Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዲስ አበባ የዓለም ነች

አዲስ አበባን የተመለከቱ ፅንፈኛ አመለካከቶች ሲራገቡ ሰንብተዋል፡፡ በነፃነት የመናገርና ሐሳብን የመግለጽ መብትን ተጠቅሞ ሁሉም የመሰለውን ሲናገር ሰምተናል፡፡ የሚመለከተውም የማይመለከተውም አብዮት ለማቀጣጠል ያስከተለው ውዥንብር የከተማዋን ነዋሪ ብዥታ ውስጥ ከቶታል፡፡

 የአዲስ አበባን ጉዳይ አጀንዳ ያደረጉ ሁሉ ለከተማዋ ትናንትም ሆነ ዛሬ ምን ፈይደውላት ይሆን? ለሚለው መጠይቅ ምን መልስ እንደሚኖራቸው ባላውቅም፣ አዲስ አበባ ሁላችንንም ታኖራለች፡፡ ወደፊትም ትኖራለች ብሎ ማለፉ ይበቃል፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች፡፡ እንደውም አዲስ አበባ ከኢትዮጵያዊም ባሻገር ነች፡፡ የአፍሪካም የዓለምም ነች፡፡ ይህንን ገጽታዋን ማጠልሸትና ማበላሸት መጥፎ የኩነኔ ተግባር ነው፡፡ ስለአዲስ አበባ ከሚወራው ጽንፈኛ ወሬ በላይ ብዙ ችግሮች ያሉባት ከተማም ነች፡፡ ይህ አውቆ የሚጠቅም መፍትሔ መላ እንደማመላከት ቁልቁል መዝቀጥ ያሳፍራል፡፡ አዲስ አበባ የዕድሜዋን ያህል አልበለፀገችም፡፡ አላደገችም፡፡ ለነዋሪዋም ምቹ አይደለችም፡፡ እንደውም ከቀደመው ጊዜ አንፃር ስናያት፣ ብዙ ይጎድላታል፡፡ ዘመን ተሻጋሪ ማስተር ፕላን የላትም፡፡ ከተሜነት ወረራት እንጂ ከተማነት አላሸነፋትም፡፡፡

በሕንፃ፣ በመንገድና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ረገድ ከአቻዎቿ ብዙ የሚቀራት ነገር አለ፡፡ በቀደመው ዘመን እንዲህ ያለው ነገር ከአሁኑ ይልቅ በቅጡ ታስቦ ይሠራበት እንደነበር ይታመናል፡፡ ማስተር ፕላንዋም በአግባቡ ይተገበር ስለነበርና ወደ ከተማዋ የሚጎርፈውም ሰው ብዛት እንደአሁኑ ስላልነበር ችግሩ ብዙም አልነበር፡፡ በቀደመው ጊዜ ከተማዋ ሰዎችን ቀድማ ሰልጥና ነበር፡፡ አሁን ግን ከተማዋም ሰዎቿም ሥልጣኔን ሊሠለጥኑበት ሲገባቸው፣ በፈንታው እየሰየጠኑ ነው፡፡ ለክፉ ድርጊትና ፀብ የሚጋበዙ የበዙባት፣ ለኑሮ የማትመች ከተማ ሆናለች፡፡

ከከተማዋ መስፋትና ከሕዝብ ቁጥሯ መጨመር አንፃር ከየአካባቢው የሚመነጩ ቆሻሻ በዚያው ልክ መብዛቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ግምት ውስጥ አስገብቶ መላ ለማበጀት የሚያስችል አሠራር ስላልነበረ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ውስጧን ብቻ ሳይሆን፣ አሏት የሚባሉ ጎዳናዎቿ ጭምር የቆሻሻ ክምሮች የሚታዩባት ነች፡፡ ነዋሪዎቿም ጉድፏን እያየን እንዳላየን እየኖርን ነው፡፡

በቀደመው ጊዜ የከተማዋ ጎዳናዎች ከቆሻሻ የፀዱ ወይም በአንፃራዊት ከዛሬ እጅግ የተሻሉ ናቸው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍረው፣ የከተማዋ መዘጋጃ ቤት ጥብቅ አሠራር ስለነበረው ነው፡፡ ዛሬ ዘመናዊነት በናኘበት፣ ቴክኖሎጂ በረቀቀበት ዘመን አዲስ አበባን ንፁህና አረንጓዴ ማድረግ ቀርቶ፣ ከተማዋ የምታመነጨውን ቆሻሻ በወጉ ማስወገድ ፈተና ሆኗል፡፡

ስንትና ስንት ወጪ የወጣበትን መንገድ ሌላው መንግሥት ይቆፍረዋል፡፡ ይቸረችፈዋል፡፡ የፈሳሽ ማውረጃዎችን በቆሻሻ ይሞላል፡፡ መንገድ አካፋይ አጥሮችን ነቃቅሎ ይወስዳል፡፡ መንገድ አፍርሶ ሕንፃ ይገነባል፡፡ የመንገድ ንብረት ይሰርቃል፡፡ የመብራት ምሰሶዎች ይገጫሉ፡፡ የሚጠገኑት ግን በመከራ ነው፡፡ ጭራሹኑ የማይጠገኑም አሉ፡፡ ለዓመታት ያገለግላል የተባለው መንገድ ከአጠቃቀም ጉድለት ያለዕድሜው ሲበላሽ ለምን የሚል የለም፡፡ ከልክ በላይ አፈርና ሌሎችም ጭነቶች የተሸከሙ ተሽከርካሪዎች ጭነታቸውን እያዝረከረኩ ስለሚጓዙ ጤናማውን አስፓልት አባጣና ጎርባጣ በማድረግ ለተሽከርካሪዎች እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ ይህ ድርጊት ያልተገባና ሕገወጥ መሆኑን ጠቅሶ ዕርምጃ ሲወስድ የሚታይ አካል የለም፡፡

መሠረተ ልማቶቿን ለመጠበቅ ፅዳትና ውበቷንም ለማስመለስ ኃላፊነት ያለባቸው የከተማው አስተዳደር ሹመኞች ጉዳዩን ነገሬ ብሎ ሳይዙ መቅረታቸው ችግሩ ከዓመት ዓመት እየተንከባለለ ዛሬ ላይ ተደርሷል፡፡ ከተማዋ ፅዳት አልባ ሆናለች፡፡ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማልማት ያሰቧቸው የከተማችን ወንዞች ካነሳንማ እውነት አዲስ አበባ የአገራችንና የአኅጉራችን መዲና ነች ወይ? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡

አዲስ አበባን ከቆሻሻ ለማፅዳት መንገዶቿን ለመንከባከብ ጎዳናዎቿን ምቹ ለማድረግ አካባቢን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር የሚረዳ አሠራር የመዘጋጃ ቤቱ ቀዳሚ የሥራ ድርሻ ቢሆንም፣ ይህ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ ዕቅድ ብቻ፡፡

ከማስተር ፕላኑ ውጪ ግንባታዎች ተሸራርፈው በጉልበተኞች መያዛቸው በመንግሥት አገር የሚገርም ውሪነት ነው፡፡ ዕርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ ብሷል፡፡ የተጠረቃቀመውን ችግር ለመፍታት ሲሞከር ጫጫታው ይበረክታል፡፡

የቀደመውን ጊዜ ትተን አሁን ሥራ ላይ ያለው ማስተር ፕላን በአግባቡ አለመተግበሩ በራሱ ይህችን ከተማ ደቁሷታል፡፡ ከማስተር ፕላን ውጭ የተገነቡ  ሕንፃዎች መፍረስ አለባቸው ከማለት ይልቅ እንዳይፈርሱ በማድረግ ቅያሱ እንዲለወጥ ይደረግ ስለነበር፣ ስለአዲስ አበባ የሚጨነቀው ማነው? ያስብላል፡፡ ለአዲስ አበባ ሳንባ ይሆናሉ የተባሉ የአረንጓዴ ሥፍራዎች በድፍረት ለሌላ ግንባታ እንዲውሉ ማድረግ ለምን በችልታ ታለፈ፡፡ በጠቅሉ ከመሬት አሰጣጥ ጋር ያሉ ችግሮች አዲስ አበባን ፈትነዋታል፡፡

ነዋሪዎቿም አልተንከባከብናትም፡፡ ስለከተማዋ መብትና ለኑሮ ምቹነት ሳይሆን፣ ለግል ማንነታችንና ፍላጎታችን ብቻ ስለምንጨነቅ፣ አዲስ አበባን በድለናል፡፡ ሁሉ አልፎ ሂያጅ የሆነባት ከተማ ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ የሁላችን ከተማ ነች ካልን መንገዶቿን መንከባከብ፣ ዙሪያ ገባዋን ማፅዳት ይጠበቅብን ነበር፡፡ ከንፁህ ውኃነት ወደ መርዛማ ጅረት እየተቀየሩ ያሉትን ወንዞች ቆሻሻና የሞቱ እንስሳት መጣያ በማድረግ አበሳ ያበዛንባት እኛው ነዋሪዎቿ ነን፡፡ ይህንን ማድረግ በሕግ ቢያስቀጣም፣ ሕጉን የሚያስከብርላት አካል አልነበራትም፡፡ ውሎ አድሮ ወንዞቿ ለራሳችን በሽታ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ ዛሬ እነዚህን ወንዞች እናክም ተብሎ ሲነሳ ደግሞ አንዳንዶች ወጪው ለሌላ አይውልም ብለው ሲሞግቱ ማየት አዲስ አበባን ድጋሚ እንደመግደል መሆኑ ሊታወቃቸው ይገባል፡፡

አዲስ አበባ የሁላችን ነች ካልን ሁላችንም ለአዲስ አበባ ምን አድርገናል? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ስኳርና ዘይት በወቅቱ አልቀረበልንም ብለን በሚዲያ ሳይቀር የምናማርረውን ያህል ማዘጋጃ ቤቱን የከተማችንን ፅዳት ልታስጠብቅልን አልቻልክም ብለን መጠየቅና ማሠራት አለብን፡፡ ወንዞቿ ተበክለዋልና ንፅህናቸው እንዲጠበቅ ካላደረክ ብሎ የሚሞግት ነዋሪ ከሌላት፣ ስለአዲስ አበባ ፖለቲካ ጉዳይ ብቻ መጮህ በቂ አይደለም፡፡ እናስውባት ተብሎ መልካም ሐሳብ ሲቀርብ ኧረ እኛም አለን እንደማለት ለትችት የምንሠለፍ ከሆነ አዲስ አበባ እንዴት ትለወጣለች?

ስለዚህ የአዲስ አበባን ገጽታ ለመቀየር በመወነጃጀል ሳይሆን፣ በስሜት ብቻ ስለአዲስ አበባ መቆርቆር አዲስ አበባን አይቀይራትም፡፡ እስካሁን የተሠሩ ያልተገቡ ተግባራትን መማሪያ በማድረግ ማረም ተገቢ ይሆናል፡፡

ነዋሪዎቿም እስከ ዛሬ ከነበረው አመለካከት መቀየርን ይጠይቃል፡፡ የዘመናዊነት አንዱ መገለጫው የምንኖርበትን አካባቢ ለኑሮ ምቹ ማድረግ ነውና አዲስ አበባን ብለን የሚመጡ ጎብኚዎቿን በአግባቡ የምናስተናግድበት ባህል ማዳበር አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ንፁህ አዲስ አበባ ታስፈልጋለች፡፡ አዲስ ነገር መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም በራሳችን ጉድለት የበከልናቸውን ወንዞች ውብ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠንክረው የያዙትን ፕሮጀክት መነሻ በማድረግ ስለአዲስ አበባ ዕድገት ሌሎች መልካም ነገሮችን በማሰብና በመሥራት ታሪክ ለመለወጥ እነነሳ፡፡ የሁላችንም እንድትሆንና በተንከባከብናት ቁጥር ውበት ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጫችንም እንድትሆን ማድረግ ይቻላልና አዲስ አበባን እንቆረቆርላታለን የምንለውን ያህል በተግባር ለውጠናት ልንጠቀምባት እንችላለን ብሎ ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት