Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የመም ውድድሮች በመጥፋታቸው ታዳጊዎች ወደ ማራቶን ለመግባት እየተገደዱ ነው›› አቶ ሀጂ አዴሎ፣ የረዥም ርቀት አሠልጣኝ

የቀድሞው የረዥም ርቀት አትሌት በአርሲ ክፍለ አገር ጭላሎ አውራጃ ጢዮ ወረዳ ደንካ ካበረቻ ቀበሌ ውስጥ ነው የተወለደው፡፡ ስመ ጥር የሆኑ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችው አርሲ ሩጫን ባህል ማድረጓ የቀድሞውን አትሌት የአሁኑ አሠልጣኝ አድርጋዋለች፡፡ ሀጂ አዴሎ የአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በመወከል ከኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጋር በወረዳ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ በመጀመር በአፍሪካና አውሮፓ መድረኮች ላይ መካፈል ችሏል፡፡ ከሃያ ዓመታት በላይ በአትሌቲክስ ውስጥ ማሰለፍ የቻለው አሠልጣኝ ሀጂ ከ115 በላይ የአገር ውስጥ የውጭ የረዥም ርቀት አትሌቶችን በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡ ከወቅታዊው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ እንቅስቃሴና የአምስት ሺሕ ሜትር ከዳይመንድ ሊግ የመሰረዝ ውሳኔ ጋር በተያያዘ ከዳዊት ቶሎሳ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡– በተለያዩ ውድድሮች በረዥም ርቀቱ ከተካፈልክ በኋላ በጤና እክል አቋርጠህ ወደ አሠልጣኝነቱ ገብተሃል፡፡ ወደ አሠልጣኝነቱ የገባህበት ሁኔታ አስታውሰን?

አቶ ሀጂ፡እ.ኤ.አ. 1998 እስከ 2002 ባለው ጊዜ ውስጥ ኦስትሪያ ማራቶንና በፈረንሣይ ውድድሮች ካደረግኩ በኋላ በአትሌቲክስ መቀጠል ስለተሳነኝ ወደ አሠልጣኝነቱ ለመግባት ወሰንኩ፡፡ አሠልጣኝነቴን ስጀምር ፈይሳ ቱሴ ከሚባል አትሌት ጋር ነበር ሀ ብዬ ጀመርኩ፡፡ ሥልጠናዬንም ረዥም ርቀት ላይ አደረግሁ፡፡ በአሠልጣኝነቱም ከ17 ዓመት በላይ ማሳለፍ ችያለሁ፡፡ በርካታ አትሌቶችንም ከግል ጀምሮ በማሠልጠን ለብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ ችያለሁ፡፡ በግላቸውም በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተወዳድረው ድንቅ ብቃት ያተረፉ አትሌቶች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡– የአትሌቲክስ አሠልጣኝነት መመዘኛው ምንድነው? በሩጫው ያሳለፈ ሁሉም አትሌት አሠልጣኝ መሆን ይችላል?

አቶ ሀጂ፡አሠልጣኝነት ቀላል አይደለም፡፡ የራሱ የሆነ ጥረትና ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ሥራህና ሥልጠናህ ሰው ላይ ነው፡፡ እያንዳንዱን አትሌት ብቃቱን መለየት ይጠበቅበታል፡፡ ለእኔ የአሠልጣኝነት ሕይወት ጉዞ በአካባቢዬ የነበረው የአትሌቲክስ ባህል ትልቅ አስተዋጽኦ አደርጎልኛል፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሁለተኛ ደረጃ የአሠልጣኝነት የትምህርት ደረጃ ወስጃለሁ፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን ተፈትኜ ያለፍኩበት ዘርፍ ስለሆነ ከባድ አልሆነብኝም፡፡ ማሠልጠን ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ አትሌቶችን ለድል ማብቃት ችያለሁ፡፡ አሁን ላይ በማራቶን ብቻ ከ70 በላይ እንዲሁም በአጠቃላይ ከ115 በላይ አትሌቶችን እያሠለጠንን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡– ከጊዜ ወደ ጊዜ የጎዳና ሩጫ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ በርካታ የውጭ አገር ማናጀሮችና አሠልጣኞችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን በማፈላለግ እያሠለጠኑ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የምትሰጠው ሐሳብ ካለ?

አቶ ሀጂ፡የቀድሞውን የአትሌቲክስ ጊዜና የአሁን የአትሌቲክስ ዘመን በጣም ልዩነት አለው፡፡ በእኛ ጊዜ በርካታ የትራክ (መም) ውድድሮች ነበሩ፡፡ አሁን ላይ አትሌቶች ወደ ጎዳና ፈታቸውን ያዞሩበት ዋንኛ ምክንያት አንደኛ የመም ውድድሮች እየተመናመኑ በመምጣታቸው ሲሆን ሁለተኛ የአገር አቋራጭ ውድድር ቁጥር መቀነስ ነው፡፡ እኔ በግሌ የማውቀው በአውሮፓ በየሳምንቱ የሚደረግ አገር አቋራጭ ውድድር ነበር፡፡ አሁን ምንም ዓይነት የውድድር አማራጭ የለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም አትሌት ወደ ጎዳና ለማተኮር ተገዷል፡፡ ሌላው ማናጀሮች መብዛታቸው ለአትሌቶቻችን ጥሩ ነው፡፡ ዋናው ነገር የማናጀሮቹ ችሎታ እስከምን ድረስ ነው የሚለውን መገምገም ነው፡፡ ስለዚህ የጎዳና ውድድሮች ላይ ተወዳዳሪዎቹ መብዛታቸው የውድድር እጥረት በመኖሩ ነው፡፡ የአትሌት ቁጥርና የውድድር መጠን ተመጣጣኝ ሊሆን አልቻለም፡፡ በአጭር ርቀት ላይ ብዙ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩንም በውድድር ላይ ማሳተፍ አቅማችን ውስን ነው፡፡ በተቃራኒው በጎዳና ውድደሮች ላይ ግን በርካታ አትሌቶችን ማሳተፍ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡– ከወራት በፊት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማኅበር የ5,000 ሜትር ውድድርን ከዳይመንድ ሊግ መቀነሱ ይታወሳል፡፡ ውሳኔውን እንዴት አገኘኸው?

