በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በእግር ኳስ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ኦሊምፒክ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ከማሊ ጋር ያደርጋል፡፡
በዋናው ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ እየተዘጋጀ የሚገኘው የኦሊምፒክ ቡድን ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ 33 ተጨዋቾችን መርጦ ዝግጅቱን ሲያከናውን የቆየው ቡድኑ በአሁኑ ወቅትም የመጨረሻዎቹን ተጨዋቾች ምርጫ አጠናቆ የጨረሰ መሆኑ ታውቋል፡፡
የመጨረሻዎቹ ተመራጮች በረኞች ምንተስኖት አሎ፣ ጆርጅ ደስታና ተክለ ማርያም ሻንቆ ሲሆኑ፤ ተከላካዮች ወንድሜነህ ደረጀ፣ ዳዊት ወርቁ፣ ደስታ ደሙ፣ ነስረዲን ጀማል፣ ኢብራሂም ሁሴን፣ ሸዊት ዮሐንስና ደስታ ዮሐንስ ሆነዋል፡፡
አማካዮች ደግሞ አፈወርቅ ኃይሌ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ሀብታሙ ተከስተና ሱራፌል ዳኛቸው ሲሆኑ፤ አጥቂዎች አማኑኤል ገብረ ሚካኤል፣ በረከት ደስታ፣ አቡበክር ናስር፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ፣ ፍቃዱ ዓለሙና ሱራፌል እሸቱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ቀደም ሲል የማጣሪያውን መርሐ ግብር ይፋ ሲያደርግ የኢትዮጵያ ቡድን የመጀመሪያውን ጨዋታ ሐሙስ መጋቢት 12 ካደረገ በኋላ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ እሑድ ባማኮ ላይ እንደሚሆን ነበር፡፡ ይሁንና የመርሐ ግብሩን መጣበብ አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለካፍ በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ተሻሽሎ ወደ ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን እንዲሆን መደረጉም ታውቋል፡፡ በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ቡድን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ ማሊ ባማኮ እንደሚያቀና ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ቡድኑ ከሲሸልስ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ባደረጋቸው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ሁለቱንም ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