Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለኢቢሲ ቦርድ አመራር መንግሥት ዕጩዎችን የሚመርጥበት መሥፈርት ጥያቄ አስነሳ

ለኢቢሲ ቦርድ አመራር መንግሥት ዕጩዎችን የሚመርጥበት መሥፈርት ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

ተሿሚዎቹ ከሚዲያ ጋር ትውውቅ የላቸውም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አዲስ የቦርድ ሰብሳቢና አባላትን ሹመት ጠንከር ካለ ክርክር በኋላ አፀደቀ፡፡ ነገር ግን መንግሥት ለቦርድ አመራር የሚመርጣቸውን ዕጩዎች የሚያቀርብበትን መሥፈርትና የትምህርት ዝግጅት ሊፈትሽ እንደሚገባ የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው 28ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡለትን አዳዲስ ተሿሚዎች በተመለከተ ሰፊ ውይይት በማድረግ፣ አቶ ፍቃዱ ተሰማን የቦርድ  ሰብሳቢ አድርጎ ሹመታቸውን አፅድቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ ፍቃዱ በአሁኑ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የገዢው ፓርቲ (ኢሕአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡

የሌሎች አምስት አዳዲስ የቦርድ አባላት ሹመት ፀድቋል፡፡ አቶ ተፈራ ደርበው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤ፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድና አብዲዋሳ አብዱላሂ (ዶ/ር) በቦርድ አባልነት ተመርጠዋል፡፡ ነባሮቹ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ካሚያ ጁነዲ በአባልነታቸው እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡

ይሁንና በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ለሹመት በቀረቡ ግለሰቦች ወቅታዊ የሥራ ኃላፊነትና ከተሾሙበት የሥራ ዘርፍ አንፃር፣ የትምህርት ዝግጅታቸው ስለማይገናኝ በዕጩነት መቅረባቸውን ተችተዋል፡፡

አንዲት የምክር ቤት አባል በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ምክር ቤቱ በቀጥታም ሆነ በቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት በተደጋጋሚ እያጋጠሙት ካሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ በቦርድ የሚመሩ ተቋማት በርካታ ድክመቶች ያሉባቸው መሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የቦርድ አመራሮች ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸውና በተደራራቢ ሥራ ስለሚጠመዱ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹አብዛኛውን ጊዜ ለቦርድ አባልነት የሚሾሙ አመራሮች በተለያዩ ተቋሞች ተመሳሳይ ኃላፊነት በመያዛቸው ተቋማት በአግባቡ እየተመሩ አይደለም፤›› ሲሉ አባሏ ገልጸዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤት አባል ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተደራራቢ የቦርድ ኃላፊነት ያላቸውን ከፍተኛ አመራሮች መሾም ፖለቲካዊ ውሳኔ እንዳለው ቢረዱም፣ ለዚህ ዘርፍ ከፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጪነት በተጨማሪ በትምህርትም ሆነ በቴክኒክ ዕገዛ ለመስጠት ተዛማጅነት ያላቸው ሰዎች ጠፍተው ነው ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹በተለይ ኢቢሲ የሚዲያ ተቋም ከመሆኑና ከተሰጠው አገራዊ ተልዕኮ አንፃር ሁሉም ተሿሚ ሆነው በዕጩነት የቀረቡት ከሚዲያ ጋር የቀረበ ትምህርትም ሆነ ልምድ የሌላቸው በመሆኑ፣ የውሳኔ ሐሳቡ በድጋሚ ታይቶ ሌላ ጊዜ ቢቀርብ ይሻላል፤›› የሚል ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡

ሌላው በተጨማሪነት ያነሱት ጉዳይ የዕጩ ተሿሚዎች አመራረጥና መሥፈርት ግልጽ አለመሆኑን ነው፡፡ ‹‹ለአብነትም ያህል ኡስታዝ አቡበከርና ሌሎች አባላት የተመረጡት ከምን አንፃር ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ይኼንን ሥጋት እንደሚጋሩት ያነሱት ሌላው የምክር ቤቱ አባል እንደ ኡስታዝ አቡበከር ዓይነት ያሉ የሃይማኖት ሰዎችን በእንዲህ ዓይነት የሚዲያ ዘርፍና ሌሎች ጥንቃቄ በሚሹ የመንግሥት ተቋማት በቦርድ አባልነት ማስገባት፣ በመንግሥትና በሃይማኖት ሚና ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ታይቷል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹በዚህ ምክር ቤት እንዲሻሻሉ ብለን የምናነሳቸው ጉዳዮች ተስተካክለው የማይመጡ ከሆነ፣ በተመሳሳይ ነገሮች ላይ መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ መወያየቱ ጉንጭ አልፋ ይሆናል፤›› ሲሉ በቦርድ በሚመሩ ተቋማት ላይ ያለውን ችግር በምሬት ገልጸዋል፡፡

ሌላ የምክር ቤት አባልም እንዲሁ ተመሳሳይ ሥጋታቸውን ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል የተሰመረውን ቀይ መስመር የሚጋጭ ነገር እንዳይፈጠር፤›› በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹እኛ ውስጥ [በመንግሥት አሠራር] እንደ ሥርዓት የተቀመጠ ቀይ መስመር አለ፡፡ ይህ መስመር ሕግ ወይም ድንበር ነው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት ተቋማትን ወይም ግለሰቦችን በመንግሥት ሥራዎች ውስጥ እየቀላቀልን የመጣንበት አሠራር አለ፡፡ ይህ አሠራር ወደፊት ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ወደማንችልበት ሁኔታ እንዳይከተን እሠጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኡስታዞች፣ የሼኮች፣ የቄሶች፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ወደ መንግሥት መሥሪያ ቤት መሪነት ወይም የቦርድ ማስተባበር ጉዳዮች ማምጣት ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

እንደ ሌሎቹ አባላት ሁሉ እሳቸውም የተሿሚዎችን የትምህርት ዝግጅትና ስም ከሚዲያ አመራር ጋር የማይገናኝ መሆኑን ተችተው፣ ‹‹የውሳኔ ሐሳቡ በድጋሚ ተመርምሮ ቢታይ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱት ጥያቄዎችና ትችቶች ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ተጠሪው አቶ ጫላ ለሚ፣ ለቦርድ ሹመት የሚቀርቡ አመራሮች ተደጋጋሚ ኃላፊነት አለባቸው መባሉን እንደሚቀበሉት ገልጸዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ አሠራር ለወደፊት መታየት አለበት መባሉን እንደሚስማሙበት በመግለጽ መንግሥት በትኩረት ያየዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

ነገር ግን ከትምህርት ጋር በተያያዘ በተሿሚዎች ላይ የቀረበውን ትችት አልተቀበሉትም፡፡ ‹‹የቦርዱ ሚና ሙያተኛውን ተክቶ እንዲሠራ ሳይሆን፣ የፖለቲካ አመራር መስጠት በመሆኑ ነው ለሹመት የቀረቡት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ሁሉም ለሹመት የቀረቡት አባላት ከሚመደቡበት ዘርፍ ጋር የሚገናኙ አይደሉም የሚለውን ትችት ‹ሁሉም ብሎ መደምደም› ስህተት ነው፡፡ ለዚህም የተሿሚዎችን ሲቪ ብንመለከት ቢያንስ ኤርጎጌ (ዶ/ር) የመጀመርያ ዲግሪያቸው ከሚዲያ ጋር ይገናኛል፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነገር ግን ሪፖርተር የተሿሚዋን ሲቪ የሚያሳየውን ሰነድ የተመለከተ ሲሆን የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በውጭ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የሠሩ ሲሆን፣ ከሚዲያ ጋር የተዛመደ የሥራ ልምድ እንዳላቸው የግል ማኅደራቸው አያሳይም፡፡

ከእነ ኡስታዝ አቡበከር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዲሁ፣ ‹‹እነዚህን ግለሰቦች በአባልነት ያካተትነው ሐሳብ የሚያፈልቁ ታዋቂ ግለሰቦች በመሆናቸው፣ እንዲሁም ባላቸው የግል ችሎታዎችና ሰብዕና ታይቶ ከኅብረተሰቡ የተመረጡ እንጂ፣ እስልምናን ወይም ሌላ የሃይማኖት ተቋም እምነትን እንዲያራምዱ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

እንዲሁም በኢቢሲ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የቦርድ አባላትን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምረጥ እንደሚችል መቀመጡን በመጥቀስ፣ የተሿሚዎችን አመራረጥ ትክክለኛነት አስረድተዋል፡፡

ከመንግሥት ተጠሪው ምላሽ በኋላ ወደ ድምፅ መስጠት መሄድ እንደሚገባ ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ገልጸው፣ በመጨረሻም የውሳኔ ሐሳቡ በአሥር ተቃውሞ፣ በ28  ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

ከድምፅ ውጤቱ በኋላ ተሿሚዎች በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ መፈጸም የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ ሁሉም አለመገኘታቸው ወ/ሮ ሽታዬ ገልጸዋል፡፡

ቀደም ብሎ የቦርድ ተሿሚዎች ተደራራቢ ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ በችግርነት የተጠቀሰው ጉዳይ፣ በቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓት ባለመገኘታቸው የፓርላማውን አባላት ፈገግ አሰኝቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ተሿሚዎች በሚቀጥለው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...