Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት መጀመርያ ላይ የመረጃ ሳተላይት እንደምታመጥቅ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት መጀመርያ ላይ አንድ የመረጃ አገልግሎት የሚሰጥ ሳተላይት እንደምታመጥቅ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ያለፉት ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በሚቀጥለው ዓመት መጀመርያ ላይ አንድ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በተባለው ጊዜ ውስጥ አንድ የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ወደ ህዋ የማምጠቅ ሙከራ ለማድረግ የሳተላይት ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ፣ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ለአገሪቱ የመጀመርያው የሚሆነውን የመረጃ ሳተላይት ለማምጠቅም የዝግጅት ሥራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በመጪው ዓመት እስከ ኅዳር ወር ድረስ ይመጥቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የመረጃ ሳተላይት፣ በዋናነት ለመሬት ምልከታ ሥራ ላይ እንደሚውል ሚኒስትሩ ጌታሁን (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

 የሳተላይት ማምጠቅ ሥራው በስኬት ከተጠናቀቀ መንግሥት ለግብርና፣ ለውኃ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለማዕድን ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ ክትትል የሚሆኑ መረጃዎችን በቀላሉ ከሳተላይቱ ማግኘት እንደሚያስችለው ገልጸዋል።

 ከዚህ በተጨማሪም በራስ አቅም የተጀመረውን የህዋ ምርምርና ተጨማሪ ሳተላይት የመገንባት አቅም የበለጠ ለማጎልበት፣ የሳተላይት ግንባታ ፋብሪካ ለማቋቋም ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡

ለሳተላይት ፋብሪካ ግንባታ ከሚደረገው ዝግጅት በተጨማሪ፣ የመገጣጠሚያና የፍተሻ ማዕከል ለመገንባትም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተጨማሪ የሳተላይት መረጃ መቀበያ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ በማስፈለጉም፣ የግራውንድ ስቴሽን ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

የዚህ ማዕከል ግንባታና የመሣሪያዎች ተከላ ተጠናቆ በመጪው ዓመት መጀመርያ ሥራ እንደሚጀምር፣ ይህም ከሳተላይ በሚደረግ የመሬት ምልከታ የሚሰበሰብ የመረጃ ፍላጎትን 50 በመቶ ይመልሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ሳተላይት የምታመጥቀው በአገር ውስጥ አለመሆኑን በጉዳዩ ላይ የተገኙ ተጨማሪ መረጃዎች ያመለክታሉ። ሳተላይቱን ዲዛይን የማድረግና የመገንባት ሥራ ከሞላ ጎደል በኢትዮጵያውያን የተከናወነ ሲሆን፣ በርካታ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት ሽግግሩን በከፍተኛ ደረጃ መደገፋቸውን፣ በአሁኑ ወቅትም ከሃምሳ በላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን በህዋ ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ የብቃት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የመጀመርያውን ሳተላይት ለማምጠቅ ከስምንት ሚሊዮን ዶላር ባላይ ወጪ መደረጉንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች