Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአንድነት ፓርቲ አዲስ አበባን ባለአደራ አካል እንዲያስተዳድራት ጠየቀ

አንድነት ፓርቲ አዲስ አበባን ባለአደራ አካል እንዲያስተዳድራት ጠየቀ

ቀን:

አዲስ አበባ የሚያስተዳድራት አካል የሥራ ጊዜውን የጨረሰ በመሆኑ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ባለአደራ አስተዳደር እስከ ጠቅላላ ምርጫ ድረስ እንዲቋቋምና ይህም ተግባራዊ እንዲሆን፣ ከሌሎች የዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር በጋራ በመሆን እንደሚታገል አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) አስታወቀ፡፡

‹‹አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መኖሪያና ሀብት ማፍሪያ እንጂ፣ አንዱ ብሔረሰብ ከሌላው በልጦ የተለየ ጥቅም የሚያግበሰብስበት አይደለችም፡፡ አዲስ አበባን በአንድ ማንነት ጥላ ሥር ለማድረግ የሚደረገውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በጥብቅ እንቃወማለን፤›› በማለት ፓርቲው አቋሙን አስታውቋል፡፡

ፓርቲው ይህን አቋሙን ይፋ ያደረገው ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነትን የሚፈታተን የለውጥ ሒደት እንዳያፈርሰን ሕዝብ በአንድነት ፀንቶ መታገል አለበት፤›› በሚል ርዕስ በራስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ አጠቃላይ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ አስመልክቶ በፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ትዕግሥቱ  አወሉና በሌሎች አመራሮች በተሰጠው በዚህ መግለጫ በአገሪቱ እየተከሰቱ ስላሉ ግጭቶች፣ መፈናቀሎችና እንዲሁም የንፁኃን ዜጎች ሕይወት መጥፋትን ለመቆጣጠርና ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ፓርቲው ጠይቋል፡፡

አገሪቱ በለውጥ ተስፋ ውስጥ እንደሆነች የገለጸው ፓርቲው፣ ‹‹ሆኖም የኢሕአዴግ ልሂቃን አካባቢያዊ ስሜትን የበለጠ በማጠናከርና ዛሬም በለውጥ ስም የሕግ የበላይነትን ወደ ጎን በመተው ሕዝቡ በአንድነቱ የፈጠረውን ኢትዮጵያዊያነቱን ከመፈታተናቸውም በላይ፣ በሥውርና በጥቅም ሥራአጥ ወጣቶችን በማደራጀት ለግጭት በማሰማራት ድብቅ አጀንዳዎቻቸውን ሕዝባዊ ለማስመሰል የሚደረገው ጥረት ሕዝብ የተረዳው በመሆኑ፣ ተፈጥሮአዊ ማንነትን የዘረኛ ፖለቲካ ማራመጃ ሰበብ ከማድረግ ይቆጠቡ፤›› በማለት፣ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን ግጭት የሚመለከታቸው ሁሉ ታግለው መፍትሔ እንዲፈልጉለት አሳስቧል፡፡

‹‹የፖለቲካ አለመረጋጋት በአገራችን ሁሉም ክልሎች የሚስተዋል ነው፡፡ ይኼንን ተከትሎ የዜጎች መፈናቀልና ስደት በስፋት ይታያል፡፡ የዜጎች መረጋጋትና ሰላምን ማረጋገጥ ካልተቻለ ሉዓላዊ አገር ሊኖር አይችልም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን ከልብ የምትወዷት ከሆነ ኢሕአዴግም ሆነ የለውጥ ኃይሉ የፖለቲካ ቁማሩን ትቶ፣ ከሁሉም የክልል ገዥዎች ጋር ቁጭ ብሎ በአገሪቱና በዜጎች ደኅንነት ላይ የምር ተወያይቶ ሰላምን ለማረጋገጥ እንደ መንግሥት ውሳኔ መስጠት አለበት፤›› በማለት፣ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን፣ ስደቶችንና መፈናቀሎችን፣ የሰው ሕይወት መጥፋትን ለማስቆም መንግሥት ውሳኔ መስጠት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

በመጨረሻም ሕዝባዊ ለውጡን ከግብ ለማድረስ መጀመርያ ከክፋትና ከድብቅ የሴራ ፖለቲካ መንፈስ በመውጣት በፍቅርና በአንድነት ተማምኖ፣ ሁሉም የየራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ሲችል እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹በአገሬ ያገባኛል የሚል የተደራጀ ሐሳብ ያለው ሁሉ ሊሳተፍበት የሚችል የለውጥ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የለውጡ አካል ማድረግ ሲቻል፣ የለውጥ ሒደቱ ዓላማውን ስቶ የቡድንና የክፍፍል ምክንያት ሊሆን አይገባም፣ መታረምም አለበት፤›› በማለት፣ አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅና በአገሪቱ ጉዳይ ሁሉም የበኩሉን እንዲያበረክት ሊመቻችለት እንደሚገባ መንግሥትን ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...