አቶ ሀጂ፡በእውነቱ ከሆነ ውሳኔውን ስሰማ በጣም ነው ያስደነገጠኝ፡፡ ምክንያቱም 5,000  እና 10,000 ሜትር ርቀቶች በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የበላይነቱን የወሰዱ መሆናቸውን እንገነዘባለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ዛሬ 5,000 ሜትር ከውድድር ለማስወገድ ከውሳኔ ያደረሱት ከዚህ ቀደም የ10,000 ሜትር ውሳኔን ዝም ብለን መቀበላችንን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን ዳግም ሊያጤኑት ይገባል ባይ ነኝ፡፡  

ሪፖርተር፡– ምክንያቱ ምንድነው ትላለህ? ችግሩስ?

አቶ ሀጂ፡የመጀመርያ ምክንያታቸው ከማስታወቂያ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የውድድሩ ጊዜ ርዝመት ለቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች አመቺ ያለመሆን ከሚል ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ርቀቱ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ብቻ የበላይነት መወሰዱ ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ አንድ አትሌት ወደ ጎዳና ሩጫ ለመግባት የመም ውድድሮችን እንደ መሸጋገሪያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ውሳኔው በዚህ ከፀና አንድ አትሌት ያለ ዕድሜው ማራቶን ለመሮጥ ይገደዳል ማለት ነው፡፡ አሁን ላይ አማራጮች ባለመኖራቸው ታዳጊ አትሌቶች ቀጥታ ወደ ግማሽ ማራቶን ውድድሮች ላይ ለመግባት እየተገደዱ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማኅበር ውሳኔውን ዳግም መመልከት ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡– ወቅታዊውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እንቅስቃሴ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ሀጂ፡በአጠቃላይ ስንመለከት ጥሩ ነገሮችም አሉ፣ መጥፎ ነገሮችም አሉ፡፡ ብዙ አትሌቶች አሉ፣ ውጤትም አለ፡፡ ግን እንደ ቀድሞ አትሌቶች በርቀቱ ላይ ነጥረው የሚታዩ የሉም፡፡ የአሁኖቹ አትሌቶች ውድድሮችን የማደባለቅ ችግር አለባቸው፡፡ የመም አትሌቶች ሆነው ወደ ግማሽ ማራቶንና ማራቶን ላይ የሚሳተፉ አሉ፡፡ ይኼ የተፈጠረው ከውድድር እጥረት የተነሳ ነው፡፡ ግን እንደ አገር ስሙ ገኖ የሚሠራና በበላይነት ያጠናቀቀ ብለህ የምትተማመንበት አትሌት የለም፡፡

ሪፖርተር፡– የረዥም ርቀቱ ውሳኔ ከኬንያ ቀጥሎ ይጎዳል ተብሎ የታሰበው ኢትዮጵያን ነው፡፡ በመካከለኛና አጭር ርቀት ውጤታማ መሆን አትችልም ብሎ መደምደም ይቻላል?

አቶ ሀጂ፡ማንኛውንም ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከተሠራ የማይቻል ነገር የለም፡፡ ግን ደግሞ በርቀቱ ተመሳሳይ ውጤት ያላቸው በርካታ አትሌቶች ቢኖሩ በየትኛው ውድድር ላይ እናወዳድራቸዋለን፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ርቀት ላይ ቢሠራ ውጤት ማምጣት ይችላሉ፡፡ ለዚህም ነው በ800 እና በ1500 ሜትር ርቀት ላይ ውጤታማ እየሆኑ የመጡት፤ ግን እንደ ረዥም ርቀት በርካታ ውድድሮችን ማግኘት ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ከአገር ውስጥ አትሌቶች በተጨማሪ የውጭ አገር አትሌቶችን በተለይ ከቻይና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶችን ተቀብለህ በማሠልጠን ላይ ትገኛለህ፣ ስለጉዳዩ ብታብራራልን?

አቶ ሀጂ፡ላለፉት አራት ዓመታት ከቻይና አትሌቲክስ ፌዴሬርሽን ጋር ስንሠራ ቆይተናል፡፡ በቅርቡ ግን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ስምንት የቻይና የረዥም ርቀት አትሌቶችን በማሠልጠን ላይ እንገኛለን፡፡ የውጭ አገር አትሌቶች ከእኛ አትሌቶች ጋር ተፎካካሪ መሆናቸው መልካም ነው፡፡ በእኔ አስተያየት በረዥም ርቀት ላይ በአፍሪካ ላይ ብቻ የሚደርሰው ተፅዕኖ እየቀነሰ ይመጣል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ከእኛ ጋር የሚፎካከሩ የተለያዩ አገሮችን አትሌቶች ቁጥር ማብዛት ከቻልን ውድድሩን ማቆየት ያስችለናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነዚህ አትሌቶች እኔ ጋ ከመጡ ጀምሮ ከ14 ደቂቃ እስከ 16 ደቂቃ ማሻሻል ችለዋል፡፡ በቅርቡ ቻይና በተከናወነ ማራቶን ውድድር ላይ በመሳተፍ 2፡10፡31 በመግባት አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ የቻለን አትሌት ለኦሊምፒክ ከወዲሁ እንዲመርጡ አስቸለናቸዋል፡፡ ስለዚህ ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...