Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሱሉልታ ከተማ ሁለት ፋብሪካዎች የእሳት ቃጠሎ ደረሰባቸው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ 2.3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ንብረቶች ተቃጠሉ

በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሱሉልታ ከተማ መጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡15 ሰዓት አካባቢ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ አንድ የሻማና የሳሙና ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ ሲወድም፣ አንድ የዘይት ፋብሪካ በከፊል ቃጠሎ ደረሰበት፡፡

የወዳጆ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ንብረት የሆነው አቢሲኒያ የሻማና ሳሙና ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ በቃጠሎ የወደመ ቢሆንም፣ የንብረቱን ግምት ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ባለድርሻዎቹ ካልተሰባሰቡ መናገር ስለማይቻል መረጃውን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ በወቅቱ በፋብሪካው የተገኙ አንድ ባለድርሻ ገልጸዋል፡፡

የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቲጃን ናስር የቃጠሎው ምክንያት አልታወቀም ብለዋል፡፡ የእሳት ቃጠሎው ከጠዋቱ 2፡15 ሰዓት ላይ በመከሰቱ ምናልባት የኤሌክትሪክ ወይም ሌላ ሊሆን ስለሚችል በመጣራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በእሳት አደጋው አቅራቢያ የሚገኘው አሳዬ በሚባል የዘይት ፋብሪካ ላይ እሳቱ የተዛመተ ቢሆንም በአካባቢው ወጣቶች፣ ከአዲስ አበባና ከሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በደረሱ የድንገተኛ እሳትና አደጋዎች መቆጣጠር ባለሥልጣን ተሽከርካሪዎች፣ የአካባቢው የፀጥታ አካላትና የሕዝብ ትብብር ሊተርፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መቆጣጠር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ሦስት ተሽከርካሪዎች፣ 140 ሺሕ ሊትር ውኃና 4,200 ሊትር ኬሚካል ፎም በመጠቀም እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡ የአካባቢው ወጣቶችና ነዋሪዎችም ከፍተኛ ዕገዛ ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በተለይ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች በተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎዎች እየደረሱ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጋቱ፣ ምክንያቱ ደግሞ ከተሞቹ በርካታ ፋብሪካዎች ቢኖሯቸውም ጥንቃቄ ስለማይደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ሠራተኞችም ሆኑ ባለንብረቶች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ከመጋቢት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች፣ በአጠቃላይ 2.3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ንብረቶች በእሳት ቃጠሎ መውደማቸውን አቶ ንጋቱ ገልጸዋል፡፡

በቡራዩ ከተማ ሸክላ ፋብሪካ አካባቢ ግምቱ 150 ሺሕ ብር የሆነ የከተማ አውቶብስ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጌቱ ኮሜርሻል በስተጀርባ ግምቱ 200 ሺሕ ብር የሆነ መኖሪያ ቤት፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጎተራ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ግምቱ 600 ሺሕ ብር የሆነ መኖሪያ ቤት፣ አራዳ ክፍለ ከተማ ቅድስት ማርያም አካባቢ ግምቱ 250 ሺሕ ብር የሆነ መኖሪያ ቤት፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ጫት ተራ አካባቢ ግምቱ 800 ሺሕ ብር የሆነ መኖሪያ ቤት፣ በኦሮሚያ ክልል ጫንጮ ከተማ ግምቱ 300 ሺሕ ብር የሆነ መኖሪያ ቤት በእሳት ቃጠሎ መውደማቸውን አብራርተዋል፡፡

ወቅቱ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት ከመሆኑ አንፃር ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አቶ ንጋቱ አሳስበዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች