቷ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፋለች፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አሳዛኝ አደጋ ጠቅሰው እስኪጣራ ድረስ ግን አውሮፕላኖች በአሜሪካ ግዛቶች ውስጥና በአየር ክልሏ እንዳይበሩ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ መስጠታቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት አሳይቷል፡፡ የአደጋው ጉዳይ ግን በዚህ የሚቋጭ አይሆንም፡፡

በአደጋው ላይ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ የውጭዎቹ የዜና ሽፋን ሰፊ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተለይ ከአንዱ ጣቢያ በቀር ሁሉም በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበሩ እንጉርጉሯዊ ዜማዎችን በማሰቢያ ሻማዎች አጅበው የሐዘን መዓት እንደወረደብን መግለጽ የጀመሩት አደጋው በደረሰ በዕለቱ ነበር፡፡ የሬዲዮ ፕሮግራሞችም መደበኛ ሥርጭታቸውን በማቋረጥ ሐዘኑን ተጋርተዋል፡፡ እንዲህ ያለውን የሐዘን ድባብና የሕዝብን ስሜት ሲያንፀባርቅ ያላየሁት አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ስለአደጋው በቅጡ መዘገቡንም እጠራጠራለሁ፡፡ ሐዘኑ የኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን፣ የ35 አገሮች ነው፣ የዓለም ነው፡፡ ለዓድዋ ድል 123ኛ ዓመት መታሰቢያ እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ያልቻለው ኢትዮ ቴሌኮም እንኳ በአደጋው ማዘኑን ለመግለጽ ከአንድም ሁለት ጊዜ መልዕክቱን አድርሶናል፡፡ መንግሥታትና ድርጅቶች፣ ኩባያዎች፣ ግለሰቦች ያለ ልዩነት ሐዘናቸውን የገለጹበት አስከፊ አደጋ ነው፡፡

አደጋው በደረሰበት አካባቢ ያሉት ነዋሪዎች፣ ከድንጋጤያቸውም ከሐዘናቸውም እየታገሉ ለሟቾች አልቅሰዋል፡፡ ዕርማቸውን ለማውጣት በአደጋው ቦታ ከሄዱ ሐዘንተኞች ጋር ሆነው ነፍስ ይማር ሲሉ ታይተዋል፡፡ ሰብዓዊነት ድንበር የለውም፡፡ ሆኖም በአደጋው ምክንያት ቁፋሮና ሌሎችም ሥራዎችን ከሚያከናውኑ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ለፈጸሙት ተግባር ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ከየቤታቸው የሚበላውን በማቅረብ ኢትዮጵያዊነታቸውንና ሥነ ምግባራቸውን ያሳዩበት ክስተትም ተስተውሏል፡፡ ለአየር መንገዱ ሠራተኞችና ለቁፋሮ ባለሙያዎች በአካባቢው ምግብና መጠጥ በማቅረብ  ያደረጉት ድጋፍም ስንት ይገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያስመሰከሩት የችግር ደራሽ፣ አጉራሽ ነዋሪዎች በመንደር ተቧድነው ኢትዮጵያዊነትን ለሚያሳንሱ ትንንሾች ትልቅ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ባለው ሕዝቧ እንጂ በጠበቡት ልክ እንደማትጠብ አሳይተዋል፡፡ ሐዘኑ የሁላችንም ነው፡፡ ፈጣሪ ያጽናችሁ፣ ያጽናን መባባል የግድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደኅንነት ችግርና ሥጋት እንደሌለበት፣ ከቀዳሚ የዓለም አየር መንገዶች ተርታ እንደሚሠለፍ በሚገባ እንዲመሰከርለት ያደረገ ክስተትም በአደጋው ምክንያት ሲስተጋባ ዓይተናል፡፡ በክፉና በአስከፊ ጊዜ ውስጥ መልካምነቱ የሚወራለት ሰውም ሆነ ተቋም ማየት እንግዳ ነገር ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደኅንነት ጋር በተያዘ ችግር አለመታማቱ ብቻ ሳይሆን፣ ምርጥ አብራሪዎች እንዳሉትም ሲነገርለት ዓለምም ስለአየር መንገዱ ያወራለት መጥፎ አጋጣሚ ስሙን አጉልቶለታል፡፡

