በሀብታሙ ግርማ
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስለሚመሩት መንግሥት የግማሽ የበጀት ዓመት አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረቡበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የለውጡ ደጋፊ ከሆኑ በዋናነት ሥነ ልቦናዊና (ሥነ ምግባራዊ) ጉዳይ ላይ ሊያስቡበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንዳመላከቱት መንግሥታቸው ለተያያዘው የለውጥ ጉዞ ፈተና የሆነባቸው፣ የኢትዮጵያዊያን የሥነ ልቦና ውቅር እየተቀየረ መምጣት አንዱ ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ ይህን ሲገልጹ፣ በቀደመው ጊዜ የኢትዮጵያዊያን አንዱ መገለጫ የነበረው በጉዳዮች ላይ አቋም ከመያዛችን ወይም ብያኔ ላይ ከመድረሳችን በፊት፣ ነገሩን በሰከነና በአስተውሎት የመመርመር ጥበብ የታደለን መሆናችን ነበር፡፡ ዛሬ ግን አስተውሎት እየራቀን፣ አጥብቦ የመረዳት (የመገንዘብ) የሥነ አዕምሮ ሁነት (Short Memory Mindset) ደግሞ እየቀረበን ነው፡፡
በግሌ የኢትዮጵያና የፖለቲካዋ ችግር ምንጭ የሥነ ምግባር እንጂ፣ የተራራቀ የፖለቲካ ልዩነት እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ለኅትመት በበቁ መጣጥፎቼ ለማንሳት ሞክሬያለሁ፡፡ በእርግጥም እኛ ኢትዮጵያውያን አርቆ አስተዋይነትና ስክነት ያሳጣንን ምክንያት የመጠየቅና የመመርመሩ ፋይዳ ላይ፣ ለገጠሙን አገራዊ ችግሮች መነሻ የሚጠቁመን በመሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ሰፊውን ምሥል ተመልክተን ነገሮችን በሰከነ ልቦና ለመረዳት የሚያስችል የአዕምሮ ሁኔታ ውስጥ አይደለንም፡፡ የዚህ አንዱ መገለጫ እንደ አገር የገጠሙን የፖለቲካ ችግሮችን መነሻ ከመለየትና መፍትሔ ለማምጣት ከመጣር ይልቅ፣ ድክመትም ሆነ ጥንካሬ መለኪያው የብሔር ማንነት መሆኑ ነው፡፡ እንደ አገርና ሕዝብ ነገራችንን ሁሉ ያከበደብን የብሔር (የማንነት) ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ መውደቃችን ነው፡፡
የዚህች መጣጥፍ ዝግጅት ፋይዳ የውስብስቡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት አንደኛው መልክ የሆነው የፖለቲካ አመራሩ ለፌዴራሊዝም መርሆች ለመገዛት ዳተኛ መሆን፣ በዚህም በብሔር (ማንነት) ፖለቲካ አዙሪት እንድንዳክር ምክንያት የሆነውን ችግር መቃኘት፣ እንዲሁም ከችግሩ ለመውጣት እንችል ዘንድ የግል ምልከታዬን ማቅረብ ነው፡፡
የማንነት ፖለቲካ አዙሪት ምክንያት የፌዴራል ሥርዓቱን ለፖለቲካ ፍጆታ የማዋል አደገኛ አካሄድ
አገራችን ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓትን መከተል ከጀመረች እነሆ ሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ ሆኗታል፡፡ የፌዴራሊዝሙ አስፈላጊነት ደግሞ ኅብረ ብሔራዊነት መገለጫው የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ ማንነቶች ተከባብረውና በአብሮነት የሚኖሩበት ሥርዓት መመሥረት ነው፡፡ ከፌዴራል ሥርዓት ምሥረታው ጀምሮ አገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን በበላይነት በመያዝ መንግሥት የመሠረተው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የፖለቲካ ፕሮግራም የሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር እንደሚለው፣ የፖለቲካ አስተዳደሩ (Political Governance) ግብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅራኔን መፍታት ነው፡፡ ለዚህ ግቡ ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ፌዴራላዊ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡
በመሠረቱ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በተለያዩ የአስተዳደር ሥልጣኖች (ግዛቶች) መካከል የሚኖር የሥልጣን ክፍፍል የሚመራበት የስምምነት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አንፃር የፌዴራል ሥርዓቱ መዘውሮች (Pillars of the Federal System) ሁለት ናቸው፡፡ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ስለማስተዳደር ሥልጣናቸው (Self Rule) እና ክልሎች እርስ በርሳቸው ስለሚኖራቸው ግንኙነት የሚደነግግ ሕገ መንግሥታዊ፣ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ (Shared Rule) መኖር ነው፡፡ የፌዴራል አወቃቀሩ ዓላማ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ፣ ግቡም ሕዝባዊ ጥቅምና አገራዊ አንድነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን ፌዴራሊዝም የሥርዓተ መንግሥት ጉዳይ እንደመሆኑ፣ አተገባበሩ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ካልፀዳ ዓላማውንና ግቡን ስቶ አገርና ሕዝብን መበተኑ አይቀርም፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን ስንገመግመው በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት የፌዴራሊዝሙን መርሆች አክብሮ ከማስከበር ይልቅ፣ በሥልጣን ለመቆየት እንደ መሣሪያ መጠቀሙ ያመዝናል፡፡ ይህ ምዛኔ ለተጋፈጥናቸው ችግሮች ሁሉ እናት ነው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ በውጤቱም በማንነት ፖለቲካ አዙሪት እንድንማቅቅ አድርጎናል፡፡
በመሠረቱ የማንነት ፖለቲካ ዓላማ የተለያዩ ማንነቶች እኩል የሚስተናገዱበት ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ በእዚህም የፖለቲካ ሥርዓቱን ከቅራኔ በማላቀቅ የማኅበረ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ዕድገት ለማምጣት መሠረትና መደላደል የሆነውን የፖለቲካ መረጋጋት መፍጠር ነው፡፡ የማንነት ፖለቲካ በባህሪው (በአፈጣጠሩ) የቡድን መብትን የሚያስቀድም ነው፡፡ በመሆኑም የግለሰብ ጥቅል መብቶችን ማለትም የሲቪል፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ ሊያስጠብቅ አይችልም፡፡ በመሆኑም የማንነት ጉዳዮችን በፍጥነት መልስ በመስጠትና ከፖለቲካ አጀንዳ እንዲወጣ፣ በዚህም ወደ ቀጣዩ የማኅበረሰብ ዕድገትና ጥያቄዎች የሚመልስ ሥርዓት ማለትም በዜግነት በፖለቲካ እንዲተካ ሀቀኛ የማንነት ፖለቲካን ማራመድ ያሻል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያን ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ ያስተዳደረው ኢሕአዴግ የአገሪቱ ፖለቲካ በማንነት ጉዳዮች አዙሪት ውስት እንዲቆይ በማድረግ፣ የፖለቲካ ዕድገት የኋልዮሽ እንዲጓዝ አድርጓል፡፡ እንዲያውም ፖለቲካው የብሔር ክፍፍል፣ የደካሞች መፈንጫና የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሥርዓቱ ከብሔራዊ እኩልነት ይልቅ ሌላ የማንነት መጨቃቆን መጥፎ ታሪክ በሕዝቦች መካከል እንዲኖር አድርጓል፡፡ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የሆነው ነገር ትናንት ጨቋኝ መደብ ተብሎ የተፈረጀው ሲጨቁን፣ ተጨቋኙ ደግሞ ጨቋኝ የመሆን አዝማሚያ እንዲያሳይ ሆነ ሲሆን ነው፡፡
ለዚህ በርካታ አስረጂዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንዱ ማሳያ ኅብረ ብሔራዊነት (የዜግነት) ፖለቲካ ያቀነቀኑ የነበሩ በዋናነት የአማራ የፖለቲካ ልሂቃን ወደ ብሔር ፖለቲካ እንዲወርዱ ያስገደዳቸው በብሔር ማንነታቸው የደረሰባቸው መገፋት እንደሆነ በግሌ አምናለሁ፡፡ ሌላኛው ማሳያ ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት የቆመ እንደሆነ በሚነገር ሥርዓት በተቃራኒው በብሔር ማንነታቸው የመጨቆን ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መጥቶ፣ ጎጠኝነት የተንሰራፋበት ሁኔታ እንዲፈጠር የማድረጉ ነገር ነው፡፡
ከማንነት ፖለቲካ አዙሪት እንዴት እንላቀቅ?
ሀቀኛ የማንነት ፖለቲካን ማራመድ ከማንነት ፖለቲካ አዙሪት እንዲላቀቅ ያስችለናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሀቀኛ የማንነት ፖለቲካ ማራመድ ሲባል የፌዴራሊዝሙን መርሆች በጥብቅ ዲሲፕሊንና የፖለቲካ ቁርጠኝነት አክብሮ የሚያስከብር የፖለቲካ አስተዳደር መዘርጋት ማለት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተዛማጅ የሆነው ደግሞ፣ የፖለቲካ አመራሩ የማንነት ፖለቲካ የሚጠይቀውን ሰብዕና የተሞላ የመሆኑ አስፈላጊነት ነው፡፡
ለፌዴራሊዝም ሥርዓቱ መርሆች ተፈጻሚነት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል
ከኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አንፃር ለፌዴራሊዝሙ መርሆች ተፈጻሚነት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያሻል ሲባል፣ በዋናነት በክልሎች መካከል የሚኖርን አስተዳደራዊና የሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ የሚነሱ ተፎካካሪ ፍላጎቶች (Competing Interests) በሰላማዊና በሠለጠነ አግባብ መልስ የሚያገኙበትን ሕገ መንግሥታዊ፣ ሕጋዊም ሆነ የድርድር (ሰጥቶ የመቀበል መርህ) ቁልፎችን በመጠቀም በማያሻማ ሁኔታ የመፍታት ቁርጠኝነት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ሁሉም የክልል መንግሥታት ራሳቸውን ከማስተዳደር (Self Rule) ሥልጣን በተጓዳኝ የጋራ ፍላጎቶች (Shared Rule) አላቸው፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ ክልሎች ይህን የጋራ ፍላጎቶቻቸውን የሚያሳኩበትን ተቋም ይመሠርታሉ፡፡ ይህ በክልሎች ይሁንታ የሚሰጠው ተቋም የፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁነቶች ግን የፌዴራል መንግሥቱ ከክልላዊ መንግሥታት የተሰጠውን የክልሎችን የጋራ ፍላጎት (Shared Rule) በቅንነት፣ በትጋትና በታማኝነት አገልግሏል ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ሲባል የፌዴራል መንግሥቱን በጎ ሥራዎች ፈጽሞ አልነበሩትም ማለት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ በፌዴራል መንግሥቱ አመራር በአብዛኛው ይስተዋል የነበረው አረዳድ፣ የክልሎች የጎንዮሽ ግንኙነት የፌዴራል መንግሥቱን እንደሚያዳክም ተደርጎ ነው፡፡ በውጤቱም ክልሎች የሚገጥማቸውን ችግሮች በንግግር ከመፍታት ይልቅ፣ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ከፌዴራል መንግሥቱና ወይም ከሌሎች ክልሎች ጋር መርህ አልባ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ሆኗል፡፡
በቅርብ ዓመታት የምንሰማው የክልሎች መርህ አልባ ግንኙነትና እስካሁን መዘዙ ያልቆመው አገራዊ ቀውስ የዚህ ማሳያ ነው፡፡ ከዚያም ከፍ ሲል ክልሎች ችግሮቻቸውን በኃይል ለመፍታት አማራጮችን ማየታቸው አልቀረም፡፡ በቀደመው ጊዜ ክልሎች ችግሮቻቸው እንዳለ ነበር፡፡ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥቱ በፖለቲካዊ ጫና በማሳደር ችግሩ ሳይፈታ ተድበስብሶ እንዲቀር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ መዳከም ከጀመረበት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በየተለያዩ ክልሎች መካከል የኃይል ፍጥጫ የማየሉ መነሻም ለዚሁ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በሶማሌና በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልላዊ መስተዳደሮች መካከል ከቃላት ጦርነት ባለፈ በክልሎቹ ልዩ ኃይል ወደ እጅ አዙር ጦርነት በሰፊው አካሂደዋል፡፡ ነገሩ በጊዜ ዕልባት ካልተሰጠው የተለያዩ ክልላዊ መንግሥታት መካከል ወደ ቀጥታ ጦርነት መግባታቸው አይቀርም፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱ ከተዘረጋበት ካለፉት 28 ዓመታት ውስጥ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱ ግንኙነትን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ ለተቀመጡት ግዴታዎች፣ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በተሞላበት አግባብ በፍጥነት መልስ መስጠት ሳይቻል ቆይቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በክልሎች መካከል ያሉ ተፎካካሪ ፍላጎቶችን ከመፍታት አንፃር ተገቢው የሕግና ተቋማዊ ማዕቀፍና የመዘርጋት ነገር ትኩረት የተነፈገው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህል አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ስለሚኖራት አስተዳደራዊ ግንኙነት የሚገልጸው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ተፈጻሚነት፣ በፖለቲካዊ ዳተኝነት ባይዘገይ የዛሬው የፖለቲካችን ራስ ምታት የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይ ቢበዛ አይፈጠርም፡፡ ቢያንስ ደግሞ ከአስተዳደራዊ ጥያቄ አልፎ ፖለቲካዊ መልክ ሊይዝ አይችልም ነበር፡፡
ለፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ተግባራዊነት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያለመኖሩ ሌላኛው ማሳያ በክልሎችና (ወይም) በፌዴራል መንግሥቱ መካከል የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ የማዕድን ልማትና አጠቃቀም ጉዳይ ክልሎችን ባሳተፈና በግልጽ አሠራር በፖሊሲ ወይም በሕግ ማዕቀፍ ሰጥቶ ዕልባት ለመስጠት ዝርዝርና ግልጽነት ይኖረው ዘንድ፣ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ከማጣቱ ጋር የተገናኙ የተለያዩ ችግሮች እዚህም እዚያም ተነስተዋል፡፡ ይህ ጉዳይ መፍትሔ ካልተበጀለት በተለይ የማዕድንና የነዳጅ ሀብት ልማቶች በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት እየተካሄዱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ አስቀድሞ ምላሽ ካላገኘ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን የብልፅግናችን ተስፋ ሳይሆኑ የጦርነት ሥጋት መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱ ለፖለቲካዊ ፍጆታ ከማዋል አኳያ ከሁሉም በላይ የከፋው በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የመኖርና የመሥራት መብቱን ከማስፈጸም አንፃር የፖለቲካ አመራሩ የነበረው ቸልተኝነት ነው፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በተለያዩ የሥልጣን ዕርከን የተሰየሙ ሹሞቹ ዜጎች ላይ አስተዳደራዊ በደል ሲፈጽሙ፣ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ሲያፈናቅሉ የከረሙ የባለ ሥልጣናትን ጥፋት ዓይቶ እንዳላየ ማለፉ የቆየ ችግር ነው፡፡ ሌላ ችግር ኖሮ ሳይሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር ነው፡፡
ማንነትን መሠረት ያደረገው የፌዴራል ሥርዓት የሚፈልገውን የአመራር ሰብዕና ማስረፅ ያሻል
በማንነት ፖለቲካ የተደራጁ ሥልጣን የያዙም ሆኑ በተፎካካሪ ፓርቲነት የሚገኙ (ነገ መንግሥት ለመመሥረት የሚፎካከሩ) ፓርቲዎች አባላት በአመራር እሳቤያቸው ከወገንተኝነት የራቁ፣ ከነባር ብሔር ተወላጆች እኩል ፍትሕ የማግኘት መብቱን ማስጠበቅ፣ በአሠራራቸውም ለራሳቸው ብሔር ከመወገን ይልቅ ሌላው ብሔር ተወላጅ በክልላቸው ሲኖር እንደ ዜጋ መብት ያለው፣ እናም የእንግድነት ወይም የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማው የሚያስችል የአመራር የመንፈስ ከፍታና የአመራር ጥበብ ሊኖራቸው የተገባ ነው፡፡
የአመራሩ ሥነ ባህሪ መሠረት መሆን ያለበት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በመቀሌ ከተማ ለሕወሓት ካድሬዎችና ለትግራይ ነዋሪዎች ያስገነዘቡት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ሲያብራሩ (የንግግራቸውን ይዘት በራሴ አገላለጽ ያዘጋጀሁት ነው) በአንዲት እናት መስለው ነበር፡፡ አንዲት እናት አለች በቤቷ ሁለት ልጆች ታሳድጋለች፡፡ አንደኛው የምትወልደው ልጇ ሲሆን ሁለተኛው የማደጎ ልጅ ነው፡፡ እናም ይህች እናት እነዚህን ልጆች በቤቷ አስማምታ ለማስተዳደር በተለይ የማደጎ ልጇ የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማው የማድረግ የቤተሰብ አመራር ሰብዕናና ጥበብ ይጠይቃታል፡፡ ሁኔታዎች ለአንደኛው ልጅ ቅድሚያ እንድትሰጥ በሚያስገድድበት ወቅት የማደጎ ልጇን ብታስቀድም ተገቢ ነው፡፡ ይህን ማድረጓ ለራሷ ስትልም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም የአብራክ ልጇ መቀየሙን በኩርፊያ ከመግለጽ አልፎ በእናቱ ላይ ቂም አይዝም የሚል ነበር፡፡
በሁሉም ደረጃ ያሉ ሕዝብን እንዲያስተዳድሩ የሚሾሙ ባለሥልጣናት የአመራር መርሐቸው ይህ ሊሆን ይገባው ነበር፡፡ ነገር ግን በተበላሸ የአመራር አስተሳሰብ ሳቢያ ብቻ ዛሬ በአገራችን ተዘዋውረን እንደ አንድ ዜጋ የመኖርና የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻችን እየተጣሰ፣ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ያለ ሥጋት የመኖር ሰብዓዊ መብቶቻችን አደጋ ላይ ወድቋል፡፡
በመጨረሻም ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመርን ለካድሬዎቹ (ለአመራር አካላቱ) በመስጠት ያጠፋውን ጊዜ፣ ገንዘብና ኃይል እጅግ ጥቂቱን ለፌዴራሊዚሙ መርሆች በሀቅና በፅናት ጥብቅና እንዲቆሙ የሚያስችል የአመራር ሰብዕና፣ ዲሲፕሊንና ተቋማትን ለመዘርጋት ቢጥር ዛሬ ላይ ለደረሰበት የፖለቲካ ኪሳራ አይዳረግም ነበር፡፡ ፌዴራሊዝሙን ለመምራት ከሕወሓት የተረከቡት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ስህተት ተምረው አገር ማስተዳደር ካልቻሉ፣ እነርሱም ከሕወሓት የተለየ ዕጣ ፈንታ አይኖራቸውም፡፡ ፌዴራሊዝሙን በሀቅ መምራት እስካልተቻለ ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከማንነት አዙሪት ሊወጣ አይችልም፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ! አሜን!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ወይም [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