Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚነሳው የባለቤትነት ጥያቄ ሕጋዊ አንድምታው ሲፈተሽ

አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚነሳው የባለቤትነት ጥያቄ ሕጋዊ አንድምታው ሲፈተሽ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባን የሚመለከቱ አጀንዳዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ የተቃዋሚም የገዥው ፓርቲም አጀንዳ ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥም አባል ድርጅቶች የተለያየ አቋም በመያዝ የአጀንዳው ተሳታፊ ናቸው፡፡ በፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ቡድኖችም እንዲሁ ያገባናል በማለት አደረጃጀት በመፍጠር መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ ከፓርቲና ከማኅበራዊ ቡድኖች አልፎም የአዲስ አበባና የፌዴራል መንግሥቱንም ትኩረት ስቧል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥም ይኼው የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቁልፍ ማጠንጠኛው አዲስ አበባን በሚመለከት የሚነሳው የባለቤትነት ጥያቄ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ጥያቄውንም ሆነ የሚስተዋሉትን “የይገባኛል” ዓይነት  ፍላጎቶች ከሕግ አኳያ ይዘታቸውና አንድምታቸው ላይ ያተኮረ ነው፡፡ 

አዲስ አበባ፣ እንደ ፌዴራል መንግሥት ዋና ከተማነቷ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ከሌሎች ተመሳሳይ ፌደራላዊ አገሮች ዋና ከተማ ጋር የሚቀራረብና የሚገጥም ሕጋዊ ግንኙነትና አሠራር አላት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ከሌሎቹ ዋና ከተሞች ጋር የማይገጥሙ፣ የተለዩ መገለጫዎች አሏት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በሕግ የተቀመጡም በልማድ የዳበሩም አሉ፡፡ አዲስ አበባ የፌደራል መንግሥቱ ርዕሰ ከተማ ናት፡፡ እንደነ በርሊንና ሞስኮ ከሌሎች ክልሎች ጋር እኩል ሥልጣንና ቁመና የላትም፡፡ እንደ ዋሺንግተን ዲሲ የፌዴራሉ መንግሥት መሬቷን ለክቶና ካርታ አውጥቶ የተረከባት ከክልሎች የተገለለች ነዋሪዎቿም መምረጥም መመረጥም የማይችሉባት አይደለችም፡፡ እንደ ደርባንና ፕሪቶሪያ (ደቡብ አፍሪካ) የማዕከላዊ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተበታትነው የሚገኙባት፣ በክልሎች አስተዳደር ሥር ያለች ከተማ አይደለችም፡፡ ከእነ ዋሽንግተን ዲሲ ከፍ ያለ፣ ከእነ በርሊን አነስ ያለ የሕግ አቋም አላት፡፡ ስለሆነም ይህ አንዱ ከሌሎች የፌዴራል ዋና ከተሞች ይለያታል፡፡ “ማንንም ሳልመስል የራሴን ልዩ መልክ ይኑረኝ” ያለች ትመስላለች፡፡ ይኼ ሕገ መንግሥቱ ይሰጣት ቁመናዋ ነው፡፡

አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልልም ዋና ከተማ ናት፡፡ ማንም እንደሚያውቀው፣ ሕገ መንግሥቱም የአዋጁን በይፋ ብሎ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል እንደምትገኝ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 (5) ላይ ገልጾታል፡፡ በኦሮሚያ መሀል ትገኛለች አለ እንጂ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት በማለት ዕውቅና አልሰጠም፡፡ የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥት መጀመርያ ላይ ዋና ከተማ በማለት ዕውቅና የሰጠው አዳማን ነበር፡፡ አዳማ ነው ቢልም አዲስ አበባ ላይ መቀመጫውን አድርጎ ቆይቶ ወደ አዳማ የሄደው በዘጠናዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ በምርጫ ዘጠና ሰባት ምክንያት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከአዳማ ተመልሶ አዲስ አበባ ሆነ፡፡ የክልሉ ሕገ መንግሥትም ተሻሻሎ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በክልሉ ሕገ መንግሥት አገላለጽ ፊንፊኔ ሆነ፡፡ ይህ ሲሆን በተናጠል ውሳኔ ያሳለፈው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር (መንግሥት) አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ቢኖረውም የኦሮሚያ ክልል በአንድዮሽ ውሳኔ ዋና ከተማውን አዲስ አበባ ላይ አደረገ፡፡ የከተማው አስተዳደር እያለ፣ ተሳትፎ ሳያደርግ በክልሉ ውሳኔ ብቻ የግዛቱ አካል ባልሆነች ከተማ ላይ ዋና ከተማውን ማድረጉና በዚያው መጽናቱ ሌላው መለየዋ ነው፡፡  በሦስተኛ ደረጃ ልዩ ጥቅም በሚል በሕገ መንግሥቱ መገለጹ በራሱ ሌላው መለያዋ ነው፡፡ ከሌሎች የፌዴራል አገሮች ዋና ከተሞች በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ መስተዳደር (የፌዴራል መንግሥቱ) እና የኦሮሚያ ክልል በሁለትዮሽ ስምምነት ሊፈቱት ወይም መፍትሔ ሊሰጡት የሚገባውን የሁለቱን አስተዳደራዊ ግንኙነቶች የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረው ልዩ ጥቅም ይከበርለታል በማለት አልፎታል፡፡ ምናልባት በሕገ መንግሥቱ መቀመጡ መነሻው የአዲስ አበባ አዋሳኝ ኦሮሚያ ክልል ብቻ በመሆኑ ወይም በሌላ አገላለጽ አዲስ አበባ የምትገኘው በኦሮሚያ መሐል በመሆኗ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በዚህም መሠረት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 (5) እንደተገለጸው ሁለት ቅርንጫፍ ያላቸው ጉዳዮች የአዲስ አበባና የኦሮሚያን ግንኙነቶች ይመለከታሉ፡፡ አንዱ ከኦሮሚያ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ወይም በተቃራኒው የሚሄዱ የተፈጥሮ ሀብትና የአገልግሎት አቅርቦትን የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሀል የምትገኝ ከመሆኗ የሚመነጭ አስተዳደራዊ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን ግንኙነቶች የሚገዛ ዝርዝር ሕግ እስካሁን አልወጣም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማቋቋሚያ ቻርተር ላይ የተወሰኑ ነጥቦች ላይ እልባት ለመስጠት የተሞከረ አለ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን፣ ረቂቅ አዋጅ ለፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመፅደቅ ሒደቱ ከቆመው ውጭ ሌላ ሙከራ የለም፡፡ 

አዲስ አበባ እንደ ዋሽንግተን ዲሲና እንደ ካንቤራ የአሜሪካና የአውስትራሊያ የፌዴራል መንግሥት መሬት አይደለችም ብለናል፡፡ የዚህን ዓረፍተ ነገር እውነታነት የሚፈታተን ሀቅነቱን የሚሸረሽር ማስረጃዎች ግን አሉ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ መሬት አይደለም እንዳንል፣ በወንጀልም ይሁን በፍትሐ ብሔር ጉዳይ፣ አዲስ አበባ የግዛት ክልል ውስጥ የተፈጸመ ወይም የተከናወነ ለፌዴራል መንግሥቱ እንደ ዋሽንግተን ዲሲ ይዞታው ያደረገው ይመስል የመዳኘት ሥልጣኑን (Local Jurisdiction) ለፌዴራል መንግሥቱ ይሆን ዘንድ በሕግ ተለይቶ ተሰጥቷል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት አዲስ አበባንና ድሬዳዋን የራሱ መሬት አድርጓቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ሕገ መንግሥቱ ስለሰጠው፣ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጸሙ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችም የመዳኘት ሥልጣንም እንዳለው ከመረዳት ባነሰ ሕግ የማውጣትና የማስፈጸም ብቻ ነው ተብሎ የሚቀነስ አይመስልም፡፡

ይሁን እንጂ ዳኝነትን በሚመለከተ፣ አዲስ አበባ እንደ ዋሽንግተን ዲሲ የፌዴራሉ መንግሥት የሆነች ይመስላል፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተተወለት ከተማ ነክ (ከከተማ አስተዳደርና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመዳኘት ሥልጣን ነው፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ (ድሬዳዋንም ጨምሮ) የፌዴራል መንግሥቱ ግዛት ነው ማለት ይችላል፡፡ ስለ ዳኝነት ሲሆን መሬቱ፣ የፌዴራሉ መንግሥት፣ ስለሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲሆን የከተማ መስተዳድሮቹ ሆኗል፡፡ እነዚህ በሕግ ልዩ ከሚያደርጓት ውስጥ በጣት የሚቆጠሩትን ብቻ በመንቀስ የቀረቡ ናቸው፡፡ ከልማድ ወደሚነሱት እንመለስ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብቷ በሕገ መንግሥቱ የታወቀ ቢሆንም የታፈረ ግን አይደለም፡፡ “መታፈር በከንፈር” እንዲሉ መታፈር በሕገ መንግሥት ግን አልሆነም፡፡ አዲስ አበባን አራት የክልል ፓርቲዎች ተወጣጥተው የመሠረቱት ኢሕአዴግ ነው የሚያስተዳራት፡፡ የራሷ ፓርቲ የላትም፡፡ ትግራይ ክልል ሕወሓት፣ አማራ ክልል አዴፓ፣ ኦሮሚያ ኦዴፓና ደቡብ ደኢሕዴን ይወዳደራሉ፡፡ ክልሎቹ ላይ ኢሕአዴግ በአባል ድርጅቶቹ ስም ይወዳደራል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ግን ኢሕአዴግ እንደ ግንባር ይወዳደራል፡፡ ሁለት ዓይነት መንገድ መከተሉ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን መሠረቱ ያደረገ የኢሕአዴግ አጋር ድርጅትም የለም፡፡ ኢሕአዴግም ከየክልሎቹ አባላቱን በማምጣት አዲስ አበባን ማስተዳደሩን ቀጥሎበታል፡፡ ይኽ ሒደት ሁለት መሠረታዊ ጉድለቶች አሉበት፡፡ አንዱ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ራሳቸውን የማስተዳደር መብታቸውን የሚጋፋ መሆኑ ነው፡፡ በምርጫ ለመወዳደር ከሆነ፣ ነዋሪ ለመባል ቢያንስ ሁለት ዓመት መኖርን፣ ለመምረጥ ከሆነ ስድስት ወራት መኖርን “ነዋሪ” ለማለት በመሥፈርትነት እንደሚወሰድ  የምርጫ ሕጉ ላይ ሰፍሯል፡፡ ሁለት ዓመት በኖሩበት ቦታ የምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ ይቻላል፡፡ ለቀበሌ፣ ለወረዳ፣ ለክፍለ ከተማ፣ ለክልል ወይም ከፌዴራል ምክር ቤቶች፡፡ ሁለተኛው፣ አንድ ሰው የአንድ አካባቢ ነዋሪ (Resident) ነው ለመባል መለኪያው በቋሚነት ለመኖር ሐሳብ እስካለው ድረስ፣ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ  175 (2) ላይ እንደተገለጸው፣ መኖር ከጀመረበት ቀን ጀምሮ ነዋሪ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ በቋሚነት የመኖር ፍላጎት ይኑረውም አይኑረውም፣ መኖር ከጀመረ ሦስት ወራት ከሞላው ነዋሪ እንደሆነ ይኼው የፍትሐ ብሔር ሕግ ከላይ የተገለጸው አንቀጽ ይናገራል፡፡  በመሆኑም፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሲባል በቋሚነት አዲስ አበባ ለመኖር አስበው እየኖሩ ያሉና መኖር ከጀመሩ ሦስት ወራት የሞላቸውን ሁሉ ያካትታል፡፡

ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ፣ የምክር ቤት አባል መሆንን በመሥፈርትነት ለማይጠይቁ የሹመት ቦታዎች ከየክልሎቹ በማምጣት አስተዳዳሪ እያደረገ የመሄድ ልማዱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ከሹመት ቦታዎችም አልፎ የከተማውን ፖሊሶችም ጭምር ከእነዚህ አራት ክልሎች ነው የሚመለምለው፡፡ ይኼ የከተማው ነዋሪዎችን ራስን የማስተዳደር መብት የጠበቀ አካሄድ አይደለም፡፡ ሁለተኛው ጉድለት፣ አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ብቻ ከሚያስተዳድሯቸው ክልሎች የሚመጡ ወይም ከአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ እነዚሁ የአራቱ ፓርቲ አባላት ብቻ አዲስ አበባን ማስተዳደራቸው ቀሪዎቹን አምስቱን ክልሎች የሚገፋና የሚያገል ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ አባላት ማለትም ሁሉም ክልሎችን ፍትሐዊ በሆነ አሠራር የሚያካትት መስመር አልተመረጠም፡፡

በመሆኑም ከአራቱ ክልሎችና ፓርቲዎች ብቻ አዲስ አበባን ማስተዳደር የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ራስን የማስተዳደር መብት ከመጋፋቱ ባለፈም አምስቱን ክልሎች ባይታዋር ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ከክልሎች በሚመጡና በአራቱ የክልል ፓርቲዎች እየተመራ መቀጠሉ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅምና ፍላጎት ማስከበርንም ማስጠበቅንም ቅድሚያ አለመስጠት ስለሚያስከትል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ተግባራዊ በሆነው የአስተዳደር ሥርዓት፣ ከፖለቲካውም አዲስ አበባ ላይ ከሚኖር የመወሰን ችሎታና ዕድልም የሚያገል ስለሆነ ፖለቲካዊ ባይተዋርነትን ያመጣል፡፡ ይኼ ደግሞ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 49 እና አንቀጽ 89 ጋር የሚስማማ አይደለም፡፡ እንደውም ይጣረሳል ማለት ይቻላል፡፡

ከላይ በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ሰሞኑን ሕዝባዊ አጀንዳ ከሆኑት የአዲስ አበባን የሚመለከቱ መወያያዎች መካከል አንኳሩ የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጉዳይ ነው፡፡ ከፖለቲካዊ ተዋጽኦ በሦስት ጎራ የሚመደቡ ምላሾችን የያዙ ቡድኖችን እናስተውላለን፡፡ ከጀርባው “አዲስ አበባ የማናት?” የሚለውን ጥያቄ ታሳቢ ያደረጉ ምላሾች ናቸው፡፡ አንደኛው፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ፣ ሁለተኛው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ በሦስተኛነት ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሉ ምላሾች ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ ሕጋዊ አንድምታና ትርጓሜውን የተመለከተ ስለሆነ ትኩረታችን ሕጉ ላይ ነው፡፡ “አዲስ አበባ የማናት?” የሚለው ጥያቄ ከሕግ አንፃር ሲታይ እንዲሁም ባለቤት ናቸው የተባሉት ሦስትዮሻዊ ወገኖች በእርግጥስ ባለቤት ናቸውን? ሊሆኑስ ይችላሉን? የሚለውን እንመለከት፡፡

አዲስ አበባ የማናት?” የሚለው ጥያቄ ከሕግ አንፃር ሲታይ ባለቤት የሌላት ንብረት ሆኗ ባለቤት እየተፈለገላት ወይም ባለቤቷን ለማጣራት የቀረበ ጥያቄ (ጭብጥ) ይመስላል፡፡ ጥያቄው የሚቀዳው ከሕገ መንግሥቱ ከራሱ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ እንዲነሳም ይገፋፋል፤ ያነሳሳልም፡፡ ምክንያቱም፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ ኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር እንጂ በነጠላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለችም፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተናጠልም ይሁን የተወሰኑት በጋራ ሆነው ክልሎች አሏቸው፡፡ ነባርና ባለቤት የሆኑባቸው ክልሎችን አቋቁመዋል፡፡ ለኩናማ፣ ለኢሮብና ለትግራይ አንድ ክልል አላቸው፡፡ ለአማራ፣ ለአዊ፣ ኽምራና ለቅማንት አንድ ክልል አላቸው፡፡ ደቡብ ላይ (በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ያላቸው) 56 ብሔረሰቦች አሉ፡፡ ሶማሌ ክልል ላይ የሶማሌ ሕዝብ አለ፡፡ ሌሎቹም ክልሎች ላይ እንዲሁ እያለ ይቀጥላል፡፡ እነዚህ ብሔሮች በክልላቸው ውስጥ ነባርና ባለቤት በመሆን ሌሎች ብሔሮችን (ለምሳሌ በሶማሌ ክልል ሶማሌ ያልሆኑት) እኩል ፖለቲካዊ መብት የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያዊ ዜግነት መብት (ለምሳሌ ንብረት የማፍራት) ነው ያላቸው፡፡ እየሆነ ያለውም ይኼ ነው፡፡

በእርግጥ ይህ ንብረት የማፍራትና በመረጡት የአገሪቱ ክልል ውስጥ የመኖር መብትም ቢሆን ማፈናቀል የተለመደ ዜና ስለሆነም እሱም በአግባቡ እየተከበረ አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት የአገሪቱ መሬት (መልከዓ ምድር) በብሔሮች ተከፋፍሎ ባለቤት ሊባሉ በሚችሉበት ደረጃ ይዘውታል፡፡ በዚህ አካሄድ ጋር የማይስማማ፣ ለአንድ ወይም ከእዚያ በላይ ለሆነ ብሔር ተለይታ በሕገ መንግሥት ያልተካለለችው (መሬቱም የዚህ ብሔር ነው ያልተባለው) አዲስ አበባ ብቻ ናት፡፡ ድሬዳዋም ብትሆን ከአዲስ አበባ በተለየ ሁኔታ በማቋቋሚያ ቻርተሩ ላይ ባለቤት ተሰጥቷታል፡፡ እንግዲህ፣ ሁሉንም የአገሪቱን መልከዓ ምድር ብሔሮች ሲከፋፈሉት የብሔር ባለቤትነት በሕገ መንግሥቱ ያልተሰጣት ቦታ (መልከዓ ምድር/ግዛት) አዲስ አበባ ስለሆነች የብሔር ባለቤት ፍለጋ ነው አዲስ አበባ የማናት? የሚለው ጥያቄ፡፡ አዲስ አበባ እንደ ክልሎቹ ሁሉ ወይም እንደ ድሬዳዋ የአንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ብሔሮች ከሆነች አስተዳደሩም ሌሎቹም ጉዳዮች ከክልል የአስተዳደር ሥርዓት ጋር ተመሳሳይ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከእነዚህ ብሔሮች ውጭ የሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሶማሌ ክልል እንደሚኖር ኦሮሞ፣ ጋምቤላ ክልል እንደሚኖር አማራ ዓይነት መብት ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ “አዲስ አበባ የማናት?” ለሚለው ጥያቄ ምላሹ የሆነን ብሔር ባለቤት የሚያደርግ ከሆነ ባለቤትነት የሚያስከትለው፣ አሁን ባለውና በተዘወተረው ልማድ፣ ከላይ የተገለጸውን ይሆናል፡፡ ስለሆነም፣ የማናት የሚለው ጥያቄ መምጣቱ ሕገ መንግሥቱ ከቆመበት ተሳቢዎች ሲውል ሲያድር የመነጨ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጥያቄው አዲስ አበባን እንደ ክልሎቹ፣ የአንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ብሔሮች ናት የሚል ምላሽን ካስገኘም ባለቤት ለሚሆነው ብሔር በክልል ላይ የሚገኙ መብትና ሥልጣንን ያህል ያስገኛል፡፡

 ከላይ ከተመለከትነው አንፃር፣ ባለቤትነት በንብረት ሕግ ላይ ከሚታወቀው ጽንሰ ሐሳብ የተለየ ይዘት አለው ማለት ነው፡፡ በንብረት ሕግ አንድ ሰው የአንድ ነገር ባለቤት ከሆነ ንብረቱን በሚመለከት ራሱን ንብረቱን ወይም የንብረቱን ፍሬ የመጠቀም አለበለዚያም የማስተላለፍም የማሰወገድንም መብት ይጨምራል፡፡ ከዚህ አንፃር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ በመረጠው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርቶ ንብረት የማፍራት መብት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ስለተሰጠ የክልሉን መሬት (መልከዓ ምድራዊ ግዛት) ለተወሰኑ ብሔሮች ብቻ የባለቤትነት መብት አላቸው ማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ይህ ዓይነቱ የባለቤትነት ስሜትና ሥልጣን ለወትሮው ከሚታወቀው የንብረት ሕግ ጽንሰ ሐሳብ ይለያል፡፡ ሌላም የሚለይበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኼውም የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሬት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት ነው፡፡

የራስን ዕድል በራስ መወሰን በሚነሳበት ጊዜ መቼም ሊታለፍ ከማይችለው ቁምነገር አንዱ የመሬት ነገር ነው፡፡ መሬት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካም ጭምር ነው፡፡ ከማንነትም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ የቡድን ማንነትን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በተለይም ራስን በራስ ለማስተዳደር፣ የታወቀ ድንበር ያለው ግዛት መኖር ጠቃሚ ነው፡፡ ግዛት ደግሞ ያለመሬት የለም፡፡ በኢትዮጵያ የመሬት ነገር ዋና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዳወሪያና ማጠንጠኛ ሆኖ መቀጠሉ አልቆመም፤ ምናልባትም ለረዥም ጊዜ ሊቀጥልም ይችላል፡፡ መሬት ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነትና ሉዓላዊነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለውም የታወቀ ነው፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40(3) የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተ መንግሥት፣ ሕዝብ እንዲሁም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው ይላል፡፡  በአንቀጽ 89 (5) ደግሞ የማስተዳደርን ሥልጣን፣ ሕዝብን በመወከል፣ የመንግሥት ሆኗል፡፡ በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51(5) ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የመሬትን አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮችና የሚወክላቸው ሌሎች ተቋማት (ለምሳሌ የሚኒስትሮች ምክር ቤትና ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች) መሬትን የሚመለከቱ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህን ሥልጣን ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(1)(ሀ) ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል፡፡

የፌዴራሉ መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎች በምን ዓይነት ሁኔታ በክልሎች ዘንድ ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ መመርያ ባያስቀምጥም ስለመሬትና የተፈጥሮ ሀብት ከሌላው በተለየ መልኩ እንዴት መፈጸም እንዳለባቸው የክልሎችን ሥልጣን በሚዘረዝርበት  አንቀጽ 52 ንዑስ ቁጥር 2 ፊደል ‘መ’  ላይ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡ “የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሠረት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራል፤” ይላል፡፡ በመሆኑም፣ የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ ያወጣል፤ ክልሎች ይህንን ሕግ መሠረት በማድረግ ወይም በመጠቀም መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራሉ ማለት ነው፡፡

በመሆኑም የአንድ ክልል ግዛት (መሬት) ምንም እንኳን አስተዳዳሪው ክልሉ ቢሆንም፣ እንዲሁም የፌዴራሉን የመሬት ሕግ በመከተል ተጨማሪ ሕግ በማውጣት የማስተዳደር ሥልጣን ቢሰጣቸውም የመሬቱ ባለቤት የክልልነት መብት ያገኙት ብሔሮች ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ አብረው እስካሉ ድረስ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት ነው፡፡ ሕግ የሚያወጣውም የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ ከመሬት አንፃር በመነሳት አንድን አካባቢ የአንድ ወይም ከእዚያ በላይ የሆኑ ብሔሮች ነው እንዳይባል ሕገ መንግሥቱ የሁሉም ብሔሮች አድርጎታል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የተለያዩ የፖለቲካና የሲቪል መብቶችን እንዲሁም የብሔርን የቡድን መብት ተግባራዊ ለማድረግ ተስማማሚ በሚሆን መንገድና ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46 ላይ ባሉት መሥፈርቶች መሠረት ክልሎች እንዲካለሉ ተወስኗል፡፡ ከማንነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸውን መብቶች ሥራ ላይ ለማዋል እንዲቻል በሚመች መልኩ የአከላለል ሒደቶች እንዲከናወኑ ነው ሕገ መንግሥቱ ታሳቢ ያደረገው፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ የማናት ሲባል ከማንነት ጋር የተያያዙ መብቶችን በተናጣል አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ብሔሮች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያመችም የሚያስገድድም ሁኔታ የለም፡፡ “አዲስ አበባ የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናት” የሚለውን አካሄድ ብንከተል፣ አስተዳደሩም ሁሉም ከ80 በላይ የሆኑት ብሔሮች በጋራ በሚፈጥሩት የአስተዳደር ቀመር መሠረት ተወጣጥተው ወደሚሠሩበት ዘዴ ይወስደናል ማለት ነው፡፡ ስንት አማራ፣ ስንት ኦሮሞ፣ ስንት ማኦና ስንት ኩናማ ወዘተ. አዲስ አበባ አስተዳደር የሚለው ጉዳይ ላይ (ከመጨረሻው ዝቅተኛ መዋቅር እስከ ከፍተኛው ድረስ ሊዘልቅ በሚችል) መሳተፍና መወከል እንዳለበት ተወስኖ (ስምምነት ላይ ተደርሶ) የሚተገበር አሠራር ይሆናል ማለት ነው፡፡ “አዲስ አበባ የማናት?” ለሚለው ምላሹ “የነዋሪዎቿ” የሚል ከሆነ መሥፈርቱ ነዋሪ መሆን ብቻ እንጂ ሌላ አይሆንም፡፡ የብሔር ማንነት ከግምት ሳይገባ ነዋሪነት በቂ ነው፡፡ ነዋሪነትን የብሔር መዋጮን (ኮታ) መነሻ አያደርግም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት ጋር በተገናኘ አንዱ የብዥታው ምንጭ ያልጠራ የፌዴራል ዋና ከተማ ሕግ፣ ልማድና ሥርዓት ነው፡፡ ከሕግም ከልማድም የሚመነጩ ከሌሎች የፌዴራል ሥርዓትን ከሚከተሉ አገሮች የዋና ከተማ አስተዳደር ዘዬ የተለዩ የተዛነቁ ጉዳዮችን ዓይተናል፡፡  በፌዴራል ሥርዓት ርዕሰ ከተማ ወይም ዋና ከተማዎች እንዴት ይተዳደራሉ? ከላይ እንዳየነው የተለያዩ ዓይነት ፈለጎች አሉ፡፡ እያንዳንዱ የፌዴራል ሥርዓት ዋና ከተማውን በሚመለከት ነባራዊ ሁኔታቸውን መነሻ ያደረገ መጠነኛ ልዮነቶች ቢኖሩም በጥቅሉ ግን ሦስት ዓይነት አካሄዶችን ይከተላሉ፡፡

አንደኛው ዋና ከተማው ከክልል ጋር በአቻነት በማቋቋም እኩል ሥልጣን እንዲኖረው በማድረግ ነው፡፡ ሞስኮ፣ በርሊን፣ ቪየናና ብራሰልስ በዚህ መልኩ የተቋቋሙ በመሆናቸው ለፌዴራሉ መንግሥት ተጠሪነት የለባቸውም፡፡ በሽግግር ወቅቱ ጊዜ አዲስ አበባም ክልል 14 ተብላ የክልልነት ደረጃ ነበራት፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ሆኖ የሚቋቋምበት ሥርዓት ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት የሚያስተዳድረው መሬት ወይም ግዛት የለም፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲውዘርላንድና ካናዳ ይኼንን ዓይነት አካሄድ መርጠዋል፡፡ ሦስተኛው በፌዴራሉ መንግሥት ሥር የሚገኝ  ከተማና ለዚህም የሚሆን የተለየ ግዛት በመከለል የሚቋቋሙ ከተሞች ናቸው፡፡ የከተሞቹም ተጠሪነት ለፌዴራሉ መንግሥት ይሆናል፡፡ በርካታ አገሮች ዋና ከተሞቻቸውን በዚህ መንገድ ነው ያቋቋሙት፡፡ አዲስ አበባም ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ክልልነቷ ቀርቶ በከፊል ወደ ፌዴራል ከተማ (Federal District) ዝቅ ብላለች፡፡ ይሁን እንጂ ከፌዴራል ወረዳነት (ከተማነት) በተለየ መልኩ የከተማው ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የመሳተፍ መብትም ጥበቃ ተደርጎለታል፡፡

አዲስ አበባ እንደ ፌዴራል መንግሥቱ ርዕሰ ከተማነቷና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መቀመጫነትንም ደርባ እንደመያዟ መጠን ዝርዝር ሕግ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ሀቅ ነው፡፡ ሕግጋቱም ሳይጡ በዋናነት በገዥው ፓርቲ ውሳኔ ላይ የተንጠላጠሉ አሠራሮችን በመከተል የፌዴራሉ የከተማዋና የክልሉ ግንኙነት ቀጠለ፡፡ ፓርቲው ላይ የተንጠለጠለው አካሄድ አመኔታ ሲያንሰው ተፃራሪ ፍላጎቶችን መልክና ቅርፅ ለማስያዝ ፈታኝ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡  እንግዲህ፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተገባው ቃል እስካሁን ተግባራዊ ሆኖ ሕግ ባለመውጣቱ ፍላጎቶች እያደጉና እየጠነከሩ ሄዱ፡፡ ሄደው. . . ሄደው “አዲስ አበባ የማናት?” የሚለውንም ሳይቀር አመጡ፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...