ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን ከንጋቱ 12፡30 ሰዓት ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጫንጮ ከተማ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ 88 ቁጥር አንበሳ የከተማ አውቶብስ፣ በተቃራኒ አቅጣጫ ይጓዝ ከነበረ ባለ ተሳቢ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ወዲያውኑ የስድስት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡
አውቶብሱ በተጠቀሰው ሰዓት ሱሉልታ ከተማ ሲደርስ ከሌላ አቅጣጫ ይመጣ ከነበረ የጭነት ተሽከርካሪ ተሳቢ ጋር የተገናኙት የአስፋልት መጠምዘዣ ላይ ሲሆን፣ ሁለቱም ሲተላለፉ ተሳቢው አውቶብሱን ስለገጨው አደጋው ሊከሰት እንደቻለ፣ የሱሉልታ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ወይንሸት ግርማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አውቶብሱ በርካታ ሰዎችን ጭኖ እንደነበር የገለጹት ኃላፊዋ፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡ በአቅራቢያው በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ዕርዳታ እንደተደረገላቸውና የተወሰኑትም ወደ አዲስ አበባ መወሰዳቸውን አክለዋል፡፡
ከሞቱት ስድስት ሰዎች ውስጥ አንዱ የአውቶብሱ ሾፌር መሆኑን ጠቁመው፣ የባለ ተሳቢው ተሽከርካሪ ሾፌር እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል ብለዋል፡፡