‹‹ባትፈልገኝ እፈልግሃለሁ›› መጽሐፍ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በፕሬዚዳንት መሐመድ ዚያድ ባሬ ትመራው የነበረችው ሶማሊያ ‹‹ታላቋ ሶማሊያን›› መገንባት ህልሟን ዕውን ለማድረግ በ1969 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ ወራሪ ጦርዋን አዝምታ በምሥራቅና በደቡብ ክፍል የተወሰኑ ቦታዎችን ይዛ ነበር፡፡
በአጭር ጊዜ የተሰበሰበው የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያን ወረራ ሲቀለብስ በዚያ ጦርነት ከተካፈሉ የአንደኛው አብዮታዊ ሠራዊት የጦር ክፍሎች መካከል የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ሊባኖስ ገዳሙ የነበረበት የሦስተኛ ፓራ ብርጌድ አንዱ ነበር፡፡
በየካቲት ወር 1970 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሠራዊት የካራማራን ተራራ ከሶማሊያ ጦር ካስለቀቀ በኋላ ወደፊት በመገስገስ አብዛኛውን የኦጋዴን አውራጃዎችን በቁጥጥር ሥር አድርጓል፡፡
ከእዚህ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል መደበኛ ጦርነት ስለመደረጉ በወቅቱ አይነገር እንጂ፣ ሶማሊያ በከባድ መሣሪያዎች የተጠናከረ ወራሪ ጦሯን አዝምታ ዋርደር ላይ ለወራት የዘለቀ ከባድ ጦርነት አካሂዳ ነበር፡፡ በእዚህ ባልተነገረለት የዋርደር ጦርነት በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ፓራ ኮማንድ ሻለቆችን ጨምሮ የነበረው የሠራዊት ብዛት ከ2,500 መቶ የሚበልጥ አልነበረም፡፡ ሶማሊያ ግን ከ12,500 በላይ ወታደሮችን ነበር ያሰማራችው፡፡
ይህንን ያልተናገረለትን የዋርደር ጦርነት በተመለከተ የሚያስነብበው የሊባኖስ ገዳሙ መጽሐፍ ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በ7፡30 ሰዓት በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ይመረቃል፡፡
በሌላም በኩል የጀርመን ባህል ማዕከል ከእናት ማስታወቂያ ጋር በመተባር ያዘጋጀው የመጽሐፍ ውይይት፣ እሑድ መጋቢት 29 ቀን ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል፡፡ ለውይይት የሚቀርበው የዳግማዊ አሰፋ ‹‹አዲስ ሕይወት›› ሲሆን፣ አቅራቢው አንዱዓለም አባተ (የአፀደ ልጅ) መሆኑ ታውቋል፡፡