ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ ዜጎች ከገንዘብ ተቋማት ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጀመርያ ዙር ወይይት ተካሄደበት።
ምክር ቤቱ ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ መግቢያ እንደሚያስረዳው፣ የአገሪቱ ዘመናዊ የብድር ሥርዓት ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በብድር መያዣነት ውለው ተጨማሪ ጥቅም ማመንጨት የሚችሉበት አሠራር ባለመኖሩ፣ የአገሪቱን ዕምቅ ሀብት በሙሉ ወደ ኢኮኖሚያዊ ልማት መለወጥ አልተቻለም።
በአገሪቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በድህነት ውስጥ ሕይወታቸውን እየገፉ መሆናቸውን የሚያመለክተው የረቂቁ አባሪ ማብራሪያ ሰነድ፣ እነዚህ ሰዎች በድህነት ውስጥ ኑሯቸውን እንዲገፉ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ የአገሪቱ የብድር ሥርዓት ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠር ውስንነት ያለበት በመሆኑ ነው።
ዜጎች ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠር የሚያስችል ብድር ከአበዳሪ የገንዘብ ተቋማት ማግኘት የሚችሉት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ብቻ በዋስትና በማስያዝ እንዲሆን ተደርጎ፣ የብድር ሥርዓቱ በመቀረፁ ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት አለመቻሉን ማብራሪያ ሰነዱ ያስረዳል።
ይህ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩም ከገንዘብ ተቋማት ብድር ለማግኘት በዋስትናነት የሚቀርቡት እንደ የመኖሪያና የአገልግሎት ሕንፃዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች የመሳሰሉት ብቻ ሆነው መገደባቸውን ይገልጻል፡፡ የአገሪቱን አጠቃላይ ሀብት አሟጦ ለመጠቀም ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በዋስትና መቅረብ የሚችሉበትን የሕግ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ እንዳደረገው ረቂቁ ያስረዳል።
በመሆኑም ረቂቅ ሕጉ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ ተጨማሪ ሀብት መፍጠር፣ በዜጎችም ሆነ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ታልሞ መዘጋጀቱን ያስረዳል።
በዚህም መሠረት የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ግኡዝ ወይም ግኡዝ ያልሆኑ ንብረቶችና ሀብቶች፣ ሰብሎች፣ የመገልገያ መሣሪያዎች፣ የባንክ ተከፋይ ሒሳቦች፣ የተረጋገጠ የገቢ ገንዘብ ማስረጃዎችን በዋስትና በማቅረብ ከገንዘብ ተቋማት ብድር ማግኘት የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በረቂቅ አዋጁ ተካተው ቀርበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ዋጋ የሚያወጡ የእንስሳት ሀብቶችና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ሀብቶችን ለብድር ዋስትና በማስያዝ ዜጎች ወይም ባለሀብቶች ከልማዳዊው ወይም ነባሩ የገንዘብ አቅርቦት አማራጭ ሌላ፣ አዲስ የኢንቨስትመንት ካፒታል ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጠር ይገልጻል።
ሕጋዊ ማዕቀፍ ማበጀቱም ዋስትናው የተጠበቀ ዘመናዊ የብድር ሥርዓትን በማስፋፋት፣ ግለሰቦችና ተቋማት ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በዋስትና በማስያዝ አዲስ የብድር ምንጭ እንዲያገኙና በዚህ በሚፈጠረው አዲስ ካፒታልም ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት፣ በሒደቱም በከተሞች ላይ ያተኮረውን የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነት ማስፋፋትና የበለጠ ማሳደግ እንደሚቻል የማብራሪያ ሰነዱ ያስገነዝባል፡፡
ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ተጨማሪ ካፒታል እንዲፈጥሩ ከልማዳዊ የዋስትና አሰጣጥ ወደ ሕጋዊና ተዓማኒነቱ የተረጋገጠ የዋስትና ሥርዓት እንዲገቡ፣ እንዲሁም ብድር የተወሰደባቸው ንብረቶች በሌላ ወገን ወይም በሌላ አካባቢ ዕዳቸውን ከፍለው ሳይጨርሱ ሌላ ብድር እንዳይወሰድባቸው ለማስቻል፣ ሁሉን አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ማዕከል እንዲከናወን የሚያስችል ድንጋጌ በረቂቁ ተካቷል።
ለዚህም ሲባል የዋስትና መዝገብ ጽሕፈት ቤት እንደሚቋቋም፣ የሚቋቋመው የምዝገባ ጽሕፈት ቤት ሥልጣንና ተግባር፣ ዋስትና ሰጪ ዋስትናን ለማስመዝገብ ማሟላት የሚጠበቅበት ተግባራትና መሥፈርቶች፣ በዋስትና መዝገብ ጽሕፈት ቤቱ የተመዘገቡ ዋስትናቸውን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግና በሕግ አግባብ መረጃ መስጠት እንደሚጠበቅበት ያመለክታል።
ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ ለበጀትና ለፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።