Tuesday, November 28, 2023

የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ስምምነት አዲስ ወይን በአሮጌ አቁማዳ ወይስ…

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ዓመት ሊሞላቸው የቀናት ዕድሜ ነው የሚቀረው፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በዓለ ሲመታቸው የተከናወነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በወቅቱ በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፊት ቀርበው ንግግር ሲያደርጉ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት ዋነኛ የሥልጣን ዘመናቸው ክንዋኔ እንደሚሆን ቃል ገብተው ነበር፡፡

በወቅቱ ንግግራቸው በተለያዩ አገሮች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ወደ አገራቸው ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ መንግሥታቸውም ድርጅቶቹ በሚያከውኗቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም እንዲሁ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪና የሰላማዊ ትግል ግብዣን ተከትሎም የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉባቸው ከነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የአሜሪካ አገሮች ወደ አገር ቤት በመመለስ በሰላማዊ የትግል ሜዳ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

ወደ አገር ቤት ከገቡት ፓርቲዎች መሀል ቀደም ሲል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ እንደ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ እንዲሁም የኦጋዴን ነፃነት ግንባር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በርካቶቹ በውጭ አገሮች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸውን ሲያደርጉ የነበሩ ድርጅቶች እናሳካዋለን የሚሉትን ውጤት የትጥቅ ትግል በሚጨምር የትግል ሥልት ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ቢሆንም፣ ወደ አገር ቤት ሲገቡ ግን ይኼንን የትጥቅ ትግል ሥልታቸውን በመተው በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ተስማምተው እንደነበር ተገልጿል፡፡

ምንም እንኳን የመንግሥትና ወደ አገር የተመለሱት ፖለቲካ ፓርቲዎች የስምምነት ነጥቦች አሁንም ቢሆን በግልጽ ይፋ ያልተደረጉ ቢሆንም፣ ወደ አገር የተመለሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በአገሪቱ ሕግ መሠረት የፓርቲዎችን ምዝገባና ምሥረታ ፈቃድ ከሚሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመሥራት ፈቃድ ባያገኙም፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የፖለቲካ ሥራቸውን እያከናወኑ ደጋፊዎቻቸውንም እየሰበሰቡ በመወያየትና በመነጋገር ላይ ይገኛሉ፡፡

የፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ለማረቅና ወጥ የሆነ አሠራር መዘርጋት እንደሚኖርበት በተደጋጋሚ ሲገልጹ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ፓርቲዎቹ የሚስማሙባቸውን ነጥቦች የሚያካትትና ተገዥ የሚሆኑበት የመጫወቻ ሜዳውን ሊያመቻች የሚችል አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፣ እነዚህን ሥራዎች እንዲያከናውን ለምርጫ ቦርድ የቤት ሥራ ሰጥተው ነበር፡፡

በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሰብስበው ለግማሽ ቀን ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሁሉም አስቀድሞ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ቀጣይ ውይይቶች የሚመሩበት ሥነ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት በመስጠት አስገንዝበው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ለአገሪቱ አይበጃትም ያሉ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹ሰብሰብ›› ብለው ቢመጡ ለአገሪቱ የሐሳብ ገበያና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ከመግለጽ ባለፈ፣ መንግሥትም ‹‹ሰብሰብ›› ብለው የሚመጡ ፓርቲዎችን ለመደገፍ እንደሚቀለውና ይኼንንም ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አውስተው ነበር፡፡

ምርጫ ቦርድም የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማካሄድ የጀመረ ሲሆን፣ ፓርቲዎቹ አሉን የሚሏቸውን ጥያቄዎች ለቦርዱ በማቅረብ በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ውይይትና ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ድርድሮቹና ውይይቶቹ መካሄድ ከጀመሩ ወራት ያስቆጠሩ ቢሆንም፣ አጠቃላይ የፓርቲዎቹን ግንኙነትና አሠራር የሚመራ ሥነ ሥርዓት ግን እስካለፈው ሳምንት ድረስ አልተፈረመም ነበር፡፡

በተለያዩ ሐሳቦች ላይ ምላሽ ለማግኘት ሲጠይቁ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ይጨመር ይቀነስ የሚሏቸውን ሐሳቦች ለቦርዱ ያቀረቡ ሲሆን፣ ጥያቄዎቹም ከሕገ መንግሥት ማሻሻል እስከ ቀጣይ ምርጫ፣ እንዲሁም እያጋጠማቸው ስለሚገኙ በርካታ ችግሮች በመዘርዘር ያቀረቡ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድም ጥያቄዎቹን በማሰባሰብ ለድርድር እንዲመቹ በማድረግ መልሶ ለፓርቲዎች ሲያቀርብና ሲወያይ ሰንብቷል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ሒደቶች ግን ቀጣይ ድርድሮችና ውይይቶች የሚመሩበት ሥነ ሥርዓት ማዘጋጀት ላይ ፓርቲዎቹ በያዙዋቸው ፅንፍ የያዙ የተለያዩ ሐሳቦች ሳቢያ፣ አንድ ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓትና መመርያ ለማዘጋጀት አዳጋች ነበር፡፡

