የአካል ማጎልመሻና ብቃት አስተማሪ የሆነው አቶ ግዛቸው ንጉሤ ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ ከአካል ማጎልመሻ አስተማሪነቱ ባሻገር በትርፍ ጊዜው ከተለያዩ የወዳደቁ ቁሳቁሶች የዕደ ጥበብ ውጤቶችን በመሥራት ያሳልፋል፡፡ የፈጠራ ሥራዎቹ የሚቀዱት አካባቢንና ወንዞችን ከሚበክሉ እንደ ፌስታል፣ ኃይላንድና የተሰባበሩ ጠርሙሶች በመጠቀም ነው፡፡ በነዚህም የተለያዩ ጀበናዎችን፣ የቢሮ ቁልፍ ማስቀመጫዎችን፣ ምንጣፎችን፣ መጥረጊያዎችን በመሥራት ለተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እንደሚሸጥ ይናገራል፡፡ ከአካል ማጎልመሻ አስተማሪነቱ አኳያ በቅርብ ጊዜ ለተሰባሰቡት የጎዳና ተዳዳሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ለማስተማር ፍላጎቱ እንዳለውም ሳይናገር አላለፈም፡፡ የሚመለከተው አካልም ሥራዎቹን ተመልክቶ ድጋፍ ቢያደርግለት ራሱንም ሆነ ማኅበረሰቡንም እንደሚጠቅም አካባቢዎችን ጽዱ ለማድረግ እንደሚያተጋው ተናግሯል፡፡ ፎቶዎቹ ተጠባቢውንና ሥራዎቹን በከፊል ያሳያሉ፡፡
በተመስገን ተጋፋው