Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየኤሌክትሮኒክ ፊርማ ሕጉ ላይ የተደረገ አጭር ምልከታ

የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ሕጉ ላይ የተደረገ አጭር ምልከታ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ከምድራዊው ዓለም በትይዩ የሚገኘው የሳይበሩ ዓለም የራሱ የሆኑ ልዩ መገለጫዎች አሉት፡፡ በዚሁ በሳይበሩ ዓለም፣ ልክ በገሃዱ ዓለም እንደሚደረገው፣ በርካታ ተግባራትን የሚያከናውኑ፣ መረጃ የሚለዋወጡ፣ የንግድ አገልግሎት የሚሰጡና የሚገኙ ሰዎች አሉበት፡፡ መረጃ ቅብብሎሽ አለ፡፡ ውሎች ይደረጋሉ፡፡ በሕግ ፊት የተለያዩ ዋጋ ያሏቸው ስምምነቶች ይደረጋሉ፡፡

እንዲህ በሚደረግበት ጊዜ ባለጉዳዮች አንዱ የሌለውን ማንነት የሚያረጋግጡበት፣ የተለዋወጡትን መልዕክት ትክክለኛነት፣ ከስምምነት በኋላ መልሶ ቃልን አጥፎ አለመካካድን ቢያንስ የሚቀንስ አሠራር ማስፈን አስፈላጊ ነው፡፡ አንዱና ተመራጩ ዘዴ በዚሁ በሳይበር ዓለም ውስጥ ሆኖ ጥቅም ላይ የሚውል የፊርማ ቴክኖሎጂ ሕጋዊ ከለላና ዕውቅና መስጠት ነው፡፡ በተለይ እያደገ በመጣው የኤሌክትሮኒካዊ ንግድ፣ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ መኖር ፋይዳው የላቀ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም አቀፍ ንግድ ሕግ ኮሚሽንም የኤሌክትሮኒክ ፊርማን አስፈላጊነት በመረዳት እ.ኤ.አ. በ2001 ለአገሮች በሞዴልነት የሚጠቀሙበትን ሕግ ከእነ ማብራሪያው አፅድቋል፡፡ ይኼን ሞዴል ሕግ የወጣው ይኼው ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በ1996 ያወጣውን ሞዴል የኤሌክትሮኒክ ንግድ ሕግና ማብራሪያ ተከታይ ሆኖ ነው፡፡ ለንግዱ ስምረት የፊርማው ደጋፊነት ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው የታወቀ በመሆኑ ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ማዕከላዊ ማጠንጠኛው፣ ባለፈው ዓመት የወጣውን የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ላይ ምጥን ቅኝት ማድረግ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ሕግ ገና አላወጣችም፡፡ አንዳንድ አገሮች ይህንን ሕግ ካወጡ ሁለት ደርዘን ዓመታት ገደማ እየሆናቸው ነው፡፡ በሳይበሩ ዓለም የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎችና ግንኙነቶች መልክ የሚያስይዙ፣ መብትና ግዴታን የሚወስኑ፣ ሕግጋት በማውጣት በኩል ኢትዮጵያ ገና ብዙ የቤት ሥራ አለባት፡፡ ይኼንን የቤት ሥራዋን ለመወጣት ስትል የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጁን አውጥታለች፡፡

አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ቀሪ ተግባራት አሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ማንም ሰው በየትኛውም ዓይነት ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ላይ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ካለው በሕግ ፊት ዋጋ እንደማያጣ አዋጁ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ የትኛውም መልዕክት በኤሌክትሮኒክ መልክ፣ ፊርማም የኤሌክትሮኒክ በመሆኑ ብቻ ተቀባይነት የላቸውም ሊባል እንደማይገባ አስገዳጅ ድንጋጌን ይዟል፡፡

በኤሌክትሮኒክ የሚደረጉ መልዕክቶች (መረጃዎች) እና ፊርማ በወረቀት ከሚደረጉት ጋር እኩል (የተመጣጣነ) ዋጋ ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ተገልጋዮችም፣ የሕግ ተማሪዎችና ባለሙያዎችም የኤሌክትሮኒክ ውሎችና ግንኙነቶች ሕጋዊ ውጤታቸውን በሚመለከት ይኼንን አዋጅ ከግምት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የአዋጁ ይዘት በአጭሩ ከቀረበ በኋላ ከኤሌክትሮኒክ ፊርማ ጋር የተያያዙ የተመረጡ ነጥቦች ላይ ማብራሪያም ትችትም ይቀርባል፡፡ አዋጁን በአግባቡ ለመረዳት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በተለይም የመረጃ ማመስጠር (Cryptography) መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦችን ማወቅ ተመራጭ ነው፡፡

የአዋጁ ይዘት በአጭሩ

አዋጁ የወጣው የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡ ‹‹የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በአምስት ክፍሎች የተዋቀሩ 54 አንቀጾችን ይዟል፡፡

በመጀመርያው ክፍል ትኩረቱ ከኤሌክትሮኒክ የፊርማ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በአዋጁም ይሁን ወደፊት በሚወጡ ደንቦችና መመርያዎች፣ እንዲሁም አሠራሮች በወጥነት ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚገባቸውን ቃላትና ሐረጋት፣ እንዲሁም ተቋማት ብያኔ መስጠት (20 ብያኔዎች ተሰጥተዋል)፣ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ተፈጻሚ የሚሆነው ምን ዓይነት የመልዕክት ልውውጦች ላይ እንደሆነ መወሰን፣ የኤሌክትሮኒክ ፊርማን መጠቀም አስገዳጅ መሆን አለመሆኑን ማሳወቅ ነው፡፡

ክፍል ሁለት የኤሌክትሮኒክ ፊርማን፣ የዲጂታል ፊርማን፣ የኤሌክትሮኒክ መልዕክትን ምንነት፣ እንዲሁም ሁለቱ የፊርማ ዓይነቶች በሕግ ፊት የሚኖራቸው ዋጋ፣ የሕግ ግምት፣ መስተባበል አልመስተባበል ስለመቻላቸው የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡

ሦስተኛው ክፍል በኤሌክትሮኒክ ፊርማ አገልግሎት ሥርዓት ውስጥ ቁልፍ ተዋናይ ስለሆነው ተቋም ተመድቧል፡፡ የኤሌትሮኒክ ፊርማ እንዲኖረው የሚፈልግ ሰው ለኤሌክትሮኒክ ፊርማ የሚሆኑ አገልግሎቶች ከሚሰጥ ድርጅት ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችን ፈቃድ የሚሰጥ፣ አሠራራቸውን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ሌላ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ስለሚያስፈልግ፣ ይኼንን ተግባር እንዲወጣ ሥልጣን የተሰጠው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ስለሆነ ከኤሌክትሮኒክ ፊርማ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያሉትን ሥልጣንና ተግባር የተዘረዘረበት ክፍል ነው፡፡ ፈቃድ እንዴት መስጠት እንዳለበትና መሟላት ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ የፈቃድ እድሳት፣ ዕገዳና ስረዛ ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎችን፣ እንዲሁም የማገድና የመሰረዝ ውጤትንም እንዲሁ አካትቷል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ፊርማ የሚኖረው ሰው ፊርማው የእሱ እንደሆነ የሚያሳይና የሚያስረዳ ማረጋገጫ (ሰርተፊኬት) ያስፈልገዋል፡፡ አዋጁ በወጥነት የሚጠቀመው ሰርተፊኬት በማለት ነው፡፡ የምስክር ወረቀት እንዳይለው በወረቀት ሳይሆን በኤሌክትሮኒክ መልክ የሚዘጋጅ ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ሰርተፊኬት የሚሰጡ ድርጅቶችን ማንነትና አስተማማኝነት የሚያረጋግጥ ሌላ ሰርተፊኬት ስለሚያስፈልግ ኤጀንሲው ‹‹ሥርወ ማረጋገጫ ሰጪ ባለሥልጣን›› ሆኖ ያገለግላል፡፡ ለዚያም ስያሜውም ‹‹ሩት ሰርተፊኬት ባለሥልጣን›› የተባለው፡፡ በርካታ አገሮችም ይኼንኑ አጠራር መከተልን መርጠዋል፡፡ አዋጁ የመረጠው  ‹‹ሩት ሰርተፊኬት ባለሥልጣን›› የሚለውን የእንግሊዝኛና አማርኛ ጉራማይሌ አጠራር ነው፡፡ ይህ ክፍል ከአንቀጽ 9 ጀምሮ እስከ 21 ድረስ ይዘልቃል፡፡

ክፍል አራት ከአንቀጽ 22 እስከ 49 ድረስ ያሉትን አንቀጾች በማካተት በአራት ንዑሳን ክፍሎች ተከፋፍሏል፡፡ የመጀመርያው ንዑስ ክፍል ለኤሌክትሮኒክ ፊርማ ወሳኝ ድርሻ ያለውን ሰርተፊኬት ስለሚሰጡት ድርጅቶች ነው፡፡ ምን ምን አገልግሎት እንደሚሰጡ፣ ሰርተፊኬት ሰጪ ለመሆን ሟሟላት ስለሚገባቸው መሥፈርቶች፣ ስለሰርተፊኬቱ ይዘት፣ በተለይም ስለቁልፍ አስተዳደርና የገንዘብ ዋስትና፣ ብሎም የመረጃ አያያዝና ጥበቃን ይመለከታል፡፡ ሁለተኛው ንዑስ ክፍል የሚያጠነጥነው የሰርተፊኬት ለመግኘት መሟላት ስለሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ ስለሚፀናበት፣ ስለሚታገድበትና ስለሚሰረዝበት አጋጣሚዎች ነው፡፡

ከዚህ በመቀጠል ያለው ደግሞ ስለሰርተፊኬት ሰጪው ኃላፊነት የሚመለከት ነው፡፡ አገልግሎቱን ሲሰጥ ማድረግ ያለበትን፣ ተጠያቂነቱን፣ ወዘተ ይዟል፡፡ አራተኛው ንዑስ ክፍል ሰርተፊኬት ያላቸውን ፈራሚዎችና ፊርማውን ተማምነው የፈራሚውን ተግባራት የሚቀበሉ ሰዎች ስለሚኖርባቸው አስቀድሞ የማረጋገጥ ኃላፊነትን  የሚመለከቱ አንቀጾች ናቸው፡፡

አምስተኛው የአዋጁ ክፍል በሰርተፊኬት ሰጪዎችና በሩት ሰርተፊኬት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፣ እንዲሁም በተገልጋዮችና በሰርተፊኬት ሰጪዎች መካከል የሚነሳን አለመግባባት እንዴት እንደሚፈታ አስተዳደራዊውንም የፍርድ ቤትንም አካሄድ የሚመለከት ነው፡፡ በተጨማሪም ሰርተፊኬት ሰጪዎችና ባለፊርማዎች በአዋጁ የተጣሉባቸውን ግዴታዎች ሳይወጡ ቢቀሩ ስለሚኖርባው የወንጀል ቅጣትም በዚሁ ክፍል ሥር ተካትቷል፡፡

አዋጁ የያዛቸው ከላይ የተገለጹትን ጉዳዮች ነው፡፡ በመቀጠል በኤሌክትሮኒክ ፊርማ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ መብራራት የሚገባቸውን የተወሰኑ ነጥቦችን እንመለከት፡፡

ኤሌክትሮኒክና ዲጂታል ፊርማዎች

አዋጁ አንቀጽ 2 (6) ለኤሌክትሮኒክ ፊርማ ብያኔ ሰጥቷል፡፡ እንዲህ የሚል ‹‹ከኤሌክትሮኒክ መልዕክት ጋር በተያያዘ ፈራሚውን ለመለየትና በመልዕክቱ የተካተተው መረጃ በፈራሚው የፀደቀ ወይም ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ለማመልከት ጥቅም ላይ የሚውል በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ላይ የተለጠፈ ወይም ከመልዕክቱ ጋር ምክንያታዊ በሆነ አኳኋን የተቆራኘ በኤሌክትሮኒክ መልክ ያለ መረጃ ነው፡፡ ‹‹አዋጁ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 5 ላይ የኤሌክትሮኒክ መልዕክትን ‹‹በኤሌክትሮኒክ አማካኝነት የሚመነጭ፣ የሚላክ፣ የሚደርስ ወይም የሚከማች መረጃ ነው›› በማለት ብያኔ ሰጥቷል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ጥቅም ላይ እንዲውል መነሻ የሆነው መልዕክት፣ በኤሌክትሮኒክ አማካይነት የሚመነጭ፣ ወይም የሚተላለፍ አሊያም የሚከማች መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት ቴክኖሎጂን የሚጠቀም መልዕክት  ላይ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ በመጠቀም የመልዕክቱ ባለቤትን ማንነት፣ መልዕክቱ በፈራሚው መፅደቁን የሚያረጋግጥ ሆኖ መልዕክቱና ፊርማው የተቆራኘ ወይም የተለጠፈም ሊሆን ይችላል፡፡

እዚህ ላይ የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ከሚባል ይልቅ የውህብ (የዳታ) መልዕክት ቢባል የተሻለ ነበር፡፡ በአንድ በኩል እንዲህ ዓይነት ፊርማ የሚጠይቁ መልዕክቶች በኤሌክትሮኒክ ቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ሳይሆን በኦፕቲካልና ሌሎችም የማስተላለፊያ ዘዴዎችን መጠቀም ስለሚቻል ነው፡፡ በሌላ በኩል ቴክኖሎጂው በፍጥነት ተለዋዋጭ በሆነበት ዓለም ‹‹በኤሌክትኒክ አማካይነት›› ብሎ መገደብ በሕግ አወጣጥ የሚመከር አይደለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ሞዴል ሕግ ሲያወጣም እዚሁ ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጎበት ውህብ መልዕክት (Data Message) የሚለውን በመምረጥ የሚመነጭበት፣ የሚላክበትን፣ የሚደርስበትንና የሚከማችበትንም ‘ኤሌክትሮኒክ’ በሚል ብቻ እንዳይታጠር አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም የሚዲያ (የቴክኖሎጂ) ገለልተኛነትም አንዱ ኤሌክትሮኒክ ፊርማ መርህም ነው፡፡ ፊርማው የሚዘጋጅበትን ቴክኖሎጂም ይሁን መልዕክቱና ፊርማውን የሚይዘውን፣ ለይቶ ‘እንዲህ ዓይነት የሆነ’ ብሎ መወሰን ለሆነ ቴክኖሎጂ መወገንንና ማዳላትን ያመጣል፡፡ ስለሆንም አዋጁ ላይ የተቀመጠበት መንገድ የሚዲያና ቴክኖሎጂ ገለልተኝነት መርህን ይጥሳል፡፡

ስለኤሌክትሮኒክ ፊርማ ይኼን ያህል ካልን ወደ ዲጂታል ፊርማ እንለፍ፡፡ ዲጂታል ፊርማ በመሠረቱ ኤሌክትሮኒክ ፊርማ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ዲጂታል ፊርማ አይደለም፡፡ ዲጂታል ፊርማ ለመባል መሟላት ያለባቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ እነዚህን መሥፈርቶች አንቀጽ 2 (4) ሥር እናገኛቸዋለን፡፡

የመጀመርያው ፊርማው የሚዘጋጅበት የምስጠራ ዓይነት ‹‹አሴሜትሪክ ክሪፕቶ ሥርዓት›› መሆን አለበት፡፡ በመቀጠል ፈራሚውን ከሌላ ሰው ነጥሎ በመለየት ማቆራኘት የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የፈራሚውን ማንነትም ማሳወቅ አለበት፡፡ በተጨማሪም ፊርማ ለመፈረም የሚያስችለውን የግል ሚስጥራዊ ቁልፍ ፊርማ በሚፈረምበት ጊዜ ሁሉ በፈራሚው ሙሉ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ የመጨረሻው  ፊርማው ከኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ጋር የተቆራኘ ሆኖ፣ ከተፈረመ በኋላ የሚደረግ የመልዕክትም ሆነ የፊርማ ለውጥን መለየት የሚያስችል ሥርዓትን የሚከተል መሆን አለበት፡፡ እነዚህን መሥፈርቶች የሚያሟላ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ዲጂታል ፊርማም ይሆናል ማለት ነው፡፡

ዲጂታል ፊርማ እንዴት ይዘጋጃል? እንዴትስ ይፈረማል? የሚሉትን እንመልከት፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ሕጉን ለመረዳት ስለሚያግዝ ነው፡፡ ከላይ እንደቀረበው ዲጂታል ፊርማ አሴሜትሪክ ክሪፕቶ ሥርዓትን መጠቀም አለበት፡፡ አሴሜትሪክ ክሪፕቶ ሥርዓት ማለት መልዕክት በኤሌክትሮኒክ ዘዴ በሚላክበት ጊዜ መልዕክቱን (ፊርማንም ጨምሮ ሊሆን ይችላል) በሚስጥር (የግል) ቁልፍ (Private key) በመጠቀም ወደ ሚስጥራዊ መረጃ በመቀየር (Encrypt በማድረግ) ይላክና ተቀባዩ ጋር ሲደርስ በሚያገኘው ይፋዊ ቁልፍ (Public key) አማካይነት በመጠቀም መልዕክቱን ወደ ቀድሞ ይዞታው በመመለስ (Decrypt በማድረግ) ፊርማው የማን እንደሆነ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ነው፡፡ ‘አሴሜትሪክ’ መባሉ መልዕክቱ ሲላክ (ፊርማውንም ጨምሮ) የተመሰጠረበት (Encrypt የተደረገበት) ቀመር (የግል ቁልፍ) እና መልዕክቱ ከደረሰ በኋላ ከመመስጠሩ በፊት ወደነበረበት ለመመለስ (Decrypt ለማድረግ) ጥቅም ላይ የሚውለው ይፋዊ ቁልፍ የተለያዩ በመሆናቸው ነው፡፡ ማመስጠሪያውም መፍቻውም ተመሳሳይ ከሆኑ ‹‹ሴሜትሪክ ክሪፕቶ ሥርዓት›› ይሆናል፡፡ ‘አሴሜትሪክ’ የሚለው እንግሊዝኛ ቃል የተለያዩ፣ አንድ ዓይነት ያልሆኑ ማለት ነው ጥቅም ላይ የዋለው፡፡ ስለሆነም ዲጂታል ፊርማ ሲፈረም መልዕክት ወይም ፊርማ ወይም ሁለቱንም ለማመስጠር የሚያገለግል የግል ቁልፍ መኖር ግድ ነው፡፡ መልዕክት ከተጻፈ በኋላ ይኼንን የግል ቁልፍ በመጠቀም ፊርማው ከመልዕክቱ ጋር ይቆራኛል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ቢኖር ፊርማውን የሚፈጥረው የግል ቁልፍ በመልዕክቱ መጠን ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ መልዕክቶቹ በተለያዩ መጠን ፊርማውም የተለያየ እንጂ ወረቀት ላይ እንደምንፈርመው ዓይነት ተመሳሳይ አይደለም፡፡ መልዕክቱና ፊርማውም አይነጣጠሉም፡፡

ፊርማው፣ ላኪው ማን ነው ለሚለው ስሙንና ሌሎች ሰርተፊኬቱ ላይ የሠፈሩትን መለያዎች ማሳየት መቻል ነው፡፡ የላኪውን ማንነት፣ የመልዕክቱን ትክክለኛነት ለማገናዘብ ደግሞ ተቀባዩ የተላከለትን (በላኪው የፊርማ ሰርተፊኬት ላይ የሠፈረውን) ይፋዊ ቁልፍ በመጠቀም ማረጋገጥ ያስችለዋል፡፡ ስለሆነም የትኛውም ዲጂታል ፊርማ ተፈጻሚ የሚሆነው በእነዚህ ጥንድ ቁልፎች (Key Pair) አማካይነት ነው ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ቁልፎች እርስ በራሳቸው የሚተዋወቁ ሲሆኑ፣ አንዱ ፊርማ ይፈጥራል፡፡ ሌላኛው የፊርማውን ባለቤት ማንነትና ለመልዕክቱ የሰጠውን ይሁንታ ለማወቅ ይጠቅማል፡፡

የግል ቁልፉ ፊርማው በተደረገበት ጊዜ በፈራሚው ቁጥጥር ሥር የነበረ ካልሆነ ሌላ ሰው ፈርሞታል ማለት ነው፡፡ ፊርማው የተደረገበትን ቀን፣ ሰዓትና ደቂቃ ማሳየትም አለበት፡፡ ወይም ደግሞ የጊዜ ማኅተም (Time Stamp) አብሮ መኖር አለበት፡፡ ፊርማ የተደረገበትን ጊዜ የሚያሳይ፡፡ አዋጁ ላይ የጊዜ ማኅተም አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ራሳቸውን ችለው ሊኖሩ እንደሚችሉ ወይም ሰርተፊኬት የሚሰጡ ድርጅቶች ይህን አገልግሎት ሊያቀርቡ እንደሚችሉ በአንቀጽ 23 መሠረት ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ አንቀጽ 25 (2) ላይ እንደምናገኘው ሰርተፊኬት ሰጪ ድርጅት የባለ ፊርማውን የግል ቁልፍ ቅጅ መያዝ እንደማይችሉና ይህን ተላልፈው ቢገኙ የወንጀል ኃላፊነትም ጭምር እንዳለባቸው አንቀጽ 52 (5) ላይ ተደንግጓል፡፡ እንደፈራሚው ሆነው የተለያዩ መልዕክቶችን ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ ከዚህ ዓይነት ሥጋት ለመጠበቅ ነው፡፡

የዲጂታል ፊርማን ለመፈረም ኮምፒዩተርና መሰል መሣሪያዎች ላይ የሚጫን ሆኖ መለያ ቁጥር በመያዝ፣ ወይም ደግሞ እንደ ባንክ አገልግሎት መጠቀሚያ ኤቲኤም ካርድ ዓይነት የሆነ ካርድ በማዘጋጀት የሚስጢር (የግል) ቁልፉን አብሮ በማተም ከኮምፒዩተር ጋር በማገኛኘት (ማስተዋወቂያ ተጨማሪ ቴክኖሎጂ በመጠቀም)፣ አለበለዚያም ደግሞ በፍላሽ መልክ በማዘጋጀት የትኛውም ኮምፒዩተር ላይ በመሰካት የተዘጋጀው ጽሑፍ ላይ የዲጂታል ፊርማ መፈረም ይቻላል፡፡

ዲጂታል ፊርማ በሚደረግበት ወቅት መልዕክቱ ላይ ፊርማ በማድረግ ወይም ጽሑፉን አስቀድሞ አመስጥሮ በግል ቁልፍ ወይም በሌላ መጭመቅ (Hash ማድረግ ወደ Message Digest መለወጥ፣ የተጨመቀውን ጽሑፍ (Hash Value) በሚስጥር ቁልፍ አማካይነት ፈርሞ መላክ  ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ይፋዊ ቁልፉ የፈራሚውን ማንነት፣ የመልዕክቱን ትክክለኛነትና የተጨመቀውን ወደ ቀድሞ ይዞታው የመመለስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ መልዕክትን ማመስጠር እንደሚቻል፣ ይህንንም አገልግሎትም ሰርተፊኬት ሰጪዎች መስጠት እንደሚችሉ ዕውቅና ቢሰጥም፣ ጥንድ ቁልፍን መልዕክት ለማመስጠርና ለመፍታት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግን  አዋጁ በአንቀጽ 25 (1) አማካይነት ከልክሏል፡፡ የወንጀል ኃላፊነትንም እንደሚስከትል አንቀጽ 52 (5) ላይ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ባሻገር አንቀጽ 25 (3) ለማመስጠርና ለመፍታት ሌላ ቁልፍ በመጠቀም፣ የማመስጠሪያ ቁልፎቹ ቅጂም አገልግሎት ሰጪው ድርጅቱ ሁልጊዜም የመያዝ ግዴታም ተጥሎበታል፡፡ ቅጂውን ሳያስቀር አገልግሎት መስጠት ክልክልም፣ ወንጀልም ነው፡፡

ተመስጥረው የተላኩ መልዕክቶችን ይዘታቸውን ለማወቅ በድጋሜ ማመስጠሪያና መፍቻ ቁልፎቹን መቀበል የሚችለው ተገልጋዩ ወይም ሕጋዊ ወኪሉ፣ እንዲሁም ከፍርድ ቤት ፈቃድ ያገኘ አካል ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ሕግ የፊርማ ጥንድ ቁልፍን በመጠቀም መልዕክትን አስቀድሞ በማመስጠር ከዚያ ፊርማን በማያያዝ መልዕክት ማስተላለፍ አይቻልም ማለት ነው፡፡

ከላይ በተገለጸው መንገድ የዲጂታል ፊርማ አገልግሎት እንዲኖር፣ ሰርተፊኬት ሰጪ ድርጅቶች ሊኖሩ ግድ ነው፡፡ ድርጅቶቹ ሰርተፊኬት በመስጠት ለሌሎች ተገልጋዮች ሰርተፊኬቱን ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመረጃ መከማቻ ቋት (ሪፖዚተሪ) ያስፈልጋቸዋል፡፡ ማንም ዲጂታል ፊርማን አምኖ የፈራሚውን ማንነትም ሆነ የመልዕክቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ሰጪዎች ያስፈልጋሉ፡፡

የኤሌክትሮኒክ ፊርማ የሕግ ዕውቅና ውጤት

በመርህ ደረጃ ማንኛውም ፊርማ በኤሌክትሮኒክ በመሆኑ ብቻ ተቀባይነት አይነፈገውም፡፡ በመሆኑም በእጅ ከሚደረግ ፊርማ ጋር አቻ ፋይዳ (Functional Equivalence) እንዳለው ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ በሕግ ወይም በአሠራር ፊርማ እንዲኖር የሚጠይቅ ድርጊት ወይም አለመፈረም የሚያስከትለው ውጤት በሚኖርበት ጊዜ አስተማማኝ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ተደርጓል በማለት የተጠየቀው የፊርማ መሥፈርት ተሟልቷል ለማለት ፊርማው ለመልዕክቱ ተገቢነት (ተያያዥነት) ካለው፣ የኤሌክትሮኒክ ፊርማን ለመጠቀም ተሳታፊ ወገኞች (ለምሳሌ በኤሌክትሮኒክ ንግድ ሻጭና ገዥ) መካከል ውል ካለ ወይም የግንኙነታቸውን ሁኔታ፣ የተዋዋዮችንና ማንነትና የመልዕክቱን ይዘት ከግምት በማስገባት ሊሆን ይገባል፡፡  በዚህ መንገድ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ መደረጉ ከተረጋገጠ፣ በሌላ ተቃራኒ ማስረጃ እስካልተስተባበለ ድረስ ለማንኛውም የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ፊርማው የባለቤቱ እንደሆነ፣ መልዕክቱን አውቆ እንዳረጋገጠው፣ ፊርማው ካረፈበት ቀን ጀምሮም መልዕክቱና ፊርማው ሳይለወጥ እንደፀና ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ይኼው የሕግ ውጤት በፀና ሰርተፊኬት ለተደገፈም ዲጂታል ፊርማም ያገለግላል፡፡ ተመሳሳይ የሕግ ውጤት አላቸው፡፡

 በመሆኑም አዋጁ አንቀጽ 6(2) አስተማማኝ የሆኑ ኤሌክትሮኒክ ፊርማዎችን ለመለየት ከግምት ስለሚገቡ ሁኔታዎች በመዘርዘር ከእነዚህ መካከል አንዱ ወይም ከእዚያ በላይ ከተሟሉ አንቀጽ 7 ላይ ያሉትን (ፊርማው የባለቤቱ እንደሆነ፣መልዕክቱን ዕውቅና እንደሰጠው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ መፅናቱን) የሕግ ግምቶች ያስከትላል ማለት ነው፡፡ እነዚህ መሥፈርቶች የፀና ሰርቲፊኬት ላለው ሰው አስፈላጊ አይደሉም፡፡ የፀና ሰርቲፊኬት መኖሩ ብቻውን ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ ግምት ያጎናፅፋል፡፡

የኤሌክሮኒክ ፊርማ ፋይዳዎችና ግቦች

ሦስት የታወቁ ግቦችን እንዲያሳካ ነው የኤሌክትሮኒክ ፊርማ በሕግ ጥበቃ እንዲደረግለት ያስፈለገው፡፡ የኤሌክትሮኒክ መልዕክቶችን በፊርማ በማስደገፍ የመልዕክቱንና የፈራሚውን ባለቤት ማንነት ለማረጋገጥ፣ የመልዕክቱ ትክክለኛነት ላይ አመኔታ የሚጣልበት መሆን አለመሆኑን ለመለየትና ተዋዋዮች ቃላቸውን በማጠፍ መከዳዳት እንዳይኖር የሚያግዝ ሥርዓት ለመዘርጋት ነው፡፡ እነዚህ ግቦች በአዋጁ መግቢያም ላይ ተገልጸዋል፡፡ የአዋጁ ስኬትም የሚለካው እነዚህን ሦስቱን ግቦች ተግባራዊ የሚያደረግ ሥርዓት መዘርጋት ሲቻል ነው፡፡

በውጭ አገር የተሰጠ ሰርተፊኬት

የተፈረመበትን አገር መነሻ በማድረግ ለፊርማ ወይም ለሰርተፊኬት ዕውቅና አለመስጠት አድሏዊ እንዳይሆን የሚያደርግ አሠራር መከተልን የሚመለከት መርህ ነው፡፡ አድልኦ ያለ ማድረግ መርህ (Non-discriminatory Principle) ይባላል፡፡ አዋጁ፣ ሌላ አገር የተሰጠን ሰርተፊኬት ኢትዮጵያ ውስጥ ዕውቅና ሊያገኝ የሚችልበትን ሁኔታ ባልጠራ አገላለጽ ጥበቃ ለማድረግ ሞክሯል፡፡

በውጭ አገር የተሰጠን ሰርተፊኬት ዕውቅና አሰጣጥን በሚመለከት አንቀጽ 20 ላይ በአማርኛ ‹‹የውጭ አገር ሰርተፊኬት ዕውቅና ስለመስጠት›› ይልና በእንግሊዝኛው ደግሞ “Recognition of Foreign Certificate Provider” በማለት መስማማት እንዲሳናቸው አድርጎ አስቀምጧቸዋል፡፡ አማርኛው ስለሰርተፊኬቱ ሲሆን እንግሊዝኛው ደግሞ ስለሰርተፊኬት ሰጪው ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ በንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ (በአማርኛውም በእንግሊዝኛውም) የተገለጸው የውጭ አገር ሰርተፊኬት ሰጪ በኢትዮጵያ ሕግ የተቀመጡትን መሥፈርቶች እስካሟላ ድረስ ሰርተፊኬት የመስጠት አገልግሎት እንዲሰጥ ሩት ሰርተፊኬት ባለሥልጣኑ ሊፈቅድለት እንደሚችል ተገልጿል፡፡ የሚሰጣቸውም ሰርተፊኬቶች ሌሎች ሰርተፊኬት ሰጪዎች ጋር እኩል ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ አንቀጽ (አንቀጽ 20) በተቃራኒው በውጭ አገር ሕግ የተቋቋመ ድርጅት ሰርተፊኬት መስጠት አገልግሎት መስጠት እንደማይችል በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 12 (1) (ሐ) ላይ ተቀምጧል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ፊርማን በሚመለከት የአገሮች ደንቦች

አገሮች እንደ ሕግ ሥርዓታቸው የተለያዩ አካሄዶችን እየተከተሉ ነው፡፡ የ‹‹ኮመን ሎው›› አገሮች የኤሌክትሮኒክ ፊርማን በሚመለከት ዝርዝር ሕግጋት በማውጣት መሰናክል ከመፍጠር በመቆጠብ ሰዎች ሊጠቀሙበት እንዲችሉ የሚያበረታታ ዝቅተኛ፣ አመቻች ሥርዓቶችን ጥቅም ላይ ማዋልን (Minimalist Approach) መርጠዋል፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳና አውስትራሊያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የኤሌክትሮኒክ ፊርማን መቼ መጠቀም እንደሚቻልና ተቀባይነት እንደሚኖረው መለኪያና መስፈሪያ ሰጪ የሆኑ ሥርዓት መከተልን የመረጡ (Prescriptive Approach)  የሲቪል ሎው አገሮች አሉ፡፡ በሕግ የተቀመጡ መለኪያዎችን እስካላሟላ ድረስ ረብ የለሽ፣ በሕግ ፊት ዋጋ ቢስ እንደሆነ የሚገልጽ አሠራርን መርጠዋል፡፡

ሁለቱንም አደባልቀው  (Hybrid Approach) ጥቅም ላይ ማዋል የፈለጉ አገሮችም አሉ፡፡ ማንም ሰው እንደፈለገ መጠቀም እንደሚችል፣ በኤሌክትሮኒክ በመሆኑ ብቻ ተቀባይነት እንደማያጣ ይገልጹና የተሻለና አስተማማኝ የሚባለውን ደግሞ እንደ ሲቪል ሎው አገሮች ለይተው ያስቀምጣሉ፡፡

ከእነዚህ አካሄዶች ኢትዮጵያ የመረጠችው ድብልቁን ይመስላል፡፡ ማንም ሰው የኤሌክትሮኒክ ፊርማ መጠቀም እንደሚችል፣ ኤሌክትሮኒክ በመሆኑ ብቻ ተቃባይነት የለውም እንደማይባል ዕውቅና ከሰጠ በኋላ የተሻላ አስተማማኝ ሊባል የሚችለው ፊርማ ማሟላት ያለበትን መሥፈርት በተጨማሪነት ለይቶ አስቀምጧል፡፡ የበለጠ ጥበቃ የሚያደርግለትን ለይቶ አሳውቋል፡፡

በኤሌክትሮኒክ ፊርማ አጠቃቀም ተዋናዮቹ

በፀና ሰርቲፊኬት የተደገፈ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ (ዲጂታል ፊርማ) ጥቅም ላይ በሚውሉበት ወቅት ቢያንስ አራት ተዋናዮች ይኖራሉ፡፡ ለነገሩ ከአራትም ሊበልጡ ይችላል፡፡ የመጀመርያው በሰርተፊኬት የተደገፈ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ እንዲኖረው የሚፈልገው ሰው (ፈራሚ የሚባለው) አለ፡፡ ፈራሚው (Signatory) እንደ ነገሩ ሁኔታ ራሱ ተገልጋይ (Subscriber) ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ድርጅት (የመንግሥት መሥሪያ ቤት) የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ካለው የግል ቁልፉን በመያዝ የሚፈርመው ሰውና መሥሪያ ቤቱን ወክሎ ሰርተፊኬቱን ያወጣው ሰው ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ የግል ቁልፉን ይዞ የሚፈርመው ሰው (ተገልጋዩ) ፊርማ የሚያደርገው ራሱን ወክሎ ሳይሆን ስለድርጅቱ ነው፡፡ በእጅ እንደሚደረገው ‹‹ስለ›› ተብሎ የሚጻፍ ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል የዲጂታል ፊርማ አገልግሎትን ለፈራሚዎች የሚያመቻች ድርጅት ያስፈልጋል፡፡ ሰርተፊኬት ሰጪ ድርጅት ማለት ነው፡፡ ለንግድ ዓላማ የሚቋቋሙ (የግልም የመንግሥትም) ናቸው፡፡ በሰርተፊኬት የተደገፈ ፊርማ ማግኘት ከሚፈልግ ሰው ክፍያ እየተቀበሉ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ለዕድሳትም እንዲሁ በማስከፈል ገቢ ያገኛሉ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ በርካታ ድርጅቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሰርተፊኬት ሰጪዎቹም ጥንድ ቁልፎችን፣ የጊዜ ማኅተሞችን፣ የመልዕክት ማመስጠር ሥራን ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡  የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ላይ አመኔታ ማሳደር ለሚፈልጉ ሰዎች  (Relying Parties) የፈራሚዎችን ሰርተፍኬት የሚያቀርቡበት የውህብ ማዕከል (ቋት) በመገንባት (ወይም በመከራየት) ‘ሪፖዚተሪ’ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡

ሰርተፊኬት ሰጪዎች ራሳቸውም ከሩት ሰርተፊኬት ባለሥልጣን የዲጂታል ፊርማ ሰርተፊኬት አስቀድመው ማግኘት አለባቸው፡፡ አመኔታ አሳዳሪዎችም የፈራሚውንም የሰርተፊኬት ሰጪውንም ማንነትና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ እንዲችሉ ለማስቻል ነው፡፡ የሚሰጡት ሰርተፊኬት ተክክለኛና አስተማማኝ ስለመሆኑ የሚሰጡት ሰርተፊኬት ላይ የገንዘብ ዋስትና (የመተማመኛ ገደብ) ማስቀመጥ  ግዴታም ነው፡፡ ተገልጋዮች አመኔታ እንዲኖራቸውም ያግዛል፡፡

