Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየፈረሰውን ባለቅርሱን ሕንፃ ወደነበረበት ለመመለስ እንቅስቃሴ ተጀመረ

የፈረሰውን ባለቅርሱን ሕንፃ ወደነበረበት ለመመለስ እንቅስቃሴ ተጀመረ

ቀን:

‹‹አፍራሹ ከእንግዲህ እንደማይነካው ማረጋገጫ ይስጥ››

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን

በቅርቡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ባመዛኙ ያፈረሰውን በቅርስነት የተመዘገበው የፊታውራሪ ዐምዴ አበራ ካሣ መኖሪያ ቤት ወደ ነበረበት ለመመለስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

ኃላፊነት የተሰጠው በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሚመራው የባለሙያዎች ቡድን ሕንፃውን መልሶ ለማቆም እየመከረበት ይገኛል፡፡ የባለሥልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጉዳቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ባይቃኝም ሕንፃው ሙሉ ለሙሉ ባለመውደቁ ማጠናከሪያ አድርጎ መልሶ ለማቆም ዕድል አለው፡፡

ግመታው ባስቸኳይ እንደሚሠራ ያወሱት ዳይሬክተሩ፣ ከእንግዲህ በኋላ አፍራሹ ኃይል ሕንፃውን እንደማይነካ ማረጋገጫ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ቅርሱ መከበሩ በሕግ አግባብ መረጋገጥ አለበት በማለት አሳስበዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ለመወያየት ቀጠሮ መያዙንም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ባሰማራው አፍራሽ ኃይል የፈረሰው የፊታውራሪ ዐምዴ አበራ ካሣ መኖሪያ ቤት ከዘጠና ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው፡፡

በቅርስነት የተመዘገበውን ይህ ሕንፃ ሲያፈርስ የነበረውን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አፍራሽ ኃይል ሕንፃው ሙሉ ለሙሉ ከማጥፋቱ በፊት የአካባቢው ነዋሪና የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አስተዳደር ባደረጉት ጥረት የማፍረስ ተግባር ማስቆማቸው በወቅቱ ተዘግቧል፡፡

በቦታው ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ስለሺ ግርማ ጋር የተገኙት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት በማኅበራዊ ገጻቸው እንዳስታወቁት፣ በዶዘር የፈረሰውን ይህንን ቤት ጨምሮ፤ በከተማዋ ያሉ 400 ያህል በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶችን፣ የግል ባለሀብቶች ጠግነው ሥነ ጥበባዊ ሥራዎችን እንዲያከናውኑባቸው የማስተላለፍ ተግባር በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ተጀምሮ ነበር፡፡  

‹‹ቅርስ ማለት ከአሮጌ ቤት፣ ሐውልት፣ ዋሻ በላይ የሕዝብ ማንነት ህያው ዋቢ መሆኑ ያልገባቸው ወይም እንዲገባቸው ያልፈለጉ አሁንም የታሪክ አሻራን መደምሰሱን ቀጥለውበታል። በታሪክ ሞት ላይ ቤት ሠርቶ፣ አከራይቶ ለመጠቀም የቋመጠ ተቋም በደብዳቤ ጭምር ማሳሰቢያ ተሰጥቶት ሳለ ማሰብ ሳይፈልግ ይኸው የሚታየውን አድርጓል። አንላቀቅም!›› ያሉት የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ነቢዩ ባዬ ናቸው፡፡ ይህም ጋለሪ እንዲሆን ታስቦነበረው የፊታውራሪ ዐምዴ አበራ ካሣ ቤት መፈረሱን ተከትሎ የተናገሩት ኃይለ ቃል ነው፡፡

እንደ አቶ ሠርፀ አገላለጽ፣ የማፍረስ ድርጊቱ ሙሉ በሙሉ ቆሞ፣ በሕግ የሚጠየቀው አካል ሊጠየቅ፣ በተመሳሳይ መልኩ፤ በፌዴራል ቤቶች ኤጀንሲ ‹‹በአዋጅ .47/67 በደርግ የተወረሱ›› በተባሉ በቅርስነት በተመዘገቡ ቤቶች ላይ የማፍረስ ዕርምጃ እንዳይወሰድ፣ እንዲሁም በከተማዋ በተለያዩ ይዞታዎች በሚገኙ 440 በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች ህልውና ላይ ከፍተኛ ምክክር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ የጀመሩት ይህ ውይይት፣ የፌዴራሉን ቤቶች ኮርፖሬሽን ቦርድ ባሳተፈ መልኩ መልካም መግባባት ላይ ደርሶ ቅርሶችን እንደሚታደግ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፕላን ኮሚሽንና የባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ባዘጋጁት ዐውደ ጥናት፣ የቅርስ መካናትንና ቤቶችን በከተማዋ ፕላን ላይ ለማመልከት ለረጅም ጊዜ በምሁራን ሲጠና የነበረው ጥናት ቀርቦ ጥልቅ ውይይት ተካሂዶበታል። የጥናቱ ውጤት ተጠናቆ ሥራ ላይ ሲውል፣ የትኛውም ዓይነት የከተማ ግንባታ ፕሮግራም፣ በፕላኑ የሚመላከቱትን መካናተ ቅርሶች ህልውና ባከበረ መልኩ እንደሚከናወንም አቶ ሠርፀ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የፊታውራሪ ዐምዴ አበራ ካሣ መኖሪያ ቤት በቅርስነት መዝገብ ዝርዝር ውስጥ የተመዘገበ በክፍለ ከተማው ውስጥ በቅርስነት ከተያዙ 51 ቅርሶች መካከል አንዱ መሆኑን ያስታወቀው የየካ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበበ ከተማ በቅርስነት ከተያዙ ታሪካዊ ግንባታዎች አንዱ እንደሆነና ለምን እንደፈረሰ በኢቢሲ የተጠየቀው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቱ በቅርስነት ስለመመዝገቡ ምንም ዓይነት መረጃ የለኝም ማለቱ ይታወሳል፡፡

የፈረሰው ታሪካዊ መኖሪያ ቤት 7 ክፍሎች፣ 12 በሮች፣ 8 መስኮቶች ያሉትና በጣውላና በጥርብ ድንጋይ የተገነባ መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...