Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለስንቀሌ ትምህርት ቤት ተስፋ

ለስንቀሌ ትምህርት ቤት ተስፋ

ቀን:

በአምቦ ስንቀሌ ወረዳ የሚገኘው ስንቀሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አንድ የመምህራን ማረፊያና አራት ረዣዥምና ከጭቃ የተሠሩ የመማሪያ ክፍሎች አሉት፡፡ የክፍሎቹ በሮችና መስኮቶች የወላለቁ በመሆኑ ክፍታቸውን ውለው የሚያድሩ ናቸው፡፡ ግድግዳቸው በከፊል የፈረሱ፣ የፊት ልስናቸውም የረገፉ ናቸው፡፡

አንድ መረብ ኳስ ከተዘረጋበት አነስተኛ ሜዳ ውጭ አብዛኛው የትምህርት ቤቱ ግቢ ጫካ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ሦስት ተማሪዎችን ብቻ የሚያስተናግደው መፀዳጃ ቤት በጫካዎቹ መሀል ይገኛል፡፡

በተሰባበረው ወንበርና ጠረጴዛ ላይ ለሚማሩ የስንቀሌ ተማሪዎች ቤተ መጻሕፍትም ሆነ ቤተ ሙከራ ቅንጦት ነው፡፡ ውኃ ለአንድ ትምህርት ቤት ወሳኝ ቢሆንም፣ በግቢው የሚታየውና በአንድ ጊዜ አራት ተማሪዎችን የሚያስተናግደው የውኃ ቧንቧ አገልግሎት መስጠት እንዳቆመ የዛጉትና የወላለቁት መክፈቻዎቹ ይናገራሉ፡፡

በዕለቱ በግቢው ያስተዋልናቸው ተማሪዎችም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ካሉ ቤተሰቦች ስለመሆናቸው ልብሳቸውና ጫማቸው ይናገራል፡፡ ከሩቅ ስለመምጣታቸውም በተማሪዎቹ ፊት ላይ የሚነበበው ድካም ይመሰክራል፡፡

በስንቀሌ ትምህርት ቤት ከሚማሩት አንዷ ጌጤ መገርሳ ናት፡፡ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ በምትኖርበት አካባቢ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ በእግሯ መጓዝ ግድ ይላታል፡፡ ‹‹የመማሪያ ክፍላችን ከአፈር የተሠራ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ዕድሳት ያልተደረገለት በመሆኑ በላያችን ላይም እየፈረሰ ያስቸግረናል፡፡ ትምህርት ቤታችንም ከጫካ ጀርባ በመሆኑ በግድግዳው ቀዳዳዎች አይጥና እባብ ወደ ክፍላችን ስለሚገቡ ትምህርታችንን አልፎ አልፎ እናቋርጣለን፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

ባልተሟላ ሁኔታም ቢሆን ተማሪዎችን ለዓመታት ሲያስተናግድ የነበረው ትምህርት ቤት፣ ግንባታው በ18 ወራት ይጠናቀቃል የተባለ አዲስ ትምህርት ቤት ሊገነባለት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ግንባታውን የሚያከናውነው የአምቦ የማዕድን ውኃ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር በአምቦ ከተማ 80 ዓመት ቢሆነውም፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ይህ ነው የሚባል ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ የሚናሩት የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ መኮንን ‹‹ፋብሪካው ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ኮካ ኮላ ቤቬሬጅስ አፍሪካ ለሚባል የግል ኩባንያ ከተዘዋወረ በኋላ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡  

ፋብሪካው ለእነ ጌጤ እረፍት የሆነውን ስንቀሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ ለማስገንባት ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በትምህርት ቤቱ ግቢ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡ የትምህርት ቤቱ ግንባታ 18 ወራት የሚፈጅ ሲሆን፣ ሲጠናቀቅም ከ600 በላይ ተማሪዎች ይይዛል ተብሏል፡፡

ስንቀሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገነባው በ1977 ዓ.ም. ነው፡፡ በፈረቃ ከዜሮ ጀምሮ እስከ 8ኛ ክፍል ከ1,200 በላይ ተማሪዎችን ያስተምራል፡፡

አቶ ሞቱማ ከበደ ስንቀሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡ ‹‹ትምህርት ቤቱ ያለበት ችግር በርካታ ቢሆንም፣ የመማር ማስተማሩን ሒደት የሚፈታተነው ከፍተኛ የክፍል ጥበትና የውኃ ችግሮች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ በአንድ ክፍል እስከ 80 ተማሪዎች በተጨናነቀ ሁኔታ እንደሚማሩም ገልጸዋል፡፡ ካለው የመማሪያ ክፍሎች ጥበት ባሻገርም፣ የመምህራን ቁጥር ከ15 ያልዘለለ መሆኑ ሌላው ፈተና ነው፡፡ ውኃ አቅርቦት ባለመኖሩ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ጀርባ ወደሚገኝ ወንዝ ወርደው ጥማቸውን ያስታግሳሉ፡፡ ይህም በብዛት ለሕመም እየዳረጋቸው ከትምህርት ገበታቸው እንዲቀሩ ሲያደርግ የኖረ ችግር ነው፡፡ ‹‹ባለብን የመምህራን እጥረትም የስምንተኛ ክፍል እንግሊዝኛ መምህር ባለመኖሩ ተማሪዎችን ወደ ሌላ ትምህርት ቤት በመላክ ለማስተማር ተገደናል፡፡ በትምህርት ቤቱ ምንም ዓይነት ኮምፒውተር፣ ቤተ ሙከራና ቤተ መጻሕፍት ባመኖሩ ልጆቹ ለቴክኖሎጂ ባዳ ናቸው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ እንደገለጹት፣ ፋብሪካው ከኅብረተሰቡ እየቀረቡ ከሚገኙ የድጋፍ ጥያቄዎች በመነሳት የፋብሪካው ሠራተኛ ልጆች ለሆኑ 50 ተማሪዎች በየወሩ 500 ብር እየከፈለ ዩኒቨርሲቲ ያስተምራል፡፡ ከ550 ሺሕ ብር በላይ በማውጣት ትምህርት ቤቱን ጨምሮ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የውኃና የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ በሦስት መቶ ሺሕ ብር ለከተማዋ ወጣቶች የመሥሪያ ቦታ ሼድ ለመገንባትም ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቋል፡፡ በቅርቡም ከጌዴኦ ተፈናቅለው በአምቦ ከተማዋና አካባቢው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከሁለት መቶ ሺሕ ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡

አምቦ የማዕድን ውኃ በ1930 ዓ.ም. በግለሰብ የተመሠረተ ሲሆን፣ ከደርግ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በመንግሥት ሲተዳደር ቆይቶ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከኮካ ኮላ ቤቬሬጅ አፍሪካ ለሚባል ዓለም አቀፍ የግል ኩባንያ ተዘዋውሯል፡፡ በሦስት መቶ ሰባ አራት ሚሊዮን ብር ወጪ ማስፋፊያ በማድረግ ከ510 በላይ ሠራተኞችን በቋሚነትና ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሠራ ይገኛል፡፡ ስምንት የተለያዩ ጣዕም ያላቸውን ምርቶችን ሲያመርት በዓመት ከ72 ሚሊዮን በላይ የታሸጉ መጠጦችን እንደሚያቀርብ ከፋብሪካው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኮካ ኮላ ቢቬሬጅ አፍሪካም በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በጋና፣ በሞዛምቢክ፣ በታንዛኒያ፣ በናሚቢያና በደቡብ አፍሪካ ባሉት ፋብሪካዎች ምርቱን ያቀርባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...