ሰርተፊኬት የመስጠት አገልግሎት ውስጥ ለመሰማራት በግለሰብ  ነጋዴትና ውጭ አገር ከተቋቋመ ድርጅት በስተቀር በሌሎች የንግድ ድርጅት ዓይነቶች መሰማራት የተፈቀደ ነው፡፡

ሰርተፊኬት ሰጪ ድርጅቶች ፈራሚን ከአመኔታ አሳዳሪዎች ጋር በማገናኘት በሳይበር ዓለም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ፣ እንዲቀላጠፉ፣ አስተማማኝ እንዲሆኑ አስቻይ ድልድይ በመሆን ያገለግላሉ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የሰርተፊኬት ሰጪዎቹንና የአገልግሎቱን ሁኔታ የሚቆጣጠረው ደግሞ ሩት ሰርተፊኬት ባለሥልጣኑ ነው፡፡

ቀሪ ተግባራት

በሰርተፊኬት የታገዘ የኤሌክትኒክ ፊርማን ሥራ ላይ ለማዋል በደንብና በመመርያ አማካይነት መወሰን ያለባቸው ቀሪ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእዚያ በኋላ ነው አገልግሎቱ ሊጀምር የሚችለው፡፡ በዚህ መሠረት ባይሆንም ኢትዮ ቴሌኮም ለውስጥ አሠራሩ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ደግሞ በአዋጅ ተፈቅዶለት ጥቅም ላይ አውሎታል፡፡  

የዲጂታል ፊርማ አሠራር ተግባራዊ ካልሆነ መንግሥት የኤሌክትሮኒክ አስተዳደር ሥርዓትን (E-Governance) በአስተማማኝነትና በተሟላ ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል አይችልም፡፡ ባለጉዳዮች ባሉበት አካባቢ ሆነው አቤቱታቸውን ወደሚፈልጉት መሥሪያ ቤት በፊርማቸው አረጋግጠው መላክም የተፈረመ ምላሽም ማግኘት አይችሉም፡፡

የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አገልግሎት መሰጠት ቢጀመር ፍርድ ቤትን ብንወስድ እንኳን በጽሑፍ የሚደረግን ቃለ መኃላ (Affidavit) በፍርድ ቤት ሬጂስትራር ፊት ቀርቦ መፈረምን ያስቀራል፡፡ ዳኞችም የተለያዩ ውሳኔዎችንና ፍርዶችን እንደሰጡ ወዲያውኑ ባለጉዳዮች እንዲያገኙት ያስችላል፡፡ የውሳኔ ግልባጮችንም ከአንዱ ፍርድ ቤት ወደ ሌላው በወረቀት እያባዙ በመውሰድ የሚጠፋውን ሀብትና ጊዜ ያስቀራል፡፡ በባንክ የሚፈጸሙ የገንዝብ ዝውውሮችን (ብድርንም ጨምሮ) አስተማማኝ ለማደረግ የኤሌክትሮኒክ ፊርማን ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ታክስና ግብርንም ባሉበት ሆኖ በአስተማማኝ ሁኔታ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ለመክፈል፣ መካካድ እንዳይኖርም የኤሌክትሮኒክ ፈርማ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ሌሎችም ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የማን ነው?

አዋጁን ያወጣው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ የማውጣት ሥልጣን እንዳለው መነሻ ያደረገውም የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 51(3) እና አንቀጽ 55(2)(ሐ) ነው፡፡ የመጀመርያው አንቀጽ ‹‹… የሳይንስና ቴክኖሎጂ አገር አቀፍ መመዘኛዎችና መሠረታዊ የፖሊሲ መለኪያዎችን ያወጣል፣ ያስፈጽማል፤›› የሚለው ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይ ነው በማለት ሕግንም እንደ ፖሊሲ፣ አገር አቀፍ መመዘኛ ነው ከሚል መነሻ  በመነሳት የፌደራል መንግሥት ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንዳለው ለማሳየት ተጠቅሞበታል፡፡

 አንቀጽ 55 (2)(ሐ) ደግሞ  የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትን የሚመለከቱ ሕጎችን ማውጣት ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠ መሆኑን ዕውቅና የሚሰጥ ነው፡፡ የመጀመርያው መጣረስ የሚመጣው ከእነዚህ ሁለት መነሻዎች ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ፊርማን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እንደሆነ ከተወሰደ በቀጥታ ሊጠቀስ የሚገባው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 (3) ሳይሆን የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 ነበር፡፡ የፖስታና የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶችን በሚመለከት ፖሊሲ የማውጣት ሥልጣን የፌዴራሉ እንደሆነ የሚደነግገውን በመተው ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመልሷል፡፡ በቀጥታ የሚገናኘውን በመተው ወደ ሌላ ሄዷል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አገልግሎት በኤሌክትሮኒክ በመሆኑ ብቻ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳይ ነው ማለትስ ይቻላል ወይ? ‹‹የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳዮችን በሚመለከት አገር አቀፍ መመዘኛና መሠረታዊ ፖሊሲ መለኪያ ማውጣት›› የሚለው ዝርዝር ሕግጋት ማውጣትን ይጨምራል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው፣ በፌዴራል መንግሥት ቢወጣ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጉልህ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል ግን መካድ አይቻልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ፋይዳ እንዳለው ከታመነበት ሕግ የማውጣት ሥልጣኑን ለፌዴራል መንግሥት እንዲሆን የሚወስነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 (6) ላይ ተገልጿል፡፡ አዋጁ ግን ያለፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ነው የወጣው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...