አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ከተጨዋችነት እስከ አሠልጣኝነት ካፈራቸው ታላላቅ ሙያተኞች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ምክትል አሠልጣኝ ሆኖ በማገልገል ለዓመታት አሳልፏል፡፡ አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የዓለም አቀፍ ኢሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) በየዓመቱ ለአባል አገሮች በሚሰጠው የኦሊምፒክ ሶሊዳሪቲ አማካይነት ለከፍተኛ የእግር ኳስ አሠልጣኝነት ሥልጠና ወደ ሃንጋሪ አምርቷል፡፡
የዋሊያዎቹ ምክትል አሠልጣኝ በመሆን በማገልገል ያለው ፋሲል የዕድሉ ተጠቃሚ መሆኑን ተከትሎ፣ ባለፈው እሑድ መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ ቡዳፔስት ከተማ ማቅናቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ አሠልጣኙ በሃንጋሪ የስፖርት ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ለሦስት ወራት ሥልጠናውን ይከታተላል፡፡
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት ተደርጎ በዋናነት ሲጠቀስ የሚደመጠው፣ የእግር ኳስ አሠልጣኞች ደረጃና ክህሎት አናሳ መሆን ነው፡፡ በመሆኑም አሠልጣኞች በእግር ኳስ ሥልጠና ላይ ያላቸውን ዕውቀት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይችሉ ዘንድ፣ የውጪ ዕድል ማግኘት እንደሚኖርባቸው ማሳሰቢያ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የኦሊምፒክ ሶሊዳሪቲ ዕድሎችን መጠቀም የሚችለው፣ በዋናነት ጉዳዩ ከሚመለከተው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር እንዳለበትም ይወሳል፡፡ በቀጣይም በአሜሪካና መሰል አገሮች የዚህ ተመሳሳይ ሥልጠና እንደሚኖር ጭምር ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