Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርትንሽ ትንሽ መሠልጠን ወይስ ጨርሶ መሰይጠን?

ትንሽ ትንሽ መሠልጠን ወይስ ጨርሶ መሰይጠን?

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

በዘመናችን የዴሞክራሲ ልምምድ የሰው ልጆችን ያሠለጥናል እንጂ ያሰየጥናል ተብሎ አይታመንም፡፡ ሰሞኑን አማራ ክልል ውስጥ በባህር ዳርና በደሴ ከተሞች የሆነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው ቢባል ፈጽሞ መሳሳት አይሆንም፡፡

ይልቁንም እሑድ መጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ በለየለት የማይምነት መንጦላእት ተጋርዶ የዘቀጠ ተቀባይነትን በሐሳብ ልዕልና ሳይሆን፣ በጦር መሣሪያ ጭምር በታገዘ ጡንቻ ከፍ ለማድረግ የተወጠነው አደገኛ የድኩማን ፕሮጀክት ተከታይ አለማግኘቱ እንጂ ፍፃሜው አስከፊ በሆነ ነበር፡፡

በእንቦጭ በሽታ ተይዞ የድረሱልኝ ጩኸት ማሰማት ከጀመረ ውሎ ያደረውን የጣና ሐይቅን ተንተርሳ የተቆረቆረችው ባህር ዳር በአገራችን ውስጥ በማደግ ላይ ከሚገኙት ውብና ፈርጥ ከተሞች አንደኛዋ ስትሆን የክልሉ መንግሥት መቀመጫ መዲናም እርሷው ነች፡፡

እንደ ብዙዎቹ መሰልና አቻ የአገሪቱ ከተሞች ሁሉ አልፎ አልፎ ሳታስበው በተናጠል የሚንጧት ደረቅ የወንጀል ድርጊቶች ባያጧትም ከተማይቱ በሰላሟ ተደራድራ አታውቅም፡፡ እሑድ መጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽና አካባቢው የተመሰከረው ሀቅም ይኸው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በዕለቱ አርበኞች ግንቦት ሰባት የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲ አገር ሰላም ነው ብሎ በማመን፣ ከአባላቱና ከደጋፊዎቹ ጋር ለመወያየት በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ ቀጠሮ ይዟል፡፡ ድርጅቱ ይኼንን ያደረገው በጨዋ ደንብ መሠረት ዕቅዱን በቅድሚያ ለመንግሥት አሳውቆና አግባብ ባላቸው የከተማይቱ ባለሥልጣናት በኩል ተፈቅዶለት ነው፡፡

ሆኖም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ወደተባለው አዳራሽ መግባትና ለስብሰባው መታደም እንደ ጀመሩ የዚያን መድረክ መጠራት ይቃወማሉ የተባሉ ወጣቶች ምግባረ ብልሹነት በተጠናወተው ሁኔታ ደርሰው ሁከት በማነሳሳት፣ የመቀመጫ ወንበሮችን በመሰባበርና በሥፍራው የተገኙትን የፖለቲካ አመራሮች ከፍ ያለ ጩኸት እያሰሙ በመዝለፍ የስብሰባው መርሐ ግብር በታቀደው መንገድ እንዳይካሄድ አድርገዋል፡፡

እነዚህን አፈንጋጭ ወገኖች ማን ወደዚያ የተከበረ የምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ ሕንፃ እንደላካቸውና ምን ዓላማ አንግበው እንደመጡ እስካሁን በግልጽ አይታወቅም፡፡ ከርቀት በጦር መሣሪያ ተኩስ ሳይቀር ይደገፍ ለነበረው ለዚህ የሽብር አድራጎት ኃላፊነት የወሰደ አካልም እስካሁን የለም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ በአካባቢው የተሰማሩ የፀጥታ ኃይሎች ባልታሰበና ባልተገመተ መንገድ ሊስፋፋና የንፁኃንን ሕይወት ያላግባብ ሊቀጥፍ ይችል የነበረውን አደጋ፣ ከሕዝቡ ጋር ተረባርበው በፍጥነት ለመቆጣጠር በመቻላቸው ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻ በቂና አርኪ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ ሁከቱን በቀጥታ የፈጠሩትን ጨምሮ ከትርምሱ በስተጀርባ ያሉት የቅርብና የሩቅ አቀናባሪዎች ሁሉ፣ በሕግ አስከባሪዎች መታደንና በአፋጣኝ ተይዘው ለፍርድ መቅረብና መጠየቅ አለባቸው፡፡

ሁከት ፈጣሪዎቹና ተከታዮቻቸው በወቅቱ አንዳንድ ወጣ ያሉ የተቃውሞ መልዕክቶችን ያሰሙ እንደነበር፣ እግር ጥሏቸው በአካል የተገኙና ትዕይንቱን በቀጥታ የታዘቡ ነግረውኛል፡፡

‹‹ግንቦት ሰባት ፀረ አማራ ድርጅት ነው››፣

‹‹አማራው ብቻ በብሔር እንዳይደራጅ አበክሮ ይሰብካል››፣…

የሚሉ ዓይነቶች፡፡

በመሠረቱ እነዚህንና ከእነዚህም የበዙ ሌሎች መፈክሮችን በማሰማት ተደማጭነትን ማግኘት ከፈለጉ ዱላ መምዘዝና ጥይት መተኮስ ወይም በአጃቢዎቻቸው ማስተኮስና ያን ያህል የሰላሙን ድባብ መረበሽ ሳያሻቸው፣ ስብሰባውን በበጎ ፈቃድ መቀላቀልና ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ ድረስም ቢሆን ማስተጋባት በቻሉ ነበር፡፡ እነሱ የመረጡት ራስን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለውንና የሚገባውን ጡንቻ ሆኖ መገኘቱ ግን ብዙኃኑን ክፉኛ አሳዝኗል፣ አበሳጭቷልም፡፡

እጅግ በዘመነው ዓውዳችን የሐሳብ ልዕልናን በጡንቻ የበላይነት ለመገዳደር መሞከር አስጸያፊ ብቻ ሳይሆን የሽንፈት መጀመርያው መሆን አለበት፡፡ ዴሞክራሲ እኮ የራሳችንን ሳይሆን የሌሎችን ትችትና አስተያየት እንደ ወረደ ለማዳመጥ የምንጠቀምበት ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡

የዘመናዊ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነው የሰው ልጅ በደመ ነፍስ ሥሌት ሳይሆን፣ ለሕግ እየተገዛና በአመክንዮ እየተመራ መኖር ይገባዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከሌሎች ታላላቅና ታናናሽ የዓለም ፍጥረታት ይልቅ በቶሎና በቀላሉ ከምድረ ገጽ ሊጠፋ መቻሉ ላይ ልንጠራጠር ከቶ አይቻለንም፡፡ የራሱን የረቀቁ መግደያም ሆነ ማቁሰያ መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች ያመረተ፣ ወይም በገንዘቡ የሸመተና ያከማቸ ጉራማይሌ ፍጡር እሱ ብቻ ነውና፡፡

ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በእንግድነት የተገኙትን ወገኖች በዚህ ደረጃ ማዋከብና የመጡበትን ተልዕኮ ሳያሳኩ እንዲመለሱ ማድረግ አሁን ምን ይሉታል?

ነፃነት የሰው ልጅ ማዕከላዊ ሰውነት የተገነባበት ዓይነተኛ ጥሬ ዕቃ ነው፡፡ እሱን በሚገባ ካልተንከባከብነው በስተቀር ሰው ራሱ በፅኑ ይታመማል፡፡ ለሕመሙ ደግሞ በቀላሉ ፈውስ ስለማናገኝለት ይበልጥ የሚጠቅመን የቅድመ ጥንቃቄ ዕርምጃው እንደሆነ፣ አያሌ የሰብዓዊ መብትም ሆነ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ጠበብት አጥብቀው ይመክራሉ፣ ያስተምራሉ፡፡

በግለሰብ ደረጃም ሆነ እንደ ቡድን ተደራጅቶ ሐሳብን በንግግር፣ በጽሑፍ ወይም በሌላ በማናቸውም አመቺ ዘዴ የመግለጽ ነፃነት ያልተካተተበት ግልብ ዴሞክራሲ አዕምሮ ያልታቀፈበትን ባዶ የራስ ቅል ይወክላል፡፡ ይህ በሚገባ እየታወቀ ቀድሞ በለመድነው መንገድ ለመጓዝ የምንመርጠው፣ ይህ ዓይነቱ የተወላገደ አካሄድ ከቶ የጤንነት ሊሆን አይችልም፡፡

በዚህ ረገድ የተጣመመውን ለማቃናትና ለዘላቂ ሰላም ጠንቅ የሆነውን አደገኛ ስብራት ፈጥኖ ለመጠገን፣ ሁላችንም ባለን አቅም መረባረብ ያለብን ቢሆንም የመንግሥት ኃላፊነት የአንበሳውን ድርሻ መውሰዱ አይቀርም፡፡

አበው ‹‹ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው›› ይሉናል፡፡ አምባገነናዊ አመለካከትም በአመክንዮ የተቃኘ አዕምሮን በሙሉ አቅሙ ተጠቅሞ ሰላማዊ ሞጋቾችን ፊት ለፊት ከመገዳደር ይልቅ፣ ተቃዋሚን በጦር መሣሪያ አስፈራርቶ ፀጥ በማሰኘት ወይም አንገት በማስደፋት አብልጦ ይተማመናል፡፡ በእርግጥ ይህ የብርቱዎች ሳይሆን የፈሪዎች መንገድ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ድባብ ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ኖረው አልኖረው ሐሳባቸውን በአደባባይ ወጥተው በድፍረት ለሚገልጹ ብርቱዎች እንጂ፣ ጠባብ ፍላጎቶቻቸውን በኃይል እንጭናለን ብለው ለሚውተረተሩ ዓይን አፋሮች ሥፍራ የለውም፡፡

በየትኛውም ደረጃ የተዋቀረ መንግሥት ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ዓይነተኛ ጠንቆች በመሆናቸው፣ እንዲህ ያሉትን ፅንፈኞች መታገስም ሆነ ማባበል አይኖርበትም፡፡ ይልቁንም የሕግን ልዕልና በመናቅና ለጠቅላላው ሕዝብ ጥቅም ሲባል የተዘረጋውን አቃፊ ሥርዓት በማናለብኝነት በመዳፈር የፈጸሙት ወንጀል በትኩሱ ተጣርቶ ሳይጠየቁ ከመቅረታቸው የተነሳ፣ ተቋማዊ አቅሙን የተፈታተኑ መስሎ እንዳይሰማቸውና ለተጨማሪ ወንጀል ስንቅ ሆኗቸው እንዳይበረታቱ ዝርዝር ጉዳዩን በትጋት ማጣራትና ጥፋተኞችን ለይቶ በአግባቡ እንዲቀጡ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት መሥራች አባል ናት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 12 ቀን 1984 በውሳኔ ቁጥር 39/11 ሰላምን በሚመለከት አንድ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ የሰላማዊ ኑሮ መብት መግለጫ (The Declaration of the Right of Peoples to Live in Peace) በመባል የሚታወቀው ይህ ታሪካዊ ሰነድ አራት ቁልፍ ጉዳዮችን አካቶ ይዟል፡፡

በሰነዱ አንቀጽ አንድ ሥር የሰፈረው ኃይለ ቃል ‹‹የምድራችን ሕዝቦች ሁሉ የማይሸራረፍ በሰላም የመኖር መብት እንደተጠበቀላቸው›› ያውጃል፡፡ እንዲህ በማለት ብቻ ሊያበቃ ያልወደደው ተጠቃሹ የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ “የዜጎቹን በሰላም የመኖር መብት በማስከበርና ደኅንነታቸውን በመጠበቅ ረገድ ቀዳሚውን ኃላፊነት የሚወስደው ታዲያ፣ እያንዳንዱ መንግሥት ‹‹ራሱ ነው›› ሲል በማያሻማ ድምፀት ደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

በየትኛውም ደረጃ የተቋቋመ ማናቸውም ዓይነት መንግሥት ቢሆን በተፈጥሮው ለሥልጣኑ ቀናዒ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ የተነሳ አስተዳደራዊ ሥልጣኑ በሚያርፍበት የግዛት ወሰን አንድ የወንጀል ድርጊት ተፈጽሞ ሲያገኝ፣ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በመያዝና ለፍርድ አቅርቦ ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲቀበሉ ለማድረግ በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ሁሉ የዜጎችን ሁለንተናዊ ትብብር መሻቱና መጠየቁ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ ዘግናኝ ወንጀሎች በአደባባይ ሲፈጸሙ እየተመለከተና አንዳንዴም በራሳቸው በሰለባዎቹ በኩል እየተነገረው እርሱም እንኳ እንደ ተራ ዜጎች ድርጊቱን በማውገዝና ልባዊ የሐዘን መግለጫዎችን በማውጣት ከተወሰነና በዚሁ ብቻ ለጊዜው የረካ መስሎ ከታየ ግን፣ በሕገ መንግሥት ደረጃ የተረጋገጠ መሠረታዊ የመጠበቅ መብት ካላቸው ዜጎች ፍላጎት ጋር በቀጥታ መላተሙ አይቀርም፡፡

ስለሆነም አርበኞች ግንቦት ሰባት በባህር ዳር የጠራውን ሕዝባዊ ስብሰባ በቀላሉ ለማደናቀፍ የተሳካለት የጉልበተኞች ጥቃት በተጠቀሰው የፖለቲካ ድርጅት ላይ የተቃጣ ብቻ ሳይሆን፣ የከተማይቱ ነዋሪዎች ባላቸው ሰላማዊ የመኖር መብት ላይ ጭምር የተነጣጠረ ከባድና ነውረኛ የወንጀል ድርጊት በመሆኑ ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ዱካ በቁርጠኝነት ተከታትሎ የሚደርስበትንና ለሕዝብ ይፋ የሚያደርገውን ውጤት ማኅበረሰቡ በንቃትና በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቀዋል፡፡ በተቃራኒው የተጀመረው ክትትል ተኮላሽቶ ተጠርጣሪዎች በአፋጣኝ ካልተያዙና የዕኩይ ተልዕኳቸው መነሻ ሳይታወቅ ተዳፍኖ ከቀረ ግን፣ ለአመፀኞቹ የልብ ልብ እንደሚሰጣቸው ቢገመትም ከዚያ ይልቅ ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ ያላቸውንና ሊኖራቸው የሚገባውን አመኔታ በእጅጉ እንደሚሸረሽረው አንድና ሁለት የለውም፡፡

ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ በወትሮው አጠራር ‹‹የወሎ ኅብረት’ የተሰኘውን ድርጅት ለመመሥረት ደሴ ከተማ ላይ በተጠራና በታደመ ሌላ መሰል የዜጎች ስብስብ ላይ እንዲሁ የወረደው ዱብ ዕዳ፣ አርበኞች ግንቦት ሰባትን ባህር ዳር ላይ ካጋጠመው ቢብስ እንጂ የተሻለ አልነበረም፡፡ ያንን ሰላማዊና ሕጋዊ የሲቪክ እንቅስቃሴ በቀዳሚነት ያዘጋጁትና የመሩት ወገኖች በጠራራ ፀሐይ ተደብድበዋል፣ ንፁኃን ተንገላተዋል፣ ሲያወሩት ይቀፋል እንጂ ከመካከላቸው የፈላ ውኃ የተደፋባቸውና በጥቃቱ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች እንዳሉም ተነግሯል፡፡ በዚህ ሳቢያም የአካባቢው ሰላም ተናግቷል፡፡

እዚህ ላይ አንድ ዘመን የማይሽረው እውነት በውል ተለይቶ ሊታወቅና ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት በመሠረቱ ድንበር፣ ብሔርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፡፡ ስለሆነም ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነት የወደቀበት መንግሥት የራሱን ግንባር ቀደም ድርሻ ያላንዳች ዝንጋኤ ወይም ዳተኝነት እንዲወጣ ድምፃችንን ከፍ አድርገን መወትወታችንን ሳንረሳ፣ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ባለን አቅም ሁሉ ሳናመነታ ልንከላከለውና ልንቆጣጠረው ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ በነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