Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የመንግሥት ሪፎርም ፕሮግራሞች በጥንቃቄ እንዲታቀዱ አሳሰቡ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በኑሮ ደረጃ ልኬት ከ80 በመቶ በላይ ሕዝብ ዝቅተኛውን ዕርከን ይዟል

  በኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ የቆዩት የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ቼይላ ፓዛርባሲዮግሉ፣ መንግሥት በርካታ የሪፎርም ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ለማድረግ መነሳቱን እንደሚያደንቁ አስታውቀው የሪፎርም አጀንዳዎቹን በጥንቃቄ ማቀድና መተግበር ብሎም ቅደም ተከተላቸውን ማስጠበቅ እንደሚገባው አሳሰቡ፡፡

  ምክትል ፕሬዚዳንቷ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወቅት የቦሌ ለሚ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርክን፣ የሞጆ ደረቅ ወደብን፣ እንዲሁም የሥራ ፈጣሪ ሴቶች ልማት ፕሮጀክትን ከመጎብኘታቸው በተጨማሪ የዓለም ባንክ በየወቅቱ ይፋ የሚያደርገውን የኢትዮጵያ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሪፖርት ዓርብ መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. የቃኘውን ሰባተኛ ዙር ዕትም ተከታትለዋል፡፡

  ከጉብኝታቸው በመነሳት ለሪፖርተር እንደተናገሩት መንግሥት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ ለንግድ ልማትና መሰል ጉዳዮች እንቅፋት የሆኑት ምን እንደሆኑ በመረዳት ማስተካከልና ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ማስፋፋት ይገባዋል፡፡ መንግሥት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚያገኘውን ተሞክሮ ወደ መላው የአገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት የሚያስችለው በመሆኑ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

  ምክትል ፕሬዚዳንቷ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ ወቅት መንግሥት በፋይናንስ ዘርፍ፣ በታክስ፣ በግሉ ዘርፍ፣ በፕራይቬታይዜሽንና በሌሎችም መስኮች የሪፎርም አጀንዳዎች አሉት ብለዋል፡፡ ለሪፎርሞቹ የሚስማማ ዕቅድ መንግሥት እንዳለው እምነታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ይሁንና የትግበራው ጉዳይ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ተገቢውን ዕቅድ በመንደፍና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዕርምጃዎች ቅድሚያውን በመስጠት መተግበር ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል፡፡

  በመንግሥትም ሆነ በውጭ ኩባንያዎች የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ምርት ሥራ በመግባት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቢጀምሩም፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚላኩ የወጪ ንግድ ምርቶች ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ዘርፍ አኳያ ያላቸው ድርሻ ከ2.5 በመቶ በታች መሆኑን የባንኩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን አገሪቱ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ በምትገኝበት ወቅትና የወጪ ንግዷ በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ መንግሥት ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ሊተገብራቸው ከሚያስባቸው የሪፎርም ዕርምጃዎች መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታነት በሙሉ ወይም በከፊል የማዘዋወሩ ጉዳይ፣ ቀስ በቀስ ሊተገበር ይገባል ወይስ በፍጥነት ይገባበት ለሚለውም በጥቂቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

  ዓለም በየጊዜው ፈታኝና እርግጠኛ መሆን በማያስችሉ ተፅዕኖዎች ውስጥ እየወደቀች በምትገኝበት ወቅት፣ አገሮች ሁሉ እንደ ሁኔታው ራሳቸውን ከተለዋዋጩ የዓለም ሁኔታ ጋር ያጣጥማሉ ያሉት የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ኢትዮጵያም በዓለም ኢኮኖሚ ተፅዕኖ ሥር በመሆኗ ለዚሁ የተስማማ ምላሽ ልትሰጥ እንደምትችል ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለወጠናቸው የሪፎርም ፕሮግራሞች ዕቅድና የቅደም ተከተል አካሄድ እንደሚኖረው ዕምነታቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ይሁንና እነዚህን ዕርምጃዎች ከውጫዊ ሁኔታዎች ጋር አጣጥሞ ማስኬድ ከመንግሥት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

  በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ የቃኘው የዓለም ባንክ ሪፖርት፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ክፍልና የድህነትና የኢኮኖሚ አቅምን ከቤተሰብ ፍጆታና የኑሮ ደረጃ ጋር በማዛመድ አመላክቷል፡፡ መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚው መስክ በተለይም በዋጋ ግሽበትና በገንዘብ አቅርቦት መጨመር፣ በአገር ውስጥ ብድር፣ በውጭ ብድር ዕዳና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ሁኔታ ላይ በግልጽነት ላይ የተመሠረተ አሠራር እንዲከተል ያሳሰቡት የባንኩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ ኖራ ዲሄል ናቸው፡፡

  መንግሥት የውጭ ብድር መቀነሱን ቢያስታውቅም፣ ከአገር ውስጥ ምንጮች የሚበደረው ገንዘብ መጠን ጨምሯል ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዋ፣ ከዚህ ባሻገር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብድር መጠንና የብድር ሥርዓታቸው በግልጽ መታወቅ እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

  ከዚህ በተጓዳኝ በድህነትና በቤሰተብ ፍጆታ ላይ በማተኮር የተጠናቀረውን ሪፖርት ያቀረቡት በድህነት መስክ የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ በርሄ መኮንን በበኩላቸው፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ከመደበኛ የኑሮ ደረጃ በታች ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ በአገሪቱ የተካሄዱ ሁለት የቤተሰብ ፍጆታና የድህነት ሁኔታ አመላካች ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ የተካሄደው ይህ የዓለም ባንክ ጥናት፣ በተለይ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች በፍጆታ ረገድ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማሳየት አልቻሉም ብለዋል፡፡ አገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ብታመስመዘግብም፣ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው 15 በመቶ ደሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮ መሻሻል ካለማሳየቱም በላይ፣ ፈጣኑ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትም ምንም አልጠቀመውም ብለዋል፡፡ 

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች