ኢትዮጵያ ከፊቷ በርካታ ሥራዎች ተደቅነዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ተቀዳሚ ተግባር በመላ አገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መሆን አለበት፡፡ ሰላም በሌለበት የፖለቲካ ምኅዳሩን በሚፈለገው መጠን ለመክፈት ያዳግታል፡፡ ለመጪው ምርጫ ለመዘጋጀት የሚያስፈልጉ ሥራዎችን ለማከናወን አይቻልም፡፡ የዴሞክራሲና የሲቪክ ተቋማትን ለማደራጀት አይሞከርም፡፡ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት ጥቅል አገራዊ ምርቱን ማሳደግም ሆነ የሥራ ፈጠራውን ለማቀላጠፍ ይቸግራል፡፡ ‹መጀመሪያ የመቀመጫዬን› እንዳለችው እንስሳ፣ የአገርን ህልውና አስተማማኝ ማድረግ የሚቻለው ሰላም በማስፈን ነው፡፡ የሰላም ጉዳይ ሲነሳ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ላይ መጣል ትክክል አይሆንም፡፡ መንግሥት የአገርን ሰላም፣ ደኅንነትና ጥቅም የማስከበር ግንባር ቀደም ኃላፊነት እንዳለበት የታወቀ ቢሆንም፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሚና የሚታለፍ አይደለም፡፡ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የትምህርት ተቋማትና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አደረጃጀቶች ተሳትፎ የግድ ይሆናል፡፡ በሁሉም ተሳትፎ የሚሰፍን ሰላም ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡
በአሁኗ ኢትዮጵያ የተለያዩ ፍላጎቶችንና ጥያቄዎችን ይዘው የተነሱ ወገኖች መረዳት ያለባቸው፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊገነባ የሚችለው በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ እንቅስቃሴ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ግን አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ተጠያቂነት እንዳለበት ጭምር ጠንቅቆ መረዳት ይኖርበታል፡፡ መንግሥት በየዕለቱ በሚያከናውነው ሥራ የመላውን ሕዝብ ፍላጎት ማርካት እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራውን ከአድልኦና ከመድልኦ ነፃ ማድረግ ሲችል፣ የአብዛኛውን ሕዝብ ይሁንታ ያገኛል፡፡ ጥያቄዎች ሲነሱም በፍጥነት በመንቀሳቀስ ተገቢውንና ተመጣጣኙን ምላሽ መስጠት ሲያውቅበት፣ ግልጽነት የጎደላቸው ነገሮች እየጠሩ መተማመን ይጎለብታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ሲደጋገሙ ግን መንግሥትና ሕዝብ ሆድና ጀርባ ይሆናሉ፡፡ ስለመተማመን መነጋገር አይቻልም፡፡ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲሰፍን ከተፈለገ፣ ሕዝብና መንግሥት መናበብ የግድ ይላቸዋል፡፡ ይህ መናበብ እየጠፋ ሰላም እንቅፋት እየገጠመው ነው የንፁኃን ደም በከንቱ የሚፈሰው፡፡
ገዥውን ፓርቲ ኢሕአዴግ ጨምሮ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከሥልጣን በፊት የምትቀድም አገርን ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው› በሚባል አጉል ብሒል በመመራት ሰላማዊውንና ሥልጡኑን የፖለቲካ ፉክክር ወደ አመፅና ግጭት መውሰድ፣ ራስን በራስ እንደ ማጥፋት ይቆጠራል፡፡ የሚቀጥለው ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተከናውኖ አሸናፊው ፓርቲ ወይም ጥምረት ሥልጣኑን መረከብ የሚችለው፣ ለፖለቲካ ምኅዳሩ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መሟላት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲከናወን የሚፈለገውን ያህል፣ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን አሟልቶ እንዲካሄድ ደግሞ የበኩልን አስተዋጽኦ ማበርከት የግድ ይሆናል፡፡ ምርጫው ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ መሆን የሚችለው ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ የተለመደው አምባገነናዊና ኢዴሞክራሲያዊ ድርጊት አይደገምም ማለት የዋህነት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ስለመጪው ምርጫ ሲነሳ ገና ካሁኑ ውጤትን በፀጋ ስለመቀበል ከመነጋገር በፊት፣ እዚያ ደረጃ ሊያደርስ የሚችለውን የንጣፍ ጉዳይ በቅጡ ማሰብ መቅደም አለበት፡፡ ይህ ንጣፍ ደግሞ ሰላም ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ለዚህ ጉዳይ ቅድሚያ ሳይሰጡ ስለምርጫ መዋከብ ከፈለጉ፣ አርቀው እያሰቡ እንዳልሆነ ሊጤን ይገባል፡፡
