Tuesday, May 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም ባንክ ግሩፕ ምክትል ፕሬዚዳንት ሴይላ ፓራባሲዮግሉ (ዶ/ር) የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ከማክሰኞ፣ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ተገኝተዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቷ በጉብኝታቸው ወቅት የዓለም ባንክ ብድርና ዕርዳታ በመስጠት እንዲገነቡ ድጋፍ ያደረገባቸው ፕሮጀክቶች ትኩረታቸው እንደሚሆኑ ከዓለም ባንክ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን፣ የሞጆ ደረቅ ወደብን እንዲሁም የሥራ ፈጣሪ ሴቶች ልማት ፕሮጀክት በጉብኝታቸው ተካተዋል፡፡

መንግሥት ለቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፕሮጀክት ግንባታ ከዓለም ባንክ ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ የብድር ገንዘብ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ የፓርኩ ግንባታ ከታሰበው ጊዜ መጓተት ቢታይበትም፣ በዚህ ዓመት ከሚመረቁት አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ እርግጥ ይመረቃል ከተባለበት ጊዜም መዘግየቱ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ባሻገር ባለፈው ጥር ወር ርክክብ የተፈጸመባቸውን ጨምሮ 13 ኮንቴይነርን ጨምሮ በብትን የመጡ ዕቃዎችን ከመኪና የሚያወርዱና የሚጭኑ ማሽኖች (ሪችስታከር) እንዲሁም በርካታ ፎርክሊፍቶችን በ150 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶ መረከቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህም በጠቅላላው ከ150 በላይ ማሽነሪዎችን የሚያንቀሳቅስ ተርሚናል ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህንን ግዥ ለመፈጸም ያበቃውን የገንዘብ ድጋፍ ያገኘውም ከዓለም ባንክ ነው፡፡

ባንኩ ለሥራ ፈጣሪ ሴቶች ልማት ፕሮጀክት የሚውል ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ መስጠቱም ሌላኛው በምክትል ፕሬዚዳንቷ ጉብኝት ወቅት የሚገመገም ፕሮጀክት ነው፡፡

የጉብኝታቸው ዓላማም እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች ያስገኙትን ውጤት በራሳቸው ዕይታ ለመገምገም በመፈለግ እንደሆነ የባንኩ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጉብኝታቸው ወቅት የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅት ከሚያገኟቸውና ከሚያነጋግሯቸው መካከል የፋይናንስ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ይገኙበታል፡፡

ቱርካዊቷ የኢኮኖሚ ባለሙያና የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ባንኩን በተመጣጣኝ ዕድገት፣ በፋይናንስና በተቋማት መስክ ባለው የኃላፊነት ዕርከን የሚመሩ ናቸው፡፡ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ሹመታቸውን ያገኙትም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሲሆን፣ ባንኩ በሚንቀሳቀስባቸው 30 በግጭት የደቀቁና ለአደጋ የተጋለጡ አገሮችን ጨምሮ በ138 አገሮች ውስጥ ከ2,200 በላይ የባንኩን ሠራተኞችን የሚመሩ፣ በ30 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ላይ ውሳኔ መስጠት የሚችሉ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ኃላፊ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በመልቀቅ የዓለም ባንክን የተቀላቀሉት የእኚህ ኃላፊ ጉብኝት፣ የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም ወደፊት በአጋርነት በሌሎች መስኮች ለመሥራት ያለውን ፍላጎት እንደሚያሳይ ባንኩ አስታውቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች