በጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
“እውነት ጫማዋን እስክታጠልቅ ድረስ ውሸት ግማሽ ዓለምን ያዳርሳል” ማርክ ትዌን፡፡
በጌዴኦ ሕዝብ ላይ ለደረሰው የጠኔ ግፍና የሕይወት ሕልፈት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ መንግሥት ከተጠያቂነት ሊያመልጥ የሚችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም። ምንም ዓይነት ሐሰት፣ ምንም ዓይነት ሰበብ የተሠራውን ጥፋት ሊሸፍነውም አይችልም። ይህችን ጽሑፍ እንድጭር ያደረግኝ፣ በፌስቡክ ገጼ ላይ፣ “በጌዴኦ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ግፍ ዶ/ር ዓብይም አቶ ለማም፣ የደቡብ ክልልም ሊወገዙ፣ እኛም ተጠያቂ ልንሆን ይገባል፤” በሚል ርዕስ ሥር አጭር ጽሑፍ ከለጠፍኩ በኋላ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤትና ከሰላም ሚኒስቴር የተሰጠው መግለጫ እጅግ ስላሳዘነኝ ነው።
አንድ የአገር መሪ በአገር ውስጥ ተቀባይነቱ ሊቀጥልና የሕዝቡን ልብ ማሸነፍ የሚችለው፣ በሥራው ላይ ለሚያጋጥሙት መሰናክሎችና ችግሮች፣ እንዲሁም የራሱን ድክመቶች በመገንዘብ ለሕዝብ እውነቱን ሲናገር ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰለቸውና ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ መጣል የሚፈልገው፣ ውሸት የሚናገሩ መሪዎችንና የማይሆን ሰበብ እየሰጡ ድክመታቸውን ለመሸፈን የሚጥሩ ገዥዎችንና መሪዎችን ነው።
እኔ እንደማምነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ብዙ መልካም ነገሮችን በአጭር ጊዜ ሠርተዋል፣ ብዙ ሲደክሙም እያይሁ ነው። የፖለቲካ ባህላችንን ለመለወጥ የሚያደርጉት ትግልና እየሠሩ ያለው በጎ ሥራ ሊያስመሠግናቸውና ሊያስወድሳቸውም ይገባል። ይህችን አገር ወደ ተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ለማሸጋገር ኃላፊነቱን ሲቀበሉ፣ ‘ሁሌም እውነቱን እነግራችኋላሁ፣ ምንም የምደብቀው ነገር የለም’ ሲሉም ቃል ገብተዋል። ይህ ከአንድ የአገር መሪ የሚጠበቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት ከመሪዎቻችን የምንጠብቀው አመለካከት ስለነበር፣ በአገራችን አዲስ የፖለቲካ አየር ለመንፈሱም ምልክት ሆኖ ቆይቷል።
እንዲህ ዓይነት ንግግሮችንም፣ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም ሰምተን ነበር። ነገር ግን የሰማነውና በተግባር ያየነው ተመሳሳይ አልሆነም። ፖለቲከኞች የሥልጣን መንበር ላይ ሲቀመጡ ለምን ውሸት እንደሚቀናቸው አላውቅም፣ ከወንበሩ ጋር የሚመጣ በሽታም ሊሆን ይችላል። ለሕዝብ ግን እውነትን እንደ መስማት ነፍሱን የሚያድስ ነገር ያለ አይመስለኝም። አንዳንዴ እውነቱን መናገር መሪር ሊሆን ይችላል፣ ዋጋም ሊያስከፍል ይችል ይሆናል። ግን ውሸት ተነግሮ ውሸትነቱ ቆይቶም ሲጋለጥ፣ የበለጠ መሪር ይሆናል፣ የበለጠም ዋጋ ያስከፍላል።
በእኔ አመለካከት በጌደኦ ሕዝብ ላይ የደረሰው የጠኔ ጥቃት፣ ምንም ዓይነት ሰብብ ሊሸፍነው የማይችል ጥፋት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤትና የሰላም ሚኒስትሯ የሰጡት መግለጫ ውኃ የማይቋጥር ሰበብ ብቻ ሳይሆን ውሸት ነው። የመከላከያ ሠራዊቱንና የፌዴራል ፖሊሱን አቅም እንኳን እኛ ዓለም ያውቀዋል። በጌዴኦ አካባቢ ያሉ ቀማተኞችን የመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ ሊቆጣጠሩ አልቻሉም ከተባልን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አስከባሪውንና የመከላከያውን ተቋም የመምራትና የማዘዝ አቅም አጥተዋል ብዬ ለመደምደም እገደዳለሁ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ትናንት በፌዴራል መንግሥቱ የተሰጠው መግለጫ፣ በማያሻማ ሁኔታ ያስተላለፈው መልዕክት፣ የፌዴራል መንግሥቱ ደካማ መሆኑን ነው። አንድን ጥፋት ለመሸፈን የተሰራ ሌላ ስህተት።
