Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሕዝብ ጥያቄ ባልሆነ ጉዳይ ካልተጠነቀቅን ጠንቁ ለአገር ሊተርፍ ይችላል››

አቶ ክቡር ገና፣ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የቀድሞ ፕሬዚዳንት

አቶ ክቡር ገና የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መጣጥፎችን በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ አዲስ አበባን በተመለከተ በሚያንፀባርቋቸው ምልከታዎችም እንዲሁ ይታወቃሉ፡፡ አሁን አዲስ አበባን ባጋጠማት የባለቤትነት ጥያቄ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአንድ ዓመት ቆይታና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ አንድ ዓመት ሆናቸው፡፡ የዛሬ ዓመት እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ አገሪቱ  ከነበረችበት የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ምን ተሰማዎት? ከዓመት በኋላ ደግሞ ያኔ የተሰማዎትን ስሜት ሲገመግሙት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ክቡር፡- ዓመት እንዲህ የሚሮጥ አይመስለኝም ነበር፡፡ ግን የማስታውሰው ከዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ለውጥ ቢደረግም፣ በዚህ ዓይነት ፍጥነት ይደረጋል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ ዋና ዋናዎቹን ስንመለከት መሠረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ነፃነት ማግኘት፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመጻፍና የመሳሰሉት መብቶች ተገኝተዋል፡፡ በትልቁ የአንድ አገር የወደፊት ዕድል የሚለወጠው እንዲህ ዓይነት ሥርዓት ሲቀመጥ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ላይ ደግሞ ሁሉም ኃላፊነት አለበት፡፡ ከኤርትራ ጋር የተደረገው መቀራረብም የተጠበቀ አልነበረም፡፡ የሚያስፈልግም ነው፡፡ ደግሞ አብሮ በኖረ ሕዝብ መሀል እንዲህ ለረዥም ጊዜ አለመነጋገርና የፖለቲካ መፍትሔ እንኳን ለመፈለግ አለመሞከር፣ በጣም የሚያስፈራና የሚያስቸግር የፖለቲካ አመራር ውስጥ ነበርን ማለት እንችላለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለእኔ ሌሎቹ እንደተጠበቁ ሆነው ዋና የሚመስሉኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጓቸው የተለያዩ ስብሰባዎችም ሆነ ውይይቶች፣ ሕዝብን አንድ ለማድረግ መቻላቸው ራሱ ቀላል ነገር አለመሆኑን ነው፡፡ ሌሎች ሊገለጹ የሚችሉ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ብዙዎቹ ግን በአብዛኛው ሕዝቡ የደገፋቸው ለውጦች ናቸው የመጡት፡፡ ከለውጦች ጋር ደግሞ አስቸጋሪ የሚሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ጊዜው እየረዘመ በሄደ ቁጥር እነዚህ ችግሮች መፍትሔ የሚፈልጉ ዓይነት ናቸው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ቶሎ መፍትሔ የሚፈልግ ዓይነት ቢሆንም፡፡ በአጠቃላይ ስንመለከተው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ዓመት ውስጥ ያደረጉት ለውጥ የኢትዮጵያን ገጽታ የለወጠ ይመስለኛል፡፡ አሁን ደግሞ ዋና ዋና ሥራዎች ይጠብቋቸዋል፡፡ በተለይ በሚቀጥለው ዓመት፡፡  

ሪፖርተር፡- እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ አገሪቱ ከነበረችበት የፖለቲካ ውጥረትና አለመረጋጋት አንፃር፣ በርካቶች ሰላምና መረጋጋት እንደሚመለስ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ይህም ለጥቂት ወራት ከዘለቀ በኋላ ግን የቦ ፍርድ፣ መፈናቀል፣ እንዲሁም የንፁኃን ዜጎች ሞት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መስተዋል በኅብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ ጥያቄዎችን ከማጫሩ በተጨማሪ የሥጋት ምንጭ ሆኗል፡፡ ከዚህ አንፃር በአገሪቱ የተስዋሉት ችግሮች በነበረው ተስፋ ላይ ጥላቸውን አሳርፈውበታል ብለው ያምናሉ?

አቶ ክቡር፡- በመሠረቱ የአቅም ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ መንግሥት ጠንካራ የሆነበት ሥፍራ ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር በመጠኑም ቢሆን በቁጥጥር ሥር የሚውል ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የምናወራው ስለትልቅ አገር ነው፡፡ ትልቅ ስንል በጆኦግራፊያዊ አቀማመጡና ብዙ ሕዝብ የሚኖርበት አገር ከማለት አንፃር ነው፡፡ የመንግሥት ኃይል ውስን ነው፡፡ ይህን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ምክንያት ሁሉም ቦታ ፖሊሱ፣ መከላከያው፣ ደኅንነቱ ፈጥኖ የመድረስ አቅሙ በጣም ውስን ነው፡፡ ስለዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች መከሰታቸው ለብዙዎች አስገራሚ ሆኖ ቢገኝም፣ እነዚህ አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮች በአብዛኛው በእኔ አረዳድ የፖለቲካና የደኅንነት ችግር ውጤቶች ናቸው፡፡ የደኅንነቱን ችግር በደኅንነት መፍታት የሚፈለግበትን ሁኔታ እንደገና ማስተካከል አለባቸው፡፡ የፖለቲካውም በዚያው መንገድ፡፡ ዝም የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዝም ከተባለ ችግሩ እየባሰ ነው የሚሄደው፡፡ ይኼ ሁሉ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቅ ነው የሚያሳው፡፡ ሥራው ግን ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ የሕዝቡም ተሳትፎ በግድ ያስፈልጋል፡፡ እንደሚመስለኝ በአብዛኛው የእኛ ችግር ሁሉን ነገር ከመንግሥት የመጠበቅ ፍላጎት ነው፡፡ ሕዝቡ ተሰባስቦና ተባብሮ ማቆም የሚችለውን ራሱ በራሱ ማቆም መቻል አለበት፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቃን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን መያዝ ተከትሎ በተደጋጋሚ የፍኖተ ካርታ (Road Map) አስፈላጊነትን በመጥቀስ፣ መንግሥት ያዘጋጀው ፍኖ ካርታ ይፋ እንዲደረግ ይጠይቃሉ፡፡ ፍኖተ ካርታውን በተመለከተ የእርስዎ አተያይ ምንድነው?

አቶ ክቡር፡- የፍኖተ ካርታ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያበሳጨ ይመስላል፡፡ እንደ ትልቅ ነገር ላይታይ ይችላል፡፡ የፍኖተ ካርታ አስፈላጊነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ሳይገባቸው ቀርቶ አይደለም፡፡ አንዳንዴ መለኪያም ያስፈልጋል፡፡ በፍኖተ ካርታው መሀል ላይ ደርሻለሁ አልደረስኩም፣ ወደ ፊት ሄጃለሁ አልሄድኩም የሚለውን ለመነጋገር ቢያንስ የጉዞ ፕላን ላይ አንድ ሰው የደረሰበትን ማወቅና ከደረሰበት ግብ ላይ ቀርቤያለሁ አልቀረብኩም ለማለት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር ብዙ ሰው የሚጠብቀው መንግሥት የፖለቲካ አደረጃጀትን እንዴት መልኩ ነው የሚያከናውነው? የልማታዊ መንግሥት ፕሮግራም ይቀጥላል? ወይስ ሙሉ በሙሉ ተትቶ ወደ ሊበራላዝድ ኢኮኖሚ ውስጥ ነው የምንገባው? እነዚህ እነዚህ ጥያቄዎች በመጠኑም ቢሆን ለንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ይጠቅማሉ፡፡ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ እሳቸው እንዳሉትም አንድ ቦታ ላይ ይኖራልም፡፡ እኔ እንደ ትልቅ ነገር አላየውም፡፡  

ሪፖርተር፡- ነገር ግን ውጤትን፣ ስኬትን፣ እንዲሁም ፈተናዎችን ከመለካት አንፃር ፍኖተ ካርታ ባንለውም የሚከናወኑ ሥራዎችን በዝርዝር መግለጽና አፈጻጸማቸውን ለመገምገም የሆነ መለኪያ መኖር የለበትም?

አቶ ክቡር፡- እንደሚመስለኝ የብዙ ሰው ጥያቄ ፍኖታ ካርታውን በቴክኒካዊ ገጽታው በመመልከት ለመለኪያ የሚሆን በቂ ፍኖተ ካርታ የለንም ከሚል ሳይሆን፣ ቢያንስ የርዕዮተ ዓለም ማዕቀፉ ምንድነው? ከሚል የመነጨ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ የሚመስለኝ እርሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቅርቃር ውስጥ እንደገባ በርካቶች እየገለጹ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ባለፉት ዓመታት በመንግሥት ሲገለጽ የነበረው የልማታዊ መንግሥት ሞዴል እንደምንከተል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከመንግሥት በኩል ግልጽ የሆነ የርዕዮተ ዓለም መገለጫ የለም፡፡ አሁን መንግሥት እየተከተለ ያለው ሞዴል ምን ዓይነት ነው? ለአገሪቱ የኢኮኖሚ መነቃቃትስ ምን ዓይነት ሞዴል የሚሠራ ይመስልዎታል?    

አቶ ክቡር፡- ግልጽ የሆነው ነገር ሊበራል ኢኮኖሚው ወይም ደግሞ ገበያ ሁሉን ነገር፣ በተለይ የሀብት ክፍፍሉን የተሻለ ያደርገዋል የሚባለው ያለ መንግሥት ድጋፍና ቁጥጥር አይሆንም የሚለው ነው፡፡ የትም ቦታ የታየ ነው፡፡ የመንግሥት ኃይል ይጠይቃል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ወደድንም ጠላንም ግዙፍ መንግሥት ነው፡፡ ነፃ ኢኮኖሚ የሚባል አገርም ነው፡፡ የመንግሥት ሚና ግን ቀላል አይደለም፡፡ የአሜሪካ መንግሥት እጁን አጣጥፎ የተቀመጠ መንግሥት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሊበራል ኢኮኖሚን ስናነሳ ጥያቄው የመንግሥትን ሚና ቀንሰን የግል ዘርፉን ሚና እናሳድግ ነው፡፡ ይህን ያደረጉ አገሮች ዛሬ ይኼ እንደማይሠራ ገብቷቸዋል፡፡ ሕዝቡ በቃኝ ኑሮዬን ማሸፍ አቃተኝ ነው የሚለው፡፡ ይህ ሥርዓት የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ የሚያጠናክርና የሚጠብቅ በመሆኑ፣ እኔን እዚያ ውስጥ ሊከተኝ ስላልቻለ በውክልና ደረጃ እንኳን የወከልኩት ሰው ስለኔ ጉዳይ ሳይሆን ስለሌላ ጉዳይ ስለሆነ የሚሠራው ይህ ሥርዓት በቃኝ እያለ ነው፡፡ ወደ ልማታዊ መንግሥት ስንመጣ ደግሞ ሁለቱን ማነፃፀር ባይኖርብንም፣ ልማታዊ መንግሥት ጠንካራ መንግሥት ይጠይቃል፡፡ ግን አቅጣጫ ይሰጣል እንጂ ሁሉንም ልሥራ አይልም፡፡ የሚል መንግሥትም ሊኖር ይችላል፡፡ በእኔ አተያይ ልማታዊ መንግሥት ማለት መንግሥት ከልማት ጋር በተያያዘ የሕዝብን ጥያቄ ሰምቶ ልማቱ ወደዚያ አቅጣጫ እንዲሄድ የማድረግ ዝንባሌ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሁለት ዓለም አለ፣ የምሥራቁና የምዕራቡ፡፡ ጠንካራው የትኛው ነው? እያደገ፣ እየጎለመሰና ጉልበት እያወጣ ያለው የትኛው ነው? የምዕራቡ አይደለም፡፡ ስለዚህ እያደገ ወዳለው ነው የምንሄደው? ወይስ እየወደቀ ወዳለው?  

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን በአገሪቱ ፖለቲካ ምኅዳር ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እያጨቃጨቀ የሚገኘው ጉዳ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ አመራሮችም ሳይቀሩ የዚህ ውዝግብ ተዋናይ ሆነው ይስተዋላሉ፡፡ በእርስዎ አረዳድ አዲስ አበባ ምን የተለየ ፋይዳ ቢኖራት ነው ትልቁ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ የሆነችው? 

አቶ ክቡር፡- የውሸት ጭቅጭቅ ነው፡፡ ትክክለኛው የአዲስ አበባ ችግር ምንድነው ተብሎ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቢጠየቅ፣ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጥያቄ በቂ ትራንስፖርት የለኝም፣ መኖሪያ ቤት የለኝም፣ ሕክምና ማግኘት አልቻልኩም፣ ልጄን ማስተማር አልቻልኩም፣ ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት ነው ያለብን፡፡ ይኼንን የሚያደርጉ ፖለቲከኞች መሰማት የሌለባቸው ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ይኼን የሚገፋ መንግሥት ለእኔ መሰማት የሌለበት መንግሥት ነው፡፡ ሕዝቡ እኮ ዛሬ ከቤቱ ወጥቶ ሥራውን ሠርቶ ይኖራል፡፡ ይህ ከተማ የእኔ ነው የሚለው ጉዳይ ጭቅጭቅ ሆኖ አያውቅም፡፡ ስለዚህ የሕዝብ መንግሥት ነው ከተባለ፣ የሕዝብን ችግር ልፈታ ነው ካለ፣ መጀመርያ ችግሩን በትክክል ማወቅና መረዳት አለበት፡፡ ችግሩ የወሰንና የባለቤትነት ጉዳይ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ጋር የሚነሳው ውዝግብና አለመግባባት አጠቃላይ የአገሪቱን ፖለቲካ ወዴት የሚወስደው ይመስልዎታል?

