Monday, March 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአገር ጉዳይ ተስፋ አይቆረጥም!

ኢትዮጵያን በመከራዋ ጊዜ የሚታደጓት ልጆቿ ናቸው፡፡ ለአገራቸው የሚጨነቁና የሚጠበቡ ኢትዮጵያዊያን ችግሮች ተደራርበው ቢመጡ እንኳ በፅናት መቆም አለባቸው፡፡ ሁሌም ለኢትዮጵያ ተስፋ ሊኖራቸው የግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ግራ ከመጋባት አልፈው ተስፋ የሚቆርጡ ያጋጥማሉ፡፡ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንምና ችግሮችን በመጋፈጥ ካሰቡበት ለመድረስ ብርታት ያስፈልጋል፡፡ በአንድ በኩል የአገር ጉዳይ አስጨንቋቸው ምን እናድርግ ብለው የሚጠይቁ እንዳሉ ሁሉ፣ በሌላ በኩል በሚያዩትና በሚሰሙት ተስፋ ቆርጠው የሚቆዝሙ አሉ፡፡ አገር በነውጠኞች ሲተራመስ፣ ኢትዮጵያዊያን ሲገደሉና ሲፈናቀሉ፣ የመንግሥት ምላሽ ዘገምተኛ ሆኖ በሐሰተኛ ወሬዎች ምክንያት ጥላቻ በብርሃን ፍጥነት ሲሠራጭና ቀውስ ሲፈጠር ብዙዎች ይከፋሉ፡፡ መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር አቅቶት ሥርዓተ አልበኝነት ሲሰፍንና በብርሃን ምትክ ጨለማ ሲንሰራፋ፣ ሆን ብለው አገር እየረበሹ ዜጎችን የሚያስመርሩ ጥጋበኞችን በሕግ አደብ ማስገዛት ሲያቅት ተስፋ የሚቆርጡ ይበዛሉ፡፡ ነገር ግን በሽግግር ወቅት መሰናክሎች በየምዕራፉ እንደሚያጋጥሙ በመረዳት፣ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ በብልኃት ክፉ ጊዜን ማሳለፍ ከአገር ወዳዶች ይጠበቃል፡፡ በአገር ጉዳይ ተስፋ መቁረጥ ተገቢ አይደለምና፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለዓመታት የዘለቀው ትልቁ በሽታ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ አለመሆን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ሲቆናጠጡ፣ ከሕዝብ ምንም የሚደበቅ የመንግሥት አሠራር እንደማይኖር ቃል ገብተው ነበር፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ግልጽነት አሁንም አይታይም፡፡ በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች ለመረጃ ዝግ ናቸው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት ሲኖረው ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያስከትላል፡፡ በየደረጃው ያለ ሹምም ሥራውን በአግባቡ ይሠራል፡፡ የመንግሥት የመረጃ ፍሰት አሁንም ችግር ስላለበት፣ ሐሰተኛ ወሬዎች ከየስርቻው ተፈብርከው በነፃነት ሲሠራጩ ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ ይከታሉ፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መሀል መኖር የሚገባውን ግንኙነት ያበላሻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እየሆነ ያለውም ይህ ነው፡፡ ሕዝብ በአገሩ ተስፋ እንዳይቆርጥ ነቅቶ መሥራት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ይኼንን ኃላፊነቱን ሲዘነጋ ሐሰተኛ ወሬዎች የበላይነቱን በመያዝ አገር ያሸብራሉ፡፡ መንግሥት ከተፀናወተው ዳተኝነት መላቀቅ አለበት፡፡ ሕዝብ በአገሩ ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡

ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ተስፋ እንዳይቆርጥና አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ እንዳይገባ፣ የመንግሥት ሕግ የማስከበር ተልዕኮ በብቃት መከናወን ይኖርበታል፡፡ ጠንካራና አስተማማኝ የፍትሕ ሥርዓት በመገንባት፣ ሕዝብን ከአጥቂዎችና ከጉልበተኞች መጠበቅ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ በመንግሥት ውስጥ ሌላ መንግሥት መፍጠር የሚፈልጉ ኃይሎች ሥርዓቱን የሕገወጦች መጫወቻ ካደረጉት የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይገባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት መዋቅሮችን እንዳሻቸው መጫወቻ ሊያደርጉ የሚፈልጉ ኃይሎች በግልጽ እየታዩ ነው፡፡ ከበስተጀርባቸው ያሠለፉትን ኃይል በመተማመን የመንግሥትን እጅ እየጠመዘዙ ያሉ ኃይሎችን በጊዜ በሕግ አደብ ማስገዛት ካልተቻለ፣ አገር የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ መሆኗ ሊያጠራጥር አይገባም፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን በማጠናከር መስመር ማስያዝ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ሕዝብ ከመንግሥት የሚፈልገው ሰላሙንና ደኅንነቱን እንዲያስጠብቅለት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ በነፃነትና በእኩልነት መኖር ይፈልጋል፡፡ ይህንን የሕዝብ የዘመናት ጥያቄ ለማሳካት የሚቻለው ሕጋዊነት በሕገወጥነት ላይ የበላይ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ያስከብር ሲባል ያገኘውን ሁሉ እያነቀ ይሰር፣ ያስፈራራ ወይም ያሳድ ማለት ሳይሆን፣ ከሕግ በላይ ሆኖ እንደፈለግኩ እፈነጫለሁ የሚለውን ኃይል ሕግ ፊት ያቅርበው ማለት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ተስፋው ይለመልማል፡፡

