የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በፋይናንስ ችግር ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳለው ተገለጸ
ከሁለት ዓመታት በፊት መጠናቀቅ የነበረበት ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በመዘግየቱና ተጨማሪ ወጪ በማስከተሉ ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎችንና ኮንትራክተሩን የወሰደውን አካል በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በአፍሪካ የመጀመርያው መሆኑ የተነገረለት ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታው በ2009 ዓ.ም. መጠናቀቁ ቢገለጽም፣ የተመረቀው ግን በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ኃይል ማመንጨት እንዳልጀመረ ታውቋል፡፡
ከፕሮጀክቱ 50 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል የኮንትራት ውሉ በተፈጸመበት ጊዜ የተነገረ ቢሆንም፣ ግንባታው ተጠናቆ በተመረቀበት ዕለት በወቅቱ በነበሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዜብ አስናቀ (ኢንጂነር) የተገለጸው ግን 25 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮንትራክተሩን፣ ኮንትራክተሩ ደግሞ ተቋሙን የችግሩ ምክንያት በማድረግ ጥፋቱ የማን እንደሆነ መተማመን ላይ ሳይደረስ ወራት ተቆጥረው ምንም ሳይባል የቆየ ቢሆንም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ግን ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ጥያቄ አንስተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄውን ያነሱት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ኢንጂነር) የስምንት ወራት የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ ነው፡፡
ሚኒስትሩ የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈጻጸም ከ95 በመቶ በላይ መሆኑንና የኮሚሽኒንግ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ የእሳቸውን ሪፖርት ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት ፕሮጀክቱ ተጠናቋል ተብሎ ከተመረቀ በኋላ ሥራ ካለመጀመሩም በላይ፣ 50 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ተብሎ የኮንትራት ውል ከተፈጸመና ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የተገኘው ኃይል 25 ሜጋ ዋት ነው መባሉ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ የነበሩና አፈጻጸሙን ሲከታተሉ የነበሩ ኃላፊዎችም ሆኑ ባለድርሻ አካላት በሕግ ስለመጠየቃቸውም ጠይቀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የኮንትራት ውሉ ሲፈጸም ጀምሮ ክፍተት እንደነበረበት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ አጠቃላይ ችግሩን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሠራ በመሆኑ ሥራው ተጠናቆ ውጤቱ እንደታወቀ፣ ከሁለቱም ወገን በሕግ የሚጠየቅ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱን በወቅቱ የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አዜብ አስናቀ (ኢንጂነር) እና የእንግሊዝ ኩባንያ ካምብሪጅ ኢንዱስትሪያል ሊሚትድ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ በወቅቱ በ120 ሚሊዮን ዶላር የተፈራረሙ ቢሆንም፣ አሁን አሥር ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ ማስወጣቱ ታውቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በፋይናንስ አቅርቦት ችግር ምክንያት የኮይሻ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እየተጓዘ አለመሆኑ ተመለከተ፡፡
በኮሜርሻል ብድር ይገነባል ተብሎ የተጀመረው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ የፋይናንስ ችግር ስለገጠመው በተያዘለት ዕቅድ መሄድ አልቻለም፡፡ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ኪሳራ ሊያመጣ ይችላል የሚል ሥጋት መፈጠሩ እየተነገረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቱ እየተካሄደ የሚገኘው በኮሜርሻል ብድር ቢሆንም፣ ብድሩን ማስቀጠል ባለመቻሉ ለተከናወኑ ሥራዎች መንግሥት ፋይናንስ እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡
የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው፣ በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ የፕሮጀክት አፈጻጸሙን 34.26 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡
‹‹ባለፉት ስምንት ወራት ለመሥራት የታቀደው 10.70 በመቶ ቢሆንም፣ የተከናወነው 4.92 በመቶ (የዕቅዱን 46 በመቶ) ብቻ ነው፡፡ አጠቃላይ አፈጻጸሙም 26.25 በመቶ ደርሷል፤›› በማለት ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ‹‹ፕሮጀክቱ የፋይናንስ እጥረት ስላለበት መፍትሔ በመፈለግ ላይ እንገኛለን፤›› ሲሉ የፋይናንስ ችግሩ እስካሁን እንዳልተፈታ አብራርተዋል፡፡
ለኮይሻ ፕሮጀክት ግንባታ በአጠቃላይ ከሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር ውል የተገባው 2.5 ቢሊዮን ዩሮ ነው፡፡ ኮሜርሻል ብድር ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልበትና በአጭር ጊዜ የሚመለስ የብድር ዓይነት ሲሆን፣ ብድሩ ከአውሮፓ የፋይናንስ ምንጭ የተገኘ ነበር፡፡ ነገር ግን ከመጀመርያው ጀምሮ የፋይናንስ ፍሰቱ የተስተጓጎለ በመሆኑ፣ 2,100 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የተጀመረው ፕሮጀክት ከወዲሁ ችግር እየገጠመው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በታምሩ ጽጌና በውድነህ ዘነበ