Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲሱ አስተዳደር የኢኮኖሚው የአንድ ዓመት  ቆይታ  

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኃላፊነት ተረክበው ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ ከነገ በስቲያ ድፍን አንድ ዓመት ይሆናቸዋል፡፡ ከፖለቲካው አንፃር በርካታ ለውጦች በታዩበትና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያልተለመዱ አካሄዶችን ያሳዩበትና ጉልህ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የተላለፉበት የአንድ ዓመት የሥልጣን ቆይታ እንደነበር ይታመናል፡፡

ይሁንና ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ከነበረው አለመረጋጋትና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ ኢኮኖሚው ሲዋልል ከርሟል፡፡ ከለውጡ በኋላም ይኸው ችግር ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ አጣብቂኙ ከሚታሰበውም በላይ በመሆኑ፣ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡ የኢኮኖሚ ባሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ኢኮኖሚው የፖለቲካውን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም የሚሉ አስተያየቶችም ሲደመጡ ነበር፡፡ ከችግር ማቅ መውጣት የተሳነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመንግሥትን ሁነኛ ትኩረት ይሻል የሚለው አስተያየትም ጎልቶ እየተደመጠ ነው፡፡ ሆኖም የመንግሥት ውሳኔዎች ተስፋ እንደሚሰጡ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ፖለቲካዊ የቤት ሥራዎችን ለመፍታት የሚታየውን ያህል መጠመድ ለኢኮኖሚ ማሻሻያውም ሲደረግ ባይታይም፣  ከጅምሩ ግን በጎና ይበል የሚያሰኙ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡

ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በበኩላቸው፣ በለውጡ ሳቢያ ይተገበራሉ የተባሉ ዕርምጃዎች መልካም ቢሆኑም፣ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው መስክ ፋይዳ ያለው ለውጥ አልተደረገም ይላሉ፡፡ የታክስ ገቢን በማሻሻል በኩል የተጀመረው አገራዊ ጥረትና ዘመቻን በመልካምነቱ እንደሚመለከቱት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ አደጋ የሆነውን የዕዳ ጫና ለማስተንፈስ የተወሰደው ዕርምጃና ውጤቱም በዚሁ ቅኝት የሚታይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዓመታት የተከማቸባትን የብድር ዕዳ መክፈል የምትችልበት አቅም ስላልነበራት፣ ለአደጋ መጋለጧን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ደጋግመው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ 

ስለዚሁ ጉዳይ በቅርቡ መግለጫ የሰጡት ይናገር (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በብድርና በዕርዳታ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ማግታቸው የዕዳ ጫናው ጊዜያዊ ዕፎይታ እንዲገኝ ረድቷል ብለዋል፡፡ የዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ማስደረጋቸውም ከትልቅ ውጤቶቻቸው ውስጥ ይጠቀሳል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት ከአየቅጣጫው የተገኘው ዕርዳታና ብድር አስፈሪ የነበረውን ችግር በጊዜያዊነት ቢያቃልለውም፣ አገሪቱ ያለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አሳሳቢ እንደሆነ ግን የብሔራዊ ባንክ ገዥው አልሸሸጉም፡፡ ሐሙስ፣ መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. የብሔራዊ ባንክን የስምንት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ደጋግመው ያመላከቱትም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነበር፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ለዓመታት የከረመ ችግር ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በወጡበት ወቅት ግን ብሶበት ነበር፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር የዘለለ ገቢ ማምጣት አለመቻሉ ለችግሩ መባባስ ዋናው ምክንያት ነው፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብም የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ አምራችና አስመጪው ፈተና ውስጥ መውደቁ ሲነገር የቆየ ቤተኛ ችግር ነው፡፡ ሊቀረፍ ባለመቻሉ ግን የውጭ ምንዛሪ ማግኛ አዳዲስ ዘዴዎች መቀየስ እንዳለባቸው የሚያስገድድ ወቅት ነው፡፡

የብሔራዊ ገዥው ሪፖርት የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ማሻሻል ካልተቻለ፣ አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችትም ለነዳጅና ለመድኃኒት ሸመታ ብቻ ሊውል የሚችል እንደሆነ አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ይናገር (ዶ/ር) አሁንም ቢሆን በጊዜያዊነት የጠቆሙት መላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን ለመታደግ ያደረጉትን ጥረት አሁንም በመድገም የውጭ ምንዛሪ ማፈላለግ እንደሚገባቸው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር ውስጥ የሚዋዥቅ በመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ በልመና ብቻ መሙላት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