ከ70 ዓመታት በላይ በዘለቀው ታሪኩ፣ ይህንኑ ስሙን የሚያገዝፍ ነገር ግን ለበርካቶች መጥፋት ምክንያት የሆነ አደጋ መከሰቱ ጉራማይሌ ስሜት ቢፈጥርም፣ ምስክርነቱን ስለሰጠለት ኩባንያ ሠራተኞችም በጎውን እንድናስብ አድርጓል፡፡

ለአንድ ኩባንያ እንዲህ ያለው ምስክርነት እጅግ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ምስክርነት ከዚህ አደጋ ጋር መያያዙ ነው እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥንካሬ የተገለጸበት መንገድ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የንግድ ተቋማት መልካም ምግባር በምንም ጊዜ ቢሆን ተፈላጊ መሆኑን ነው፡፡  

አደጋው የደረሰበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን አየር መንገዱ የገነባው መልካም ስም ጥንካሬውን የበለጠ እንዲያፈረጥም ስንቅ የሚሆነው ደግሞ ከአደጋው በኋላ አንድም በረራ አለመስተጓጎሉ ነው፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት ቲኬት የቆረጡ ሁሉ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ የአየር መንገዱ አብራሪዎች መደበኛ ሥራቸውን በቁጭትና በሐዘን ውስጥም ሆነው እየተወጡት ነው፡፡ አስተናጋጆቹ ሐዘናቸውን ችለው መንገደኞቻቸውን ማስተናገድ ቀጥለዋል፡፡ ምናልባትም በሌሎች የአየር መንገዶች ሠራተኞች ዘንድ እምብዛም ያልታየ ጽናትና አንድነት በእኛዎቹ ልባሞች ዘንድ ከሚጠበቀው በላይ ጎልቶ ታይቷል፡፡ ጉዳት አጠንክሯቸዋል፡፡

ከደኅንነት አንፃር ሙሉ እምነት ያላቸው ደንበኞቹ አሁንም ቀጣይ ጉዟቸውን በዚሁ አየር መንገድ በማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም አየር መንገዱን እንደሚመርጡት በይፋ እየገለጹ ነው፡፡ ይህም በጭንቅ ጊዜ እንኳ ሳይቀር ደንበኞቹ የሚመሰክሩበት ሳይሆን፣ የሚመሰክሩለት ብርቅዬ ተቋም አድርጎታል፡፡ መልካም ስም ከምንም እንደሚልቅ፣ በክፉ ጊዜም ወርቅነቱን ዓለም በአየር መንገዱ ዓይቷል፡፡ ነገን አሻግሮ ይስኬዳል፡፡ ከአገልግሎት አሰጣጥና ከደኅንነት አኳያ እምነት የማይጣልበት ተቋም ቢሆን ኖሮ አየር መንገዱ ከሰሞኑ የደረሰበት አደጋ በወደፊት እንቅስቃሴው ላይ ጥላ ባጠላበት ነበር፡፡ አሁን የምናየውና የምንሰማው ምስክርነት ግን አየር መንገዱ የተመሰከረለት በመሆኑ እንደ አገር እንድንኮራበት ያደርገናል፡፡ አደጋው ያስከተለው አጥንት የሚነካ ሐዘንም ጥሩ ዝናና ከበሬታ ያተረፈ ኩባንያ መገንባት ጥቅሙን ጭምር ምን እንደሆነ የምንማርበት ነው፡፡

ከሰሞኑ እንደሰማነው፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ እምነት ያላቸው ዜጎች በሌላ አየር መንገድ የነበራቸውን በረራ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በማዞር ጭምር ያሳዩት ድጋፍ፣ አየር መንገዱ ይገባዋል ብቻ የምንልበት ሳይሆን ከዚህም በላይ የምንተማመንበት እንዲሆን ያደርጋል፡፡ አሁንም በአየር መንገዳችን እንበራለን፡፡ ሌሎችም ይበራሉ፡፡ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች፣ መልካሙን የዕረፍት ሥፍራ እየተመኘን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለዘመድ አዝማድ ሁሉ መፅናናትን እንዲሰጥልን ፈጣሪን እንጠይቃለን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት