Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ የቦርድ ሊቀመንበር ሹመት ውድቅ ተደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኩባንያው አዲስ ሊቀመንበር ይመርጣል

የጥቅም ግጭት አለው የተባለውና በድጋሚ ተመርጠው የነበሩትን የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ የቦርድ ሊቀመንበር ሹመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያፀድቅ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አደረገ፡፡ የቀሪዎቹን ተመራጭ የቦርድ አባላት ሹመት አፀደቀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከአንድ ወር ተኩል በፊት የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ የቦርድ አባላት ምርጫ ላይ ከፍተኛ ድምፅ ካገኙት ተመራጮች ውስጥ አንዱ የነበሩትና እስካሁንም በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲያገለግሉ የቆዩትን የአቶ ኃይለ ሚካኤል ኩምሳን ሹመት ያለማፅደቁን ያስታወቀው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ ባንኩ ይህን ውሳኔ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ አቶ ኃይለ ሚካኤል የጥቅም ግጭት በሚያስነሳ ሌላ ተመሳሳይ ኩባንያ ውስጥ በቦርድ አባልነት የሚሠሩ ስለሆነ፣ መመረጣቸው አግባብ አይደለም የሚለውን ጥቆማ በመያዝ የኩባንያውን አስመራጭ ኮሚቴ ማብራሪያ ጠይቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ማብራሪያውን የጠየቀበት ዋነኛ ጭብጥም በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በአንድ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ በቦርድ አባልነት የሚያገለግል በሌላ ተመሳሳይ ተቋም ውስጥ በቦርድ አባልነት ማገልገል የማይችል መሆኑን የሚደነግግ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት በተደረገው ማጣራትም አቶ ኃይለ ሚካኤል በአፍሪካ ሪ በተባለ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ ውስጥ በቦርድ አባልነት እየሠሩ መሆኑን በማረጋገጡ፣ በኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ውስጥ ማገልገል የማይችሉ መሆኑን በማረጋገጥ ሹመታቸውን ሳያፀድቅ እንደቀረ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ከእርሳቸው ጋር የቦርድ አባል በመሆን የተመረጡትና ሹመታቸውን ለባንኩ ያቀረቡት ሌሎች የቦርድ ተመራጮች ሹመት ግን ፀድቋል፡፡

በዚሁ መሠረት ሹመታቸው የፀደቀላቸው የቦርድ አባላት አቶ ሽፈራው በንቲ፣ አቶ ኃይለ ማርያም አሰፋ፣ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ዓለማየሁ፣ አቶ ሔኖክ ተሰማ፣ አቶ ጅባት አለምነህ፣ ወ/ሮ መሊካ በድሩ፣ አቶ ሽፈራው ሩፌና አቶ ካሳሁን በጋሻው መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ አዲስ ተመራጮች ተሰብስበው አቶ ኃይለ ሚካኤልን የሚተካ አዲስ የቦርድ ሊቀመንበር ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ ሁሉንም የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የተለያዩ ባንኮችን በባለአክሲዮንነት ያካተተና በዘርፉ ትልቅ የሚባል ኩባንያ ነው፡፡ በ2010 የሒሳብ ዓመት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ የተቋቋመበትም ዋነኛ ዓላማ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ የጠለፋ መድን ሰጪዎች የጠለፋ መድን አገልግሎት የሚከፍሉትን ክፍያ ለመቀነስ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ኩባንያው የተቋቋመው በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች