ትምህርት ቤትና ሆስፒታል እንዲገነባ ጠይቀዋል
ከጅማ 45 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘውና ነዋሪዎች የሠፈሩበትን ጨምሮ 166 ሺሕ ሔክታር በሚሸፍነው ‹‹በለጠ ጌራ›› ደን ውስጥ የጫካ ቡና በማምረት የተሰማሩ አርሶ አደሮች፤ የጃፓን መንግሥት ተራድኦ ድርጅት (ጃይካ) እያደረገላቸው በሚገኘው የአቅም ግንባታ ሥራ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ፡፡
መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ጃይካ ከኦሮሚያ አካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣንና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ‹‹Ethiopian Wild Coffee a Gift to the World›› [የኢትዮጵያ ጫካ ቡና፤ ለዓለም የተሰጠ በረከት] በሚል ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የተገኙት የአካባቢው የቡና አርሶ አደሮች፣ ማኅበራትና ኮፕሬቲቭ ኃላፊዎች፣ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅትና ጃይካ በጋራ በሚተገብሩት የጫካ ቡና ሰርተፍኬሽን ፕሮግራም፣ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በበለጠ ጌራ ጫካ በ2002 ዓ.ም. የተመሠረተውና 121 አባላት ያሉት የሸቤ ሳምቦ ሚግራ ኮፕሬቲቭ ገንዘብ ያዥ አቶ ዙቤር አባኦሊ እንደነገሩን፣ ጫካ ውስጥ ከሚኖረው አርሶ አደር ቡና ሰብስበው ለኢንተርፕራይዝ ለመላክ በሚያደርጉት ሒደት ቡናው ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ጃይካ እገዛ ያደርጋል፣ በርካታ የጃፓን ባለሙያዎችም ሥፍራው ድረስ በመሄድ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ በሚሆንበት መንገድ ያግዛሉ፡፡
ማኅበሩ ከዓመት ዓመት በሚሸጠው ቡና ከነጀንፈሉ የሚያገኘው ገቢ እያደገ ቢሆንም፣ ለኢንተርፕራይዝ ሲያስረክቡ የሚከፈላቸው በኪሎ ከ30 ብር እስከ 32 ብር ዋጋ አነስተኛ መሆኑን አቶ ዙቤር ይገልጻሉ፡፡
ከዓመት ዓመት የተሻለ ገቢ እየተገኘ የቡና አቅርቦቱም እየጨመረ ቢሄድም፣ ችግሮች መኖራቸውንም አቶ ዙቤር ተናግረዋል፡፡ ማኅበራቸው 2003/4 ዓ.ም. 20 ሺሕ ኪሎ ግራም ቡና አቅርበው 29 ሺሕ ብር ብቻ ማግኘታቸውን በመኮነን፣ እስከ 2006 ዓ.ም. ቡና ለኢንተርፕራይዞች ማቅረብ ማቆማቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ ከኢንተርፕራይዞች ጋር ተነጋግረው ምርቱን ማቅረብ መጀመራቸውን፣ ገቢውም ጥሩ መሆኑንና ዘንድሮ የተሻለ ገቢ ማግኘታቸውንም ይናገራሉ፡፡
‹ሕዝቡ ጥሩ ሠርተን ጥሩ እናገኛለን› ብሎ ተስፋ ማድረጉን፣ ሆኖም ገዥዎች በጊዜው አለመግዛት ማለትም ማኅበራት ቡና ሰብስበው ሲጠብቁ አለመምጣት፣ በሚመጡበት ጊዜ ደግሞ የሁለት ወይም የሦስት ሳምንት ጊዜ ብቻ የሚሰጡ መሆኑንና ማኅበራቱ ጊዜው ስለማይበቃቸው ቡናውን ሰብስበው ወደ ሚፈለገው ቦታ ሳያደርሱ ጊዜው የሚያልቅ በመሆኑ ለኪሳራ የሚዳረጉበት ጊዜ መኖሩ ችግር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ብዙ ኪሎ ግራም ቡና አቅርበው ጥቂት ገንዘብ ያገኙ እንደነበር፣ አሁን በመሻሻሉ ግን ማኅበራቱም፣ አርሶ አደሩም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አክለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በኢንተርፕራይዝ በኩል ቡና በጊዜ አለመቀበል፣ ኬሻ አለማግኘትና ገንዘብ ቶሎ አለመክፈል የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ይህ እየተለወጠና እየተሻለ መጥቷል፣ ሆኖም የሚቀሩ ሥራዎች አሉ ብለዋል፡፡
በ2002 ዓ.ም. በ84 አባላት ተመሥርቶ አሁን ከ660 አባላት ውስጥ 120 ሴቶችን በመያዝ በበለጠ ጌራ ጫካ የሚሠራው ናኖ ሰበቃ ማኅበር ፀሐፊ አቶ ያሲን አባቢያ በበኩላቸው፣ ማኅበራቸው ከሌሎች በተሻለ፣ ቡና ከነጀንፈሉ፣ የተቀሸረና የታጠበ እንደሚያቀርብ፣ በዚህም ጥሩ ገቢ እያገኙ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ዘንድሮ 76 ሺሕ ኪሎ ግራም ቡና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ መሸጣቸውን ገልጸው፣ ቡናን ለኢንተርፕይዝ በማቅረብ በኩል ማኅበሩ ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ያሲን፣ ቡናውን በሚቀበሉ ኢንተርፕራይዞች በኩል ቡናን ድንገት አምጡ የማለት፣ ከአርሶ አደሩ ተሰብስቦ ከመጣ በኋላ ጊዜ አልፏል እንደሚባል፣ ማኅበራት በፈለጉት መጠን የቡና ማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ እንደማይሟላ፣ ይህንን ለማስተካከል ቃል እንደተገባላቸው ገልጸዋል፡፡
ቡናውን ከአርሶ አደሩ ሰብስቦ ኢንተርፕራይዝ እስኪደርስ ባለው ሒደት አንዳንዴ ችግር የሚያጋጥም ቢሆንም፣ ጃይካ ከገባ ወዲህ ነገሮች እየተሻሻሉና ገቢም እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጃይካ ኃላፊ ሚስተር ማኮቶ ሺካዋሳን፣ እ.ኤ.አ. በ2003 የተጀመረው ፕሮጀክት፣ የጫካ ቡናን ጠብቆ ለማቆየት፣ ደኑን ለመጠበቅ የቡና ምርቱ ዘላቂ ማድረግን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም ለአገር ውስጥ ፍጆታ ያቀርቡ የነበሩ አርሶ አደሮች ወደ ውጭ እንዲልኩ ማስቻሉን፣ ከአየር ንብረቱ ጋር የተስማማ የቡና ግብርና እንዲስፋፋ ማድረጉንና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበለጠ ጌራ ጫካ ዙሪያ በቅርቡ የተሠራው ጥናትም ተመናምኖ የነበረው ደን ማገገም መጀመሩን ማሳየቱን አውስተዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ሕዝቡ በተለይ ሆስፒታልና ትምህርት ቤት በአካባቢው ባለመኖሩ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያስነሳም መልስ እንዳልተገኘ የማኅበራት ተወካዮች ገልጸዋል፡፡
ጃይካና የኦሮሚያ ደንና የዱር እንስሳት ድርጅት በጋራ በሚሠሩት የበለጠ ጌራ የጫካ ቡና ፕሮጀክት የሰርተፍኬሽን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ቂጡማ ጃለታ እንደሚሉት፣ ፕሮጀክቱ የተጀመረው እ.ኤ.አ. 2003 ነው፡፡
ፕሮግራሙ ሲጀመር የአካባቢው አርሶ አደሮች ደኑን እንዲጠብቁ የነበረ ቢሆንም፣ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የቡና ሰርተፍኬሽን ፕሮግራሙ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ በጅማ ዞን በበለጠ ጌራ ጫካ በሚገኙት በሸቤ ሰምቦና በጌራ ወረዳዎች የሚተገበረው ፕሮጀክት፣ አርሶ አደሩ በጫካው የሚገኘውን ቡና እየለቀመ ጫካውን እንዲጠብቅ ለማድረግ ያለመም ነው፡፡
አርሶ አደሩን ለመጥቀም ተብሎ የተጀመረው የቡና ሰርተፍኬሽን ፕሮግራም፣ የጫካውን ቡና ጥራት እየጠበቁ፣ በማኅበር እየተደራጁ፣ ለኮፕሬቲቭ እየሸጡ፣ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ወደ ጃፓን የሚልክበት ሥርዓት ተበጅቷል፡፡ ከበለጠ ጌራ ጫካ የሚሰበሰበው የጫካ ቡና የሚላከው ወደ ጃፓን ሲሆን፣ እስካሁንም ዘጠኝ ጊዜ ልከዋል፡፡
የጃፓን ገዥዎች ለማኅበራቱ ከሚከፍሉት በተጨማሪ አርሶ አደሩ የአካባቢ ጥበቃን ስለሚሠራ ለማበረታታት በገዙት ቡና ልክ ተጨማሪ ይከፍላሉ፡፡ ከክፍያው 30 በመቶ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ወስዶ፣ ቀሪው ለኮፖሬትቮች ይከፋፈላል፡፡ ገበሬውም ባቀረበው ቡና ልክ ተጨማሪ ክፍያ አለው፡፡
ይህ አሠራር አርሶ አደሩ የጫካ ቡናንም ሆነ የአካባቢውን ደን እንዲጠብቅ አግዟል፡፡ በፕሮጀክቱ በሁለቱ ወረዳዎች 124 ማኅበራት ሲኖሩ፣ ሰባት ኮፖሬቲቮች ይገኛሉ፡፡ 100 ሺሕ ያህል ነዋሪዎችም በጫካው ዙሪያና ውስጥም ይገኛሉ፡፡ ሆኖም በአካባቢው ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም አለመኖሩ ችግር ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ከቡና ውጭ እንደማይሠራ፣ ሆኖም የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ዘንድሮ ማግኘት በጀመረው ተጨማሪ ክፍያ ይሠራል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ቂጡማ ተናግረዋል፡፡