Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመውለድ የተቸገሩ ሰዎች በጉጉት የሚጠብቁት የጤና ማዕከል

መውለድ የተቸገሩ ሰዎች በጉጉት የሚጠብቁት የጤና ማዕከል

ቀን:

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሥነ ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል (ሴንተር ፎር ፈርቲሊቲ ኤንድ ሪፕሮዳክቲቭ ሜዲሰን) በሚቀጥለው ወር አገልግሎቱን መስጠት ይጀምራል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ለመውለድ የተቸገሩ 1,000 ሰዎች ተመዝግበው አገልግሎቱን ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የማዕከሉ መሥራች አስታወቁ፡፡

የዴን ማርክ አልጋ ወራሽ ልዕልት ሜሪና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሚሲዝ ኡላ ቶርነስ የኮሌጁን ምቹ ክሊኒክና ማዕከሉን መጎብኘታቸውን በማስመልከት የማዕከሉ መሥራች ሠናይት ፍስሐ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ ይህ ዓይነት አገልግሎት በመንግሥት ሕክምና ተቋም ሲሰጥ የመጀመርያው ነው፡፡

አገልግሎቱ በጣም ውድ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉም ነገር በነፃ ይሰጥ ቢባል የማይሆን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አገልግሎት ፈላጊዎች የሐኪሙንና የዕቃውን እንደማይከፍሉ፣ በተረፈ መድኃኒቱን እየገዙ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው፣ መድኃኒቱ በጣም ውድ መሆኑ ከወዲሁ መታወቅ እንደሚኖርበት፣ ይህም ሆኖ ግን የመግዛት አቅም ለሌላቸው ተጠቃሚዎች በዕርዳታ ለማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ በመመቻቸት ላይ እንዲሆነ ተናግረዋል፡፡

ሕክምናው ቀላል አይደለም፣ ውስብስብ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ በሙያው ለመሠልጠን በቅድሚያ መደበኛውን የሕክምና ትምህርት ማጠናቀቅና ከዚያም በማኅፀንና ጽንስ ሕክምና እንደገና ለአራት ዓመት መከታተል ግድ ይላል፡፡ ይህም እንዳበቃ በፈርቲሊቲ ሙያ ለመሠልጠን ተጨማሪ ሦስት ዓመት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ጽንስና ማኅፀን ሕክምና የተማሩ ብዙ ሐኪሞች እንዳሉ፣ ችግሩ ግን ፈርቲሊቲን በተመለከተ የተማሩ ባለሙያዎች ወይም ሐኪሞች እንደሌሉ ከፕሮፌሰር ሠናይት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለዚህም ችግር እንደ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደው የጽንስና ማኅፀን ሐኪሞችን ወደ ህንድና ሌላም አገር እየሄዱ በመሠልጠን ላይ ሲሆኑ፣ ልምድና ተሞክሮ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ሠናይት አሜሪካ ከሚገኘው ሜሽጋን ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ብቁ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ ሙያተኞች እየመጡ የማዕከሉን ይዘትና አደረጃጀት እየተከታተሉ መሆኑንም አክለዋል፡፡ አገልግሎቱ ሲጀመር ከተጠቀሰው ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ሙያተኞች በየአራት ዓመት እየመጡ አገልግሎት እንደሚሰጡ፣ በዚህም አጋጣሚ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ሥልጠና እንደሚያገኙና በዚህ ዓይነት መልኩ ሥራዎች ከተከናወኑ ቢያንስ ከሦስት ዓመት በኋላ አገሪቱ ያለ ዕርዳታ የሚሠሩና የበቁ ሐኪሞችን ታፈራለች ብለዋል፡፡

ልዕልት አልጋ ወራሽ ሜሪና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሚስዝ ኡላ ቶርነስ በሆስፒታል ቅጥር ግቢ የሚገኘውን ምቹ ክሊኒክና በዚህ ሆስፒታል ሥር የሚተዳደረውንና በተለምዶ 22 ማዞሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የሥነ ተዋልዶ ጤና ማዕከልን ጎብኝተው እንዳበቁ ከሴቶች መብት ተሟጋቾችና ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር ዝግ ውይይት አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሮያል ዳኒሽ ኤምባሲም ጉብኝቱን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በውይይቱ የተነሱትን ጉዳዮችና እንግዶቹ የሰጡት አስተያየት ካለ እንዲያብራሩልን ፕሮፌሰር ሰናይትን ጠይቀን እንደነገሩን፣ እናቶች በወሊድ ሳቢያ እንዳይሞቱና የቤተሰባቸውን መጠን እንዲያቅዱ፣ የተደረጉ ሥራዎችን ከልብ አድንቀዋል፡፡

ያለ አቻ ጋብቻ፣ ጠለፋ፣ የፆታ ጥቃት፣ ትንኮሳና መደፈርን በተመለከተ በወረቀት ላይ ያለውና ተግባራዊ እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ሆኖ እንዳገኙት አስረድተዋል፡፡

ከመግለጫውም ለመረዳት እንደተቻለው ልጃገረዶችና ሴቶች ልጅ ይፈልጉ እንደሆነ፣ ስንትና መቼ መውለድ እንደሚፈልጉ የመምረጥ መብታቸው ትኩረት ሊነፈገው አይገባም፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አንዲት ሴት ሰባት ልጆችን ትወልድ እንደነበር፣ በ2008 ዓ.ም. ግን የአንዲት ሴት የመውለድ መጠን ወደ 4.2 መውረዱን በአንፃሩ የወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀም ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ለሴቶች እየተደረገ ባለው የጤና ክብካቤ በወሊድ ሳቢያ ይከሰት የነበረው የእናቶች ሞት መጠን እየቀነሰ መምጣቱንም መግለጫው አመልክቷል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ከአራት ወላዶች መካከል አንዷ ብቻ በሠለጠነ የሕክምና ባለሙያዎች (ነርሶና ዶክተሮች) እንደምትወልድ ተገልጿል፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ በሙከራ ደረጃ የተቋቋመውም ክሊኒክ የቤተሰብ ዕቅድ ምክርና አገልግሎት የእርግዝና መከላከያ፣ የአፍላ ወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ጤና፣ የጽንስ ማቋራጥ፣ እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ አገልግሎት በመስጠት የማይናቅ አስተዋጽኦ ማበርቱን የክሊኒኩ ኃላፊ ሲስተር ፍቅርተ እሸቴ አስረድተዋል፡፡

ይህ ዓይነት ክሊኒክ በአሁኑ ጊዜ በመቀሌ፣ በጅማ፣ በአዳማና በመቱ መስፋፋቱን ከሲስተር ፍቅርተ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...