የመረጃ ማግኘትና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት አለመከበር በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎችን ለረዥም ጊዜ ሲያወዛግቡ ከቆዩ አጀንዳዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
እንደ አራተኛ መንግሥት የሚቆጠረው የመገናኛ ብዙኃንና የመንግሥት ግንኙነት ባለፉት በርካታ ዓመታት ባለመግባባት፣ በፍጥጫ፣ በማሰር፣ በማሳደድና እርስ በርስ በመወነጃጀል የተቃኘ እንደነበር በርካታ ምሁራን በተለያዩ መጣጥፎቻቸውና መጻሕፍቶቻቸው ሲገልጹት የሰነበተ ጉዳይ ነው፡፡
በ1987 ዓ.ም. የፀደቀውን ሕገ መንግሥት ተከትሎ የሳንሱር መቅረትና የመገናኛ ብዙኃን መስፋፋት እንደሚችሉ የሚያበስሩ አዋጆች ቢታወጁም ቅሉ በሥራ ላይ የቆዩት አዋጆች፣ ሕጎችና ደንቦች አፋኝ በመሆናቸው ለበርካታ ባለሙያዎች ስደት፣ እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኃኑም መዘጋት ምክንያት መሆናቸው በተደጋጋሚ ከሚገለጹ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በተለያዩ ዓለም አቀፍ አደባባዮች ላይ ሲገኝ ከሚቀርቡበት ወቀሳዎችና ክሶች መካከል ከዚህ ከመረጃ የማግኘት ነፃነት መብት፣ እንዲሁም ተያያዥ ሕጎች አፋኝነትና ኢዴሞክራሲያዊ መሆን ተጠቃሽ ነው፡፡
ምንም እንኳን መንግሥት በአገሪቱ ያሉ ሕጎችና አዋጆች በመልካምነታቸው አቻ የማይገኝላቸው ናቸው እያለ ሲሟገትና ሲያስተባብል የቆየ ቢሆንም ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ሙግቱን በመሞገት ክፍተቶችን ሲያመላክቱና እንዲሻሻሉም ሲወተውቱ መሰንበታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
የዛሬ ዓመት ገደማ የገዥውን ፓርቲ ኢሕአዴግ ሊቀ መንበርነትና የአገሪቱን የጠቅላይ ሚኒትርነት ማዕረግን በእጃቸው ያስገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከሕጎች ጋር በተያያዘ አገሪቱ ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ ወቀሳዎችን መፍትሔ ለመስጠት በማሰብ፣ በአገሪቱ እየተተገበሩ ያሉ ሕጎች እንዲሻሻሉና እንዲከለሱ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ለተለያዩ የሕግ ምሁራንና የየዘርፉ ባለሙያዎች ኃላፊነትን ሰጥተዋል፡፡
በዚህም መሠረት የፀረ ሽብር፣ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የምርጫ ቦርድን የመሳሰሉትን የሚገዙና የሚያስተዳድሩ ሕጎችና አዋጆች በባለሙያዎች ጥናት እየተደረገባቸውና እንዲሻሻሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ አጠቃላይ ሥራው ደግሞ እየተከወነ ያለው በፍትሕና የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ አማካይነት ነው፡፡
በፍትሕና የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ሥር ከተዋቀሩት አንዱ ደግሞ ከስድስት ወራት በፊት ሥራውን የጀመረው የመገናኛ ብዙኃን ሕጎች ላይ የሚሠራው የጥናት ቡድን ነው፡፡ ይህ የጥናት ቡድን ሲጀምር አሥር አባላት የነበሩት ሲሆን፣ በሒደት ግን ከዘርፉ ፍላጎት ያሳዩና ይህ ጉዳይ ይመለከተናል ያሉ ሌሎች አባላትንም በማካተት በአሁኑ ጊዜ የጥናት ቡድኑ አባላት 15 ናቸው፡፡
ይህ የጥናት ቡድን በዋነኛነት ዓላማው፣ ‹‹ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትንና የፕሬስ ነፃነትን ሕገ መንግሥቱንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ ያሉ መሥፈርቶችንና ድንጋጌዎችን ባከበረ መልኩ ያሉንን ሕጎች ማሻሻልና መቃኘት›› እንደሆነ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሚኒስትር ዴኤታ ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡
የጥናት ቡድኑ ባለፉት ስድስት ወራት ስላከናወናቸው ተግባራት ዝርዝር መረጃዎችን ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ የጥናት ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ጎሹና የጥናት ቡድኑ አባል አቶ ምሥጋናው ሙሉጌታ፣ የጥናት ቡድኑ የደረሰበትንና በሒደትም የለያቸውን ክፍቶችና መሻሻል ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ቅዳሜ ዕለት በኢሊሌ ሆቴል በተካሄደው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ምንም እንኳን የጥናት ቡድኑ የተደራጀና ዝርዝር መረጃዎችንና ማብራሪያዎችን ቢያቀርብም፣ በዘርፉ ካሉ ተዋንያን አንፃር የታዳሚዎች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡
ለዚህም ይመስላል ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው እንዲሳተፉና ግብዓት እንዲሰጡ በአጽንኦት የጠየቁት፡፡
‹‹በዚህ ዘርፍ ላይ ለረዥም ጊዜ የሠራችሁ፣ ልምድና ሙያ ያላችሁና ያገባናል፣ ይመለከተናል የምትሉ ሰዎች በጎ የሆነ ለውጥ በዘርፉ ላይ ለማምጣት መልካም ዕድል ስለሆነ ይህ ዕድል እንደ አገርና እንደ ሕዝብ ባያልፈን፣ በተቻላችሁ መጠን በውይይቱ ብትሳተፉ፣ ረቂቁ ሲቀርብ ወይም ከፀደቀ በኋላ አልተሳተፍንበትም፣ አላወቅንም፣ በይዘቱ ደስተኛ አይደለንም፣ መብታችንን አላከበረም፣ ወዘተ የሚል ቅሬታና ስሞታ ሳይመጣ በዚህ ሒደት ላይ ግብዓት ብትሰጡ፤›› በማለት በአደራ ጭምር ጠይቀዋል፡፡
ጥናቱ ያለፈበትን ዝርዝር መንገዶችና ሒደቶች ውስን ለነበረው ታዳሚ ያብራሩት አቶ ሰለሞንና አቶ ምሥጋናው ሙሉጌታ የጥናቱን ዓላማና የተካሄደበት መንገድ፣ የጥናቱን ዘዴ፣ ጥቅም ላይ የዋሉ ሕጎችና ልዩ ልዩ ሰነዶችን (ከአገር ውስጥም ከዓለም አቀፍ) በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በመቀጠልም የመገናኛ ብዙኃን ሚና ምን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የመገናኛ ብዙኃን የዜጎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ማረጋገጫ መሣሪያ መሆን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ማኅበረሰብ ግንባታ እጅግ አስፈላጊ ሚና መጫወት፣ በአንድ አገር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወት፣ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር፣ እንዲሁም ሕዝቦች በመብታቸውና ጥቅማቸው ላይ የመወሰን መብታቸው በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጥ ማገዝን እንደሚያካትት፣ የሕግ ባለሙያውና ዘለግ ላሉ ዓመታት በጋዜጠኝነት የሠሩት አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ስምምነቶች መሠረት፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 በተረጋገጠው መሠረት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በተሟለ መንገድ ሊያረጋግጥ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት፣ የጥናት ቡድኑ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸው ተግባራት መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህም አንፃር ከቁጥጥር ይልቅ ነፃነትን፣ ከገዳቢነት ይልቅ ፈቃደኝነትን፣ ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል፣ የመገናኛ ብዙኃን በመልካም አስተዳደርና ሰብዓዊ መብቶች፣ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት ውስጥ ያላቸውን ሚና የሚያጎለብትና ዕውቅና የሚሰጥ፣ መገናኛ ብዙኃን ከሕዝብ ጋር ያላቸውን አጋርነት የሚያጠናክር፣ እንዲሁም ውሱንና ተመጣጣኝ ቅጣቶች የሚያስቀምጡ ሕጎችን ማውጣት የሚሉት ደግሞ የጥናት ቡድኑ መሠረታዊ መርሆዎች መሆናቸውን አስምረውበታል፡፡
በእነዚህ መርሆዎች ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው የጥናት ቡድኑ በእነዚህ ማነፃፀሪያዎች መሠረትም በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን አሠራር ላይ የታዩ ችግሮችን መቃኘቱን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በጥናት ቡድኑ በዋነኛነት የተለዩት ችግሮች ራሱን የቻለ የሚዲያ የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ከመንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት በአጋርነት መርህ ላይ የተመሠረተ አለመሆን፣ መንግሥት ለመገናኛ ብዙኃን ያለው አመለካከት አሉታዊ መሆኑ፣ አፋኝና ተቆጣጣሪ የሕግ ማዕቀፎችና አተገባበር ላይ በተለይ የግል ሚዲያው እንደ አጥፊ መታየቱ፣ በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙኃን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ፣ ማስፈራራት፣ እስር ስለሚያጋጥም ለስደት መዳረጋቸው፣ የአቅምና ከፍ ያለ የሙያ ደረጃ አለመኖር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት አለመኖር፣ እንዲሁም የራስ በራስ አስተዳደር ሥርዓት አለመኖር የሚሉት ናቸው፡፡
በተግባር ላይ ያለውን የመገናኛ ብዙኃን መረጃ የማግኘት ነፃነት አዋጅን አንቀጾችን በመንቀስ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ምሥጋናው በበኩላቸው በአዋጁ ለብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ከተሰጠው ኃላፊነት፣ ከስም ማጥፋት፣ እንዲሁም በምርጫ ወቅት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረጉ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም አሠራሮችን የተመለከቱ ሐሳቦች ላይ የተለዩ ክፍተቶችን፣ እንዲሁም የጥናት ቡድኑ ያመላከታቸውን መፍትሔዎች ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡
የአቶ ሰለሞንና የአቶ ምሥጋናው ማብራሪያን ተከትሎ አስተያየት የሰጡ ተሳታፊዎች፣ ስለጥናቱ ያላቸውን አተያይና አረዳድ በመግለጽ ይጨመሩ፣ ይቀነሱ የሚሏቸውን ሐሳቦች ሰንዝረዋል፡፡
ተሳታፊዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳሰበው ጉዳይ ግን የሚረቀቀው አዋጅ የጋዜጠኝነትንና የአክቲቪዝምን ሚና በቅጡ እንዲለይ፣ የማኅበራዊ ሚዲያው ጉዳይ ምን መሆን እንዳለበት፣ እንዴትስ እንደሚቃኝ፣ ከዚህ ቀድም የነበሩ የዓቃቤ ሕግ ክሶችንና ሌሎች ተያያዥ ጽሑፎችን በጥናቱ ስለመታየታቸው፣ ስም ማጥፋት ወንጀል ለምን እንደሚሆን፣ በቅርቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ሚዲያ ለሕዝብ ያሳውቁ የሚባል ነገር ስላለ ይህንንስ እንዴት ታዩታላችሁ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠኑ ነበሩ፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያው የፈለገውንና ጽንፍ የወጣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትና ጋዜጠኝነትን ከአክቲቪዝም ሊለይ ይገባቸዋል የሚሉት ጥያቄዎች ግን የአብዛኛው ተሳታፊ ራስ ምታት እንደሆነ፣ ይህንን ሊያርቅ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት የጥናት ቡድኑ አባል አቶ ታዬ በላቸው፣ ‹‹ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የመጡ ሁኔታዎች ጋዜጠኝነትንና አክቲቪስትነትን እያደበላለቁብን ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ የአዋጁ መግቢያ ወይም ትርጓሜ የሚባለው ክፍል ላይ ቀደም ሲል የወጣው አዋጅ ላይ የመገናኛ ብዙኃን ምን ማለት ነው የሚለው ላይ ይህ ነገር መታከል አለበት፡፡ አለበለዚያ ጋዜጠኝነትና አክቲቪዝም ተደበላልቆ ከሙያው እንዳንወጣ ሥጋት አለኝ፤›› በማለት የሚዘጋጀው አዋጅ በጋዜጠኝነትና በአክቲቪዝም መካከል ግልጽ መስመር ማስመር ሊኖርበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
መልካሙ ወጉ የተባሉ የሕግ ባለሙያ ደግሞ፣ ‹‹ስም ማጥፋት እንደ ወንጀል መቀመጥ አለበት ወይ?›› የሚል ጥያቄ በማቅረብ፣ ‹‹በሌሎች አገሮች እንደምንመለከተው በመገናኛ ብዙኃን ስም ማጥፋት የፍትሐ ብሔር አካል ነው፡፡ ስለዚህ ወንጀል መሆኑ መቅረት አለበት የሚሉ አቋሞች አሉ፡፡ ስለዚህ በእኛ አገር እንደ ወንጀል መቀመጡ አስፈላጊ ነው ወይ?›› በማለት በመገናኛ ብዙኃን የስም ማጥፋት የወንጀል ሳይሆን፣ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አካል መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ መላኩ ደምሴ በበኩላቸው፣ ከመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር የተያያዙና ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች ለመረጃ የማግኘት ነፃነት ከፍተኛ ማነቆዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ መንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉን በሦስተኛ ወገን ቢያስተዳድረው (Out Source) ቢያደርገው ይሻላል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ጉዳይ ይዘው ለመንግሥት መልዕክታቸውን እንዲያስተላልፉላቸው ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ባለፈው ሳምንት ስምምነት የተደረገበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ፓርቲዎች ለሕዝቡ ያላቸውን የመገናኛ ብዙኃን ይፋ ያድርጋሉ የሚለው አገላለጽ በአገሪቱ ካሉ ሕጎች ጋር የሚቃረን በመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ አመለካከቶችም በጥናት ቡድኑ በሰፈው ቢቃኙ መልካም ነው፤›› የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ያወጣቸው ሕጎች ለአሠራር ምቹ አለመሆኑን፣ በሚያወጣቸው ሕጎች አማካይነት መገናኛ ብዙኃኑን ለመቆጣጠርና ለማዳከም ሕጎችን ሥራ ላይ አውሏል የሚሉት ወቀሳዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡
ከዚህ አንፃር የሚረቀቀው አዋጅ የቀደመውን አሠራር በመቀልበስ ለዘርፉ ተዋንያን መብት ይሰጣል የሚል ተስፋ ያደረጉ በርካቶች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የሚወጣው አዋጅ በአንድ ጀንበር አዲስ አሠራር ለመዘርጋት ባያስችልም፣ መንግሥት እነዚህ አሠራሮች እንዲጀመሩ ፈቃደኛ መሆኑ መልካም ጅምር ነው የሚሉም አሉ፡፡
ዋነኛው ነገር ግን አሁን ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና የግለሰቦች ያሻቸውን ሐሳብ በስመ ነፃነት መግለጻቸው ሕግ በማውጣት ብቻ ማረቅ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል፣ አጠቃላይ ማኅበረሰባዊ መልካም አስተምህሮዎችንና ልምዶችንም ከሕግ ማውጣቱ እኩል መመልከቱ መልካም እንደሆነ የሚመክሩም አሉ፡፡
በዝግጅት ላይ የሚገኘው የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅም ከመደበኛ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በባሰ፣ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ የሚሳተፉ አካላትን ማረቅ ከፍተኛ ተግዳሮቱ ሊሆን እንደሚችልና ይህንንም በቅጡ ማመን እንደሚገባ የብዙዎች አስተያየት ነው፡፡