በስተመጨረሻ ግን ፓርቲዎቹ ሐሙስ መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነትና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ሥነ ሥርዓት ቃል ኪዳን ፈርመዋል፡፡

በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈው ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ በሦስት ክፍሎችና በሃያ ምዕራፎች የተዋቀረ ሲሆን፣ ወደፊት በፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ለማረቅ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተካፈሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል፡፡

የቃል ኪዳን ስምምነቱን መፈረም ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶች እየሰጡ የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይ የፓርቲዎች ቁጥር ወደ 107 ማሻቀቡ የብዙዎችን ትኩረት የሳበና ያወያየ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የፓርቲዎች ቁጥር እጅግ በዛ ከሚለው አንደኛው ፅንፍ፣ የለም አገሪቱ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር ቁጥሩ አልበዛም እስከሚለው ድረስ መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ፣ በአንዳንዶች ዘንድም የሽሙጥ ምንጭ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

ከዚህ አንፃር በመሠረታዊነት 110 ሚሊዮን ሕዝብ ላላት አገር 107 ፓርቲዎች አልበዙም የሚሉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ናቸው፡፡ ‹‹ነገር ግን ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሀብት፣ ከሰው ሀብት፣ ከዕውቀትና እንዲሁም ከጊዜ ብክነት አንፃር የፖለቲካ ፓርቲዎች በተቻለ መጠን ሰብሰብ ቢሉ የተሻለ አማራጭ ይሆናል፡፡ እኛ እንደ አብን አገራዊ በሆኑና በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ በተለያየ ቅርፅና አድማስ ከማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርበን ለመሥራት ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ቁጥሩ እንዳልበዛ በመጥቀስ፣ ወደፊት ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ግን አስቸጋሪ እንዳሚሆን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹እንደ አጠቃላይ የሐሳብ ልዩነታችን 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች በዙ የሚባሉ አይደለም፡፡ ነገር ግን ወደፊት ለሚኖረው አጠቃላይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተፎካካሪ ሆኖ መንግሥት ወደ መሆን ፍላጎት ማሳደር የሚቻልበትን አቅጣጫ ግን የሚይዝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በአካባቢ የተደራጀ ፓርቲ እንኳን የአካባቢውን ድምፅ አግኝቶ ውክልና አገኘ ቢባል፣ መንግሥት ሊያስመሠርተው የሚያስችለውን ድምፅ ሊያገኝ አያስችለውም፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ከጠንካራ ጎኑ ይልቅ ደካማ ጎኑ እያመዘነ ነው የሚሄደው፤›› በማለት፣ በፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ላይ ያላቸውን አተያይ ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ምኅዳሩ መስተካከል እንዲህ ያሉ ችግሮችን ሊያርቅ እንደሚችል የሚያምኑት ደግሞ ታዋቂው ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ መሰባሰብ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ ‹‹ዋናው ጉዳይ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስተካከል ነው፡፡ ሜዳው ከተስተካከለ ውሎ አድሮ የፓርቲዎች የቁጥር ጉዳይም የሚስተካከል ይመስለኛል፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በ107 ፓርቲዎች አማካይነት የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ሁሉም የስምምነቱ ፈራሚዎች አሸናፊዎች እንደሆኑ በመጥቀስ የራሳቸውን ፓርቲ ኢሕአዴግን ጨምሮ ሁሉም ፓርቲዎች በቃል ኪዳኑ ሰነድ ለተደነገጉት ሐሳቦች ተገዥ በመሆን፣ የአገሪቱን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዲያግዙ አሳስበዋል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም የተወሰኑ ልዩነቶች ቢኖራቸውም፣ በዴሞክራሲያዊና በሰከነ መንገድ የጎደሉት እንዲሟሉ እንደሚታገሉ በመግለጽ የስምምነት ሰነዱን መፈረማቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹም የስምምነቱ መፈረም በቀጣይ የሚኖሩ አጠቃላይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ለማረቅ እጅግ አስፈላጊ ሰነድ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡

ከዚህ አንፃር የኢዴፓ ሊቀመንበር ጫኔ (ዶ/ር) የቃል ኪዳን ሰነዱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በተለይ በአገር ውስጥ ስንወዳደርና ስንፎካከር የቆየን የፖለቲካ ድርጅቶች ይኼንን ስምምነት በጣም ነው የምንፈልገው፡፡ ምክንያቱም ለዚህች አገር የሚያስፈልጋት ውይይት፣ ድርድርና የሐሳብ መለዋወጥ ነው፤›› በማለት፣ ይህ የቃል ኪዳን ስምምነት ቀጣይ ውይይቶችና ድርድሮች በሰከነና ለአገር በሚጠቅም መንገድ ለማስኬድ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡

የቃል ኪዳን ሰነዱ ፓርቲያቸው ያቀረባቸውን ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ማካተቱን ገልጸው፣ ‹‹የጋራ ምክር ቤት ተቋሙ በሚመራበት ወቅት የፋይናንስና የሎጂስቲክስ አጠቃቀም የመሳሰሉ ነገሮች አልተካተቱም የሚል አስተያየት አለን፤›› ብለዋል፡፡ የሚቋቋመው የጋራ ምክር ቤት ስለሚኖረው የፋይናንስና የሎጂስቲክስ አጠቃቀም የሚመለከት ሐሳብ እንዲካተት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የአብን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የቃል ኪዳን ሰነዱ መፈረም ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች እኩል የሚያደርግ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ማዕከላዊነትን በጠበቀና ሥርዓት ባለው መንገድ ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ፣ መንግሥትም ሕግና ሥርዓትን እንዲሁም ፍትሕን የማስፈን ተልዕኮውንና የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርለት ነው ብለን እናምናለን፤›› በማለት፣ የቃል ኪዳን ሰነዱ መፈረምን ጠቀሜታ አውስተዋል፡፡

ምንም እንኳን የቃል ኪዳን ሰነዱ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ ቢገልጹም፣ የተወሰኑ ሐሳቦች ላይ ግን ፓርቲያቸው የተለየ አቋም እንዳለውና እነዚህንም በሒደት  እንዲስተካከሉ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው እንዲስተካከል ከሚፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ ከመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚዲያ ተቋም ማስተዳደር፣ መቆጣጠር፣ እንዲሁም በባለቤትነት ሊያስተዳድሩ አይችሉም ይላል፡፡ የቃል ኪዳን ስምምነቱ ላይ ግን ይህንን አዋጅ በመቃረን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያስተዳድራቸውንና በባለቤትነት የሚመራቸውን ሚዲያ ማሳወቅ አለባቸው ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ሕግ ይጥሳል፡፡ እንዲሁ በጥቃቅን ነገሮች ሳንፈርም አንወጣም በሚል ነው እንጂ፣ ይህንን አንቀጽ አልተቀበልነውም፡፡ በሒደት በሰላማዊ መንገድ እንዲሻሻል እንሠራለን፤›› ሲሉ አቶ ክርስቲያን አስታውቀዋል፡፡

የቃል ኪዳን ሰነዱ መፈረም አለመፈረም ዋነኛ ጉዳይ እንዳልሆነ የሚገልጹት መረራ ጉዲና ፕሮፌስር በበኩላቸው፣ ዋናው ጉዳይ ሥራ ላይ መዋሉና መተግበሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ስምምነቱ ሥራ ላይ ከዋለ ጥሩ ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት 101 ጊዜ ስንፈራረም ነበር፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲ በኩል በቁርጠኝነት ነገሮችን በሥራ ላይ የማዋሉ ጥያቄ እስካሁን ያስቸግር ነበር፡፡ አሁን እንግዲህ ስምምነቱን በሥራ ላይ ለማዋል ገዥው ፓርቲ በቁርጠኝነት እሠራለሁ በማለት ቃል ገብቷል፡፡ ስለዚህ በቁርጠኝነት ከሠራ ሁኔታዎችን ሊያሻሽል ይችላል የሚል ግምት አለኝ፤›› በማለት፣ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት የገዥው ፓርቲ ቁርጠኝነት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል፡፡

በአገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ለማድረግ የአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ነው የቀረው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉኝ የሚሏቸውን ሐሳቦች ለሕዝብ ለማቅረብና የእርስ በርስ ግንኙነታቸውንም ለማረቅ ይህ የተፈረመው ሰነድ ዓይነተኛ ሚና እንዲጫወት የብዙዎች ሐሳብ ነው፡፡

ፓርቲዎቹ በፈረሙት የቃል ኪዳን ሰነድ ተገዥ በመሆን ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተደራድረውና ተወያይተው በምርጫው ተፎካካሪና አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት፣ ስምምነቱን ከመፈረምና ተፈጻሚ ከማድረግ ባለፈ በርካታ የቤት ሥራዎች እንደሚጠብቃቸውም የሚገልጹም ብዙ ናቸው፡፡ የስምምነቱ ወደ ተግባር መቀየርና ፓርቲዎችም በዚህ የስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ መንቀሳቀስ መቻላቸው በመጪዎቹ ጥቂት ወራት የሚታይ ይሆናል ሲሉም ያክላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -