አውሮፓዊቷ ዴንማርክ በአርሁስ ያሰናዳችው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ተጠናቋል፡፡ ኢትዮጵያም ዳግም በሩጫው መስክ ስሟን ያደሰችበትን ውጤት ብቻ ሳይሆን በደረጃ ስንጠረዡ የዓለም ቁንጮነቷን ያሳየችበት ድል አስመዝግባለች፡፡ በድል ለተመለሰው ቡድን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በአራራት ሆቴል በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት አቀባበልና ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
በሻምፒዮናው የተመዘገበውን ድል ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም ቀዳሚ እንድትሆን ያበቋት አትሌቶቿ፣ ዛሬም በዘርፉ የማይነጥፍ ድል አድራጊ ትውልድ እንዳለ ያስመሰከረችበት መሆኑ በአስረጅነት እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ በአምስት የወርቅ፣ በሦስት ብርና በሦስት የነሐስ በድምሩ በ11 ሜዳሊያ ከዓለም አንደኛ በመሆን ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ወርቅ ላገኙ 30,000 ብር፣ ብር 20,000 ለነሐስ 10,000 ብር፣ ለዲፕሎማ 6,000 ብርና ለተሳታፊዎች 3,000 ብር እንዲሁም ለአሠልጣኞችና ሌሎች ልዑካን ቡድን አባላት እንዳስመዘገቡ ውጤት በድምሩ 650,000 ብር ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ፣ የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳውና የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል አድርገውለታል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ውጤቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሥራት የሚገባቸውን በመሥራታቸው መላው ኢትዮጵያውያን የቀደምቱን ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› እንዲያስታውሱ ብቻ ሳይሆን የውጤቱ መመለስ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ለሚደረጉ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር በማድረግ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጎን በመሆን እንደሚሠራ ማስረዳታቸውም ታውቋል፡፡
የስፖርት ከሚሽነር ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፣ ‹‹ውጤቱ እንደ አገር የምንኮራበትና ለቀጣይ ውድድሮች የበለጠ እንድንዘጋጅ የሚያደርግ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ይህንኑ ለማስቀጠል ደግሞ ኮሚሽኑ በአስፈላጊው ሁሉ ፌደሬሽኑን ለመደገፍ ዝግጁ ነው፤” ማለታቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡ በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዓቃቤ ነዋይ ወ/ሮ ሔሮዳዊት ዘለቀ በተገኘው ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተመዘገበው ውጤት የሚያኩራራ ሳይሆን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለበለጠ ውጤት ወገቡን ጠበቅ አድርጎ መሥራት እንዳለበት አመላካች እንደሆነ ያስረዳው ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም ነው፡፡
‹‹የሯጮች ምድር›› የሚለው ስያሜ ያተረፈችው ኢትዮጵያ፣ የሻምበል አበበ ቢቂላን እግር በተከተሉ አትሌቶቿ ክብሯንና ዝናዋን እንዳስጠበቀች ዛሬ ላይ መድረሷ አይሳትም፡፡ አትሌቲክሱ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በውጤት መውጣትና መውረድ መዳረጉ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
በተለይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሕጋዊ ሰውነት ካላቸው ተቋማት ራሱን በማስተዳደር ደረጃ የተሻለ ቁመናና አደረጃጀት ያለው መሆኑ ቢታመንም፣ ስፖርቱ ከደረሰበት ደረጃ አኳያ ከአትሌቶች ምርጫ፣ ከሙያተኞች ምደባና መሰል አሠራሮች ጋር በተያያዘ ክፍተቶችን ማስተካከልና የዕርምት ዕርምጃ መውሰድ ያለመቻሉ ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡
ይሁንና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በነዚህና መሰል ተግዳሮቶች ቢወቀስም ኢትዮጵያ በአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች የመልካም ገጽታዋ መገለጫ መሆኑ አልቀረም፡፡ ለዚህም ባለፈው ቅዳሜ በዴንማርክ አርሁስ በተከናወነው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ እጅግ ፈታኝ የሆነው የውድድር ዓይነት በሁለቱም ጾታ በአዋቂ ወንድና ሴቶች፣ በወጣት ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያኑ ማረጋገጫ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ አምስት የወርቅ፣ ሦስት የብርና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማስገኘት የዓለም አገር አቋራጭ ንግሥናዋንና አይበገሬነቷን ብቻ ሳይሆን በቀዳሚነት እንድታጠናቅቅ ያስቻሏት አትሌቶቿ፣ ከእነ አበበ ቢቂላ ጀምሮ አሁንም ድረስ “የአረንጓዴው ጎርፍ” መፍለቂያነቷን ያደሰችበትን ገድል ተወጥታለች፡፡
የውድድሩ ባህሪ በራሱ በውጣ ውረዶች የሚበዛበት ጭቃማና አሸዋማ በሆነው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ከተሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን የመጀመርያው የወርቅ ሜዳሊያ የተመዘገበው፣ በድብልቅ ሪሌ የቀረቡት በሴቶች ፋንቱና ቦኔ፣ በወንዶች ደግሞ ታደሰ ለሚና ከበደ እንዳለ መሆኑ ለቀሪዎቹ ለሌሎቹ አትሌቶች መነሳሳትን የፈጠረ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ድል አድራጊነት ያበሰረችው ፋንቱ ወርቁ በአጨራረስ ብቃቷ ብዙዎችን ያስደነቀ እንደነበር የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ማኅበር ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
በሰለሞን አረጋ፣ በሞገስ ጥኡማይ፣ በአንዱዓለም በልሁ፣ በእንየው መኮንን፣ በቦንሳ ዳዲና በአብዲ ፉፋ የተመራው የአዋቂ ወንዶች ተሳትፎ ምንም እንኳን በግል ወርቁን ባያገኝም፣ በቡድን የወርቅ ሜዳሊያውን አስመዝግቧል፡፡ በተመሳሳይ አዋቂ ሴቶች በደራ ዲዳና ለተሰንበት ግደይ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ በተጨማሪ ዘነቡ ፈቃዱ፣ ሃዊ ፈይሳ፣ ፀሐይ ገመቹና ፎቴን ተስፋዬ ብርቱ ፉክክር በቡድን የወርቅ ሜዳሊያ ተመዝግቧል፡፡
ለኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋዎችና ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት ወጣት ሴቶች ደግሞ፣ ዓለሚቱ ታሪኩና ፅጌ ገብረሥላሴ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ግርማዊት ገብረ እግዚአብሔር፣ መሰሉ በርሔ፣ ውዴ አያሌውና ሚዛን ዓለም ጠንካራ ፉክክር ማድረጋቸው ለቀጣይ ተስፋ ሰጪ መሆናቸው ታይቷል፡፡ በወጣት ወንዶች ሚልኬሳ መንገሻና ታደሰ ወርቁ የወርቅና የብር ሜዳሊያ በተጨማሪ በዚህ ቡድን በተካተቱት ፀጋዬ ኪዳኑ፣ ጌትነት የትዋለ፣ ገብረጊዮርጊስ ተክላይና ድንቃለም አየለ ባደረጉት ብርቱ ፉክክር በቡድን አምስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያውን አስመዝግበዋል፡፡