Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ ከኃይል ማመንጨት መውጣቱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለተበደረው ገንዘብ ከወለድ በቀር መክፈል እንዳልቻለ ገልጿል

የረጲ ኃይል ማመንጫ ከሦስት ወራት በኋላ ሥራ ይጀምራል ተብሏል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ ሙሉ በሙሉ በመውጣት፣ ትኩረቱን በኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ ብቻ እንደሚያደርግ  አስታወቀ፡፡ ተቋሙ ለገናሌ ዳዋ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ ካሣ በመክፈል ግድቡን በውኃ መሙላት መጀመሩንም ይፋ አድርጓል፡፡

ተቋሙ በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ መቆየቱን ያስታወቁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅት በወሰዳቸው የለውጥ ዕርምጃዎች ሳቢያ ተቋሙ የኮርፖሬት ንግድ ተቋምነት ባህርይ እንዲላበስ መደረጉን፣ ሐሙስ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሠራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ላለፉት ሦስት ዓመታት በካሣ ክፍያ ጥያቄ ሳቢያ ውኃ መያዝ ሳይችልና ኃይል ሳያመነጭ፣ እንዲሁም ማሽነሪዎቹ ተተክለው ቆሞ የቆየውን የገናሌ ዳዋ ሦስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ስምምነት ከአባባቢው ነዋሪዎች ጋር መደረሱን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ መክፈል የሚጠበቅበትን የ2.9 ቢሊዮን ብር የካሣ ክፍያ በመፈጸም፣ ኅብረተሰቡም ለግድቡ ውኃ ማጠራቀሚያ በሚውለው ቦታ ላይ የሚገኘውን ደን ለመመንጠር ተስማምቶ በነበረው መሠረት ሁለቱም የድርሻቸውን ለመወጣት ተስማምተው፣ የውኃ ሙሌት ሥራው ከየካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ከ2.57 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለት ከመነሻው ይገነባል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ገናሌ ዳዋ ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ፣ ከ250 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በገናሌ ወንዝ ላይ በገነባው ግድብ አማካይነት ኃይል እንደሚያመነጭ ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የገናሌ ዳዋ ፕሮጅክት የግንባታ ሥራው ከ97 በመቶ በላይ በመጠናቀቁ ኃይል ለማመንጨት መቃረቡም ተጠቁሟል፡፡

አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ከመጣ ወዲህ የለውጥ ዕርምጃዎች በመወሰዳቸው፣ ገናሌ ዳዋን ጨምሮ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክትም እንዲያንሰራራና ከዚህ በፊት የተጓተቱ ሥራዎችም እንዲንቀሳቀሱ መደረጋቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቀሪ ሥራዎቹ ስላልተጠናቀቁ እንዲቆም የተደረገው የረጲ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም፣ ከተቋራጩ ኩባንያ ጋር ድርድር ተደርጎ በመጪዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ቀሪዎቹ ሥራዎች ተጠናቀው ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከሌሎች የተቋሙ ሥራ ኃላፊዎች በመሆን ለሠራተኞች በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል የሚያመነጨው ይህ ፕሮጀክት እንዲሁ ቆሞ ድርድር ከሚደረግ ይልቅ፣ ሥራውን እየሠራ ክርክሮች እንዲካሄዱ መወሰኑንና ኩባንያውም ሆነ መንግሥት ያሏቸውን ጉዳዮች ሥራው እየተሠራ ለመነጋገር በመስማማታቸው፣ የኃይል ማመንጫው ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በፋይናንስ ዕጦት ሳቢያ ከተጓተቱት ፕሮጀክቶች መካከል እንደ ኮይሻ ያሉ ኃይል ማመንጫዎች ግንባታዎች ለመቆም ተገደው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በ26 በመቶ የግንባታ ደረጃ ላይ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት መንግሥት ፍላጎቱ ላላቸውና የራሳቸውን ገንዘብ ይዘው ለሚመጡ ኩባንያዎች እንደሚያስተላልፈው፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይፋ አድርገዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር መንግሥት የአጭር ጊዜ ብድር እንዲቆም በማድረጉ ምክንያት ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኃይል የሚያቀርበውን መስመር ጨምሮ፣ ለባህር ዳር -ወልዲያ – ኮምቦልቻ፣ ለአቃቂ – አቦና ቅሊንጦ የኃይል ማሠራጫ መስመሮች ዝርጋታ የዋለውን የብድር ገንዘብ ዋናው ዕዳ መክፈል እንዳልቻለ ተቋሙ ይፋ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት አቅሙ የብድር ወለድ ብቻ መክፈል እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ይህ በመሆኑም መንግሥት የውጭ ብድር ዕዳውን እንዲጋራው ጥያቄ አቅርቦ ይሁንታ ማግኘቱንና ለአገር ውስጥ አበዳሪዎችም የብድር ማራዘሚያ ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ ምንም ገንዘብ ሳይኖረው አብዛኛውን ፕሮጀክት በብድር ሲያስገነባ መቆየቱን ያስታወቁት አብርሃም (ዶ/ር)፣ ከዚህ በኋላ በኃይል ማመንጫ ሥራዎች ውስጥ እንደማይሳተፍ፣ በአገሪቱ ያሉትን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በአግባቡ በማስተዳደርና የተቋሙን የሀብት መጠን በማስጠናት፣ ብሎም የተሻለ ገቢ በሚያስገኙለት ሥራዎች ላይ በማተኮር እንደሚንቀሳቀስ አብራርተዋል፡፡

መንግሥት ወደ ግል እንደሚያዛውራቸው ይፋ ካደረጋቸው መንግሥታዊ የልማት ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ሀብቱን በማስገመት ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ተቋሙ ከኃይል ማመንጨት ሥራ መውጣቱ ዋናውን ሥራውን ለሌሎች አሳልፎ የመስጠት ዕርምጃ በመሆኑ፣ ይህ ተቋም ወደፊት ከመንግሥት እጅ በመውጣት የግል ኩባንያ እንዲሆን የታቀደለትን አካሄድ ከወዲሁ መከተል እንደጀመረ አመላካች ዕርምጃ ተደርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር ዕዳ እንዳለባቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ዕዳ ውስጥ ከግማሽ ያላነሰው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሆነም ተናግረው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች