Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በግራም በቀኝም እየተስተዋለ!

እነሆ መንገድ። ከቦሌ ወደ ፒያሳ ኪሎ ልንጓዝ ነው። “እስኪ ረጂም አብራላቸው፤” ወያላው ነው። ፍንጭት መሀል ጥርሱ ላይ መፋቂያውን ሸንቁሮ፣ ከፊል ከወገቡ በመስኮት ወጥቶ ከማለዳው ንፋስ ጋር ይክለፈለፋል። “አጭር ያላበራን ሰዎች በምን አቅማችን ረዥም አብረተን እንደምንዘልቀው እንጃ፤” ትላለች ጋቢና የተሰየመች የቀይ ዳማ። “ዝም አትይውም? ነገር ሊያመጣብኝ አስቦ ካልሆነ በቀር አሁን ረዥም ባበራ ለምርመራ መፈለጌ ይቀራል?” ይላታል ሾፌሩ። “ጉድ እኮ ነው እናንተ? አሁን የተሽከርካሪው ዓይን ብልጭ ብሎ ድርግም ባለ ማን ነው አንተን ለምርመራ የሚፈልግህ? ኧረ እባካችሁ ዝም ብላችሁ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ስም አታጥፉ?” ባዩ ደግሞ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ጎልማሳ ነው። “አሁን እኔ መንግሥት የሚል ቃል ወጣኝ? ፖሊስ የሚል ቃል ወጣኝ?” ሲል ሾፌሩ፣ “የለም! ሐኪም ማለትህ ነዋ፤” አለው ጎልማሳው በነገረኛ አንደበት። ‹‹ጉድ እኮ ነው እናንተ? ማን ነው በሕዝብ የተመረጠው?›› ሲል አንዱ ሾፌሩ ሳቅ እያለ፣ ‹‹አንተ ደግሞ የአራዳ ልጅ አይደለህ እንዴ አረጋጋው እንጂ . . .›› ብሎ መሀል ሲገባ ነገሩ ረገበ፡፡

ይኼን ጊዜ ወያላው እጁን አፉ ላይ አድርጎ፣ “ከምንጊዜው ጠብ ጀመራችሁ በመድኃኔዓለም? በቃ እኔ ከሌለሁ ቀጣናው መረጋጋት አይችልም ማለት ነው?” እያለ ማፌዝ ጀመረ። “ይልቅ ስላቁን ትተህ እሱን መፋቂያ ወዲያ ጣል፤” ብሎ ሾፌሩ ገላመጠው። “እንዴ! በገዛ ጥርሴ? በገዛ መፋቂያዬ? በገዛ ድዴ? እንዲህም ደግሞ ተጀመረ?” ብሎ ጎልማሳውን ሊያግባባ ሲጠቅሰው፣ “ምን ትጠቅሰኛለህ? ይኼም ያልዳበረው ዴሞክራሲያችን፣ የብሔር ችግራችንንና የዘር ጣጣችንን ነው ብለህ ስድብ ለመጀመር ነው?” ብሎ አፋጠጠው። “ኧረ ፍሬንድ ረጋ በል። ቢሆንስ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ትችት ስድብ የሆነው?” ከማለቱ መሀል መቀመጫ ከጎኔ የተቀመጠች እሸት፣ “አላዋቂ ተቺና ገምጋሚ ነኝ ባይ ሁሉ እየተነሳ ፖለቲከኛ ልሁን ካለበት ዕለት አንስቶ . . .” አለችው። አዳሜ ይኼን ጎራ ከፍሎ ሽምቅ መጠባጠብን ወዶት ነው ወይስ ትርፍ ይገኝበት ጀምሯል? ዘንድሮ ያለ ትርፍ ስንዝር የሚጓዝ ጠፍቷላ!

በራሪዋ ታክሲያችን ሞልታለች። ወያላው ቀልቡን ሰብስቦ ተቀምጧል። ከጎልማሳው ፍጥጫ በኋላ ቀልደኝነቱም ዋዘኝነቱም ርቀውት የቆጠረውን ገንዘብ ደጋግሞ ይቆጥራል። “ኧረ በቃህ! ነው ወይስ እንቁልልጭ መሆኑ ነው?” አለው መጨረሻ ወንበር እግሩን ጎማ ላይ ዘርግቶ የተቀመጠ ወጣት። “እኔን ነው?” ይላል ወያላው። ‹‹ታዲያ ካንተ ሌላ የቆጠረ አለ? ብሩም እኮ ቶሎ የሚያረጀው አንድም እንዲህ እንዳንተ ቆጥረው የማይጠግቡ ሰዎች አሥር ጊዜ ሲፈትጉት ነው፤” አለው። ‹‹ካልክስ . . .›› ብላ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ወይዘሮ ጉሮሮዋን ጠራረገች። “. . .ካልክስ አሉልህ ባልዋለበት ባልሠሩበት ሥፍራ ጎታቸውን ሞልተው ጥሪታቸውን አካብተው ያልተነቃባቸው። እሱስ እያየነው የሰበሰበውን ነው የሚቆጥረው፤” ስትለው፣ “እኔ ምለው? ፀረ ሙስና የሚባለው የት ሄዶ ነው ግን ምድረ ዘራፊ የድርሻውን ይዞ ጠያቂ የሌለው?” አለች ከጎኗ።

 “እሱን እንኳን እዚህ ታክሲ ውስጥ አይደለም ምክር ቤቱም ግራ የተጋባበት ነገር ሆኗል አሉ። አሉ ነው እንግዲህ። የእኛ አገር ምክር ቤት መቼና እንዴት ግራ እንደሚጋባ በግልጽ መረጃ ባንሰማም፤” አለቻት ወይዘሮዋ መልሳ። “ይቅርታ አልገባኝም . . .” ሲል ጎልማሳው ተጠማዞ ዞሮ፣ “ይለፈኝ! እኔም ለራሴ የተናገርኩት አልገባኝም፤” ብላ ወይዘሮዋ ሳቀች። “እሺ መተላለፉ እንዳለ ሆኖ መንግሥት ተረኛ ሌባ ሲፈለፈል ዝም ብሎ የሚያየው እስከ መቼ ነው ተባለ?” ብላ ከጎኔ የተቀመጠችዋ ስትጠይቅ ደግሞ፣ “ቅርጫፉን ትቶ ግንዱን የመንካት ወኔ እስኪያዳብር መሰለኝ። እንጃ ግን መሰለኝ ነው፤” ባዩዋ ጋቢና የተቀመጠችዋ ቀዘባ ናት። ውበትና ነገር ሲጣመሩ ደግሞ አንዳንዴ አላሳልፈን ያለውን መሰናክል ‘ዙም’ ያደርጉታል መሰል? ወይስ እንደ አተያያችን ይለያይ ይሆን? ውበትና ትንተና እንደ ተመልካቹ ነው እንዳትሉ ብቻ!

“እንዲያው መኖርን የመሰለ ነገር የለም። የማቱሳላ ዕድሜን ይስጣችሁ፤” ብላ ወይዘሮዋ ወራጅ አለች። በእሷ ምትክ አንድ አዛውንት ተተኩ። “እስኪ ይታያችሁ በዚህ ኑሮ ላይ የማቱሳላ ዕድሜ ተጨምሮበት፤” ትላለች አጠገቤ የተቀመጠችው። “ሌላ አንድ ሺሕ ዓመት በኑሮ ውድነት፣ በፍትሕ ዕጦት፣ በመፈናቀልና በእሪታ ልንዘልቅ?” ይላል መጨረሻ ላይ የተቀመጠ ወጣት። “ኧረ እባካችሁ ተው ዕድሜ ፀጋ ነው! አሁን ለምን ኖርኩ ይባላል?” አዛውንቱ ጨዋታችንን ተቀላቀሉ። “ምን እናድርግ አባት? በአፈር ቤት የማቱሳላን ዕድሜ መመኘት እንዴት ይሆናል?” ትላለች ከጋቢና። እንዴ ይኼ ሁሉ ሕንፃ የት ሄዶ ነው የአፈሩ ቤት ጎልቶ ያታያችሁ? የኮንዶሚኒየም ቤት ባለይዞታነታችንን ሳናመሰግን ደግሞ ባለቪላ አንሆንም፤” ብለው አዛውቱ የልምምጥ ያህል አደብ ግዙ አሉ፡፡

 “የለም አባት እያወራን ያለነው መላውን አገር የተመለከተ ጨዋታ ስለመሰለን ነው። ኑሮ ለአንዳንዱ ቦሌና አካባቢውን፣ ለአብዛኛው ግን የጋርይዮሽ ዘመንን ስለሚያስታውስ ነው። አይመስልዎትም?” አለቻቸው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተየሰመችው። “እህ መቼስ ምን ይደረግ ታዲያ? ተማሩ ሲሉን መማር አንወድ። ተደራጁ ሲሉን አይዋጥልን። ተይውና ሌላውን ኮንዲሚኒየም ምዝገባ ስንቱ ሰው ነው በሽማግሌ ተመክሮና ተዘክሮ ሲመዘገብ የኖረው? እኔ ልጄ ኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ሲወጣልህ በህልሜ ታይቶኛልና ተመዝገብ ስለው ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ?” ሲሏት ከፊል ገጿን ፈገግታ እየሸበሸበው “ምን አለዎት?” አለቻቸው። “ይገርምሻል ምን እንደታየው አላውቅም፣ ‹አይ እናቴ ነገ ማንም ተነስቶ በማን መሬት ላይ እያለ ፉከራ የሚያሰማ ጀብደኛ በሚኖርበት አገር ምን አለፋኝ› ሲለኝ ተናድጄ ነበር፡፡ ለካ እሱ ነብይ ነበር . . .›› ብለው ተከዙ። ቆየት ብለው፣ ‹‹እንዲህ ነው ይኼውልሽ የእኛ ነገር . . .›› ብለዋት ሲቆዘሙ ብዙዎች አንገታቸውን ደፍተው ነበር፡፡ ወይ ይኼ ጎዳና!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው ሒሳብ ተቀብሎ መልስ እየመለሰ፣ ‹‹መስኮት . . . መስኮት . . .›› ብሎ ድንገት ጮኸ። ‹‹መስኮት ክፈቱ። በአዲስ አበባና አካባቢው ያለው ከባድ ወበቅ አልተቻለም። ክፈተው ወንድም . . .” ብሎ መጨረሻ ወንበር ወደ ተመቀጠው ወጣት ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ። “ምነው ልጄ? በስንት ውጣ ውረድ ያልተበገርን ሰዎች፣ ስንቱን የጠላት ወረራ ድባቅ መተን አሳፍረን ያስመለስን ሕዝቦች በወበቅ እናልቃለን ብለህ ፈራህ?” አዛውንቱ በማስተዛዘን ወያላውን ያዩታል። “ወደን ሆነ እንዴ የምንሸነፈው? ተገደን እኮ ነው!” በወዲያኛው ጥግ የተቀመጠ ባለባርኔጣ ወጣት ከመጨረሻ ረድፍ አስተጋባ። መቼ ይሆን ድል አድራጊ የምንሆነው? ትጠይቃለች መሀላቸው የተየሰመች። ‹‹ምንድነው ሰው የሚያወራው? የተወራው ስለወበቅ? ሰው ኳስና ፖለቲካ እየቀላቀለ መናገር በቃ ፋሽን አደረገው?›› ትለኛለች ከጎኔ። ይኼን ስትል ጎልማሳው ሰማት።

‹‹እኔ ግን ዝም ብዬ ሳስበው ከባዱ ወበቅ ያለው ፌስቡክ ውስጥ ይመስለኛል፡፡ ይኼ አሁን ያልሽውን ጨምሮ . . .›› ብሏት አረፈው። ‹‹የወበቅ ቫይረሱ አስተላላፊዋ ትንኝ ክሊክ ናት እያላችሁ ነው? ኧረ እባካችሁ አሁንም እንደ ዛሬ መቶ ዓመት እናስብ ፕሊስ?›› ባዩዋ ጋቢና የተሰየመችው ናት። ኢንፍሉዌንዛ ነው የወባ ወረርሽኝ የተከሰተው? ይላል ግራ የገባው ደግሞ። ሲጣራለት ወዲያው መልሶ፣ ‹‹ታዲያ ወበቅን ከትንኝና ከክሊክ ጋር እዚህ ምን አመጣው?›› ብሎ ይጠይቃል። ሁሉም ዝም። ‹‹አያድርስ! ሲያመን አንስማማ፣ ሲሻለን አንስማማ፣ ደግሞ ብለን ብለን አሁን በወበቅ ስንወረር ያለ ታሪካችን ያለ ገድላችን መስማማት አቆምን?›› ብለው አዛውንቱ ቢናገሩ ደግሞ፣ ‹‹ኧረ አባባ የወበቅንንና የጦርን ወሬ እየለየን እናውራ እባክዎ። እንኳን ወረራ ጨምረንበት እንደዚሁም የክተት አዋጁ ሥራ አላሠራ ብሎናል፤›› ብሎ ጎልማሳው ጨዋታውን ቀጨው። ‹‹ሦስት ሺሕ ምናምን ዓመታት በሥራ ብቻ እንዳለፉ ሁሉ መሥራት አቃተን ይባልልናል፣ ጉድ እኮ ነው!›› የምትለው አጠገቤ ያለችው ነገረኛ ናት፡፡

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹እስኪ ጫፍ ላይ ጣለኝ…›› ይላል አንዱ ተሳፋሪ። ‹‹ጊዜ እንደ ዕቃ የሚጥለን አልበቃ ብሎ ራስህን በሰው ፊት ትጥላለህ?›› ይጠይቃል ጎልማሳው። ምን ይደረግ? የዛሬ ጊዜ ሰው ከጊዜ በፊት ነው የሚወድቀው። ሰበብ ፈላጊም ጠፍቷል እኮ ጎበዝ?›› ትላለች ቀዘቢት። ‹‹ለምኑ ነው ደግሞ ሰበብ ፈላጊ የጠፋው?›› ይጠይቃል ከመጨረሻ ወንበር ባለ ባርኔጣው። ‹‹ለውድቀቱም ለመነሳቱም ሰበብ የማናጣ ሆነናል፤›› ታብራራለች እንደ ጀመረችው። ‹‹እንዴ ምነው ታዲያ ይኼ ሁሉ የፖለቲካ ትችት፣ ማኅበረሰባዊ ትችት፣ ግለሰባዊ ትችት . . . ያጥለቀለቀን?›› አዛውንቱ የምራቸውን ግራ ተጋብተው ጠየቁ። ‹‹ሰበብ በማጣት ውስጥ ሰበብ ፍለጋ ነዋ። የጨነቀው እኮ እርጉዝ ያገባል?›› ብሎ የባሰውን ጎልማሳው አወሳሰበው።

‹‹አሁን ከዚህ ሁሉ ምናለበት አርፈን አገራችንን ብናለማ? ለሌላው ነገር ምን ጨነቀን?›› ሲሉ አዛውንቱ ነገር አመጡ። ‹‹በየት በኩል ጋሼ? አንዱ ወደፊት ሲራመድ አንዱ ወደኃላ ይጎትታል። አንዱ ሲያልም ሊላው ይቃዣል። አንዱ ሲሞላ ሌላው ያጎላል። ከዚህ ሁሉ ደግሞ የባሰን ባልተጨበጠና ባልተያዘ ነገር የሚያስለፋን ጉዳይ መብዛቱ ነው። አቤት ስንቱ! ስንቱ!›› እያለች ስታነበንብ የጋቢናዋ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። ‹‹እንደ አንድ ሆነን የጋራ ራዕይ መቅረፅ ቢሳነን እንዴት እንደ ብዙ መተባበር፣ መቀራረብ፣ መደማመጥ፣ ችግርን ማጥራትና ማጣራት ያቅተናል? በጉንጭ አልፋ ወሬ ሆድ ይሞላል እንዴ? በሐሰተኛ ወሬ አገር ያድጋል እንዴ? ከገዛ ወገን ጋር እየተላተሙ ይዘለቃል እንዴ? በገዛ ወገን ላይ መደንፋትና መሸለል ሥልጣኔ ነው እንዴ? በጋራ ጥረት ያደገ ከተማን የእኔ ብቻ ነው እያሉ ማቅራራትስ ይቻላል እንዴ? በግራ በቀኝም ኧረ እየተስተዋለ?›› የሚል ድምፅ ቢሰማንም ቀሪውን መንገዳችንን  በእግራችን ቀጥለናል፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት