በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢ በ1990 ዓ.ም. ወባ የሰውን ሕይወት እየቀጠፈ ነበር፡፡ ችግሩ በ1990 ዓ.ም. ላይ ጎልቶ ይውጣ እንጂ፣ ከ1980 አጋማሽ ጀምሮ መባባሱ አልቀረም፡፡ የበረሃ በሽታ ማለትም ቆላ አካባቢ የሚከሰተው ወባ በደጋማ አካባቢዎችም መታየት ጀመረ፡፡ በሰሜኑ በተለይም ጎጃም የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ የሚታወቀው ወባ ተስፋፋ፡፡ ቀድሞ ከባህር ወለል ከ1,500 በላይ የማይከሰተው ወባ ከባህር ወለል በላይ እስከ 2,000 መከሰት ጀመረ፡፡ ሰዎች በብዛት መታመምና መሞት ጀመሩ፡፡ ወደ ሐኪም ቤት የሄዱ እንኳን አይድኑም ነበር፡፡ በመሆኑም በ1990 ዓ.ም. ከሚያዝያ እስከ ሰኔ በነበሩት ወራት በጎጃም ደንበጫ በሚባል ከተማ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ብቻ በቀን እስከ 12 ሰው ይቀበር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከደንበጫ አዲስ አበባ የመጣ ሰው ደንበጫ ላይ ሕዝቡ እያለቀ መሆኑን ሲነግራቸው ‹‹መንግሥት ሕዝቡን ሊጨርስ ነው›› ብለው መነሳታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ለዚህም የባለቤታቸው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበርም፡፡ ‹አንተ ለሕዝብ ምን አድርገሃል› ስትላቸው፣ እውነት ነው በማለት ጥቂት ጓደኞቻቸውንና ዘመዶቻቸውን አሰባስበው ደንበጫ ላይ በወባ የሚያልቀውን ሰው ለማዳን መነሳታቸውን ይናገራሉ፡፡ አቶ አበረ ምሕረቴ በ1990 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበርን መሥርተው በወባና በተለያዩ ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ መሥራት ከጀመሩ 21 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- አነሳሳችሁ ወባ በተለይ በደንበጫ አካባቢ ያደረሰውን እልቂት ለማርገብና ብሎም ለወደፊቱ ለመቆጣጠር ነበር፡፡ በደንበጫና በሌሎች አካባቢዎች በወባ ዙሪያ የሠራችሁትን ቢነግሩን?
አቶ አበረ፡- ሁሉንም ጎጃም ባያጠቃልልም አዊ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃምና ባህር ዳር ልዩ ዞን ላይ ትኩረት አድርገን ነበር፡፡ ሥፍራዎቹ ደጋማ ቢሆኑም ወባ ከፍተኛ እልቂት ያደረሰበት ነበር፡፡ በባህር ዳር ደንበጫ፣ ጫጫ፣ ይልማና ዴንሳ፣ ቡሬ፣ ቋሪት ወረዳዎች በምሥራቅ ጎጃም ሸበል በረታ፣ ሞጣ ወረዳዎችን ጨምሮ 29 ወረዳዎች በወባ ተጠቅተው ነበር፡፡ የፈለግነው ሕዝቡን ከሞት ማዳን ነው፡፡ ምዕራብ ጎጃም ዞን ትኩረት የሚሻ ስለነበር ከአካባቢው ጤና ቢሮ መረጃ ሰብስበን ገንዘብ አሰባስበን፣ መድኃኒት ገዝተንና ባለሙያ አሰባስበን ገበያ ላይ ሳይቀር መመርመርና ሲታመሙ መድኃኒት መስጠት ጀመርን፡፡ የሕክምና ባለሙያዎችም በየጤና ጣቢያ እየገቡ ዕገዛ አደረጉ፡፡ ለውጥ መታየትና ብዙዎችም መዳን ጀመሩ፡፡ ዓላማችን ሕዝብን ከሞት ማዳን ነበር፡፡ በእኛ ግምትም ከ180 ሺሕ በላይ አደጋ ላይ የነበረ ሕዝብ አድነናል፡፡ ችግሩ ከግንዛቤ ችግር የመነጨም ስለነበር የማስተማሪያ መጻሕፍትና በድምፅ የተቀረፀ በማዘጋጀትና በጎ ፈቃደኞችን ከዩኒቨርሲቲ አሠልጥነን በማሰማራት ሠርተናል፡፡ 1990 ዓ.ም. መጨረሻ ተቋቁመን 1991 ዓ.ም. ክረምት ላይ 2,000 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አሠልጥነን በኢትዮጵያ አሰማርተናል፡፡ በ1992፣ 1,500 አሠልጥነን አሰማርተናል፡፡ በ1993 ዓ.ም. በኤድስ ዙሪያ፣ የሚሠሩ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገንዘብ እየከፈሉ ማሰማራት ስለጀመሩ እኛ አቆምን፡፡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ፊታችንን አዙረን በጎጃም በሚገኙ 23 ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎች ለሁለት ክረምት ኅብረተሰቡን እንዲያስተምሩ አደረግን፡፡ ወጣቶች፣ እድር፣ የሴት ማኅበራት አደራጅተን በወረዳ ደረጃና በቀበሌ ፀረ ወባ ኮሚቴ እያዋቀርን ዘመቻ አካሄድን፡፡ ዘመቻው የመንግሥት ድጋፍ ነበረው፡፡ በሥፍራው የነበረውን ጭንቅ የገላገለም ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ከጎጃም በዘለለ ወባማ በሆኑ አካቢዎች ላይ ምን ሠርታችኋል?
አቶ አበረ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ የማስተማሪያ ጽሑፎችን ለየክልሉ አሰራጭተናል፡፡ በድምፅ የተቀረፀ የ60 ደቂቃ ካሴት አዘጋጅተን አገር አቋራጭ አውቶቡሶች በቀን ቢያንስ አንዴ እንዲከፍቱ፣ በሻይ ቤቶችም እንዲደመጥ አድርገናል፡፡ በቪዲዮ የተደገፈ ትምህርት አዘጋጅተን አርሶ አደሩን እናወያይ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የገቢ ምንጫችሁ ከየት ነበር?
አቶ አበረ፡- ለተከታታይ ሦስት ዓመታት አዲስ አበባ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየጠየቅን ነበር የምንሠራው፡፡ መጋቢት 12 ቀን 1991 ዓ.ም. የገቢ ማሰባሰቢያ አዘጋጅተን 523 ሺሕ ብር አገኘን፡፡ በወቅቱ ብዙ ገንዘብ ነበር፡፡ ከውጭም በዶላር ይላክልን ገባ፡፡ በወቅቱ ከአዲስ አበባ ስወጣ የሆቴልና የትራንስፖርት ይከፈልልኝ እንደሆን እንጂ ነፃ አገልጋይ ነበርኩ፡፡ በቀን እስከ ስምንት ሰዓት እያስተማርኩ ከስምንት ሰዓት በኋላ የነበረኝን ተጨማሪ ሥራ መስዋት በማድረግ የማኅበሩን ሥራ እየሠራሁ ነው የቆየሁት፡፡ ቦርድ አዋቅረን ሰባት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነበረን፡፡ ሰባታችንም በበጎ ፈቃድ በመሥራት የወባ ችግር ጎልቶ እንዲወጣና ምላሽ እንዲያገኝ በአገር አቀፍ ደረጃ ሠርተናል፡፡ የማስተማር ሥራው ጎልቶ እንዲሠራ ብናደርግም የምንፈልገውን ያህል አልሠራንም፡፡ በየሄድንባቸው ክልሎች ምን ያህል ገንዘብ ይዛችኋል? ነበር ጥያቄያቸው፡፡ እኛ አብረን እንሥራ ነበር የምንለው፡፡
ሪፖርተር፡- ለወባው መስፋፋት ምክንያቱ ምን ነበር?
አቶ አበረ፡- አንዱ ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ ነበር፡፡ በአገር ውስጥ የሚትሪዎሎጂና የወባ ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ ተገናኝተው አይናበቡም ነበር፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ አዲስ እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሁለቱን በማገናኘት እንዲወያዩና አብረው እንዲሠሩ አድርገናል፡፡ ከፈረንሣይ ድርጅት ጋር በመሆንም በድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ጅማ አዊና ባህር ዳር ላይ ስድስት የሙከራ ጣቢያ አድርገን የሚትሪዮሎጂና የሕክምና ባለሙያዎች እየተገናኙ መረጃ እንዲለዋወጡ፣ ወባ ሊከሰት ይችላል አይችልም የሚለውን እንዲተነብዩ ማድረግ ጀምረን ጥሩ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት ከግማሽ ከአሜሪካ ሳውዝ ዳኮታ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የአማራ ክልልን የትንበያ ሥራ ለብቻ አጠናን፡፡ በጥናቱ የ45 ወረጃዎችን ተሞክሮ ወስደን በየሳምንቱ የወባን ሁኔታ መተንበይ የሚያስችል ሥርዓት ዘረጋን፡፡ ሥራውን እንዲቀጥሉበት ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ለክልሉ ጤና ቢሮ አስረክበናል፡፡ ወባን በተመለከተ የአቻ ለአቻ ትምህርትም አለን፡፡ የባህሪ ለውጥ ላይ መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ የባህሪ ለውጥ ካመጣን፣ ፖለቲካውና ለአገራችን ዕድገት እናመጣለን፡፡ አዕምሮአችን ላይ ለውጥ ካላመጣን፣ አሁን ባለን አያያዝ ለውጥ አናመጣም፡፡ ልጆቻችን ላይ መሥራት አለብን፡፡ ልጆች ወላጆችን መቀየር ይችላሉ፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ወረዳዎች የአቻ ለአቻ ትምህርት እየሰጠን ነው፡፡ ማኑዋልም ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ለውጥ ዓይተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በትንበያ ሥራው እክል አልገጠማችሁም?
አቶ አበረ፡- አንድ ወቅት ላይ አስቸግሮን ነበር፡፡ ከተለያዩ ወረዳዎች የሚመጣው የወባ ሪፖርት ከአየር ንበረቱ ጋር አልጣጣም ብሎ አስቸገረን፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ስናጠና፣ ለሥራ ሌላ አካባቢ ሄደው የሚመለሱ ይዘውት የሚመጡት የወጣ ችግር መሆኑን ደረስንበት፡፡ ከዚህ በኋላ ለሥራ የሚወጡ ሰዎች እንዲመዘገቡ ሲመለሱ ምርመራ እንዲያደርጉ ተደረገ፡፡ ከአንድ ቀበሌ ለሥራ የወጡ 182 ሰዎች ሲመለሱ መርምረን፣ 78ቱ ላይ ወባ አግኝተናል፡፡ መጀመርያ ላይ አጎበር ተጠቃሚውም 15 በመቶ ነበር፡፡ አጎበር የሚጠቀም፣ የሌለው፣ እያለው የማይጠቀም እያልን በር ላይ በቀለም ምልክት በማድረግ የተጠቀምነው ዘዴ 93.7 በመቶው አጎበር እንዲጠቀም አስችሏል፡፡ ይኼንን በሠራንባቸው አካባቢዎች በወባ ምክንያት ሞት የለም፡፡ እስካሁንም 200 ትምህርት ቤቶች ላይ ሠርተናል፡፡ ለሥራችን የሃይማኖት አባቶችንም ተጠቅመናል፡፡ ወደፊት ከአማራ ከልል ወጥተን ሥራችንን እናስፋፋለን ብለን እናስባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ስለተቀናጀ ጤና ፕሮግራማችሁ ቢነግሩን?
አቶ አበረ፡- የእኛ ዓላማ የኅብረተሰብን ደኅንነት መጠበቅ፣ ደኅንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንዲኖር፣ ለመኖሪያ ምቹ የሆነ አካባቢ መፍጠርና ኅብረተሰቡም ይኼንን ማግኘት አለበት የሚለው ነው፡፡ ለዚህ በጤናው ዘርፍ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ዕውቀት ነው፡፡ የእኛ ሕዝብ መሠረታዊ የጤና ግንዛቤ እጥረት አለበት፡፡ ስለሆነም ይኼንን መለወጥ ይገባል፡፡ ወባ፣ ኤችአይቪ፣ የግልና አካባቢ ንፅህና፣ ሥነ ተዋልዶ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ መሠራት አለበት፡፡ ለምሳሌ ወባና ኤችአይቪን ብንወስድ ለወባ አካባቢን ንፁህ ማድረግ፣ ከአቆረ ውኃ መጠበቅና ቤትን በንፅህና መያዝ አለብን፡፡ ለኤችአይቪም ቢሆን የግልና የአካባቢ ንፅህና ብሎም የሥነ ተዋልዶ ጤና መጠበቅ ግድ ነው፡፡ ስለሆነም የተቀናጀ የጤና ፕሮግራም የጀመርነው ቀድመን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፕሮግራሙን የጀመራችሁት መቼ ነው?
አቶ አበረ፡- በ1994 ዓ.ም. ነው፡፡ በኤድስ ዙሪያ ትልቁ ትኩረታችን ማስተማር ነው፡፡ ንፅህናን በተመለከተ የንፁህ ውኃ አቅርቦትን ለማስፋፋት ጉድጓድ ውኃና ምንጭ በማጎልበት ላይ እንሠራለን፡፡ ጎንደር ሰረባ ከሚባል ቦታ ጀምሮ እስከ ደጀን ባሉ ከተሞች ሴተኛ አዳሪዎች ቡና እየጠጡ አቻ ለአቻ ትምህርት ላይ እንዲሳተፉና ራሳቸውን እንዲያውቁ፣ ሌላውን እንዲጠብቁና፣ ከሴተኛ አዳሪነት እንዲወጡ የማመቻቸት ሥራ በሰፊው ሠርተናል፡፡ በትምህርት ቤትም ወላጆቻቸው ለሞቱባቸው ልጆች ድጋፍ፣ 25 ትምህርት ቤቶች መርጠን የአቻ ለአቻ ትምህርት ማስፋፋትና ማሠልጠኛ ማኑዋል በማዘጋጀት ሠርተናል፡፡ ባለራዕይ ማድረግ፣ የወላጆችን እሴት ወደታች ማውረድና የአቻ ግፊትን መቋቋም፣ ተወያይ መሆንና የአካባቢ ተፅዕኖ መቋቋም ትኩረት የሰጠናቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ሁለቱንም ወላጆቻውን ያጡ ልጆች አሠልጥነን መቋቋሚያ ሰጥተን ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርገናል፡፡ ሴቶች ላይ ብቻ ያተኮረ የችግረኛ ልጆች ማዕከል በደብረ ማርቆስ አለን፡፡ በማዕከሉ የሚገቡት በሙሉ የሚማሩ ናቸው፡፡ አስተምረናቸው ዩኒቨርሲቲ የተመረቁና ሥራ የያዙ፣ ዩኒቨርሲቲና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩም አሉ፡፡ በአቻ ለአቻ ትምህርቱ ልምድ ስላካበትን እኛ እንድንሠራው ጤና ሚኒስቴርን ከግሎባል ፈንድ ገንዘብ እንዲሰጠን እየጠየቅን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በክረምት ወንዝ ሲሞላ ሰዎች የሚቸገሩበት ሁኔታ አለ፡፡ እዚህ ላይ ማኅበሩ ምን ሠርቷል?
አቶ አበረ፡- በአማራ ክልል በክረምት ውኃ መሻገር የማይቻልባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ በመሆኑም በርካታ ቦታዎች ላይ የብረት ድልድይ ሠርተናል፡፡ ሁለት የወጣት ማዕከላት በደንበጫና በዳንግላ ከተማ ገንብተናል፡፡ በደንበጫ ቤተ መጻሕፍት፣ ባህር ዳር ላይ ክሊኒክ ገንብተናል፡፡ ለኅብረተሰቡ ይጠቅማሉ የሚባሉ ነገሮች ላይ ሁሉ እንሰማራለን፡፡ ጊኒዎርም ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ ሬሽሚኒያስስ (በአንዳንድ አካባቢ ቆንጥር ይባላል) ማለትም አፍንጫ ላይ የሚቆስለው ላይ ትምህርት ሰጥተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በትምባሆ ዙሪያ መንግሥት አዋጅ ለማውጣት እስኪወስን ሠርታችኋል፡፡ ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶችም በዘርፉ ይሠሩ ነበር፡፡ በእናንተ በኩል የነበረው አስተዋፅኦ ምን ይመስላል?
አቶ አበረ፡- ትምባሆ የሚያመጣውን ችግር እገነዘባለሁ፡፡ በጤና ላይ ያለው ችግርም ቀላል አልነበረም፡፡ ቶባኮ ፍሪ ኪድስ የተባለው ድርጅት በትምባሆ ዙሪያ አዋጅ እንዲወጣ እንድንሠራ ሲጠይቀን፣ ኀብረተሰቡ ላይ መሠራት አለበት የሚለውንም ጨምረን ሚዲያውን በመያዝ ሠራን፣ ለውጥ ማምጣትም ችለናል፡፡ ትምባሆ በችርቻሮ እንዳይሸጥ፣ ዋጋ እንዲወደድ፣ ሰው ባለበት መቶ ሜትር ራዲየስ እንዳይጨስ፣ ማሸጊያው በአስፈሪ የጤና ቀውስ ሥዕሎች እንዲሸፈን መደረጉ የአጫሹን ቁጥር ይቀንሰዋል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ እንዲሆን ኅብረተሰቡን ማንቃትና አጠገቡ ሰው ሲያጨስ ሲያይ አትችልም ማለት እንዲችል ማስተማር ያስፈልገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለደም ሥርና ልብ ሕመሞች ምክንያት የሆነውን በምግብ ውስጥ የሚገኝ ትራንስ ፋቲ አሲድ በተለይም በፋብሪካ በሚቀነባበሩት ምግቦች ላይ የሚገኘው መጠን ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት እንዲሆን፣ አሊያም እንዲወገድ፣ ቀዳሚ በመሆን ሥራ ጀምራችኋል፡፡ በዚህ ላይ ለመሥራት ምን አነሳሳችሁ?
አቶ አበረ፡- ትራንስ ፋቲ አሲድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡ እነ አሜሪካ በጉዳዩ ዙሪያ ሄደውበታል፡፡ መጠኑን ከምግብ መቀነስም ችለዋል፡፡ እኛ አገር ከሚገቡ ምግቦች ትራንስ ፋቲ አሲድ በከፍተኛ ደረጃ ያለባቸው አሉ፡፡ አደጋውን ቀድመን ማሳየት አለብን፡፡ ሕዝቡም የሸቀጥ ማራገፊያ መሆን የለበትም፡፡ ጥራቱን የጠበቀና በደንብ ቁጥጥር የሚደረግበት ምግብ ኅብረተሰቡ እንዲመገብ እንፈልጋለን፡፡ በየጊዜው የተበላሹ ምግቦች ስለመያዛቸው እንሰማለን፡፡ ይህ ጥራቱን የጠበቀ ምግብ እንደማይገባ ከምንመዝንበት ክስተት አንዱ ነው፡፡ የእኛን ባህላዊ ቅቤ ጨምሮ ብዙ ምግቦች ላይ ትራንስ ፋቲ አሲድ (ስብ) አለ፡፡ ምግቡ በተፈጥሮ ከሚይዘው በተጨማሪ በፋብሪካ ጣዕሙን ለመጠበቅና ረዥም የመደርደሪያ ጊዜ እንዲኖረው ለማስቻል የሚያልፈው የሃይድሮጅኔሽን ሒደት ለጤና ጠንቅ ነው፡፡ ስትሮክ (ምት) እና የልብ ሕመም በየጊዜው እየሰማን ነው፡፡ ስለዚህ የአኗኗር ዘይቤ መቀየር በተለይ አመጋገባችን ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰቡ የሚመገበውን ማወቅ አለበት፡፡ መንግሥት ወደአገር የሚገባው ምግብ ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት ጤናው የተጠበቀ ኅብረተሰብ እንዲኖር መሥራት ግዴታው ነው፡፡ አገር ውስጥ የሚገቡ ዘይቶችን ጨምሮ ምግብ አስመጪዎች ጥራቱን የጠበቀ እንዲያስገቡ፣ ደረጃ አውጪዎችም ጠንካራ ደረጃ እንዲያወጡና ተቆጣጣሪው ጠንክሮ እንዲሠራ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ ኅበረተሰቡም ግብሩን በአግባቡ የሚከፍልና ጤንነቴ ተጠብቆልኛል? የምፈልገው ተሟልቷል ወይ ብሎ የሚጠይቅ መሆን አለበት፡፡ ትራንስ ፋቲ አሲድ ላይ ለመሥራት የተነሳው ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ትራንስ ፋቲ አሲድን እ.ኤ.አ. በ2023 ከምግብ ውስጥ ለማስወገድ ግብ አስቀምጦ እየሠራ መሆኑን ተከትለን ነው፡፡