የፌዴራል መንግሥቱ ቀማተኞችን በአንዲት ትንሽ አካባቢ ለመቆጣጠር ባለመቻሌ፣ ለተፈናቃይና በጠኔ ለተጠቁ ዜጎች እህል ማቅረብ አልቻልኩም ወይም ያቀረብኩት የዕርዳታ እህል በቀማኞች ተነጥቀዋል ካለ፣ ትልቁን አገር ተቆጣጥሬ ሕግ አስከብራለሁ እንዴት ሊል ይችላል? በተለያየ መንገድ የፌዴራል መንግሥቱን እየተፈታተኑ ላሉ ጽንፈኛ ኃይሎችስ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው? የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያውን አቅም ለሚያውቅ ሕዝብ፣ በፌዴራል መንግሥቱ የተሰጠው “የመቀነቴ አደናቀፈኝ” ሰበብ በምንም ሁኔታ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።
ስለዚህ ጠቅላ ሚኒስትር ዓብይ ራሳቸው፣ የፌዴራል መንግሥቱ ያለውን አቅም አስተባብሮ መሥራት ያለበትን ሥራ ባለመሥራቱ ለተፈናቀለውና በጠኔ ለተጠቃው የጌዴኦ ሕዝብ በአፋጣኝና በበቂ ሁኔታ እንዳልደረሰለት በመግለጽ፣ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅና በድጋሚ እንዲህ ዓይነት ነገር ደግሞ እንደማይፈጠር ቃል መግባት አለባቸው። በዚህ ጉዳይም ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ካሉ፣ ሊገሰፁና ለጥፋታቸውም ተመጣጣኝ ዕርምጃ ሊወሰድ፣ ከከፋም ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ሊደረግ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት ከቤቱ ተፈናቅሎ በጠኔ እየተጠቃ ላለው የጌዴኦ ሕዝብ በአስቸኳይና በተገቢ ሁኔታ ስላልደረሰለት፣ ተገቢ የወቀሳ ውሳኔ ማስተላለፍ ይገባዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ጠርቶ በዚህ ጉዳይ ላይ ማነጋገር ይጠበቅበታል፡፡
አገሪቱ የሽግግር ወቅት ላይ በመሆኗ ብዙ ጉደለቶች እየታዩ በዝምታ እየታለፉ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን ለሕዝብ ሲዋሹ እየሰማን፣ በዓይናችን የምናየውን ነገር እንዳናምን ሲነገርን በዝምታ የምናልፍበት ህሊና ሊኖረን አይገባም። እኔ በበኩሌ የምደግፈውም ሆነ የምተቸው ግለሰብን አይደለም ሥራውን ነው። አንድ ሰው ጥሩ ሲሠራ ሊወደስ፣ ሲያጠፋ ደግሞ ሊወቀስ ይገባዋል። ከምንም በላይ ሕዝቡ መሪዎቹ እውነት እንዲነግሩት ይፈልጋል። የሚፈልገው መሪዎቹ ፍፁም እንዲሆኑ አይደለም፡፡ የሚጠብቀው ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናልም ብሎ አይደለም፡፡ ከምንም ነገር በላይ ግን መሪዎቹ እውነት እንዲነግሩት ይፈልጋል። ሕዝብ ያውቃል፣ እውነትና ውሸት የመለየት ብቃት አለው። ሕዝቡን መናቅ ዋጋ ያስከፍላል። እንኳን አሁን መረጃ በድምፅ ፍጥነት በሚራባበት ጊዜ ይቅርና ሬድዮ በዳንቴል ተሸፍኖ ይደመጥ በነበረበት ጊዜ እንኳን፣ ሕዝብ መረጃ አግኝቶ እውነትና ውሸቷን ይለይ ነበር።
ስለዚህ አትዋሹን፣ ሥራችሁን ሥሩ፣ የማትችሉት ነገር ካለ ለሕዝብ ንገሩ፡፡ አገራችን የኢኮኖሚ ደሃ ናት፣ ይገባኛል። “የልጆች ደሃ” ግን አይደለችም። የፌዴራል መንግሥቱ አቅሙ ውስን ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ እንደ ትናንት አይደለም፣ ሕዝቡን አስተባብሮ አስፈላጊ ዕርዳታ ለማድረስ ይቻላል። የፈረንጆችን ስንዴ የምንጠብቅበት ጊዜ ሊያልፍ የሚችለው፣ ተባብረን ሕዝባችንን እንድንረዳ ጥሪ የሚያቀርብልን እውነተኛ መሪ ሲኖረን ነው። ያ ካልሆነ ከጠኔና ከለማኝነት አንድንም። ዛሬም እንደ ትናንት መታወቂያችን ጠኔ አይሁን።
ይኸው እጅግ የማከብረው አርቲስት ታማኝ በየነ ለኢትዮጵያ ልጆች ባደረገው ጥሪ፣ በአጭር ጊዜ የተሰጠውን ምላሽ ዓይተናል፡፡ ይህ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ከሚገኘው ኢትዮጵያዊ በትንሹ የተሰጠ ምላሽ ነው። ማርክትዌን እንዳለው ውሸት ተፈናጥራ ዓለምን ታዳርስ ይሆናል፣ እውነት ጫማውን ለማጥለቅ ጊዜ ቢፈጅበትም፣ ማራቶኑን ግን ማሸነፉ አይቀርም። እውነት ንገሩን፣ አስተባብሩን፣ የመፍትሔው አካል አድርጉን፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ብቃት ያለውና የሚመጥን አመራር ስጡን። በአገራችንም “እውነት ትቀጥን ይሆናል እንጂ አትሰበርም” ይባላል። ስለዚህ እውነቱን ንገሩን፣ ቢጎዳንም እንቀበለዋለን። ውሸቱ የበለጠ ይጎዳናል ውሸት ስትናገሩ ለወደፊትም እንዳናምናችሁ ያደርገናል። ይህ ደግሞ አገራችን ልትሸከመው የማትችል ውድቀት ያመጣብናል። ልብ ያለው ልብ ይበል። እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