‹‹እባብ ወተት ጠጥታ መርዝ ትተፋለች፣ ቅዱስ ግን መርዝ ጠጥቶ ወተት ይተፋል!››
በፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
መግቢያ!
አሁን ያለንበት ዘመን 21ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፣ ብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችና አሜሪካንም ጨምሮ፣ እንዲሁም ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ ዛሬ ደግሞ ቻይና በሳይንስ አማካይነት የቴክኖሎጂን ምጥቀት በማግኘት አነሰም በዛም የተረጋጋ ኅብረተሰብ ለመገንባት ችለዋል። በተለይም ባለፉት አራት አሠርታት የተፈጠሩትና ገበያ ላይ የዋሉት ቴክኖሎጂዎች ቀደም ብለው ከነበሩት ቴክኖሎጂዎች ጋር ሲወዳደሩ በጥራትም ሆነ በምቾት እጅግ ተሽለው የሚገኙ ናቸው። የዛሬ ዓርባ ዓመት ገበያ ላይ የነበሩና ለፍጆታ የቀረቡ ምርቶች ዛሬ በፍፁም አይታዩም። እንዲሁም ቴክኖሎጂዎች እጅግ ከመሻሻላቸው የተነሳ በተወሰነ ሰዓትና የሰው ኃይል ብዙ ምርቶችን ማምረት የሚቻልበት ወቅት ውስጥ ነው የምንገኘው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ መኪናንና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በግማሽ ወይም በሙሉ በአውቶማቲክ ወይም ሮቦት እየታገዙ ነው የተለያዩ ክፍሎችን የሚገጣጥሙትና ወደ አንድ ወጥ ምርትነት የሚለውጡት።
ስለሆነም በዚህ የቴክኖሎጂ ዓለም በመታገዝ እኛም በብዙ ሺሕ ማይልስ የሚቆጠር ርቀትን አልፈን መጥተን አውሮፓና አሜሪካ፣ እንዲሁም ሌላ ሠለጠነ የሚባለው ዓለም ውስጥ ተበታትነንና ተደላድለን በመኖር የቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚዎች ለመሆን በቅተናል። አዳዲስ መኪናዎችን የምናሽከረክር፣ በኢንተርኔት ዓለም ውስጥ በመኖር ኢንፎርሜሽኖችን አንድ ደቂቃ በማይፈጅ ጊዜ ውስጥ የመለዋወጥ ዕድል አለን። የምንኖርበት ቤትም ማንኛውንም ነገር ያሟላ ነው። እነዚህ ሁሉ ቴክኖሎጂዎች የተገኙት ዝም ተብለው አይደለም ወይም ከሰማይ ዱብ ብለው የወረዱ አይደሉም። ከፍተኛ ምርምርንና ሙከራን በማድረግ ነው ቴክኖሎጂዎቹ የተገኙት። የጥቂት አገሮችና ሕዝቦች የሥራ ውጤቶች በመሆን ከእነሱ አልፈው የዓለም ማኅበረሰብ እንዲጠቀምበት አድርገዋል። እስቲ እናስብ የአውሮፓ አገሮችና ሌሎችም የሃይቴክ ባለቤት የሆኑ አገሮች ዕድሜያቸውን በሙሉ የሚሆን የማይሆን ነገር አንስተው ቢጨቃጨቁ ኖሮ እንደዚህ ዓይነቱን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ማየት ይችሉ ነበር ወይ? በፍጹም! አንድም ዕርምጃ ወደ ፊት መራመድ ባልቻሉም ነበር። የእነሱ ዕጣ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው የዓለም ሕዝብም ዕጣ የጨለማና የድህነት ኑሮ በሆነ ነበር። እንደኛው በድህነትና በረሃብ እንዲሁም በስደት በማቀቁ ነበር።
ወደ እኛ አገር ስንመጣ፣ ምናልባት ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት የተነሳ የብሔረሰብ ችግርና ጭቆና የሚሉት ነገር ጭንቅላታችንን ወጥሮት ዛሬም እንደ አዲስ አጀንዳ ይዘን ስንጨቃጨቅ እንገኛለን። ዋናው ችግራችንና የሥልጣኔውም ቁልፍ እሱን በመፍታት ብቻ ይገኝ ይመስል፣ ብሔሬ ተበደለ፣ ተጨቆነ፣ ተናቀ፣ አማርኛን ተገድጄ ነው የተማርኩት፣ መለያዬን እንደገና መልሼ ማግኘት አለብኝ በማለት ያልተወራረደ ሒሳብ ያለን ይመስል በዚህና ሌሎች እልክ አስጨራሽና፣ የሰውን ጭንቅላት ወጥረው በሚይዙ፣ ግን ደግሞ የአንድን ኅብረተሰብ ችግር ለመፍታት በማይችሉ ነገሮች ላይ ስንጨቃጨቅና ሰሚናርም ስናዘጋጅ እንታያለን። ይህንን ያረጀና በታሪክ ውስጥ ካለማወቅ የተነሳ የተደረጉ ስህተቶችን እየደጋገምን በማንሳት የታዳጊውን ትውልድ ጭንቅላት በርዘናል። ለማቲማቲክስ፣ ለፊዚክስ፣ ለኬሚስትሪ፣ ለባዮሎጂና፣ እንዲሁም ለሌሎች የሕዝባችንና የአገራችንን ችግሮች መፍቻ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ ከመረባረብ ይልቅ የብሔር ጥያቄ የሚሉትን የቅኝ ገዢዎችን የመከፋፈያ አስተሳሰብ የራሳችን በማድረግ ሃምሳ ዓመት ያህል እርስ በርሳችን ተከሳክሰናል። ጦርነት ከፍተን በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲያልቁ አድርገናል። ከፍተኛ የታሪክና የባህል ወንጀል ሠርተናል።
