Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ነፃ የቢዝነስ ውድድር ለጤናማ ኢኮኖሚ

በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ውድድር የግድ ነው፡፡ ውድድሩ ግን ጤናማ መሆን ይኖርበታል፡፡ አገራችን ነፃ ገበያና ነፃ ሥርዓት እየተከተለች ነው ቢባልም፣ በአግባቡ እየተተገበረ ነው ማለት አይቻልም፡፡ መንግሥት እንደ አንድ ተወዳዳሪ ከግሉ ዘርፍ ጋር ፉክክር በሚገባበት አገር እንዴት ነፃ ገበያ ይታሰባል ሊባል ይችላል፡፡ ትክክል ነው፡፡ መንግሥት የግሉ ዘርፍ በቀላሉ ሊሠራቸው የሚችሉ ሥራዎች ላይ መግባቱ ከነፃ ገበያ ሥርዓት ጋር የሚቃረንና ጤናማ ያልሆነ ውድድር ሥር እንዲሰድ አድርጓል   የሚለውም ሐሳብ እውነትነት አለው፡፡

ከዚህ በመለስ ግን በገበያ ሥርዓት ውስጥ የሚታየው የውድድር ሥልት ደግሞ የበለጠ አሳሳቢ መሆኑን እያየን ነው፡፡ አብዛኛው ውድድር የንግድ ተጠቃሚዎችን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በትውውቅ፣ በአካባቢ ልጅነትና በመሰል ጉዳዮች ላይ ተመሥርቶ ሲሆን ደግሞ እጅግ ያሳዝናል፡፡ እከክልኝ ልከክልህም ሆኖ ሲታይ በውድድር ለሚሠራ ሥራ እንቅፋት ይሆናል፡፡

ያልተገባ የቢዝነስ ግንኙነት ወይም ያለውን ቢዝነስ ለማሳደግ ሲባል በግል ዘርፉ የእርስ በርስ ውድድሩ እንዲህ ባለው አመለካከለት ከተቃኘ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡

ትክክለኛውን የውድድር መንፈስን ትቶ ገበያን ‹‹ከራስ ወገን›› ብቻ አገኛለሁ በሚል መጓዝ፣ የነፃ ገበያን ከመጣረስ በላይ ጠንካራ ኩባንያዎችን ለመፍጠርም አያስችልም፡፡

ያልተገባ ‹‹ውድድር›› ትናንሽ በምንላቸው ብቻ ሳይሆን በትልልቆቹ ላይም ይታያል፡፡ አንዳንድ ትልልቅ የሚባሉ ኩባንያዎች አፈጣጠር ዘርን መሠረት አድርገው ከመቋቋማቸው ጋር ተያይዞ ችግሩን ሲያባብሱት እየተመለከትን ነበር፡፡ አሁንም በቡድን ተጠራርቶ የሚሠራ ሥራ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የኩባንያ አወቃቀር የቱንም ያህል ውጤት እያስመዘገበ ነው ቢባል ውሎ አድሮ የሚያመጣው መዘዝ ቀላል ባለመሆኑ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በተለይ በበርካታ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚንፀባረቅ በመሆኑ ደግሞ ሁኔታው ያሳስባል፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ከየትኛውም በአክሲዮን ደረጃ ከተዋቀሩ ኩባንያዎች አትራፊና ውጤት የሚታይባቸው ቢሆኑም፣ አሁንም የመወዳደሪያ አዝማሚያቸው ግን ጤናማ አለመሆኑን የሚያሳዩ ምልክች አሉ፡፡

ለዚህ አንድ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንድ ባንክ ለሚሰጠው ብድር እንደመሥፈርት የሚያቀርበውን መመልከት ይቻላል፡፡ አንድ ተበዳሪ ከሚወስደው ብድር ጋር ተያይዞ የመድን ሽፋን ቢፈልግ፣ አበዳሪው ባንክ በድፍረት ተበዳሪው የመድን ሽፋኑን ማግኘት ያለበት ከእከሌ የኢንሹራንስ ኩባንያ መሆኑን ይነግረዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ተበዳሪው ባይፈልግ እንኳን በመሬት ላይ ያለው አሠራር ያስገድደዋል፡፡ ወይም ብድሩን ለማግኘት ከፈለገ የግድ አበዳሪው ባንክ ወደሚጠቀምበት ኢንሹራንስ ኩባንያ መሄድ ግድ ይለዋል፡፡ ተበዳሪው የተሻለ ዋጋ የሚሰጠው ወይም ለዘመናት ደንበኛ ወደሆነበት የኢንሹራንስ ኩባንያ መሄድ አይችልም ማለት ነው፡፡

እንዲህ ያለው አካሄድ ተወዳዳሪ አያደርግም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ከዚህ ቀደም እንደምንሰማው አንድ ለገንዘብ ያደረ የሕክምና ባለሙያ በሽተኛ መርምሮ መድኃኒት ሲያዝ፣ ይህንን መድኃኒት መግዛት ያለብህ እከሌ ከሚባለው ፋርማሲ ነው እንደሚለው ዓይነትም ነው፡፡ አሊያም እዚያው ጤና ተቋሙ ውስጥ ወዳለው ፋርማሲ ይመራዋል፡፡ ይህ ታካሚ መድኃኒቱ እዚያ ካለው ዋጋ ባነሰ የሚገኝበት ፋርማሲ የሚያውቅ ቢሆን እንኳን ዕድሉን እንዳያገኝ ይደረጋል፡፡ አሁንም የፋይናንስ ተቋማት የሚያደርጉት የውድድር መንፈስ እንዲህ ዓይነት ከሆነ፣ ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ አይደለም ማለት ነው፡፡

ተጠቃሚ በገበያ ውድድር መርጦ እንዲጠቀም የሚያስችለው ዕድል ከሌለ፣ በውድድር የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር እንዴት እንደሚቻል ያጠያይቃል፡፡

ችግሩ በዚህ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ባልተገባ መንገድ የሚገኝ ገበያን የለመደ ተቋም፣ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያበቃውን ወሳኝ ሥራ ይዘነጋል ማለት ነው፡፡ እውነተኛ ውድድሩ ሲመጣም ይቸገራል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገርም ጦስ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ችግሩ የተቋማቱ ብቻ ሳይሆን የተገልጋዩም የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ በእከከኝ ልከክልህ ወይም በሠፈር ልጅነት የሚፈጠር ቢዝነስ ውሎ አድሮ አደጋ አይጠፋውም፡፡ ለምሳሌ አንድ ተገልጋይ የተሻለ ኢንሹራንስ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሰጠኝ ማነው? የተሻለ ሊያበድረኝ የሚችለው ማነው? ብሎ ማሰብና ሒሳቡን ሠርቶ ወደ ተሻለው ሄዶ መገልገል እየቻለ፣ በትውውቅ ወይም በአገር ልጅነት አሥልቶ የሚሄድ ከሆነ አሁንም ነፃ ገበያ አልገባንም፡፡ ነገ የሚመጣው መዘዝ ቀላል እንደማይሆን አለማሰብ ነው፡፡

የተያዘው መነጣጠቅ ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ቢዝነስ እጅ ጠምዝዞ ለመውሰድ የሚያቀርበው ነገር ገበያን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡፡፡

በእርግጥ ገበያውን ለማግኘት አሳማኝ የሆነ ዋጋና የተሻለ አገልግሎት ቀርቦ ከሆነ ምንም ችግር የለውም፡፡ ችግር የሆነው ግን ከዚህ ውጪ ባለ መንገድ መሆኑ ነው፡፡

በአካባቢ ልጅነት የሚቋቋሙ ኩባንያዎች በዚህ መንገድ መጓዝ እንደሌለባቸው ቢታወቅም፣ በውድድር ያላገኙትን ገበያ ለመያዝ የሚረግ ጥረት በፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

ገንዘብና ቢዝነስ ዘር የሌላቸው መሆኑን ማወቅ ተገቢም ይሆናል፡፡ አንዳንዴ በዘርና በአካባቢ ልጅነት፣ እንዲሁም በሃይማኖት ጭምር ተቋቋሙ የሚሉ ተቋማት አገልግሎታቸውም በዚያው ልክ ሊጠብ የሚችል ስለመሆኑ መገመት አያቅትምና፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አመለካከት መውጣት ያስፈልጋል፡፡ እንዲያውም ጠንካራ ለመሆንና እከሌ የእከሌ ባንክ ነው ከሚለው አመለካከት ለመውጣት ተሰብስበው ወይም ተዋህደው ተወዳዳሪ ለመሆን ማሰብ የሚጠበቅባቸው ይሆናል፡፡

ደግሞም አገሪቱ እንዲህ በተበታተነ ሁኔታና በአካባቢና በሠፈር ልጆች ስለመቋቋማቸው የሚነገርላቸው የፋይናንስ ተቋማት ከፊታቸው ያውም በአጭር ጊዜ ውድድር የሚጠብቃቸው በመሆኑ፣ ከአሁኑ ቢያስቡበት መልካም ነው፡፡ ገበያና ቢዝነስ አገልግሎትና ዋጋን መሠረት በማድረግ እንደ አገር ለሚጠብቃቸው ውድድር ራሳቸውን ቢያዘጋጁ ይመረጣል፡፡ ነገ ውድድሩ አሁን እንደለመድነው አይሆንምና ቢዝነስ ዘር የማይመርጥ ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ጭምር በማሰብ ቢሠራ ይመረጣል፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት