Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከመጣንበት ይልቅ አብረን የምንጓዝበት መብለጡን ነጋሪ ያስፈልገናል ወይ?

ከመጣንበት ይልቅ አብረን የምንጓዝበት መብለጡን ነጋሪ ያስፈልገናል ወይ?

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ከፍተኛ የሕዝብ የለውጥ ፍላጎት፣ ቀላል የማይባልም ለውጥ ታይተዋል፡፡ በዚህ ሒደትም የፍላጎት ግጭቶችና የፖለቲካ ውዝግቦች በማጋጠማቸው ዜጎች ለሰላም ዕጦት ተጋልጠዋል፡፡ የብሔሮች ግጭትና የሕዝቦች መፈናቀል፣ የባለሀብቶች መጎዳትና የልማት መስተጓጎልም እንደቀጠለ ነው፡፡

በዚህ ላይ የፖለቲካ ምኅዳሩና የዴሞክራሲው መስተጋብር አመርቂ ለውጥ ቢያሳይም አሁንም የጥላቻ ንግግር፣ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ውዝግብና አሉባልታ የአብሮነታችን እንቅፋት መሆናቸው አልቀረም፡፡

ይኼን ተከትሎም ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ድረ ገጽ አጠቃቀም ዙሪያ ጠበቅ ያለ መመርያ መውጣት እንዳለበት፣ ዜጎችም ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የመጠቀም ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡ ከዚህም በላይ ግን የሃይማኖት አባቶች በቅርቡ ባካሄዱት ጉባዔ ባወጡት የአቋም መግለጫ ላይ የሰፈረች መሪ ቃል፣ የዛሬ ጽሑፌ ማጠንጠኛ ብትሆን መርጫለሁ፣ ‹‹ከመጣነው አብረን የምንጓዘው ይበልጣል!›› የብልህ ጥልቅ አባባል፡፡           

አገራችን ከነበረችበት ጥልቅ የጭቆናና የበደል ታሪኳ ተላቅቃ እነሆ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ መራመድ ከጀመረች ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ የሆነ ጊዜ አልተቆጠረም፡፡ ቢያንስ ጭፍኑና ጨካኙ፣ ወታደራዊ ሥርዓት በኃይል ከተወገደ በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዕድሜዋ ሦስት ሺሕም ተባለ፣ የአሁኑን ቅርጿን ከያዘች ወዲህ ያለው ብቻ ተቆጥሮ 150 ቢባል በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶችና ታሪኮችን ሰብስባ የያዘች ምድር ነች፡፡ በጂኦግራፊ አቀማማጧም ሆነ በተፈጥሮ ፀጋዋ ጠላት የበዛባት፣ በዚያው ልክም ሕዝቦቿ ለዘመናት ሉዓላዊነቷን በደምና በአጥንታቸው ያስከበሩላት የጀግንነት ምድር ናት፡፡

በዚያው ልክ ከማንም የላቀ ሀብት ኖሯት፣ ከማንም በታች ሆና በድህነትና በኋላ ቀርነት የኖረች፣ ከማንም ያላነሰ ታታሪና አገር ወዳድ ሕዝብ እያላት በድህነት ስትማቅቅ የዘለቀች አገርም ነች፡፡ መደማማጥና ሥልጡን የፖለቲካ ባህል ባለመገንባቱም፣ እርስ በርስ ሲፋጁ የነበሩ ትውልዶችም ያለፉባት ናት፡፡ የዚያ መዘዝ በዚያው የታሪክ ምዕራፋ ባለመቋጨቱም እስካሁኑ ትውልድ ውዝግቡና ተቃርኖው ዘልቆ ከትርምስ ለመላቀቅ አልተቻለም፡፡ ምንም ቢሆን ግን፣ ‹‹ከመጣነው አብረን የምንጓዘው ይበልጣል!” የሚለውን የብልህ አባቶች ጥልቅ ምክር ማሰብና መገንዘብ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡          

ኢትዮጵያ ሀብቷ እልፍ ነው፡፡ በከርሰ ምድር ውስጥ ያለውን ሀብት ትተን እንኳን በሕዝቦቿ መካከል ያለውንና ዓለምን የሚያስደምመውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርስ ወይም  የብዙኃነት ሀብት ብንመለከት፣ እንደ ኢትዮጵያ የታደለ አገር ማግኘት ሲበዛ ብርቅ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ይህ ሀብቷ ለዘመናት ውበቷና ጌጧ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ የጭቆናና የተዛባ ታሪክ ሰለባ በመሆናችንም እርስ በርስ ስንባላባት መቆየታችንም አይዘነጋም፡፡ አስከፊው እውነት አሁን እየገጠመን ያለው ደግም የጋራ ሀብቶቻችንን የጋራ ዕድላችንን ለመወሰን ተሳስበን ማድረግ ሲገባን፣ በክልልና በመንደር ታጥረን ወደ ቀውስ የምናመራ በመሆናችን ነው፡፡ ኧረ ጎበዝ? ቆም ብለን እናስብ የሚያስብለውም ለዚህ ነው፡፡

በእርግጥ ይህ የብሔር ውዝግብም ሆነ የጥላቻ ፖለቲካ ዛሬ ብቻ የመጣብን አይደለም፡፡ ይልቁንም ከጥንት በተለይም ከቅኝ ገዥዎች ሴራ በኋላ በላያችን ላይ እንደተነዛን የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ይህ የተዛባ የእርስ በርስ ግንኙነት መታረም በነበረበት ጊዜ ባለመታረሙ፣ መስተካከል በነበረበት አጋጣሚም ሳይስተካከል በመቅረቱ፣ የአገራችን ዕድገት እንደ ግመል ሽንት የኋልዮሽ ሲፈስ እንደኖረ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ ቢያንስ አሁን በዕርቅና አብሮነት ጉዞ ተደማምጦ ማስተካካል የሚገባው ይህን እውነት በሆነ ነበር፡፡

እንደ አንድ አገር ሕዝቦች ከተማ/ገጠር፣ ቆላ/ደጋ፣ ዳር/መሀል ሳይባል አንዳችን ለሌላችን እኩል ማስፈለጋችን ሳይገለጥልን፣ ወይም እንዲገለጥልን ሳንፈልግ ለዘመናት በመኖራችን መድረስ በነበርንበት ሥፍራ ላይ ሳንደርስ ኖረናል፡፡ ይኼ እንደ አገር ሊያንገበግበንና ሊያስቆጨን ሲገባ አሁንም ስለመለያያትና ውዝግብ ብሎም ስለግጭትና ትርምስ መስበክ እጅግ አሳፋሪና ኋላቀር አስተሳሳብ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን  የደረስንበትን ሁሉን አቀፍ ዕድገት ከማስቀጠልና ፍትሐዊነቱን አረጋጋጦ ከማስፋት ይልቅ፣ ወደኋላ እንደመመለስ ያለ ጭቃ ውስጥ መግባት ሊኮነን ይገባዋል፡፡  

በመሠረቱ ሁላችንም የዚህች አገር ዜጎች በተለይም የአዲሱ ትውልድ አባላት ‹‹ከመጣነው አብረን የምንጓዘው ይበልጣል!›› ማለት ይገባናል ስንል፣ በቅንነትና በመተሳሳብ ጎዶሏችንን ለመሙላት ነው፡፡ እውነት ለመናገር የደርግ ሥርዓት ወድቆ በዚች አገር ላይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሲጀምር፣ በሕዝብ ልጆች ደምና ላብ በተመሠረተ ተጋድሎ ነበር፡፡ በ1984 ዓ.ም. ሁሉንም የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ሕገ መንግሥት መቅረፅ ባይቻልም፣ ለበርካታ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዕውቅና የሰጠ ሰነድ እንደነበርም ሊካድ አይችልም፡፡ ያም ሆኖ ተገነባው ሥርዓትና የተቀረፀው ሕገ መንግሥት በአፈጻጸም ጭምር ተዳክሞ፣ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ መሠረት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ ለሚታዩ ትልልቅ ክፍተቶች በር ከፍቷል፡፡

ይህ ሥርዓትና ሕገ መንግሥት ለአሁኗም ብቻ ሳይሆን ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ዋስትና ሊሰጥ የሚችለው ግን፣ እንዳለፉት ጊዜያት ጭራሹን ጠፍቶ አዲስ በመጻፍ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዳግም ማሻሻል ሲቻል ነው፡፡ አፍሪካ የቅርብ ዓመታት የዴሞክራሲ ልምምድ አላት ስንል በተደጋጋሚ ጊዜ ሕገ መንግሥት ሊያሻሉ ይችላ እንጂ እያፈረሱ ሲገነቡ እንዳልነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም እኛም ከበረታንና ከተደማማጥን በዚህ ሕገ መንግሥት 24 ዓመታት አብረን መጓዝ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም እያሻሻልንና ጎዶሎዎችን እየሞላን ዕልፍ ዘመን ተያይዘን እንጓዝበታለን፡፡ ለዚህም ነው አብረን ከመጣነው ገና የምንጓዘው ይበልጣል ማለታችን፡፡

አሁን ላይ ለውጥ እየተጀመረ እንኳን በግልጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ገና ወደፊት አብረን የምንጓዘው ዘመን ይልቃል ሲባል ግን የምንጓዝበት መንገድ አልጋ በአልጋ ነው ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አሁንም ድረስ ለሕገ መንግሥታዊነትም ሆነ ለአገሪቱ ጉዞ አደጋ የሆኑ ችግሮች ገና መልክ መልክ አልያዙምና ነው፡፡ እነዚህ እንከኖች ከፅንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ከማኅበራዊ ድረ ገጽ የጥላቻ ዲስኮርስ መስፋፋት፣ የእኔ የእኔ ከማለትና የርቅ መንገድን ከመሳት ጋር ያላቸው ዝምድናን ለይቶ ለማረምም መረባረብ ያስፈልገናል፡፡ እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም፡፡

በእርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተፈቃቅደውና ተከባብረው በአንድ ላይ ለመኖር የጋራ ሰነድ ካፀደቁ 24 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ የጋራ ሰነድ የጋራ ቤት ለመገንባት ውል ያሰሩበት የጋራ ፍኖተ ካርታቸው፣ የቃል ኪዳንም ማሰሪያቸው ጭምር ቢሆንም በድንጋጌውም ሆነ በአፈጻጸሙ ምንም ችግር የሌለው ነበር ሊባል አይችልም፡፡ ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመሥርቶ መፈተሽም ያስፈልጋል፡፡

በቀዳሚነት የአስተዳዳር ወሰንና የክልል አስተዳዳርንን ከጎሳና ብሔር ጋር ብቻ ማቆራኘቱ የውድቀቱ መጀመርያ ነው፡፡ የአገሪቱን ዋና ከተማና የኦሮሚያ ክልልን ጉዳይ የያዘበት መንገድ፣ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ አጠቃቀም፣ የአንቀጽ 39 ጉዳይና መሰል ድንጋጌዎችም ዳግም መታየት ያለባቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን ያለው የለውጥ አመራር ያለው ቁርጠኝነት አጋዥ ስለሆነ፣ መላው የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡም በሆደ ሰፊነት በመጪው ዘመን በጋራ የምንኖርበትን ዘላቂ መንገድ አገናዝቦ መታገል ይጠበቅባቸዋል፡፡

አንዳንድ ምሁራን አሁን ያለው ሕገ መንግሥት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግብ ያለው ነው ይላሉ፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀኖና ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት በመሆኑ፣ አሳታፊና አቃፊ አይደለም በሚል የሚተቹትም ትንሽ አይደሉም፡፡ ምንም ተባለ ምን እንደታሰበው ወደ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መሄድ ያለበት ጉዞ በሚፈለገው ፍጥነት እየተተገበረ ካለመሆኑም ባሻገር፣ እንደ ሕዝብ ረዥም ርቀት አስተሳሳሮን እንዲቀጥልም መደረግ አለበት፡፡

በእርግጥ መንግሥትም ቀደም ካለው ጊዜ አንስቶ ለኢኮኖሚ አንድነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለፖለቲካ አንድነቱ አልተሰጠም ሲል ቆይቷል፡፡ ችግርን ማመን ወይም ችግሮችን መለየት የመፍትሔ ግማሽ አካል ነውና በስሜት ሳይሆን፣ በተጨባጩ መነጋጋርና ቁርጠኝነት ለዘለቄታው የሚጠቅም ሕገ መንግሥትን አሻሻሎ ለትውልድ ማስተላላፍ የለውጥ ሁሉ ቁልፉ ኃላፊነት ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ አብረን የምንሄደው ጉዞና ዘመን ይልቃልና ከወዲሁ መሠራት ያለበት ሁሉ በሁሉም ወገኖች ሊሠራ ይገባል፡፡

የማይካደው እውነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በልዩነት ውስጥ አንድነት የነበራቸው በኢፍትሐዊ አገዛዞችም ዘመን ጭምር ነበር፡፡ ድርብ ጭቆና ያለባቸው ወገኖች ቢኖሩም ያልተጨቆነ ሕዝብም እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡ ይሁንና እንደ ሕዝብ እርስ በርስ ካለመተዋወቅ፣ ካለመከባበርና ተቻችሎ ካለመኖር የተነሳ እኔ እበልጣለሁ በመባባልና ዝቅ ከፍ በመደራረግ ዘመናትን ገፍተዋል። ግጭት ውስጥ ገብተው ጥቃትም ተሰናዝረዋል። ቢያንስ ያን ምዕራፍ ከሞላ ጎደል ለሦስት አሥርት ዓመታት ተሻግረነው ሊያገረሽ አይገባም፡፡ እንዲያውም በመነጋጋርና በዴሞክራሲያዊነት እያረቅነው መሄድ ይጠበቅብናል፡፡

በተለያዩ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችና ጦማሪያን ስብከት ግን ወደ የተዛባ ግንኙነት ትርክትና የግጭት አዙሪት ለመግባት መንደርደር፣ ፍፁም ሊወገዝ የሚገባው ነው፡፡  አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው ከአካባቢያቸው መሰደድ፣ በማንነት መገለልና መሸማቀቅ ሊያሳዝነን የሚገባው ሁላችንንም ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ክስተት እየተባባሰ ከሄደ ለልማት ሊኖር የሚገባውን ተነሳሽነት ማወኩ አይቀሬ ነው፡፡ ድርቅና ረሃብም ይቀሰቀሳል፡፡ የአገር ገጽታ ከመበላሸቱ ባሻገር ወደ ተሻለ የአገር ግንባታ ምዕራፍ የሚደረገው ጉዞም ይስተጓጎላል።

በመሠረቱ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱም ቢሆን ከፍፁም አዳዊነት ተላቆ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ብዙ ትግልና መስዋዕትነት ተከፍሎበታል። ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ፣ እርስ በርሳቸው ከመተዋወቅም አልፈው ለጋራ አገራቸው ልማት በኅብረት ለመሥራትና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ለመሆን እንዲነሳሱ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አስተዋፅኦ አልዳረገም ሊባልም አይችልም፡፡

አሁን በተደረሰበት የታሪክ ምዕራፍ ግን የሁሉም ሕዝቦች ዓላማ በአንድ አገር ተባብሮና በእኩልነትና በፍትሐዊነት መኖር እንዲሆን መሥራት ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጠባብ ብሔርተኝነትና ለእኔ ብቻ ከማለት በመውጣት በመተሳሳብና በጋራ መኖር ይጠበቅብናል።

ፖለቲከኞች ወደ ራሳቸው ፍላጎት እየጠመዘዙት እንጂ ከዚህ በኋላ አሀዳዊነትም ሆነ ጨፍላቂነት አብቅቶላቸዋል፡፡ ማንም ያለ ፍላጎቱ ተገዶ አንድ ቀን መቀጠል አይፈልግም፡፡ የኃይል ሚዛን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ይህ አስተሳሳብ የሁሉም ሕዝቦች ሆኗል፡፡ ዛሬም ሆነ ወደፊት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍላጎት ሥርዓቱ ለአንዱ ሰጥቶ ሌላውን የሚከለክል ሳይሆን፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ እንዲሆን ነው የሚባለውም ከዚሁ እውነታ አንፃር ነው።

እናም ይህን ፍላጎታቸውንና እምነታቸውን ማክበርና ማስከበር መንግሥትና የመንግሥት ኃላፊዎች በትኩረት የሚከታተሉትና የሚሠሩበት ሊሆን ይገባል። በተለይ የፖለቲካ መሪዎችና ድርጅቶች በዚህ ላይ ተመሥረተው አብሮነትን፣ ዕድገትንና ብልፅግናን ለማረጋጋጥ የሚረዱ መንገዶችን መጥረግ ነው የሚበጃቸው፡፡

የለውጡ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ደጋግመው እንደተናገሩትም ሆነ እንዳሳሰቡት፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎች አሁን ያለውን ፌዴራላዊ ሥርዓትና ውጤቶቹን ማጣጣል ሳይሆን ተጋግዞ ለመሥራት፣ የተዛነፈ ካለም ለማረም ተቀራርቦ መነጋጋር ያስፈልጋቸዋል። መንግሥትም ለዚህ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። ስለዚህ እንደ ፖለቲከኛ፣ እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ መንግሥት የቆምንበትን መሠረት ፈትሾ ለዘላቂ ጥቅምና ነገ ትውልድ ስለሚኖርባት የጋራ አገር አስቦ መሥራት ያስፈልገናል፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ልጆቿን በጉያዋ አቅፋ እንደያዘች የህዳሴ ጉዞዋን ትቀጥላለች እንጂ፣ ወደ ቀድሞዋ አስከፊ ሁኔታ መመለስ ፈፅሞ አትፈልግም፡፡ ከዚያ ለመውጣትም በተለያዩ ጊዜያትና ሥፍራዎች ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ጥገኛና አፍራሽ ኃይሎች ውዥንብር ከመንዛት ባይወጡም፣ ልጆቿ ተቻችለውና ተከባብረው ለመኖርም በቃል ኪዳን ተሳስረዋል፡፡ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በጋራ በሚገነቧት አገር በጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተማምነውና ተሳሳበው እንዲዘልቁ ማድረግ ግን፣ የመንግሥትና የዚህ ትውልድ ቀዳሚ ኃላፊነት ነው፣ መሆንም ይኖርበታል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ብርሃን ፈንጥቋል፡፡ ልጆቿ ከድቅድቅ ጭለማ ወጥተው የብርሃን፣ የዕድገትና የብልፅግና ጎዳናውን እየዘለቁት ይገኛሉ። ነገር ግን በደንብ ሳይነጋ ማጨለምን የሚያልሙ ኃይሎች ከፊታቸው ተደቅኗል። ሳይነጋ ጨለማ በህልም እንጂ በዕውን ሊሆን እንደማይችል ያልተረዱት እነዚህ ኃይሎች የብርሃኑ ጭላንጭል ደማቅና ብሩህ ሳይሆን በጅምር ሊያስቀሩት ይደክማሉ። አሁንም በመንደር አስተሳሳብና በጥቃቅን የሠፈር አጀንዳዎች ጦር ሊያማዝዙን ይሻሉ፡፡ እነዚህን ማሳፈርና ማስቆም ብሎም ትልቁን አገራዊ ኅብረትና አብሮነት ማማተር ያለብንም እኛውና እኛው ብቻ ነን፡፡ በዚህ ላይ መንግሥትም ቆፍጣና አቋም ይዞ ሕግን ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡

ኢትዮጵያዊያን እስኪሻሻልም ሆነ እስኪቀየር አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ገዥ መመርያቸው መሆኑን ሊጠራጠሩ አይገባም፡፡ ስለሆነም ዋነኛ መመርያቸውን ማክበርና ማስከበርን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች የተስተዋሉ ውዝግቦችንና ሕገወጥነቶችንም ሆነ ሌሎች ዳር የወጡና የተወለካከፉ አስተሳሰቦችን  እንደማይቀበሉ፣ ለአገራቸውና ለጋራ ሕገ መንግሥታቸው ታማኝና ዘብ በመሆን ማረጋጋጥ አለባቸው፡፡ ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች በግልም ሆነ እንደ ቡድን  እኩልነታቸውን፣ አንድነታቸውንና በጋራ ለልማትና ለዕድገት መቆማቸውን ማረጋገጥ የሚችሉት በዚሁ መንገድ ብቻ ነውና፡፡ ‹‹ከመጣነው አብረን የምንጓዘው ይበልጣል!››  የሚለውን የአባቶችን ምጡቅ ሐሳብ አክብረን ልንፈጽም የምንችለውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...