Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ‘ላይና ታች ተሁኖ ጎጆ እንዴት ይቀለሳል?’

  እነሆ መንገድ! ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ ልንጓዝ ነው። ሰው ብርቱው በመንቀሳቀስ ፍላጎቱ መንገድ አበጅቶ መራመድ አይታክተውም። ከወዲያ ይመጣል፣ ወዲያ ይሄዳል። የመገንባት ጥረቱ ሳይነጥፍ የማፍረስ ጥበቡም አይቅርብኝ እንዳለ በመንታ ማንነት ይወዛወዛል፡፡ ‹‹ታክሲ! ታክሲ!›› ይጮሃል አንድ ሰው። ሾፌራችን የታክሲዋን ፍጥነት ይቀንሳል። የተጣራው ሰው ሊደርስብን ይሮጣል። ‹‹በዚህ አሯሯጣችን ሁላችንም አትሌት አለመሆናችን ብቻ ይገርመኛል፤›› ትላለች ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ተሳፋሪ። ‹‹ሜዳሊያ ማጥለቅና ዝና ቀረብን እንጂ አትሌቶች እኮ ነን፤›› ይላታል አጠገቧ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ኧረ ዞር በል! ደሃ አትሌት ዓይተን አናውቅም፤›› ይለዋል መሀል መቀመጫ አጠገቤ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹አቤት ሰው ግን በቃ ከገንዘብ ጋር ሳያገናኝ ወግ መሰለቅ ተሳናነው ማለት ነው?›› ስትል ደግሞ ከጀርባችን የተቀመጠች ደማም፣ ‹‹የዓረፍተ ነገሩ መጨረሻ ላይ ‘ማለት ነው’ ማለት ምን ያስፈልጋል? እንዲያው ዝም ብዬ ሳስብሽ በድፍረትና በፈጣጣነት ባልተገራ አማርኛ ሲያደናቁሩን የሚወሉ፣ አንዳንድ የኤፍኤም ሰዎችን ትመስይኛለሽ፤›› ይላል ከአጠገቧ ጓደኛዋ መሆኑ ነው።

  ልጅት እየሳቀች፣ ‹‹እኔ እኮ ለምን የአማርኛ መምህር ሳትሆን እንደቀረህ ይገርመኛል?›› ስትለው፣ ‹‹ትቀልጃለሽ? አበበ እኮ እስከ ዛሬ የሚበላው በሶ አለው። እኔ በዚህ የተቃጠለ ኑሮ ምንም ሳልበላ የአበበን ጉርሻ ልቆጥር ነው የአማርኛ መምህር የምሆነው?›› ይላታል። ሁለቱ ሲሳሳቁ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ አዛውንት፣ ‹‹አይ የዛሬ ልጆች! ቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ብልጥ ትመስሉኝ ነበር፡፡ ለካ ነገርም ታውቃላችሁ?›› ይላሉ። ‹‹ምን እናድርግ አባትና እናት የሚያወርሱን ብናጣ እኮ ነው?›› ብሎ አጠገባቸው የተቀመጠ ተሳፋሪ ይመልሳል። በዚህ ቅፅበት ያስቆመን ተሳፈሪ እያለከለከ ገብቶ ጣውላ አግዳሚ ላይ እየተቀመጠ፣ ‹‹ተመስገን!›› አለ። ‹ምን ያድርግ ታክሲ የማራቶን ያህል ሮጦ እየያዘ› እንዳትሉ ብቻ!

  ‹‹እኔን የሚገርመኝ. . .›› ከአፍታ ዝም ዝም በኋላ መጨረሻ ወንበር ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ተሳፋሪ ከወዳጁ ጋር ይጫወታል። ‹‹…የዘንድሮ ልጅ ሲበዛ ፈጣን ነው። ተመልከት እስኪ አሁን ሦስት ዓመት ትመስላለች?›› የልጁን ፎቶ እያሳየው የጓደኛውን አስተያየት በጉጉት ይጠባበቃል። ‹‹አንተ ቁርጥ እናቷን አይደል እንዴ የምትመስለው? በል ቶሎ ወንድ ልጅ ወልደህ ወገን አደራጅ፣ ዘንድሮ በተደራጀ ነው፤›› አለው ወዳጁ። ‹‹ዝም በል አይቀርም፤›› ይፎክራል። ‹‹ሆሆ! እንዴት አድርገን ኅብረ ብሔራዊ እንሁን እያልን መከራ እያየን፣ ጭራሽ አንድ ቤተሰብ በተመሳሰል ሊወግን ያሴራል? ኧረ ይኼ ዘረኝነት እንዲያው ምን ይሻለዋል?›› ይለኛል ጎልማሳው ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ። ከአዛውንቷ አጠገብ የተቀመጠው ወጣት ሰምቶት ኖሮ፣ ‹‹ሰው ያለ ቡድን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም’ ተብሎ ሳይፈጠር ቀረ ብለህ ነው? እያደር ነገሩን ያከረረው እኮ ይኼ ይኼ ነው። በዓይን፣ በአፍንጫ፣ በጆሮና በቅንድብ የእኔ ነው የእኔ እያሉ አሳድገው ነገ በሃይማኖት፣ በዘርና በቀለም እየተቧደነ ትውልድ ሲተራመስ ዕዳው መልሶ ለአገር ይሆናል. . . እሳቸው ቅድም ያሉት ማለት ነው፤›› ይላል።

  ከኋላ ቀጥለዋል። ‹‹ደግሞ ቴሌቪዥን ስታይ ልክ እንደ ትልቅ ሰው ነው። ቁጭ ካለች በቃ መነቃነቅ የለም፤›› ይላል። ዓይኑን በዓይኑ ዓይቶ ያልጠገበው አባት በስስት። አዛውንቷ ተቆጥተው፣ ‹‹ኤድያ! ወልዶ ማሳደግ በእኛ ጊዜ ቀረ። አሁን እስኪ ልጅ በትኩረት ማጥናትና ማየት ያለበት አካባቢውን እንጂ ቴሌቪዥን ነው? ደግሞስ በዚህ ወሬው ሁሉ አደንዝዝ በሆነበት ጊዜ አያድርስ እኮ ነው እናንተ?›› ብለው አፋቸው በነጠላቸው ይሸፍናሉ። እውነት በዘንድሮ አያያዝ ‘ወሬ ልጆች የማይደርሱበት ቦታ ርቆ ይቀመጥ’ ሳይባል ይቀራል! ማን ያውቃል?

  እየተጓዝን ነው። ወያላው ሒሳብ ሰብስቦ እንዳበቃ ያስተዋለው ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠው ወጣት፣ ‹‹እሺ ምዕመናን አንዴ ትኩረታችሁን ወደ እኔ!›› ሲል አንቧረቀ። አጠገቤ ያለቸው ደግሞ፣ ‹‹ጋይስ ተንቀሳቃሽ ‘ቸርች’ ተከፈተ እንዴ?›› ብላ ፌስብክ ላይ ትለጥፋለች። ‘ኮሜንት’ ይግተለተላል። ለጊዜው ቀልቤን ወደ ወጣቱ መልሻለሁ። ‹‹ያው እንደምታውቁት ከአንድ ወር በኋላ ዓመት በዓል ነው። ይህ ዓመት በዓል ሃይማኖታዊ አንድምታው የጎላ እንደመሆኑ የተቸገሩትን ለመርዳት የቻልነውን ያህል እጃችንን መዘርጋት አለብን። ‘ስጡ ይሰጣችኋል’ ይላል። እኔ አላልኩም እሱ ነው። እና አሁን . . .›› ጉሮሮውን ትንሽ ያፀዳዳና ይቀጥላል።  ‹‹. . . እና አሁን እኛ በአካባቢያችን የሚገኙ አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ለዓመት በዓል መዋያ የሚሆን ነገር ለማድረግ መዋጮ እየሰበሰብን ነው። የተቻላችሁን እጃችሁን ብትዘረጉ እግዚአብሔር ከማያልቀው በረከቱ ይዘግንላችኋል፤›› ብሎ እንዳበቃ ‘የተቻላችሁን’ ሲል የነበረው ሰውዬ ‘ከሃያ ብር በታች አልቀበልም’ ማለት ጀመረ።

  ይኼን ጊዜ ጎልማሳው፣ ‹‹ሃያ ሳንቲምም ሃያ ብርም ስጦታ ነው። ኧረ ለመሆኑ ግን አንተ ማን ትባላለህ? እስኪ የወከለህን ማኅበር ወረቀት አሳየን?” ብሎ አፈጠጠበት። ያላሰብነውና ያልጠረጠርነው ነገር መምጣቱ ገብቶናል። ‹‹ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው’ አላለም መድኃኔዓለም?” አለ ወጣቱ። ሊሰጥ አሰፍስፎ የነበረ ሁሉ የጎልማሳው ጥርጣሬ ተጋባበት። ጭራሽ መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት አንደኛው፣ ‹‹ዝም ብለህ እኮ የበርጫ ሙሉልኝ ምናምን ብትለን ካለን እንሰጥህ፣ ከሌለንም የእኛን እናስቅምህ ነበር፤›› አለው። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሦስተኛው ሰማይ ደርሶ የመጣ ይመስል የነበረው የወገን ደራሽ ቀልቡ ተገፎ ወያላው ላይ ‹‹አውርደኝ!›› ብሎ ጮኸ። ታክሲዋ ልትቆም ዳር እስክትይዝ ሳይታገስ በሩን ከፍቶ ዘሎ ወረደ። ወይዘሮዋ፣ ‹‹እግዜር እኛ በስምህ የሚነግዱትን እንዲህ አሽቀንጥረን እንደምንጥል፣ እባክህ አንተም በስማችን የሚነግዱትን ወረበሎች አሽቀንጥረህ ጣልልን፤” ብላ አጉተመተመች።

  በወረደው አጭበርባሪ ምትክ ሁለት እናቶች ተሳፍረዋል። ስለዋሉበት ገበያ እያወሩ ነው። ‹‹እንዲያው ስለስምንተኛው ሺሕ ፍካሬ ኢየሱስ ሲናገር በቃ ተስፋ የለውም ነው የሚለው አንቱ!›› አንደኛዋ ይጠይቃሉ። ‹‹እርስዎ ደግሞ ገና የጀማሪ ጥያቄ መጠየቅ ይወዳሉ። ምን ሆነው ነው ግን? ስምንተኛው ሺሕ ማለት ገበያው እንጂ ሌላ ምን ሆነና?›› ይመልሳሉ የወዲያኛዋ። ‹‹ታዲያ እንዲህ ከሆነማ መድኃኔዓለም እስከ መቼ እየተወለደ፣ ተገርፎ፣ ተሰቅሎ፣ ተነስቶ ያርጋል? እኛ እንኳን በዓሉ ሲደርስ ዶሮና እንቁላል መግዛት ከብዶናል። ለምን መጥቶ አይገላግለንም?›› ከወዳጃቸው ገርጀፍ የሚሉት እናት ከአጠያየቃቸው ማስመሰል የሚያውቁ አይመስሉም። ‹‹ሰዓቱና ቀኑ ሲደርስ ይመጣል። አንቺ ዶሮና እንቁላል ለአንድ ፋሲካ መሸመት ከበደሽና ምፅዓት መቅረብ አለበት? ሆሆ! እንኳን የላይኛው የታችኞቹም አላዘኑልን፤›› ቆፍጠን ብለው ወዳጃቸውን እየተቆጡ የወዲያኛዋ መለሱ።

  በመሀል ገና ጉዟችን ሳይጀመር በስልክ ይነጋገር የነበረው ተሳፋሪ፣ ‹‹ወዲያ በል! ቁም ነገር የሚባል አታውራኝ አሁን። ቁም ነገር ነው የሰለቸኝ። ቁም ነገር በማውራት ቢሆንማ በስብሰባ የምናጠፋው ጊዜ ተደምሮ የትና የት ባደረሰን ነበር?›› ይላል። እንዲያ ሲል በስልክ የሚያናግረው ደንበኛው ሳቀ መሰል፣ ‹‹ግዴለም እጠብቅሃለሁ ተረጋግተህ ሳቅህን ጨርስ!” ሲል ሰማነውና ደነገጥን። ‹‹እንዴ ይኼ ሰውዬ እስካሁን በስልክ እያወራ ነው?›› መጨረሻ ወንበር ከተመቀጡት ወጣቶች አንደኛው አዳንቆ ጠየቀ። ‹‹ምን ይታወቃል ‘ቴሌ’ በተዓምር እንደ ‘ፍሪ ስኮላርሺፕ ፍሪ ኔትወርክ’ ማደል ጀምሮ ይሆናላ?›› ሲል ጎልማሳው ተሳፋሪዎች የምፀት ሳቃቸውን ለቀቁት። ‘ነፃው ቀርቶብኝ ላቤን ባልነጠቀኝ’ ይሉት ምፀት መሆኑ ነው! ጉድ እኮ ነው!

  ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ከወዲያ በኩል፣ ‹‹እኮ የዓለም መንግሥታት ምን እያሰቡ ይመስላችኋል?›› ብሎ ጥያቄ ያነሳል። ‹‹ምንስ ቢያስቡ ምን አገባን? እዚህ የጓዳችንን መዓት ችግር አንድ ነገር ሳናደርግ ምን ‘ኬላ’ ያሻግረናል?” ትላለች ከወዲህ። ‹‹እንዴ ዘመኑ እኮ የግሎባላይዜሽን ነው፣ ኬላ አይደለም ህዋም ያሻግራል ጊዜው፤›› ይላል ሌላው። ‹‹የፍሳሽ ቦይ ተደፍኖ ያቆረውን ውኃ መሻገር ያቃተንን አትርሱን ፕሊስ፤›› ትላለች ከወደ ጋቢና። ‹‹አሽሟጣጭ ሰውና ጋሬጣ አንድ ናቸው የሚያልፈውን ሁሉ በመቦጨቃቸው፤›› ይላል ድምፃዊው ከተማ መኮንን። ‹‹እኛን ያስቸገረን እኮ ታዲያ የሚያልፈው አይደለም። እኔም አላልፍም እናንተም አታልፉም ብሎ መንገዱን የዘጋው ነው፤›› ራሰ በራው ይቀጥላል። ‹‹በስንቱ ይሆን ይኼ መንገድ የሚዘጋው?›› ትላለች ከአጠገቡ። ‹‹የዛሬ ጓደኛ ዋንጫ አገናኘው፣ መለኪያ አገናኘው፣ ሸርተት ሸርተት ይላል መከራ ሲያገኘው፤›› ከተማ ቀጥሏል። ‹‹እውነት ነው! ይኼው የመከራ ዕለትማ አለሁ ባዩ ሁሉ ቤቱን ዘግቶ ተቀመጠ፤›› ወይዘሮዋ አጉል ነገር ጠመዘዘች። ‹‹የምን መከራ ነው የምታወሩት?›› ከወደ መጨረሻ ይጠየቃል።

  “ኧረ ባትሰማ ይሻልሃል። እኛስ ሰምተን ምን ፈየድን? ስምንት ሚሊዮን ተራቡ፣ ይኼን ያህል ሚሊዮን ተፈናቀሉ፣ እንትን የማን ነው? ቁጥራችን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ደረሰ፣ ወዘተ እያልን መደመር እንማርልሃለን ይኼው፤›› ወይዘሮዋ ቀጥላለች። ‹‹እስካሁን መደመር አልተማርንም እንዴ?›› ነገር ያልገባው ነገር ሊያቦካ ድንጉር ይላል። ‹‹እንጃ! ተደመሩ ተብለን እሺ ካልን በኃላ ድንገት መቀነስ ያምረናል። በሌላ በኩል ደግሞ ይኼው ነገር እንደምራለን፤›› ይላል መሀል መቀመጫ ላይ ያለው። ‹‹ብቻ ዘንድሮ የምንፈልገውን በቅጡ ካላወቅን እንጃልን?›› ትላለች ደግሞ ከጎኔ። ‹‹እኛ ስንት ሆነን ነው እነሱን አንድ የምናደርጋቸው?›› ብለው አዛውንቱ ጣልቃ ሲገቡ፣ ‹‹እንዴት?›› እንደ ጥያቄ ተከተላቸው። ‹‹ምን እንዴት አለው? ይኼው እንደ ባቢሎን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላልቋል እኮ? አንዱ የሚናገረውን ሌላው አይሰማም። ወዲያ የፈለገውን ሲል ወዲህ የፈለገውን ይቀጥላል። ችግሮቻችን ውስብስብ፣ ቋንቋችን ውስብስብ፣ ቀለል አድርገን ብንደማመጥ እኮ ልዩነትም ውበት ነበር፡፡ ግን. . .›› ብለው ሳይጨርሱ ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ የጉዞውን መደምደም አበሰረ። ‹‹ኧረ መላ መላ. . .›› የከተማ እጆች ክራሩን ተያይዘውታል። እኛ ግን ወርደናል። አዛውንቱ ያንጠለጠሉትን ጨዋታ አንዱ፣ ‹‹ነገራችን ዳምኖ ፖለቲካ ካልሆነ አይዘንብም ማለት ነው በቃ?›› ሲል አዛውንቱ ከአፉ ቀበል አድርገው፣ ‹‹ሰማህ ወዳጄ! በፖለቲካ ልዩነትን ማክበር እኮ መሠልጠን ነው፤›› ሲሉት የዕውቀት ክፍተት የፈጠረው ልዩነት ጥልቅ መሆኑ ግልጽ ነበር፡፡ ‘ላይና ታች ተሁኖ ጎጆ እንዴት ይቀለሳል?’ ያለው ማን ነበር? መልካም ጉዞ!