ዕጣው መውጣቱን አንዳንድ የደረሳቸው ዕድለኞችም ተቃውመዋል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣ ያወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ለባለዕድለኞች መተላለፋቸው ታግዶ እንዲቆይ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አጣ፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ቅድሚያ ቤት ለማግኘት መቶ በመቶ ክፍያ ፈጽመው የተዋዋሉ 98 ግለሰቦች ያቀረቡትን ክስ የመረመረው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ የቀረበለትን ክስ መርምሮ ሦስት ትዕዛዞች ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጀመርያ የሰጠው ትዕዛዝ ክስ የቀረበባቸው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለቀረበባቸው ክስ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ምላሽ እንዲሰጡ ነው፡፡ ሌላው ሁለቱ ወገኖች (ከሳሾችና ተከሳሾች) ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. በችሎት ቀርበው ክርክር እንዲያደርጉ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ትዕዛዞች ከሰጠ በኋላ፣ የግለሰቦቹ ተወካይ ጠበቃ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዕጣ የወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣው ለወጣላቸው ግለሰቦች ሊተላለፉ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ስለዚህም እንዳይተላለፉ ዕግድ እንዲጣልላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ዕግድ የሚጣለው ቤቱ ዕጣ ለደረሰው እንዳይሰጥ ነው? ወይስ የወጣው ዕጣ እንዳለ እንዲታገድ ነው?›› በማለት ጠበቃውን ሲጠይቃቸው፣ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ዕጣ ለወጣላቸው እንዳይተላለፍ ታግዶ እንዲቆይ መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ይኼማ ሊሆን አይችልም፤›› ካለ በኋላ፣ ዕጣ የወጣባቸው ቤቶች ለወጣላቸው እንዳይሰጥ የሚለውን ጥያቄ በማለፍ፣ ‹‹ስመ ሀብቱ›› ወይም የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ (ካርታ) የፍርድ ቤቱ ክርክር እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዕጣ ለወጣላቸው ግለሰቦች እንዳይተላለፍ (እንዳይሰጥ) ዕግድ ጥሎበታል፡፡
ሐሙስ መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለመስማት በአካል ችሎት ከተገኙት 98 ከሳሽ ግለሰቦች ጋር በ13ኛው ዙር የ40/60 ዕጣ የወጣላቸውም ግለሰቦች በፍርድ ቤት ተገኝተው፣ የዕጣ አወጣጡ ሥርዓት ትክክል አይደለም በማለት ለከሳሾች ድጋፋቸውን ሲሰጡ ታይተዋል፡፡ ዕጣ የደረሳቸውና አወጣጡን ተቃውመው ለድጋፍ በፍርድ ቤት የተገኙት ወይዘሮ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እሳቸው ቤቱ ስለደረሳቸው ደስተኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን የዕጣ አወጣጡ ሥርዓት ትክክል አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም መቶ በመቶ ክፍያ የፈጸሙ ሰዎች ገንዘብ ተርፏቸው ሳይሆን፣ ካሳለፉት የቤት ችግና የአከራይ ተፅዕኖ ለመገላገል እስከ 13 በመቶ ወለድ እየከፈሉ ተበድረው የከፈሉ መሆናቸውን ስለሚያውቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመነሻው ውል ማስፈጸም ሥራ ውስጥ መግባቱ ወንጀል መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮዋ የባንኩ ሥራና ሥልጣን ገንዘብ ማበደር ሆኖ ሳለ፣ በሌለው ሥልጣንና እስከ መጨረሻው ማስፈጸም የማይችለውን አሠራር ለመተግበር መነሳቱ ተጠያቂ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡ ኮንትራት ወይም ውል ሕግ መሆኑን አክለው፣ ፍርድ ቤቱ ወይም ዳኛ ሕጉንና ሕጉን ብቻ ዓይቶ ውሳኔ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