አቶ መላኩ አስቸኳይ የፖሊሲና የስትራቴጂ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እግር ከወርች የቀሰፈውን የውጭ ምንዛሪ ዕጦት ጉዳይ፣ የወጪ ንግዱ መቀዛቀዝና በታቀደው ልክ አለመጓዝ፣ ሕገወጥነትና ኮንትሮባንድ በወጪ ንግዱ ላይ የፈጠሩት ተፅዕኖ፣ ብሎም የገቢ ዕቃዎች ዋጋ በየጊዜው መናር ትኩረት ሊያገኙ የሚገባቸው መሠረታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹በየመድረኩ የምናቀነቅንለት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከተደረገለት ድጋፍና ማበረታቻም በኋላ የሚጠበቀውን ያህል አለመጓዙ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል አሁንም የሚጠበቀውን አለማምጣቱና በገቢ ዕቃዎች ላይ ተኪ ሚናውን ባለመጫወቱ መታየት የሚያሻው ነው፤›› በማለት አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸው እየተነገረ ነው፡፡ ነጋዴው የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ሲቸግረውና ችግሩም ሲብስበት እየታየ ነው፡፡ የግንባታ ሥራዎች መዳከም ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ እያሳረፈ መምጣቱ ታይቷል፡፡ የዓለም ባንክ ሪፖርት እንደሚሳያው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ 7.7 በመቶ ወርዷል፡፡ ለዚህ የመንግሥና የግሉ ዘርፍ የግንባታና መሰል ሥራዎች መቀዛቀዝ አንዱ ምክንያት ነው፡፡

መንግሥት ያገኘውን የውጭ ምንዛሪ አስገዳጅ ለሆኑ ዕዳዎች ክፍያ ማዋሉና ተጨማሪ ሊበደር አለመቻሉ ብቻም ሳይሆን፣ ለሁለት ወራት ተኩል ብቻ የሚበቃ ክምችት በመኖሩ በአብዛኛው መሠረታዊ ለሆኑ የገቢ ዕቃዎች ግዥ እየዋለ ነው፡፡ ይህ ለአኮኖሚው መቀዛቀዝና ከድርብ አኃዝ ዕድገት መውጣት ምክንያትነቱ የጎላ ነው፡፡ ከለውጡ ወዲህ አገሪቱ የምትመራበት የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ምን እንደሆነ አለመታወቁ ችግር ነው የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ኢኮኖሚውን የሚመራው ፍኖታ ካርታ ከሌለ ከችግሮች ተላቆ መራመድ እንደሚቸግር ያሳስባሉ፡፡ አሁን ላለው ችግር መፍትሔ ሊሆኑ ከሚችሉ ዕርምጃዎች አንዱ የውጭ የፋይናንስ ተቋማት እንዲገቡ መፍቀድ እንደሆነ የሚያምኑት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ይህንንም በየደረጃው መተግበር እንደሚያስፈልግ ሳያመላክቱ አላለፉም፡፡

የውጭ ኩባንያዎች የ25 በመቶ ድርሻና ከዚያም ቀስ በቀስ የ49 በመቶ ድርሻ ይዘው እንዲገቡና ወደፊትም ሙሉ በሙሉ ድርሻቸውን ይዘው በመግባት በዘርፉ እንዲሠሩ የሚያደርግ አሠራር መከተል ተገቢ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡ ነገር ግን የውጭ ኩባንያዎች እስኪገቡ ድረስ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ክፍት ማድረግ እንዲጀመር ያሳስባሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪና አቅርቦትን ለማሻሻልና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ፣ አሁን ካለው ችግር አንፃር እንዲህ ያለውን መንገድ ማየቱ ተገቢ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም፣ ኢኮኖሚውን የተመለከቱ ለውጦች ስለመታየታቸው የጠቀሱት አቶ መላኩ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊለወጡ አይችሉም፣ አይነኬ ናቸው ተብለው ይታዩ የነበሩ አስተሳሰቦች ተቀይረው፣ የኢትዮጵያን አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ሊያጎሉ የሚችሉ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል ይላሉ፡፡ ምንም እንኳ ገና ጅምር ላይ ቢሆንም የካፒታል ወይም የአክሲዮን ገበያ፣ የፕራይቬታይዜሽንና መሰል ለውጦች መታየታቸውን አውስተዋል፡፡ በፋይናንሱ ዘርፍ ዳያስፖራዎች እንዲሳተፉ ጥናት መጀመሩ፣ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በማስያዝ ብድር መፈቀዱ መልካም እንደሆነ የጠቀሱት መላኩ፣ የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት በፓርላማ መጽደቁ ትልቅ ዕርምጃ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከ15 ዓመታት በፊት የተጀመረው ውጥን እንደ አዲስ እንቅስቃሴ የተጀመረው በዚህ ዓመት ሁሉ ተስፋ የተጣለባቸው የለውጥ መንገዶች ናቸው ቢሉም፣ ኢትዮጵያን ሊጠቅሙ በሚችሉበት አግባብ መቃኘት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ በአፍሪካ ገበያ ውስጥ ለመወዳደር ምን ያህል ተዘጋጅተናል የሚለው አቶ ኢየሱስ ወርቅንም ያሳስባቸዋል፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በአዲስ ተተክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የልማት ባንክ ፕሬዚዳንቶች በአዳዲስ ተሿሚዎች እንዲመሩ ተደርጓል፡፡ እነዚህን ባንኮች የሚመሩ አዲስ የቦርድ ሰብሳቢዎችና የቦርድ አባላት በወራት ልዩነት እንዲተኩ ተደርጓል፡፡

ይህ የአመራር ለውጥ ምን ያህል ሠርቷል? የሚለው ጥያቄ ግን የብዙዎች ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፎርም የተጠበውን ያህል አለመሆኑ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በለውጡ በብሔራዊ ባንክ ወደ አሥር የሚሆኑ ሕጎች ተሻሽለዋል፡፡ ዳያስፖራው በፋይናንስ ዘርፉ እንዲገባ ረቂቅ መዘጋጀቱ በራሱ አዎንታዊ ዕርምጃ እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ያመለክታሉ፡፡

ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሲመጣ ሌላው የለውጥ አቅጣጫ ውጤት ነው ተብሎ ለመተግበር የተጀመረው ፕራይቬታይዜሽን ነው፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳይ አንፃር ይህ ሐሳብ ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹም ሆኑ የንግድ ኅብረተሰቡ የሚስማማበት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ነገር ግን እስካሁን ይህንን አዲስ የመንግሥት አቅጣጫ ወደ ተግባር ለመወለወጥ  የተከናወነው ኢትዮ ቴሌኮምን ፕራይቬታይዝድ ለማድረግ የሚያስችሉ ሰነድ ብቻ ነው፡፡ የሌሎች ኩባንያዎች ዝግጅት ብዙ የሚቀረው ቢሆንም በዚህ ተግባር የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን እየሠራ ነው፡፡ መንግሥት እንደ ቴሌኮም ያሉ ተቋማትን ወደ ግል የማዛወር ውሳኔ ላይ መድረሱ አገሪቱ ካለባት ችግር አንፃር ተገቢ  ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ውሳኔውን የሚሞግቱም በርካቶች ናቸው፡፡ በተለይ አገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል መፍትሔነቱ ይጠቀሳል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መንግሥት የወሰደው ሌላው ዕርምጃ የወጪ ቅነሳ ነው፡፡ ከፍተኛ ወጪ ሊያስወጡ የሚችሉ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች በጀት እንዲያዝላቸው ተደርጓል፡፡ በእጅ ያሉት ሜጋ ፕሮጀክቶች ደግሞ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተነጥቀው ለሌሎች ተቋራጮች የተሰጡት፣ መንግሥት ወጪውን ለመቀነስ በማሰቡ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ ከበደ (ዶ/ር) እንዲህ ያለው ዕርምጃ ተገቢ ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ትላልቅ ግንባታዎችን ጋብ ማድረግ የመንግሥት ወጪን በመቀነስ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት ረገድ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የሚጠይቁት የውጭ ምንዛሪ መጠን እንዲቀነስ አድርጓል፡፡

ይህንን መሰሉ ውሳኔ ሌሎች የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ይስማሙበታል፡፡ የኢኮኖሚውን ግለት ረገብ ማድረግ ችግሮችን ለማብረድ ያግዛል ይላሉ፡፡ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በተካሄደው የአዲስ ወግ ውይይት ወቅትም መንግሥት ኢኮኖሚውን በዚህ መንገድ ማንቀሳቀሱ ተገቢነት እንዳለው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

በአንፃሩ ኢኮኖሚው ያሉበትን ችግሮች ለማከም መፍትሔዎቹ ቢመላከቱም ትላልቆቹ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በተለይ የስኳር ፕሮጀክቶች አሁንም ድረስ ደካማ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆናቸውንና ምርታማነታቸው መቀነሱ፣ በወራት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብለው እስካሁን ድረስ ግንባታቸው ሲጓተት መክረሙ ለአንገብጋቢ ችግርና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ሆኖ የሚታይ ነው፡፡

በፋይናንስ ዘርፉ ብሔራዊ ባንክ ካከወናቸው ጉዳዮች ውስጥ የተለያዩ መመርያዎችን ስለማስተካከሉ፣ ዳያስፖራውን አሳታፊ የሚያደርግ ሕግ መርቀቁ የአሥር ዓመት ፍኖታ ካርታ ቀርፆ የፋይናንስ ተቋሙ ለውጭ ክፍት እንዲሆን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ፣ ስቶክ ማርኬት ለመጀመር የሚያስችል ጥናት እየተደረገ መሆኑ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ አዳዲስ ሊባሉ የሚችሉ አወንታዊ ዕርምጃዎች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡

ቀደም ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ከባንኮች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት የአዛዥና ታዛዥ እንደነበር የሚያስታውሱ የባንክ ኃላፊዎች፣ ከለውጡ ወዲህ በኢንዱስትሪው ላይ መለወጥ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ መስማማት ባይኖር እንኳን ተቀራርቦ የመነጋገርና ሐሳብ መለዋወጥ መጀመሩ በመልካም ጎን የሚታይ ነው ይላሉ፡፡

በአንፃሩ ግን በዚህ ለውጥ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፎርም በታሰበው ደረጃ አለመሆን አሳሳቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት ያለበትና አሁንም ብዙ የሚቀረው ተቋም ስለመሆኑ ያመለክታሉ፡፡

ለዚህም እንደማሳያ የሚጠቀሰው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ሚና ያለው የምክትል ገዥው የኃላፊነት መደብ ባዶ ሆኖ መቆየቱ ለአብነት ይነሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ገዥው በሰጡት መልሶ ከስቶክ ማርኬትና ሌሎች ተያየዥ ሥራዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሙያ ለማግኘት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ይህንኑ ለማድረግ ባለቤት የማፈላለጉ ሥራ ስለመቀጠሉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ስለማይክሮ ኢኮኖሚው ሲታሰብ ዋናው ነገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተደራጀ ባለሙያ መጠናከር ስለመሆኑ የሚጠቅሱት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ አሁን ባለው ደረጃ ግን ብሔራዊ ባንክ ብዙ የሚቀረው ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ የመስጠት ኃላፊነት ያለበትና የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ሆነ ተያያዥ ሥራዎች በማዕከላዊ ባንኩ ባለሙያዎች ከመሠራቱ አንፃር፣ ተቋሙን በባለሙያ ማደራጀት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

ከውጭ ዕዳና የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች የሚያስፈልጉ ሲሆን፣ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚታሰቡ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ግን ከአገር ሰላም ጋር የተያያዙ በመሆኑ መንግሥት ለሕግ የበላይነትና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

በተለይ ኢኮኖሚውን ለማጎልበት የግሉ ዘርፍ ሚና ትልቅ ትኩረት እንደሚሻ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን ሚናውን በትክክል ለመግለጽ ጥርት ያለ ፍኖተ ካርታ የሚያሻ ስለመሆኑ ከተሰጡ አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ አሁን ካለው የአገሪቱ አቅጣጫና ከጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደተገለጸው የግሉ ዘርፍ ሚና ለዚህች አገር ወሳኝ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ከዚህ በኋላ የግሉን ዘርፍ መሪነት የሚያሳይ ተግባር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እስከዛሬ የነበረው አካሄድ መንግሥት መር የሆነ አቅጣጫና ኢኮኖሚውን የሚመራው ፖለቲካው ነበር፡፡ አሁን ግን ኢኮኖሚው ሊመራ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በእስከዛሬው ጉዞ ትልቁ ድክመት ኢኮኖሚውን የሚያወዛውዘው ፖለቲካው  መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ አሁን ግን ይህ መቅረት አለበት ብለዋል፡፡ ኢኮኖሚው መቅደም አለበትም ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ገበያ መር ኢኮኖሚ እንዲኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያሳዩ ያለውን አመለካከት የሚቀበሉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች