Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ተስፋና ሥጋት

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ተስፋና ሥጋት

ቀን:

በመጪው ዓመት ለሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመርያ ማጣሪያውን ከማሊ አቻው ጋር መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲዮም ያደረገው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ጨዋታውን በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ብዙዎችን አስቆጭቷል፡፡ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ በበኩላቸው በተጨዋቾቻቸው እንቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ ወደ ማሊ ባማኮ አቅንቷል፡፡ 

ዋና አሠልጣኙ ዋሊያዎቹ ለዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በነበራቸው ምድብ ማጣሪያ ለሻምፒዮናው የሚያበቃቸው ውጤት ከተሟጠጠ በኋላ ነበር ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ለማሠልጠን ዕድሉን ያገኙት፡፡

አሠልጣኙ ለኦሊምፒክ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ ከ33 በላይ ተጨዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ ጭምር መርጠው ለሁለት ሳምንት ያህል ከተመለከቱ በኋላ የመጨረሻዎቹን 23 ተጨዋቾች ይፋ ያደረጉት ከማሊው ጨዋታ ሁለት ቀን በፊት ነበር።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ጠንካራ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ከታየባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገሮች በተለይም በታዳጊ ወጣቶች ማሊ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ የማሊ ታዳጊና ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች በአኅጉራዊ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ጭምር ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱም ይህንኑ ጥንካሬያቸው መነሻ በማድረግ ምስክርነታቸውን ከጨዋታው በኋላ ውጤቱን አስጠብቆ በሜዳው ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ዕድሉን አመቻችቷል፡፡

የሁለቱም ቡድኖች አሠልጣኞች ከጨዋታው በኋላ ተጨዋቾቻቸው በሜዳ ላይ የነበራቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተውም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ፣ ተጋጣሚያቸው በጥንካሬያቸው ከሚታወቁ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች አንዷ ከሆነችው ማሊ ጋር በመሆኑ በውጤቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ተጨዋቾቼ በኳስ ቁጥጥርና የጎል ዕድሎች በመፍጠር ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ነበሩ፣ ከሰሞኑ ያደረግነውን የወዳጅነት ጨዋታ ጨምሮ ልምምዳችንን ስናደርግ ሁለት መሠረታዊ የሚባሉ ዕቅዶችን መነሻ አድርገን ነበር፡፡ ቡድናችንም የተሰጠውን ታክቲክ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ተግብሮታል ማለት ባልችልም፣ የሚችሉትን ያህል ሞክረዋል፣ በተለይ የተከላካይ ክፍላችን፤›› በማለት ደስተኛ መሆናቸውን ጭምር ተናግረዋል፡፡

አሠልጣኝ አብርሃም ለቡድናቸው እንቅስቃሴ ውጤታማነት በተናጠልም ያመሠገኗቸው ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ተጫዋቾች መካከል የኢንተርናሽናል ልምድ ሳይኖረው፣ የተሻለ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ልምድ ያላቸው የማሊ ተጫዋቾችን እንቅስቃሴ ከማክሸፍ ጀምሮ አፈወርቅ ኃይሉ የሰጡትን ትክክለኛ ታክቲክ የተገበረ ስለመሆኑ ጭምር በመግለጽ አድናቆታቸውን ቸረውታል፡፡

የቡድናቸው ክፍተት ያሉት አሠልጣኙ፣ ‹‹የአጨራረስ ብቃት ማነስ በመሆኑ ይህንኑ በቀሪው የልምምድ ጊዜ እንሠራበታለን፤›› ብለው በተለይ ፊት መስመር ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የመቐለ 70 እንደርታው አማኑኤል የሕመም ስሜት እየተሰማው ሜዳ ውስጥ እንዲቆይ ያደረጉበት ዋናው ምክንያት ከተጨዋቹ ጋር በቅርበት እየተነጋገሩ ጉዳቱ ለክፋት እንደማይሰጠው ስለገለጸላቸው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ከነገ በስቲያ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ባማኮ ላይ ስለሚኖራቸው የመልስ ጨዋታ አስመልክቶ ያከሉት አሠልጣኝ አብርሃም፣ ‹‹ወደ ሥፍራው የምናቀናው ውጤቱን ለመቀልበስ ነው፣ ለዚህ የሚሆን ጠንካራ የሆነ የሥነ ልቦና ሥራ እንሠራለን፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የታክቲክ ለውጥ እናደርጋለን፣ ባለን የተጣበበ አጭር ጊዜ በክፍተቶቻችን ላይ የማስተካከያ ሥራዎችን ሠርተን ለተከታዩ ዙር የሚያበቃንን ውጤት እንደምናስመዘግብ ሙሉ እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

የማሊ ኦሊምፒክ ቡድን አሠልጣኝ ፋኑሬ ዲያራ በበኩላቸው፣ ‹‹አሁንማ አልፈናል፤›› ብለው ምን ትጠብቃላችሁ ዓይነት ፌዝ ጣል አድርገዋል፡፡ የቡድናቸውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አስመልክቶ አሠልጣኙ፣ ‹‹ጨዋታውን ያደረግነው በሁለት ከፍለን ነው፣ በመጀመርያው ግማሽ የተጋጣሚያችንን ቡድናዊ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ጎል ማስቆጠር የሚል ሲሆን፣ በዚህም የእኛ ቡድን ከተጋጣሚው አንፃር የተሻለ ነበር፡፡ በሁለተኛው ግማሽ ግን የኢትዮጵያውያን ጫና ተደርጎብናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ጎል ቀድመን በማስቆጠራችን ውጤቱን አስጠብቀን ለመውጣት ያደረግነው ጥረት ተሳክቶ ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቀናል፤›› ብለው፣ በተለይ የአዲስ አበባ ስታዲዮም ለተጨዋቾቻቸው አስቸጋሪ ሆኖ ማለፉን ጭምር ተናግረዋል፡፡ 

በአሠልጣኝ አብርሃም የተሞካሸው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን በዕለቱ በነበረው አጠቃላይ የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ ደስተኛ ያልነበሩ ታዳሚዎችም አልጠፉም፡፡ እንደእነዚህ ከሆነ የኢትዮጵያ ቡድን ዕድሉን አሳልፎ የሰጠ ስለመሆኑ ያምናሉ፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ‹‹የማሊ ኦሊምፒክ ቡድን እንደተሰማው ከሆነ፣ ወሳኙን ጨዋታ ያደረገው አዲስ አበባ በገባ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሜዳ ላይ ከታክቲክ ጀምሮ አስፈሪ የጎል ሙከራዎችን ሲያደርግ ታይቷል፡፡ ጎል የማስቆጠር ቅድሚያ የነበረውም የማሊ ቡድን ነው፡፡ አቻ የምታደርገው ጎል የተገኘችው ከተከላካይ ሥፍራ ተነስቶ በሄደ ተጨዋች ነው፤›› በማለት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ሰፊ ክፍተት እንደተመለከቱበትና ገና ብዙ እንደሚቀረው ነው ያስረዱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...