የዛሬው የአገራችን ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፣ ሕዝባችንም የመረረ ትግል በሚያደርግበት ወቅት አንዳንዶች የትግሉን አቅጣጫ ለማዘናጋት የብሔረሰብን አጀንዳ እንደዋና የችግሩ ምንጭ አድርገው በማንሳት ወጣቱን በስሜት እየቀሰቀሱትና የማሰብ ኃይሉን ችግርን በማይፈታ ነገር ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ላይ ናቸው። እንደሚታወቀው፣ በተለይም ኋላቀሩ በሚባሉ አገሮች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችና በሕዝብ ላይ በተለያየ መልክ የሚደርሱ ጭቆናዎች አብዛኛውን ጊዜ ካለማወቅ የተነሳ ነው። ኅብረተሰብዓዊ ተሃድሶ በሌለበትና ብዙ ነገሮች በዘልማድ በሚሠሩበት አገሮች ውስጥ ሥልጣንን የጨበጡ ኃይሎች የአንድ ሕዝብ ኑሮ መሻሻልና ነፃ መውጣት ጉዳይ እስከዚህም ድረስ የሚታያቸው አይደለም። እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ የነበረው የአገራችን አስተሳሰብ ይህንን ይመስል ነበር ብሎ ከሞላ ጎደል መናገር ይቻላል። ከዚህ ስነነሳ ቀደም ብለው የተነሱት የመደብና የብሔረሰብ ጥያቄዎች የአገራችንን መሠረታዊ ችግሮች ያላገናዘቡ፣ የሳይንስን መሠረተ ሐሳብ ያልተከተሉ፣ በተለይም በጭንቅላት ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችን ያላወጡና ያላወረዱ ነበሩ። በመሆኑም ዛሬም እንደትላንትናው ከዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ባለመላቀቅ ያለንበትን ሁኔታ በመረዳትና ትግላችንን በሐሳብ ዙሪያ አሰባስበን ከመታገል ይልቅ ጊዜው እንዳያመልጠን በማለት ኃይልን በሚበታትንና የአገራችንንም ችግር በማይፈታ ላይ እንረባረባለን። የ27 ዓመቱ የአንድ ብሔር ኃያልነት የሰፈነበት የጭፍጨፋና የዘረፋ ዘመን አለፈ ስንልና ደስታችንን ሳናጣጥመው፣ ጊዜው የእኛ ነው ብለው በተነሱ፣ የታሪክን ኃላፊነት ባልተገነዘቡና ሞራላዊ ግዴታ በማይሰማቸው ኃይሎች አገራችንና ሕዝባችን ወደማይሆን አቅጣጫ እንዲያመሩ እየተደረገ ነው። መሠረታዊ በሆኑ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ፣ ማለትም ድህነትን መቅረፍ፣ የሥራ መስክን መክፈትና ለወጣቱም የሙያ ሥልጠና ከማቋቋምና አገራችንን በፀና መሠረት ላይ ከመገንባት ይልቅ አሁንም እንደትላንትናው የተያዘው ፈሊጥ በዚህም በዚያም ብሎ የአንድ ብሔረሰብ የበላይነት ማስፈን ነው። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ያለውን ችግር የሚፈታ ሳይሆን የሚያባብሰውና ለአዲስ የወንድማማቾች ጦርነት የሚጋብዘን ነው። ፖለቲካ ሳይሆን ተራ ሽወዳና አገራችን በውጭ ኃይሎች እንድትወረር የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው።
ይህንን መሠረት በማድረግ በምንም ዓይነት የአንድን ኅብረተሰብ ችግር መፍታት የማይችለውን የብሔረሰብ ጥያቄ እየተባለ የሚወተወተውን ኢሳይንሳዊ ጽንሰ ሐሳብ ለማሳየት እሞክራለሁ። ከዚህም በመነሳት የአንድ ሕዝብ መሠረታዊ ችግሮችና አትኩሮዎች የማኅበረሰባዊ ችግሮች (The Social Question) መሆናቸውን ለማረጋገጥ እሞክራለሁ።
ለመሆኑ ብሔር የሚባል ነገር አለ ወይ?
በመጀመሪያ አንድ ሰው ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ ከሚባለው ክፍል መወለዱ ተፈልጎና ተመርጦ አይደለም። አንድ ሰው እንደ ሰው ሆኖ ነው የሚወለደው እንጂ እንደ ብሔረሰብ ሆኖ አይደለም የሚወለደው። ስለሆነም የአንድ ሰው መለኪያው ልክ እንደማንኛውም ሌላ ሰው ሰው መሆኑን የሚያረጋግጡ አካልና ልዩ ልዩ ባሕሪዎችን ያዘለው አዕምሮ ሲኖሩት ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ የሰው ልጅ ውስጠ ኃይል ስላለው አንድ ቦታ ረግቶ ስለማይኖር ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በመጋባት ልጆች ይወልዳል። በዚህም የተነሳ በተለያዩ ብሔረሰብ እየተባሉ በሚጠሩ የሰው ልጆች ዘንድ በመጋባት የተነሳ አንድ ወጥ ባህል ሳይሆን ከተለያዩ ብሔረሰቦች ተጨምቆ የሚወጣ ባህል የሚሉት ነገርና በአንድ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የሚያግባባ ቋንቋ ይፈጠራል። በሌላ አነገጋር፣ በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ ብሔረሰብ እየተባሉ የሚጠሩ ሰዎች ቢኖሩም ይህም ማለት በንጹሕ መልክ አንተ ኦሮሞ ነህ፣ አንተኛው ደግሞ አማራ ነህ፣ አንቺ ከፍቾ ነሽ እያሉ መናገር በፍፁም አይቻልም። አንድ ሰው የአንድን ብሔረሰብ ቋንቋ አቀላጥፎ በመናገሩ ብቻ አማራ ነው ወይም ኦሮሞ ነው የሚያስብለው አንዳች ነገር ሊኖር አይችልም። ስለሆነም አንደኛው አንድ አካባቢ በመወለዱና በማደጉ ብቻ አማራ፣ ጉራጌ ወይም የም ወይም ሌላ እየተባለ እየተፈረጀበት፣ ከሌላው እሱን መሰል ከሆነው በእግዚአብሔር አምሳል ሆኖ ከተፈጠረው ወንድሙ ወይም እህቱ ጋር የሚያጣላው ምንም ምክንያት የለም። በሦስተኛ ደረጃ፣ ከላይ እንዳልኩት የሰው ልጅ ውስጣዊ ኃይል ስላለውና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠርና በንግድ አማካይነት በመለዋወጥ እርስ በርሱ ስለሚገናኝ በአንድ አካባቢ የሚኖር ብሔረሰብ በዚያው ሁኔታ መቶና ሁለት መቶ ዓመታት ሊቆይ በፍጹም አይችልም። በሥራ ክፍፍልና በንግድ አማካይነት በሚፈጥረው ግንኙነት በመዋለድና በመጋባት ብሔረሰብ የሚባለው ነገር እየከሰመ ይሄዳል። ስለዚህም በዛሬው በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ሕዝብ በብሔረሰብ በመከፋፈልና በመቁጠር ይኸኛው የዚህ ብሔረሰብ አካል ነው፣ ሌላው ደግሞ የዚያኛው አካል ነው እያሉ መጥራት በፍፁም አይቻልም።
ወደ ታሪካዊ ሁኔታዎች ስንመጣና የአገራችንን ሁኔታ ስንመረምር፣ በተለይም ከአንደኛው ብሔረሰብ የተውጣጡ የገዢ መደቦች፣ ለመስፋፋት ሲሉ በሃይማኖትና እንዲያም ሲል በጦርነት አንዳንድ ግዛቶችን በመያዝና በቁጥጥራቸው ስር ካደረጓቸው የገዢ መደቦች ጋር በመጋባት ልዩ ዓይነት ኅብረተሰብዓዊ እመርታን ሊሰጡ ችለዋል። ስለሆነም አማራዎችን ይወክላል የሚባለው የገዢ መደብ፣ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በመጀመሪያ ግዛቱን ለማስፋፋት ሲል አስተማሪዎች በደቡቡ ክፍል በማሰማራት የክርስትናን ሃይማኖት በማስተማርና እዚያ ካሉት ብሔረሰብ ተብለው ከሚጠሩት ጋር በመጋባት በአካባቢው ልዩ ዓይነት ባህል ሊስፋፋና ሊዳብር ችሏል። በመሆኑም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛትና የደቡቡን ክፍል በሚገዙት አምስት ንጉሣዊ አገዛዞች መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። ይህ እንግዲህ ኦሮሞዎች ዛሬ ኦሮሚያ እያሉ የሚጠሩትን ግዛት ከመውረራቸው በፊት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ኦሮሞዎች ከአንድ አካባቢ በመነሳትና ቀስ በቀስ አምስቱን የደቡብን ንጉሣዊ አገዛዞች በመደምሰስ የራሳቸውን ግዛቶች ይመሠርታሉ። ቀድሞ የነበሩ የከተማና የመንደሮችን ስሞች በመቀየር ሌላ የኦሮምኛ መጠሪያ ስም ይሰጧቸዋል። ቀስ በቀስም ከከብት አርቢነት ወደ ተቀማጭ አራሽነትና መሬትንም በመቆጣጠር የገዢ መደብ ባሕሪን ያዳብራሉ። ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሲያመሩ ደግሞ በዚያ አካባቢ ብዙ ጉዳት ካደረሱና ብዙ ሕዝብ ለኅልፈት ከዳረጉ በኋላ ቀሰ በቀስ ከተቀረው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በመጋባት እዚያ ለነበረው ባህል ልዩ እመርታን ይሰጡታል። ወደ ገዢ መደብነትም በመቀየር ታሪክን ሠሪ ለመሆን ችለዋል። በሌላ አነጋገር፣ ልክ እንደ ሌሎች አገሮች መዋጥና መዋዋጥ እንዳለ ሁሉና፣ አንደኛው ሌላውን አሸንፎ አንድ ትልቅ አገር ለመግዛት እንደሚፈልግ ሁሉ ይህም ዓይነቱ ታሪካዊ ግዴታና ድርጊት በእኛ አገርም ተካሂዷል። የሚያሳዝነው ግን ከዚህ ብሔረሰብ ብቻ ነው የፈለቅነው የሚሉ ግለሰቦች የራሳቸው ብሔረሰብ ሲስፋፋ ያደረሰውን በደልና ዝርፊያ ወደ ጎን በመተው እነሱ ብቻ ተጎጂዎች የሆኑ በማስመሰልና በማውራት ታሪክን በማጣመምና የማይሆን ነገር በማውራት ሰውን ለማሳመን ሲሞክሩ ስናይ እነዚህ ሰዎች የቱን ያህል የታሪክ ሒደትና የኅብረተሰብ ዕድገት ያልገባቸው መሆኑን እንመለከታለን።
ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአገራችን ምድር አዲስ የተፈጠረው ኅብረተሰብዓዊ ግንኙነት ከካፒታሊዚም ጋር በጥብቅ የሚገናኝና የሚተሳሰር ነው። ውስን በሆነ መልክ የገባው ካፒታሊዝም የተወሰነ የኅብረተሰብ ግንኙነት እንዲፈጠር ቢያደርግም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ባልተስተካከለ ዕድገት ምክንያት የተነሳ በአንድ አካባቢ የሚኖር የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ሳይሆን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል በድህነት ውስጥ የሚኖር ነበር። ይሁንና ግን ይህ ዓይነቱ ያልተስተካከለ ዕድገት ከተሳሳተ የዘመናዊነት (modernization) አገባብና ሒደት ጋር የተያያዘ መሆኑ ቀርቶ የብሔረሰብ ጭቆናና የመደብ ችግር ተብሎ በመወሰዱ እንደዚህ ዓይነት የተሳሳተ ምሁራዊ ግንዛቤ አሉታዊ ኃይል (Negative Energy) ያላቸው ኃይሎች ብቅ እንዲሉና አለመረጋጋት እንዲኖርና፣ በተለይም በተወሰኑ አካባቢዎች ጦርነት እንዲስፋፋ በማድረግ የአገሪቱን አንድነትና ቀስ ብሎ በጥገናዊ መልክ ሊስተካከል የሚችለውን ሁኔታ መፈታተን ጀመሩ። እንደ አንዳንድ አገሮች ለጥገናዊ ለውጥ ከመታገልና ሰፋ ያለ ምሁራዊ ዕውቀት ከማዳበር ይልቅ በጊዜው የነበረውን ጭቆና የሚባለውን ነገር በጦርነት ብቻ ነው ማሸነፍ የሚቻለው በማለት አገራችንን ወደ ተወሳሰበና በቀላሉ ሊፈታ ወደ ማይችል የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከተቷት። ረጋ ካለና ጥልቅነት ካለው ምሁራዊ ጥናትና ውይይት ይልቅ በተወሰኑ ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር ማኅበራዊና ኅብረተሰብዓዊ፣ እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ አጀንዳዎች ትኩረት እንዳይሰጣቸው አደረጉ። የኢትዮጵያ ዋናው ችግር አገሪቱ ‹‹የብሔረሰቦች እስር ቤት›› በመሆኗ ነው የሚለውን ኢሳይንሳዊና ምሁራዊነት የሌለውን የተረት ተረት በማስፋፋት አንድ ሕዝብ ታሪክን እንዳይሠራ አገዱት። በተለይም ወያኔ ሥልጣንን በበላይነት በሚቆጣጠርበት ዘመን ለብዙ ዘመናት ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ይጠቀምበት የነበረው ፖሊሲ የብሔረሰብን ጥያቄ ዋናው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ መሣሪያ በማድረግ ነበር። ከሞላ ጎደል ወያኔ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ ደግሞ የሕዝባችንን ዕውነተኛ የነፃነትና የሥልጣኔ ጥም የተገነዘቡ ኃይሎች ፍላጎቱን ለማዳፈንና የጨለማውን ዘመን ለማርዘም ማንም ሳይመርጣቸው የኦሮሞ ብሔረሰብ ተጠሪ ነን በማለት ፖለቲካውን በመጥለፍና (Highjack) ለራሳቸው የአጭር ጊዜ መጠቀሚያ በማድረግ በወንድማማች ሕዝብ መካከል መተማመን እንዳይኖርና የመጨረሻ መጨረሻ በውጭ ኃይል የሚደገፍ ፋሺስታዊ አገዛዝ ለማስፈን ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ። ወጣቱን ያሳስታሉ። እንደፈለጋቸውም በመውጣትና በመግባት ቅስቀሳ በማድረግ የፖለቲካውን አየር ሊበርዙት ችለዋል። እንዲከፍቱ በተፈቀደላቸው የዜና ማሠራጫ አማካይነት ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሠረት የሌለው ዜና አይሉት ነገር በማናፈስ ሕዝባዊ ዕልቂት እንዲፈጠር በማድረግ ላይ ናቸው። ለዚህ ድርጊታቸው ደግሞ የኢትዮጵያዊነትን ዓርማ የለበሱ የዜና ማሠራጫዎች እየተባበሯቸው ነው። በዚህ አካሄዳቸው ግን እንታገልለታለን የሚሉትን ብሔረሰባቸውንም በፍጹም አይጠቅሙትም። የድህነቱንና የኋላቀርነቱን ዘመን ከማራዘም በስተቀር ምንም ፋይዳ ሊሠሩ አይችሉም። የሚፈልጉትንም ነፃነት ሊቀዳጁም በፍጹም አይችሉም።
የአገራችን ችግር ማኅበራዊና ኋላቀርነት እንጂ የብሔረሰብ ጥያቄ አይደለም!
ያለፉትን ስድሳ ዓመታት የአገራችንን የመንግሥት አወቃቀርና ከዚህ የሚመነጨውን ፖሊሲ ለተከታተለ፣ ሦስቱም አገዛዞች በሳይንስ የተጠና፣ ፍልስፍናንና ንድፈ ሐሳብን (ቲዎሪን) መሠረት ያደረገ፣ አገራችንን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ሊያደርጋት የሚችል ፖሊሲ እንዳልነበራቸው መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ሕዝባችን ኋላቀር ከሆነ የአኗኗር ስልት ተላቆ ምርታማነትን በማሳደግና ኑሮውን አሻሽሎ ሰፋ ያለና ጠንካራ ኅብረተሰብ እንዲመሠርትና ተከታታይነት እንዲኖረው የወሰዱት ሳይንሳዊ ፖሊሲ በፍጹም አልነበረም። የአገራችንን ሁኔታና የሕዝባችንን ፍላጎት ያላገናዘበና፣ የተከታዩንም ትውልድ ዕድል ቁጥር ውስጥ ያላስገባ፣ በውጭ ኃይሎች የተነደፈና ተግባራዊ ያደረጉት ፖሊሲ በአገራችን ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ኅብረተሰብዓዊ ሀብት እንዳይፈጠር ለማድረግ በቅቷል። በ20ኛውና በ21ኛው ክፍለ ዘመኖች በአገራችን ምድር ሥልጣንን የጨበጡ የገዢ መደቦች አገራችን ያላትን ተፈጥሮአዊ ሀብት በሥነ ሥርዓት መጠቀም ስላልቻሉና እውነተኛ የሆነ ብሔራዊ ሀብት ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረጋቸው በጠቅላላው አገሪቱ ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይፈጠር አድርገዋል። ከተሞች እንዳይገነቡ፣ ሰፊው ሕዝብ በተለያየ ሙያ በመሠልጠን፣ በንግድ አማካይነት እንዳይተሳሰርና እንደ አንድ ሕዝብ ታሪክን እንዳይሠራ በአብዛኛው ጎኑ ሳያውቁት ከፍተኛ መሰናክል ሊፈጥሩ ችለዋል። ስለሆነም ድህነትን ለመቅረፍ ቀን ከሌሊት ደፋ የማይል አገዛዝ በመሠረቱ ጥሎ የሚያልፈው ያልተረጋጋና በሆነው ባልሆነው የሚናቆር ሕዝብ እንደሆነ የአንዳንድ አገሮችም ታሪክ ያስተምረናል። እንደዚህ ዐይነቱ በሰፊ የኢኮኖሚና የማኅበረሰብዓዊ መሠረት ላይ ያልተገነባ አገር ደግሞ መጥፎ ህልም ለሚያልሙ ጥራዝ ነጠቅ ለሆኑ የውስጥ ኃይሎችና፣ የአገራችንን መዳከምና እንዲያም ሲል መበታተን ለሚፈልጉ ኃይሎች ቀዳዳ መስጠቱ የማይቀር ጉዳይ ነው።
ስለሆነም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የብሔረሰብን ጥያቄ አንግቦ ነፃ እወጣለሁ በማለት እዚህና እዚያ የሚሯሯጠው ኢትዮጵያዊ ኃይል በሙሉ በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ጦርነት አውጇል። በውጭ የስለላ ኃይሎችና በአካባቢው በሚገኙ የአገራችንን መጠናከርና መረጋጋት በማይፈልጉ አጎራባች አገሮች በመታገዝ አገራችንና ሕዝባችን በቀላሉ ሊወጡ የማይችሉት ችግር ውስጥ ከቷቸዋል። እነዚህ ለነፃነታችን እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች በራሳቸው ላይ አጉል ዝቅተኛ ስሜት በማሳደርና፣ ወጣቱን በመቀስቀስና አመፀኛ እንዲሆን በማድረግ እንዳየነውና እንደቀመስነው ለብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ሰው ሕይወት መጥፋትና፣ አገራችንም አሁን ባለችበት ሁኔታ እንድትገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ‹‹በቡሃ ላይ ጆሮ ደግፍ›› ተጨምሮበት እንደሚሉት አነጋገር፣ ሌሎችም ከብሔረሰብ ጋር ያልተያያዙ ኃይሎች በዚህና በዚያኛው ሙያ የተሰማሩ የአገራችን ምሁሮች ከሲቪሉም ሆነ ከወታደሩም የተውጣጡ የውጭ የስለላ ኃይሎች የሚሰጧቸውን ምክርና የገንዘብ ድጋፍ ተገን በማድረግ አገራችንን እንደነቀርሳ በሽታ ሰርስረዋታል፡፡ በፊውዳላዊ ተንኮል ክፉኛ አዳክመዋታል። እነዚህ ኃይሎች በተለይም ቀደም ብለው ከነበሩት የገዢው መደቦች ጋር በጥብቅ የተሳሰሩና ዝምድናም የነበራቸው ሲሆኑ፣ ዋናው ዓላማቸው በተለይም አገራችንና ሕዝባችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ጠንካራ አገር እንዳይመሠርቱ ማድረግ ነው። በዚህ ዓይነቱ የአንድን አገር ህልውና የሚያወድምና ተከታታዩ ትውልድም በየጊዜው አዳዲስ ታሪክ እንዳይሠራ የማርክሲዝምን ዓርማ አንግቦ እታገላለሁ ይል የነበረው ኃይል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የአገራችንን ውድቀት አፋጥኗል ማለት ይቻላል።
ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ፣ በተለይም እንደነ ጃዋር የመሳሰሉት አዳዲስ የፖለቲካ ተዋናይ ነን ብለው የፖለቲካን ትርጉም ሳይረዱ የተሰጣቸውን የሚዲያ ዕድል በመጠቀም የሚያስፋፉት ቅጥ ያጣና የተዘበራረቀ ልፍለፋ፣ የፖለቲካውን ትግል እየረበሸውና አብዛኛውን ሕዝብ ደግሞ ግራ እያጋባው እንደመጣ እንመለከታለን። ሕዝባችን በፍርሃት በመዋጥ ፈጣሪን እየለመነ እንዲኖር አድርገውታል። በመተባበርና በመከባበር አንድ ለሁሉም የምትሆን ነፃ አገር እንዳትገነባ አለመተማመንን አስፋፍተዋል። ጃዋርና ተከታዮችም ሆነ በዳውድ የሚመራው የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅት ‹‹ተጨቁነናል፣ ነፃነታችንንም መልሰን ማግኘት አለብን›› የሚለውን ከማራገብና ሕዝብን ከማወናበድ በስተቀር፣ ይህ ነው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲያችን ብለው ሲያስተምሩና ሲከራከሩ በፍጹም አይታዩም። በመሠረቱ ሳይንስን፣ ፍልስፍናንና ቲዎሪን መሠረት አድርጎ የማይካሄድ ትግል ወደ ፋሺዝም ነው የሚያመራን። እንዳየነውና በታሪክም እንደተረጋገጠው በብሔረሰብ ላይ የተመረኮዘ ናሺናሊዝም ከሌላው የተለየሁኝ ነው ብሎ ስለሚያምን ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው እሱን እንዳለ በመግደል ወይም በመጨረስ ብቻ ነው። ይህም ማለት ሂትለር የመጨረሻው መፍትሔ (The final Solution) በአገራችንም ምድርም ተግባራዊ የማይሆንበት ምክንያት የለም። ወያኔም እስከተቻለው ድረስ ይህንን ዓይነቱን አንድን ብሔረሰብ የማውደም ፖለቲካ ሲከተል ነበር። የአሁኖቹም ጽንፈኞች ይህንን ከማድረግ አይቆጠቡም። በየቦታው የሚካሄደው መፈናቀልና መሰደድ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። ሂትለር ለጀርመን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ይሁዳዎችን በመጥላትና ዝቅተኛ ስሜትም ስላደረበት ነው ዘመቻ ያደረገባቸውና የመጨረሻ መጨረሻም ለስድስት ሚሊዮን ሰዎች ማለቅ ምክንያት የሆነውና ሆሎኮስት የሚባለውን ዘግናኝ ድርጊት የፈጸመው። እነ ሻቢያና ሕወሓት የሚባሉትም ገዢዎች በአጀማመራቸው የማርክሲዝምን ዓርማ ይዘው ቢነሱም ዋናው ዓላማቸው የአማራውን ሕዝብ ቅስም ለመስበርና እነሱ በጭንቅላታቸው ውስጥ የቀረጹትን የአማራውንና የኦርቶዶክስን ሃይማኖት የበላይነት ማዳከምና የራሳቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ ነበር። ድርጊታቸው ከፋሺዝም የሚያንስ አይደለም ማለት ነው።
በአገራችን ምድር ውስጥ እስካሁን ድረስ የተካሄዱት ትግሎች በሙሉ ራሳችንን የሚያዳክሙ እንጂ ለማንም የሚጠቅሙ አይደሉም። የታሪክን ሒደትና የኅብረተሰብን ዕድገት፣ ከዚህም በላይ ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ያለን ምሁራዊ ድክመትና፣ ጠለቅና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አለመኖር ያላገናዘቡ በመሆናቸው እርስ በእርሳችን እንድንፋተግ ተደርገናል። የድንቁርናችን ሰለባ በመሆን ተባብረንና ተቻችለን ታሪክን ከመሥራት ይልቅ የውጭ ኃይሎች ተጠሪና ተመካሪ በመሆን የአገራችንን ውድቀትና መበታተን እያፋጠን እንገኛለን። የተማርነው ትምህርት ሁሉ ጭንቅላታችንን አንጾት የተቀደሰ ተግባር ከመሥራት ይልቅ መጥፎ ነገር የተማርን ይመስል በክፉኛ መቀናናትና መጠላላት በመወጠር መሥራት ያለብንን ነገር እንዳንሠራ ታግደናል። ይህ ዓይነቱ ታሪክን ያላገናዘበ ትግል ግን አንድ ቦታ ላይ መገታት አለበት። እያንዳንዱ ምሁር ራሱን በራሱ በማግኘት ታሪክ ሠሪነቱንም የሚያረጋግጥ መሆን አለበት እንጂ የአገራችንን ውድቀት ለማፋጠን ከውጭ ኃይሎች ጋር መሥራት የለብትም። እርስ በርስ መመካከርና ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ እንጂ ከውጭ ኃይሎች ምንም ዓይነት ምክር የሚጠይቅበት ምክንያት የለውም።
‹‹የኦሮሚያን ሪፐብሊክ›› እንመሠርታለን ብለው ደፋ ቀና ለሚሉት ኃይሎች የመጨረሻ ጥሪዬ፣ በኢትዮጵያ ምድር ታሪክን ልትሠሩ የምትችሉት በዚህ ዓይነቱ አካሄድ ሳይሆን፣ ከሌላው ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር በመመካከርና ሐሳብ ለሐሳብ በመለዋወጥ ብቻ ነው። ዓላማችንም ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚስማማና፣ ተደላድሎና ተከባብሮ ለመኖር የሚያስችለውን አገር መገንባት ብቻ ነው። ስለሆነም የብሔረሰብና የሃይማኖት ጥያቄዎች የኅብረተሰብ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ አይደሉም። የአንድ ኅብረተሰብ ችግር በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው። የንጹህ ውኃ ጉዳይ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ በደንብ የተሠራ መጠለያ፣ ሕክምናና ጭንቅላትን ክፍት የሚያደርግና፣ ሰው መሆናችንን እንድንገነዘብ የሚያደርገው ሁለገብ ትምህርት የጠቅላላው ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህን ለመሳሰሉት ጥያቄዎችና የሕዝብ ፍላጎቶች መልስ መስጠት የምንችለው በተናጠል በመታገልና የራሴ አጀንዳ አለኝ በማለት ሳይሆን፣ በአንድ የአስተሳሰብ ዙሪያ ስንሰባሰብ ብቻ ነው። ዛሬ ሠለጠኑ የሚባሉ አገሮች ቀናውን መንገድ በመከተልና በመደማመጥ ብቻ ነው ለማደግና ዓለምን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር የቻሉት። ስለዚህም ወዲህና ወዲያ ከምንሯሯጥ ይልቅ እስቲ አንድ ጊዜ ተቀምጠን የምንሠራውን ሥራ ሁሉ እናሰላስል። አስተሳሰባችንን በሙሉ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በፍልስፍና ዙሪያ እናድርገው። ለብሔረሰብ ሳይሆን ለእነዚህ ነገሮች ቅድሚያ እንስጣቸው።
የዛሬውን የዶ/ር ዓብይን አገዛዝ የማሳስበው ውስጥ ሆነው አደገኛ ፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱ ግለሰቦችን መግታት አለባቸው። ፖለቲካቸው ጠቅላላውን ሕዝብ የሚመለከትና ኃይሉንም የሚሰበስብ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ የውስጥ ፖለቲካ ተብሎ የሚጠራና አንድን ሕዝብ እንደማኅበረሰብ የሚያሰባስበውና የሚያጠናክረው ሰፋ ያለ ፖሊሲ አለ። የዚህም ፖሊሲ ፍልስፍናዊ መሠረት ጠቅላላው ሕዝብ ከየት እንደመጣ፣ ለምን እንደሚኖር፣ ምን ማድረግ እንዳለበትና ወዴትስ እንደሚጓዝ የሚያስገነዝበው ነው። ይህንን ለማረጋገጥና በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት ደግሞ በሳይንስና በፍልስፍና የተፈተነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ብሔራዊ ሀብትን የሚፈጥር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን አለበት። እንደማየውና እንደምከታተለው ከሆነ አሁንም አገዛዙ የውጭ ምክርንና ትዕዛዝን በመቀበል ነው ወደፊት ለመጓዝ የሚጥረው። በተለይም እየደጋገሙ የገንዘብ ቅነሳ ማድረግና በገበያ ስም የተካሄደውና የሚካሄደው ፖሊሲ አገሪቱን የባሰ ደሃ ነው ያደረጋት፡፡ ሕዝባችንን በኑሮ ውድነት እንዲማረር አድርጎታል። ስለሆነም አገዛዙ ከቻይናዎችና ከሩሲያዎች እንዲሁም ከደቡብ ኮሪያ መንግሥታት መማር አለበት። በራስና በሕዝብ ላይ መተማመን ብቻ ነው አንድን ሕዝብ ነፃና የተከበረ ሊያደርገው የሚችለው። ከዚህ ስንነሳ በተለይም ከዓረብ መንግሥታት ጋር ያለው ግንኙነት በጥብቅ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው። ውስጥ ለውስጥ የሚካሄድ ሳይሆን ለውይይትና ለክርክር መቅረብ አለበት። የአገራችን ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ሕዝባችንም ጉዳይ ስለሆነ አጠቃላዩ የውጭ ፖሊሲያችን ወይም ፖለቲካችን ሕዝብ ሳያውቀው በዝግ ችሎት የሚካሄድ መሆን የለበትም። በዚህ ዓይነት ፖለቲካ ብሔራዊ ነፃነታችን መደፈሩ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ አገር እንዳንገነባ እንታገዳለን። መልካም ግንዛቤ!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