አቶ ክቡር፡- አገሪቱን ሊያጠፋት ይችላል፡፡ በትንሽና የሕዝብ ጥያቄ ባልሆነ ጉዳይ ካልተጠነቀቅን ጠንቁ ለአገር ሊተርፍ ይችላል፡፡ ማንን እንደሚወክሉ በማይታወቁ የተወሰኑ ፖለቲከኞች የሚደረገውን እንቅስቃሴ መፍቀድ የለብንም፡፡ ይህ እንዳይሆን ማድረግ የሚችለው ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ወይም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው ብዙኃኑ ግን ድምፁ የማይሰማው (Silent Majority) ነው፡፡ ቤት ተቀምጦ ጉዳዩን የሚያብሰለስልና አያገባኝም በማለት የተቀመጠው የኅብረተሰብ ክፍል ሲመጣበት ግን መሄጃ የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ኅብረተሰብ ክፍል መነጋገር መቻል አለበት፡፡ ፍላጎቱን ለፖለቲከኞቹ ማስረዳት አለበት፡፡   

ሪፖርተር፡- ከባለቤትነት ጋር ተያይዞ ለሚነሳው አወዛጋቢ ጥያቄ መፍትሔ ይሆናሉ ተብሎ በመሠረታዊነት ሁለት መፍትሔዎች ይቀርባሉ፡፡ በአንድ ወገን ችግሩ የሚሻው ፖለቲካዊ መፍትሔ ነው የሚሉ ወገኖች የሚገኙ ሲሆን፣ በተቃራኒው ወገን ደግሞ የአዲስ አበባ ችግር መፈታት ያለበት በሕጋዊ መንገድ ነው ይላሉ፡፡ በእርስዎ ዕይታ የአዲስ አበባ ችግር መፍትሔ የሚያገኘው በፖለቲካዊ ወይስ በሕጋዊ መንገድ ነው?

አቶ ክቡር፡- ሕጋዊ ወይም ፖለቲካዊ መፍትሔ ወደሚለው ከመግባታችን በፊት የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚፈልገው ምንድነው? የሚለውን መለየት የሚሻል ይመስለኛል፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚፈልገው ከፖለቲካው ይልቅ ጥሩ አገልግሎት ማግኘት እችላለሁ ወይ የሚለውን ነው፡፡ የቤት ኪራይ ለመክፈል የሚያስችል አቅም አለኝ ወይ? መሬት አግኝቼ ቤት መሥራት እንዴት እችላለሁ? እነዚህ አገልግሎቶች በትክክል እስከተሰጡ ድረስ የአዲስ አበባ ሕዝብ ማንኛውንም ፖለቲከኛ የሚቀበለው ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም አዲስ አበባ መተዳደር ያለባት በፖለቲከኞች ሳይሆን፣ ተወካዮቿ ከፖለቲካ ውጪ በግላቸው ተመርጠው ቢመጡ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ከፓርቲ ውጪ፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ መተዳደር ያለባት በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ፣ ከፓርቲ ውጪ፣ በሕዝብ ተመርጦ የሕዝብን ጉዳይ እንደ ራሱ ጉዳይ አድርጎ የሚያስተዳድር ሲሆን ጥሩ ከተማ ይኖረናል፡፡ የአዲስ አበባ ጥሩ መሆን ደግሞ የሚጠቅመው ለጠቅላላ ኢትዮጵያ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ተጣልተን ሁሉንም ከምናጣ አዲስ አበባ ላይ ተወያይተን አዲስ አበባ ለኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላ ኢትዮጵያ እንድትሆን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነጥብ አዲስ አበባን የገነባት ከጫፍ ጫፍ የመጣ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው፡፡ ምክንያቱም የሕጋዊ መፍትሔ ችግር አሸናፊና ተሸናፊ ያስቀምጣል፡፡ ፖለቲካዊው ግን በደንብ ከተሠራበት ሊያቀራርብ የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡  

ሪፖርተር፡- በእርስዎ አተያይ ይህን የተካረረ የአዲስ አበባ ችግርን መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው?

አቶ ክቡር፡- መፍትሔው በተወሰኑ ሰዎች እጅ ነው ያለው፡፡ በአዲስ አበባ ሕዝብ እጅ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ድንበር አቁሞ አንተ እዚህ፣ አንተ እዚያ አላለም፡፡ ይህን የሚሉት የተወሰኑ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ለዚህ እኮ ነው እነዚህን ፖለቲከኞች ከዚህ ውስጥ ማውጣት መቻል አለብን የምለው፡፡ ዝም ያለውና መስመር ላይ የተቀመጠው አብዛኛው ሕዝብ ወጥቶ እንዴት ነው ብሎ አንተም እረፍ፣ አንተም እረፍ ብሎ የራሱን ፍላጎት የማስቀመጥ ግዴታ ይጠበቅበታል፡፡  

ሪፖርተር፡- አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ምን ዓይነት አዲስ አበባ ይናፍቃሉ?

አቶ ክቡር፡- የሰውን ችግር የሚፈታ፣ ከሰው ጋር የሚገናኝ፣ ኅብረተሰቡን የሚያስተዳድርና ጥያቄውን የሚመልስለት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረ ማርያም፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...