በመሀላቸው የነበረውን አለመግባባት በመፍታት ወቅቱ የሚጠይቀውን የፖለቲካ ቁመና በመላበስ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡
በፓርቲው አመራሮች መሀል በተፈጠረ አለመግባባት የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ረዘም ላለ ጊዜ ተገልለው የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ግን አራት አባላት ባሉት ኮሚቴ ውይይት ሲደረግ ቆይቶ አመራሮቹ በጋራ ለመሥራት እንዲችሉና እንዲመለሱ፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መወሰኑን ሊቀመንበሩ በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ይህን ያስታወቁት ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የፓርቲ ጽሕፈት ቤት ከፓርቲው ወጥተው ከነበሩ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን፣ የተደረገውን ዕርቀ ሰላም በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በዚህም መሠረት ከዚህ በፊት በመኢአድ ውስጥ በተፈጠረ ያለመግባባት ምክንያት አኩርፈውም ሆነ በአቋም ልዩነት ድርጅቱን ትተው የወጡ አመራሮችና አባላት፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለሱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መወሰኑን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡
‹‹በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ የመኢአድ አባላትና ደጋፊዎች ከዚህ በፊት ተፈጥሮ የነበረውን የሐሳብ ልዩነት በመነጋገር ወደ አንድ ሐሳብ የመጣን መሆኑን በመረዳት፣ ልዩነትን ወደ ጎን በመተው ከእናት ፓርቲያችሁ ጎን በመሆን ትግሉን ተቀላቀሉ፤›› ሲሉ ጥሪ አስተላለፈዋል፡፡
በዕርቀ ሰላም ዳግም ወደ ድርጅቱ የተመለሱት የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ በቀጣይ ለሚያደርገው አገር አቀፍ ትግል በተናጠል ሳይሆን በጋራ የሚሠራ የተባበረ ክንድ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ የተደረሰው ዕርቀ ሰላምም ልዩነትን አቻችሎ በጋራ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ ለማከናወን የሚያስችል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
መኢአድ በሽግግሩ መንግሥት ወቅት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) በሚል ስያሜ በታዋቂው የሕክምና ባለሙያ አስራት ወልደየስ (ፕሮፌሰር) አማካይነት የተመሠረተ ሲሆን፣ በ1995 ዓ.ም. መኢአድ ተብሎ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ድርጅትነት መሸጋገሩ የሚታወስ ነው፡፡ መኢአድ በታሪካዊው ምርጫ 97 ቅንጅትን ከመሠረቱት አራት ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ እንደነበርም እንዲሁ ይታወሳል፡፡