በአሁኑ ወቅት ብዙዎችን እያነጋገረ ያለው የዛሬ ዓመት አካባቢ በሕዝብ ድጋፍ የተጀመረው ለውጥ ጉዳይ ነው፡፡ ይኼንን ለውጥ ለመደገፍ በአንድነት ተነስተው ከነበሩት መሀል የማይናቅ ቁጥር ያላቸው እያፈገፈጉ ነው፡፡ የሚያዩትና የሚሰሙት የሚያበሳጫቸው እነዚህ ወገኖች ለውጡ ተቀልብሷል የሚል እምነት ሲኖራቸው፣ ለውጡ በሌሎች ኃይሎች ተጠልፏል በማለት የሚጠራጠሩም አሉ፡፡ በሚያጋጥሙ ችግሮች ምክንያት አናፈገፍግም የሚሉ ደግሞ አሉ፡፡ ኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ውስጥ ስትገባ ለምን መሰናክል ይበዛባታል ብለው የሚበሳጩም ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ የለውጡ መሪና ግንባር ቀደሞች እኛ ነን ብለው እየፎከሩ አቅጣጫውን በማሳት የሚያተራምሱም ሞልተዋል፡፡ እዚህ መሀል መፈራራትና መጠራጠር እየተፈጠረ ወርቃማ ዕድሎች እየተበላሹ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ ችግሩ ምንድነው ተባብሎ የጋራ አማካይ መፍጠር ሲገባ፣ እንደ ጠላት ማዶ ለማዶ እየተያዩ የሚዛዛቱ ጽንፈኛ ኃይሎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ በየአቅጣጫው ግራ መጋባቶችና ማጉረምረሞች እየተሰሙ ነው፡፡ ታዲያ ሕዝብን አረጋግቶ ለውጡን መስመር ማስያዝ ይሻላል? ወይስ እንደተለመደው የሴራ ፖለቲካ ሰለባ ሆኖ ትርምስ ውስጥ መግባት? በተለይ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ከአድፋጭነት አባዜ ውስጥ ካልወጡ አዙሪቱ ይቀጥላል፡፡ ለሕዝብ ተስፋ ሰጪ መፍትሔ ይዞ የማይመጣ ፖለቲከኛ እንደሌለ እንደሚቆጠር መታወቅ አለበት፡፡ ተስፋ ቆርጦ ሕዝብ ተስፋ እያስቆረጠ ነውና፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሌላው ቀርቶ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለመቻላቸው ያሳፍራል፡፡ አገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ ከውጭ የመጡት መንግሥትን ከማጀብና ዙሪያውን ከማንዣበብ ያለፈ፣ ይህ ነው የሚባል የፖሊሲ ሰነድ ወይም ፍኖተ ካርታ ሳይነድፉ እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠዋል፡፡ እነሱ ኃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው ምክንያት፣ ግለሰብ የፖለቲካ አክቲቪስቶች በማኅበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያ ብዙ ርቀው ተጉዘዋል፡፡ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ማመላከት አለባቸው ተብለው የሚጠበቁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ሲያንቀላፉ፣ አክቲቪስቶች ሜዳውን ተቆጣጥረው በየዕለቱ ቀውስ ይቀፈቅፋሉ፡፡ የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚራዘም ሲሰማና የመጪው ምርጫ በጊዜው የመከናወን ጉዳይ ሲያጠራጥር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሽ ብለው ተኝተዋል፡፡ ቢያንስ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ እነዚህ ሁለት ወሳኝ ጉዳዮች እንዴት መከናወን እንደሚገባቸው ሐሳብ ሲያቀርቡ አይሰሙም፡፡ በቁጥራቸው ለሰሚ እስኪያስደንቅ ድረስ ቢበዙም፣ ቁም ነገራቸው ግን ተስፋ የሚጣልበት ባለመሆኑ ብዙዎችን ያሳስባል፡፡ አክቲቪስቶቹ ደግሞ ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ፖለቲካውን ተቆጣጥረውታል፡፡ ያም ሆነ ይህ አገራቸውን የሚወዱና በሐሳብ የበላይነት የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን የወቅቱን ሁኔታ በቅርበት በመከታተል፣ ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦችን ማመንጨት አለባቸው፡፡ የተሳሳቱን በማረም፣ ከመስመር የወጡትን በመገሰፅ፣ ጽንፍ የረገጡትን በማለዘብና የጋራ የሆነው ብሔራዊ ጉዳይ ላይ በማተኮር አገርን ከአዝቅት ውስጥ ማውጣት ግዴታ ነው፡፡ ሕዝብ አገሩ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና አምባ እንድትሆንለት ይፈልጋል፡፡ በአገር ጉዳይ ተስፋ አይቆረጥምና!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...