Saturday, December 9, 2023

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ፈታኝ አገራዊ ተግዳሮት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አሁን ያለችበትን ቅርፅ ይዛ በእቴጌ ጣይቱ ብጡል አማካይነት ከተመሠረተች የ130 ዓመታትን ገደማ ዕድሜ ያስቆጠረችው አዲስ አበባ፣ ከአገልግሎት ጥራትና ከአቅርቦት ጋር የተያያዙ የነዋሪዎቿን ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ከመስማት ባለፈ ለዘለቄታው የሚሆን መፍትሔ ፍለጋ አሁንም በመኳተን ላይ ትገኛለች፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የከተማዋ የባለቤትነት ጥያቄ ከበርካታ የከተማዋ ጥያቄዎች በላይ ገዝፎ የከተማዋን ነዋሪዎች እያሳሰበ የሚገኝ ዓብይ አጀንዳ የሆነ ሲሆን፣ የአገሪቱ ልሂቃንን ደግሞ ለሁለት ጎራ ከፍሎ በማወዛገብና በማጨቃጨቅ ላይ ነው፡፡

በባለቤትነት ጥያቄ፣ በመሠረታዊ አገልግቶች አቅርቦት አለመሟላት፣ እንዲሁም ከአስተዳደር ውክልና ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጽንፍ በቆሙ ሐሳቦችና አመለካከቶች የታጨቀችው አዲስ አበባ፣ ከዕድሜዋ በላይ እርጅና የተጫጫናት አስመስሏታል፡፡

ከከተማዋ የባለቤትነት መብት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ምንም እንኳን በተወሰነ ደረጃ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ግን ከፍተኛው ጡዘት ላይ ደርሶ ፈሩን መሳቱን የሚያትቱ በርካቶች ናቸው፡፡

ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ጉዳይ አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ፖለቲከኞችን እያወዛገበ መሆኑ እንደ አዲስ ነገር ቢታይም፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ በኢሕአዴግ ውስጥ የሥልጣን ሽግሽግ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ ገፊ ምክንያት ከነበረው፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ሲደረግ ከነበረው ተቃውሞ ጋርም የሚያያዝ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ፣ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተጀመረው የተቃውሞ ድምፅ አድማሱን እያሰፋ ሄዶ ወደ ሌሎች የመብት ጥያቄዎች መሸጋገሩ፣ አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱን ፈተና ውስጥ በመክተት የአመራር ለውጥ እንዲከሰት ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ከዓመታት በፊት ተቀስቅሶ የፖለቲካ ሥርዓቱን ጥያቄ ውስጥ የከተተው ይህ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ ከዓመት በፊት ወደ መንበረ ሥልጣን የመጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መልሶ አጣብቂኝ ውስጥ ይከታቸዋል በማለት የገመተ አልነበረም፡፡ ሆኖም ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላንና መስፋፋት ጋር በተያያዘ ሲነሱ የነበሩት ጥያቄዎች አሁን ‹‹አዲስ አበባ የእኔ ነች›› ወደሚል አዲስ ጥያቄ ተሸጋግረው አሁንም የሥርዓቱ ፈተና ሆነዋል፡፡

ይህ የአዲስ አበባን ባለቤትነት የተመለከተው ጥያቄ ከከተማዋ ነዋሪዎች ባለፈ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች የተለያዩ አስተያየቶችን እንዲሰጡ ያስገደደ ሲሆን፣ ይህ ጉዳይ መልሶ አገሪቱን ከዓመት በፊት ወደነበረችበት አለመረጋጋት እንዳይመልሳት የሚሰጉ በርካቶች ናቸው፡፡

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የአዲስ አበባ ጉዳይ ዋነኛው የአገሪቱ የፖለቲካ ማጠንጠኛ፣ መሟገቻና የተካረሩ ሐሳቦችን እንዲያስተናግድ ያደረገው ደግሞ በተለይ በኮዬ ፈጬ አካባቢ የሚገኙና ዕጣ የወጣባቸው ኮንዶሚኒየሞች ለባለ ዕድለኞቹ ሊተላላፉ አይገባም በሚል በተፈጠረ መካረር ሳቢያ ነው፡፡

በወቅቱ ‹‹በኦሮሚያ መሬት ላይ የተሠራ ኮንዶሚኒየም ለማንም ተላልፎ አይሰጥም›› ተብሎ የተንፀባረቀውን አቋም ተከትሎ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ሐሳቡን በመደገፍ ሕዝባዊ ትዕይንት ከመካሄዱም በላይ ጉዳዩም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት በመሳብ የንትርክ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡

በተለይ ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ለሐሳቡ ድጋፍ መስጠቱ የበርካቶችን ትኩረት በመሳብ ሲያወዛግብ፣ በአጠቃላይ ከዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ሲወጡ የተገባው ቃል ኪዳን ተረስቶ ወደ አዲስ የፓርላማ ትርክት ገብተዋል የሚል ትችት እንዲሰነዘር ምክንያትም ሆኗል፡፡

በዚህ መነሻነት ደግሞ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አነሳሽነት ከሳምንታት በፊት በባልደራስ አዳራሽ በመሰባሰብ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት መቋቋሙ ጉዳዩን ሌላ መልክ አስይዞታል፡፡

የዚህ ሁሉ ክርክር ውዝግብና ምክንያት የሆነው የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ በተለያዩ መንገዶች የሚቀርብ ሲሆን፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ የታሪክ አረዳድና ትርጓሜዎች የመቆራቆሻ ምንጭ በሆኑበት ዓውድ ውስጥ የአዲስ አበባም ጉዳይ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህ የታሪክ አረዳድና አተረጓጎም ላይ መስማማት እስከሌለ ድረስ ውስብስብ የባለቤትነት፣ የማንነትና የውክልና ጥያቄዎችን መፍታት በቀላሉ የማይቻል መሆኑን የሚጠቅሱም ብዙ ናቸው፡፡

በዚህ ዓውድ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ታሪክም እንዲሁ በአወዛጋቢነት የሚታወቅ ሲሆን፣ በተለይ አሁን የተለያዩ ቡድኖች ከተማዋ ‹‹የእኔ ነች›› ወደሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር መሸጋገራቸው የከተማዋን ነዋሪ ሥጋት ውስጥ ከትቶታል፡፡

የተለያዩ የኦሮሞ ምሑራን ‹‹ፊንፊኔ›› የኦሮሞ የነበረችና በምኒልክ መስፋፋትና ወረራ ሳቢያ ቀደምት ነዋሪዎቿ ተፈናቅለው አሁን ያላትን ቅርፅ ያዘች እንጂ የኦሮሞ ናት የሚል ሐሳብ የሚያቀነቅኑ ሲሆን፣ በአማራ ልሂቃንም በኩል ‹‹በረራ›› ትሰኝ  የነበረች ጥንታዊ ከተማቸው እንደሆነች በመጥቀስ ‹የእኔ ነች የእኔ ነች› አተካራ ውስጥ ገብተዋል፡፡

ከተማዋ ‹የእኔ ነች የእኔ ነች› በማለት ዕጣ የሚጣጣሉትን ወገኖች የከተማው ነዋሪ ከመመልከት ባሻገር የተለየ ሚና የሌለው መሆኑ ደግሞ፣ ጉዳዩን እንዳወሳሰበው የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

ለዚህም እንደመከራከሪያ የሚያቀርቡት ሐሳብ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ባለው የሥርዓት ለውጥን ተከትሎ በ1987 ዓ.ም.  የፀደቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ የአዲስ አበባንና የነዋሪዋን ጉዳይ በተመለከተ ያስቀመጠው አንቀጽ ግልጽና አሻሚ መሆኑን ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ርዕሰ ከተማዋን የተመለከቱ አምስት ንዑስ አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ አሁን ላለው የባለቤትነት ጥያቄ በሩን የከፈተው ንዑስ አንቀጽ 5 እንደሆነ የሚያትቱ በርካታ ድርሳናት ይገኛሉ፡፡ ይህንን በመደገፍ እንደ መብት የሚጠይቁም በርካቶች ናቸው፡፡

ይህ ንዑስ አንቀጽ 5 ‹‹የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፤›› የሚል ሲሆን፣ ይህን ልዩ ጥቅም አስመልክቶ ይመጣል የተባለው ዝርዝር ሕግ ግን ብቅም አላለ፡፡

ነገር ግን ይህን ንዑስ አንቀጽ በመንቀስና ልዩ ጥቅም የምትለውን ሐረግ በመምዘዝ ብቻ የባለቤትነት ጥያቄ ማቅረብ ተቀባይነት የሌለው ሐሳብ ነው በማለት የሚያትቱ በርካቶች ናቸው፡፡

ሐሳቡን በመቃወም ሐሳባቸውን የሚገልጹትም ቢሆን ሙግታቸውን ለማጠናከር መልሰው የሚጠቀሙት ሕገ መንግሥቱን ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ደግሞ መሬት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆኑን በመጥቀስ አንድ ብሔር ይህ መሬት የእኔ ነው ብሎ የሚጠይቅበት ምንም ዓይነት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን እየገለጹ ይሟገታሉ፡፡

አዲስ አበባን አስመልክቶ ያለው ሙግት ከሕገ መንግሥቱ ማርቀቅ ወቅት ጀምሮ የነበረ በመሆኑ፣ በወቅቱ ክልል 14 ወክለው በሒደቱ የተሳተፉ ግለሰቦችም ‹‹ልዩ ጥቅም›› የሚለውን ሐረግ ከመቃወም ባለፈ፣ አዲስ አበባ እንደ ሁሉም ክልሎች እኩል የውክልና መብት እንዲኖራት የሚጠይቁ ነበሩ፡፡ ከዚህ በተቃራኒም አዲስ አበባን በሚመለከት የቀረቡትን አንቀጾች ምንም ሳይነኩ እንዲፀድቁ የሚፈልጉ አባላትም ነበሩ፡፡

የኦሮሚያ ክልል የተለየ ጥቅም ያገኛል የሚለውን ሐሳብ በወቅቱ ከተቃወሙ ግለሰቦች መካከል ከክልል 14  አቶ አዳሙ ደገፋ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ፣ የእሳቸው የተቃውሞ ቃልም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጉባዔ ቃለ ጉባዔ ጥራዝ አራት ላይ ሠፍሯል፡፡

የእሳቸው የተቃውሞ ሐሳብ፣ ‹‹ከተማው ቢያድግ ለጥቂቶች ሳይሆን የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖርያ በመሆኑ የሁሉም የጋራ ሀብት ሆኖ ሳለ፣ በንዑስ አንቀጽ 4 የኦሮሚያ ክልል የተለየ ጥቅም ያገኛል ተብሎ መቀመጡ የተባለው ግብርም ሊሆን ስለሚችል፣ እንዲህ ዓይነት ድርድር የያዘን ንዑስ አንቀጽ ማስቀመጡ አግባብ ስለማይሆን እንዲወጣ፤›› በማለት ሐሳባቸውን አቅርበው እንደነበር በቃለ ጉባዔው ገጽ 22 ላይ ሠፍሮ ይገኛል፡፡

ልዩ ጥቅም የሚለውን ሐሳብ ደግፈው ሐሳባቸውን ያቀረቡት በወቅቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት ኮሚቴ አባል የነበሩትና የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ደግሞ ‹‹ለአዲስ አበባ ከተማ በልዩ ሁኔታ ዝርዝሩ በሕግ የሚወሰን ራሱን የማስተዳደር ሥልጣን መስጠቱና ነዋሪዎቹም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጥንቅር እንደመሆናቸው መጠን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና እንዲኖራቸው መደረጉ አግባብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም የሚያገኘው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ እንደሆነና የከተማው መስፋት አርሶ አደሩን የሚነካ ከመሆኑም ሌላ፣ ቀደም ሲል እንደተባለው በተፈጥሮ ሀብትና በመሳሰሉት ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ በረቂቁ እንዳለ መቀመጡ ለሁለቱም የልማት እንቅስቃሴ የሚበጅ እንደሆነ ገልጸዋል፤›› በማለት ቃለ ጉባዔው ይገልጻል፡፡

እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት አዲስ አበባን በሚመለከት የቀረበውን አንቀጽ ለማፅደቅ ለድምፅ ቀርቦ በ507 ድጋፍ፣ እንዲሁም በስድስት ድምፅ ተዓቅቦ ፀድቋል፡፡

በዚህ ሁኔታ የፀደቀው አዲስ አበባን የተመለከተው አንቀጽ ምንም እንኳን  በወቅቱ ለአጭር ጊዜ የዘለቀ ውዝግብ ቢያስከትልም፣ ጉዳዩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዋነኛ የፖለቲካ  አጀንዳ ለመሆን አልበቃም ነበር፡፡ አሁን ግን ከፖለቲካዊ አጀንዳነቱ ባሻገር አጠቃላይ የአገሪቷን መፃኢ ዕድል ከሚወስኑ ጉዳዮች እንደ አንዱ እየሆነ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት በርካቶች ከሕጋዊ መፍትሔና ክርክር ይልቅ ጉዳዩን በሰከነና በሠለጠነ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲፈታ የሚመክሩት፣ የፖለቲካዊ መፍትሔ አስፈላጊነትን ከሚመክሩት ግለሰቦች መካከል አቶ ክቡር ገና አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው፡፡ ምክንያም የሕጋዊ መፍትሔ ችግር አሸናፊና ተሸናፊ ያስቀምጣል፡፡ ፖለቲካዊው ግን በደንብ ከተሠራበት ሊያቀራርብ የሚችልበት ሁኔታ በርካታ ነው፤›› በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነው የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄን አስመልክቶ ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹በመሠረቱ አዲስ አበባ የማናት የሚል ጥያቄ በእኛ ደረጃ አንስቶ መወያየት አሳፋሪ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ‹‹አዲስ አበባ የኔ ናት›› የሚለው ትርክት ገዝፎ ዋነኛው የፖለቲካ መከራከሪያ ከመሆኑ አንፃር ‹አሳፋሪ› ቢሆንም፣ ስለጉዳዩ ተወያይቶ ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት አስፈላጊነትን ብዙዎች ይመክራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -