በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በየወሩ ይፋ እየተደረገ የሚገኘው የቡና አፈጻጸም ሪፖርት፣ የየካቲት 2011 ዓ.ም. አፈጻጸም በቅርቡ ይፋ ተደርጓል፡፡ በየካቲት ወር 20,343.59 ቶን የቡና ምርት በመላክ 73.38 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ ይጠበቅ ነበር፡፡
ሆኖም የዕቅዱን 79.63 በመቶ የሚወክል 16,198.77 ቶን ቡና በመላክ፣ 55.31 ሚሊዮን ዶላር ገቢ (ከዕቅዱ አኳያ 75.38 በመቶ) መሳካቱን መረጃው ይጠቁማል፡፡ የወሩ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀርም በመጠን የ408.24 ቶንና ከገቢ አኳያም የ4.78 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
በዚህ ሪፖርት መሠረት፣ የስምንት ወራት አፈጻጸሙን ተካተው የቀረቡት አኃዞች እንደሚያሳዩት፣ በስምንቱ ወራት ውስጥ ወደ ውጭ የሚላክ 168,336.16 ቶን የቡና ምርት፣ 607.75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ታቅዶ ነበር፡፡
በአፈጻጸሙም 130,472.23 ቶን ቡና ወይም የዕቅዱን 77.51 በመቶ በማሳካት በገቢ ደረጃ 422.91 ሚሊዮን ዶላር እንዳስገኘ የባለሥልጣኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ6,945.05 ቶን ወይም የ5.05 በመቶ ቅናሽ ሲታይበት፣ የ58.96 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ12.24 በመቶ የገቢ ቅናሽም አስመዝግቧል፡፡
ከዕቅዱ አኳያ በስምንት ወራት ውስጥ ከታየው ቅናሽ ውስጥ በተለይ በመጠን ከፍተኛ ቅናሽ የተመዘገበው በነሐሴ ወር እንደነበር ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ ይህም 93.34 በመቶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በኅዳር ወርም እንደዚሁ የ62.2 በመቶ በመጠን ቅናሽ የታየበት አፈጻጸም ሲመዘገብ፣ በነሐሴ ወር በገቢ ረገድ የ87.52 በመቶ በኅዳር ወርም የ50.89 በመቶ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