በዚህ ጊዜ ሌላ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው የፖለቲካ አቀንቃኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ወገኖች ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች ድምፃቸው ከማንም በላይ ጎልቶ መሰማቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት ጥረት በሰላም ካልታጀበ ውጤታቸው ነውጥና ግጭት ነው፡፡ የፖለቲካ አቀንቃኞች በአደረጃጀትና በአተያይ የተበጣጠሱ በመሆናቸው (በኅብረ ብሔራዊነትና በብሔርተኝነት)፣ የሁሉንም ዋይታ በእኩልነት ለማስተጋባት ይሳናቸዋል፡፡ አንደኛው ወገን የዜግነት ፖለቲካን ብቻ ነው የማራምደው በማለት ብሔርተኝነትን ሲያጣጥል፣ ሌላው ወገን ደግሞ ከወጣሁበት ብሔር ውጪ ሌላው ለራሱ ይጨነቅ በማለት ኅብረ ብሔራዊነትን ወደ ጎን ይገፋል፡፡ በዚህ ምክንያት የፖለቲካ አቀንቃኞች በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚፈጥሩት ተቃርኖናና ሽኩቻ መሬት ላይ የግጭት ማዕበል ይቀሰቅሳል፡፡ ለአገር ሰላም ጠንቅ ይሆናል፡፡ በዓለም ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች በየትም ሥፍራ የሚደርስ በደልን ለመቃወም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ለእነሱ የሰው መበደል፣ መጠቃት፣ መሰቃየት፣ መታሰር፣ ሞት፣ ወዘተ ነው የሚያሳስባቸው፡፡ የራሴ ወገን የሚሉት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃና ገለልተኛ ናቸው ተብለው ይታሰባሉና፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ግን ይህንን ሰብዓዊ እሳቤ የሳቱ በመከሰታቸው ምክንያት ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ችግሮቹ ደግሞ ለሰላም ጠንቅ እየሆኑ የአገርን ህልውና ይፈታተናሉ፡፡ ሰብዓዊነት ሁሉንም የሰው ዘር በእኩልነት ማገልገል አለበት፡፡ ይህም ብርቱ የሆነ ግንዛቤ ያስፈልገዋል፡፡
ሌላው ለሰላም ጠንቅ ሊሆን የሚችለው ባለድርሻ አካል ሚዲያው ነው፡፡ ሚዲያው ተልዕኮውን ሲወጣ ሙያው ከሚጠይቀውና ከሥነ ምግባር ውጪ ከተንቀሳቀሰ ትልቅ ችግር ይፈጠራል፡፡ ጋዜጠኝነት ሚዛናዊነት፣ ልብ ሙሉኑትና ያልተውሸለሸለ አጋላጭነት መገለጫው ናቸው፡፡ አጫፋሪም አዋዳቂም መሆን የለበትም፡፡ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ይልቅ ለእውነት፣ ለሚዛናዊነትና ለነባራዊነት (Objectivity) ታማኝ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ምግባርና ጨዋነት አማካይነት ብልሽቶችንና ጉድለቶችን ከመንግሥት ቤት እስከ የግል ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ድረስ እየገለባበጠ ለሕዝብ የሚያቀርብ ሚዲያ ማበልፀግ የሚቻለው፣ ነፃነቱንና ገለልተኝነቱን በሕግ ማዕቀፍ ማረጋገጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት ይኼንን መሠረታዊ ጉዳይ የማስረፅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሚዲያን ለራስ ዓላማ ብቻ እየኮተኮቱ የማሰማራት ከንቱ ድርጊት ሊያበቃ ይገባል፡፡ ሚዲያውን ተላላኪ ማድረግም ሆነ በጠላትነት ፈርጆ ተገቢ ያልሆነ ስያሜ ከመስጠት በፊት የራስን ድርጊት መፈተሽ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለ በፌዴራል መንግሥት፣ በክልል ብሔራዊ መንግሥታት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በግል ይዞታ ሥር ያሉት ሚዲያዎች በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ሚዲያዎቹም ካላስፈላጊ ድርጊት ይታቀባሉ፡፡ በዚህ መሠረት መሥራት ከተቻለ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ድርጊቶች ይወገዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ከሆነች የታሰበው ሁሉ ይሳካል፡፡ ለዚህም ነው ሰላም ለኢትዮጵያ መባል ያለበት፡፡ ለሰላም ቅድሚያ ያልሰጠ ዓላማ በአጭር ይቀጫልና!